የወራት ዕድሜን ብቻ ቢያስቆጥርም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዓለምን በማዳረስ ይህ ጽሑፍ እስከተጠናቀረበት ጊዜ እንኳን ከ200 ሺሕ የሚልቅ የዓለም ሕዝብን ታማሚ በማድረግ በአንድም በሌላ በለይቶ ማቆያ ክፍል እንዲቀመጡ አድርጓል። በዚህ ብቻ ሳይበቃ፤ ቫይረሱ መጀመሪያ ከጀመረባት የቻይናዋ ዉሃን ግዛት በመነሳት ወደ አራቱም የዓለም አቅጣጫ ተጉዞ ከ8 ሺሕ 900 በላይ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል። በኢትዮጵያም አዲስ ማለዳ ለሕትመት እስከበቃችበት ሰዓት ድረስ ዘጠኝ ሰዎች በኮሮና ተይዘው በለይቶ ማቆያ ስፍራ እንዳሉ ይታወቃል። ከእነዚህም ውስጥ ኹለቱ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ የውጪ ዜጎች ናቸው።
ኮሮና በሚል የወል ሥም እና ኮቪድ 19 በሚል የግል ሥም ዓለምን እያሸበረ ስለሚገኘው ይኸው ቫይረስ፣ የዓለም መገናኛ ብዙኀን በየሰዓቱ ሰፊ የዜና ሽፋን በመስጠት እና አዳዲስ መረጃዎችን በማድረስ ላይ ይገኛሉ። የቫይረሱን ገዳይነት እና በፍጥነት መዛመት ተከትሎም በርካታ የዓለም አገራት ወደ ቻይና የሚደረጉ በረራዎችን አግደዋል። የዓለም አቀፍ በረራዎችን ማገድ እና ይህንም ተከትሎ በርካቶች ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ ሲያደርጉ የኖሩት እንቅስቃሴ ተገድቧል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድም በ19 አገራት ውስጥ ወደሚገኙ 21 መዳረሻዎቹ እንዳይበር መታገዱን ይፋ አድርጓል። በዚህ ብቻም ሳይበቃ ከሳምንት አስቀድሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተዛመተ በመጣው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት፣ አየር መንገዱ ገቢው እየቀነሰ በመምጣቱ ሠራተኞች ቅነሳ ለማድረግ እንደሚገደድ የሚገልጽ የኢሜይል መልዕክት ለጠቅላላው ሠራተኞቹ መላኩም ተሰምቷል።
ከጉዞ እገዳዎች እና እንቅስቃሴዎች መገታት ጋር ተያይዞም፣ ዓለም ዐቀፉ የንግድ እንቅስቃሴ በእጅጉ ተቀዛቅዟል። ከፍ ሲልም የፍጆታ እቃዎች ከፍተኛ እጥረት አጋጥሟል። በዚህ ደግሞ በአሜሪካ በዋሽግተን ግዛት ሲልቨር ስፐሪንግ ክፍለ ግዛት የሸቀጦች እጥረት በማጋጠሙ ተገልጋዮች ከተፈቀደላቸው መጠን በላይ መግዛት እንደማይችሉ እስከመነገር እንደደረሱ የአዲስ ማለዳ ምንጮች ከስፍራው ተናግረዋል።
በተለይ ደግሞ ወረርሽኙን ለመከላከል ከተቀመጡት መንገዶች አንዱ ብዙ ሰዎች ከተሰበሰቡበት አካባቢ መራቅ በመሆኑ፣ ይህንንም ተከትሎ ትልልቅ መሥሪያ ቤቶች ሠራተኞቻቸውን ቤታቸው ሆነው መሥራት የሚችሉበት መንገድ በማመቻቸቱ፣ ግለሰቦች ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ ምግብ እና የፍጆታ ዕቃዎችን በመግዛት አሰባስበዋል። ይህም እጥረቱን ማባባሱን የተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ሳይቀሩ ዘግበዋል። በተለይ ደግሞ የጠረጴዛ ለስላሳ ወረቀቶች እና የእጅ ማጽጃ ኬሚካሎች በገበያ ማእከላት አስተናባሪዎች ተመጥነው ለተገልጋይ ይሰጣሉ። በጣም ከባሰም ከመደርደሪያዎች ላይ መታጣታቸው ግድ ሆኗል።
ይህ ችግር ታዲያ በዓለም ዙሪያ ሁሉ ተመሳሳይ ሁኔታን በመፍጠር ዓለም በአንድ አይነት ችግር ውስጥ መውደቋን ማሳያ ነው። ከሸቀጦች ባለፈም አየር መንገዶች በረራ በማቆማቸው ለከፍተኛ ኪሳራ ተዳርገዋል። ሆቴሎች እና ምግብ ቤቶች በደንበኛ እጥረት ስጋት ውስጥ ይገኛሉ። በተለይ ደግሞ የገቢ ምንጫቸው በእለት እለት የሥራ እና ገቢ ጋር የተመረኮዙ በርካታ ሰዎች፣ ከባድ ችግር ውስጥ ገብተዋል። ለዚህ ደግሞ ቃልኪዳን አመሃ ዋነኛው ማሳያ ነው።
