በመቀሌ የስንዴ ዱቄት እጥረት የራስ ምታት ሆኗል

0
678

በትግራይ ብሔራዊ ክልል መዲና መቀሌ ከስንዴ ዱቄት አቅርቦት ችግር ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የዳቦ እጥረት መከሰቱ ተገለጸ። ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በድጎማ መልክ ወደ ክልሉ ይገባ የነበረው ስንዴ መቋረጡን ተከትሎ የአቅርቦት ችግር እንደተፈጠረም የክልሉ የከተማ ልማትና ንግድ ቢሮ አስታውቋል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ ዳንኤል መኮንን ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት በከተማዋ አንድ ብር ከ30 ሳንቲም ሲሸጥ የነበረው መቶ ግራም ዳቦ ሁለት ብር ከ50 ሳንቲም ገብቷል። ይህም በእጥፍ ማደጉን ያሳያል። እንደ ዳንኤል ገለጻ ሕዝቡ በከፍተኛ የዳቦ እጥረት ችግር ውስጥ ሲሆን ስንዴም በኩንታል እስከ ሁለት ሺሕ 300 ድረስ እየተሸጠ ነው።
ነቀዝ የበላው ስንዴ በመርከብ ስለገባ እና የግዢ ሒደቱ መዘግየት ስለታየበት ነው ከሚል በዘለለ ከፌድራል መንግሥት የተሰጠ አጥጋቢ ምላሽ አለመኖሩንም ዳንኤል አስታውቀዋል።
ችግሩ ከሚያዚያ 2010 ጀምሮ ለተከታታይ ወራት የዘለቀ ነው። በኢትዮጵያና በኤርትራ በኩል ያለው ድንበር መከፈቱ እንዲሁም ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው የሚመጡት የክልሉ ተወላጆች መብዛትን ተከትሎ የስንዴ አቅርቦቱን ማዳርስ አዳጋች አድርጎታል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በአገር ውስጥ ሲቀርብ የነበረው የስንዴ ምርትም ከፍተኛ የዋጋ ንረት አሳይቷል።
በመቀሌ በዱቄት አቅራቢነት የሚሠሩት ሃዱሽ ሃይሉ በበኩላችው ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚቀርበው የስንዴ ምርት በማነሱ ምክንያት ለኪሳራ መዳረጋችውን ያስረዳሉ። ችግሩንም ለመፍታት መንግሥት በድጎማ የሚገባውን ስንዴ በአግባቡ ማከፋፈል አለበት ይላሉ።
በተጨማሪም ምርቱን ወደ ክልሉ ለማስገባት የትራንስፖርት ችግርም እንደ ምክንያት ይነሳል።
ከግማሽ ሚሊየን በላይ ሕዝብ በሚኖርባት የመቀሌ ከተማ ዳቦ በብዛት ለምግብነት ይውላል። ከወራት በፊት የድንብር መከፈቱን ተከትሎ በክልሉ አጋጥሞ የነበረው የጤፍ እጥረት መቃለሉን የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ቢገልጽም አንድ እንጀራ እስከ ሰባት ብር ድረስ በከተማዋ እንደሚሸጥ ምንጮች አስታውቀዋል።
የመቀሌ ነዋሪ የሆኑት መኮንን ፍሰሃ “የዱቄት ዋጋ መጨመሩ አይገርምም ምክንያቱም በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ድንበር አካባቢ ያለው የንግድ ቁጥጥር መላላት ያመጣው ችግር ነው ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኛች ኮሚሽን መረጃ እንደሚያመላክተው ትግራይ በሚገኛ አራት የስደተኛ መጠሊያ ጣቢያዎች ከ175 ሺህ በላይ የሚሆኑ ኤርትራዊያን ስደተኞች ይገኛሉ። በየቀኑም 291 ያህል ስደተኞች የኤርትራን ድንበር አቋርጠው ወደ ትግራይ ክልል ይገባሉ።
ለስደተኞቹም ከሚቀርቡ ምግቦች መካከል ዳቦ ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ከክልሉ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታት ከፌድራል መንግሥት ጋር ውይይቶች እንደሚደረጉ አቶ ዳንኤል አስታውቀዋል።
በተቃራኒው የማዕከላዊ ስታትስቲከስ ኤጀንሲ ባሳለፍነው ሳምንት ባወጣው መረጃ የ የአገሪቷ ዋጋ ግሽበት ንረት 10 ነጥብ 3 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል። ይህ ቁጥርም ባለፉት ዐሥራ አምስት ወራት ከተመዘገበው ጋር ሲነጻጸር ትንሹ ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 5 ታኅሣሥ 6 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here