ቃልኪዳን ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ታሪካዊ ስፍራዎችን በማስጎብኘት ሥራ ነበር የሚተዳደረው። ለሚሰጠው አገልግሎትም በቀን እስከ 500 ብር ድረስ ያገኛል፤ በዚህም ታናሽ እህቱን በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ እየከፈለ ያስተምራል። ይሁን እንጂ ከሰሞኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው ወረርሽኝ በሥራው ላይ ትልቅ ጫና ፈጥሮበታል። ‹‹ምንም አይነት ጎብኚ ወደ ኢትዮጵያ እየገባ አይደለም። በተለይም ደግሞ ለእኔ እና ጓደኞቼ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ የሚሆኑን ለረጅም ጊዜያት ኢትዮጵያ ውስጥ በመቆየት ኹሉንም ታሪካዊ ስፍራዎች ጎብኝተው የሚመለሱ ጎብኚዎች ናቸው። አሁን ግን ለአጭር ጊዜ የሚመጡትም ጠፍተዋል›› ሲል ቃልኪዳን ይናገራል።
ቃልኪዳንን እንደማሳያ አነሳን እንጂ፣ በማስጎብኘት ሥራ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረው ክብረአን አስጎብኚ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ከተከሰተው ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ በርካታ ደንበኞቹ በኢንተርኔት በኩል ያስያዙትን የ‹እንመጣለን› ቀጠሮ ሙሉ በሙሉ እና በከፊል መሰረዛቸውን ለአዲስ ማለዳ ያስረዳል። በአሁኑ ሰዓት ከአንድ ወር በፊት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በክብረአን አስጎብኚ በኩል የኢትዮጵያን ክፍል እየጎበኙ የሚገኙ ኻያ ጎብኚዎች መኖራቸውንም የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ያስረዳሉ።
ይህ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ የሆቴል ኢንዱስትሪው እና በአዲስ አበባም የምግብ ቤቶች እና ካፌዎች ላይ ጥላ አጥልቶባቸዋል። አዲስ ማለዳ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ባለ አምስት እና ባለ አራት ኮኮብ ሆቴሎች ላይ ባደረገችው ቅኝት እና አመራሮቻቸውም ጋር ባደረገችው አጭር ቆይታ፣ ለውጦችን እና የገበያ መቀዛቀዞችን ለመታዘብ ሞክራለች። ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አዲስ ማለዳ ቅኝት ያደረገችባቸው ሆቴሎች የሥራ አመራሮች እንደሚናገሩት፣ ከወራት በፊት አስቀድመው የሆቴል አገልግሎቶችን ለማግኘት በድረገጽ አማካኝነት ቦታ ያስያዙ እንግዶች የተወሰኑት ሙሉ በሙሉ ትዕዛዛቸውን የሰረዙ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ ለሆቴሎች አስፈላጊውን መልዕክት በመላክ ላልተወሰነ ጊዜ የመምጫቸውን ቀን ያራዘሙ መሆናቸውን ገልጸው በቀጣይ ትክክለኛውን ቀን እንደሚያሳውቋቸው የሚገልጽ መልዕክት እንደላኩላቸው ይናገራሉ።
በዋናነት ደንበኞቻችን ከወደ አውሮፓ፣ አሜሪካ እና መካከለኛው ምሥራቅ ናቸው የሚለው በመሃል ካዛንችስ የሚገኘው ባለ አምስት ኮከቡ ሆቴል፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰተው ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ገቢ እንዳጣ ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል። በዚሁ ሆቴል ውስጥ ሊካሄዱ የታሰቡ እጅግ ትላልቅ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች መሰረዛቸውን ይናገራሉ። ከስብሰባው ጋር ተያይዞ ሆቴሉ ለተሰብሳቢዎች ምግብ፣ ሻይ እና ቡና እንዲሁም መኝታ በማቅረብ ከፍተኛ ገቢ ለማግኘት አቅዶ እንደነበርም ሳይጠቅሱ አላለፉም።
ከዚህም በተጨማሪ በደኅናው ጊዜ በሆቴሉ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም መኝታ ክፍሎች ተይዘው እንግዶች የሚመለሱበት ጊዜ መኖሩን የጠቆሙት የሆቴሉ የሥራ ኃላፊ፣ አሁን ግን በሆቴሉ ውስጥ 20 በመቶ የሚሆኑት የመኝታ ክፍሎች ብቻ መኖራቸውን ነው ለአዲስ ማለዳ የሚናገሩት። ‹‹በሆቴላችን ውስጥ ለአስቸኳይ ወይም ለአስገዳጅ የሥራ ጉዳይ ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ የገቡ እንግዶች እና ከረጅም ጊዜ በፊት ወደ ሆቴሉ የመጡ እንግዶች ብቻ ናቸው እየተስተናገዱ የሚገኙት›› ብለዋል።
አያይዘውም ከውጭ አገራት እንግዶች ባሻገርም ኢትዮጵያውያንም ቋሚ ደንበኞች መሆናቸውን ጠቅሰዋል። በተለይም ከሻይ ቡና ከፍ ብሎ አልኮል መጠጥ ተጠቃሚዎች ቢኖሩም፣ ወረርሽኙን ተከትሎ ግን ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚዎች መጥፋታቸውን አስታውቋል፤ ሆቴሉ። ምንም እንኳን ወረርሽኙ ከፍተኛ መቀዛቀዞችን በዚህ ሆቴል ውስጥ ቢያሳድርም፣ ዓለም ዐቀፍ ሆቴል እንደመሆኑ መጠን በሌሎች አፍሪካ አገራት ቅርንጫፎች በመኖሩ የደንበኞች ብዛትን በሚያወዳድርበት ወቅት በአዲስ አበባ የሚገኘው ቅርንጫፍ የተሻለ የደንበኞች ብዛት እንዳለው አልደበቀም።
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ እና አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ የተመለከተቻቸው ሆቴሎች የመኝታ ክፍሎቻቸው፣ ሁሉም ሊባል በሚችል ሁኔታ ከእንግዳ እጦት የተነሳ ክፍት ናቸው። አምስት እንግዶች ብቻ እየተስተናገዱ ያሉበት ሆቴልንም አዲስ ማለዳ ለማየት ችላለች። በዚህ ሆቴል ውስጥ በየደረጃው አልጋዎች ቢኖሩም፣ ለአንድ አዳር ከ2 ሺሕ 800 እስከ 3 ሺሕ 500 ብር ድረስ የሚያስከፍሉ እንደሆኑ ለመረዳት ተችሏል። 129 ጠቅላላ ከፍሎች ያሉት ይኸው ሆቴል አዲስ ማለዳ ቅኝት ባደረገችበት ጊዜ አምስት እንግዶች ብቻ እንዳረፉ ገልጿል።
ምግብ ቤቶች እና ካፌዎች
ለወትሮው በሰዎች በመጨናነቅ የሚስተካከላቸው የሌላቸው በአዲስ አበባ የሚገኙ ምግብ ቤቶች እና ካፊቴሪያዎች ከሰሞኑ መቀዛቀዛቸው እጅግ በርትቷል። በተለይም ደግሞ በሥራ መውጫ ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ የሚገኙ ምግብ ቤቶች እና ካፊቴሪያዎች ቫይረሱ በኢትዮጵያ ውስጥ መከሰቱን ተከትሎ ማኅበረሰባዊ ፈቀቅታን (Social Distancing) ተግባራዊ ለማድረግ ይመስላል፣ የዘወትር ደንበኞች ዱካቸው ጠፍቷል።
ከቦሌ መድኃኒዓለም ወደ ብራስ ሆስፒታል በሚወስደው መንገድ ላይ የሚገኘው 9+ የሻዋርማ ቤት፣ ከዚህ ቀደም የሥራ መውጫ ሰዓት ላይ ዘግየት ብሎ ወደ ስፍራው ለደረሰ መቀመጫ ብቻ ሳይሆን ለዐይን ማማተሪያ እንኳን ቦታ አያገኝም ነበር። ይሁን እንጂ አዲስ ማለዳ በስፍራው በተገኘችበት ወቅት ዐስር የማይሞሉ፣ ፊታቸውን በፊት መሸፈኛ የሸፈኑ እና ተራርቀው የተቀመጡ ተስተናጋጆችን ማየት ችላለች። በቀን ከ500 እስከ 800 የሚደርሱ ደንበኞችን እንደሚያስተናግዱ እና አሁን ግን እጅግ በዛ ከተባለ የተስተናጋጆች ቁጥር በቀን ከመቶ እንደማያልፍ የምግብ ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡበከር ሐሰን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በዚህም ምክንያት ከገበያ መቀዛቀዙ ጋር ተያይዞ በቀን በኹለት ፈረቃ እንዲያስተናግዱ የተቀጠሩ በአጠቃላይ ስምንት ያህል አስተናጋጆችን ለመቀነስ እንደሚገደድ እና በአራት አስተናጋጆች ለመሥራት እንዳሰበ አስታውቋል። ‹‹በወር 25 ሺሕ ብር የቤት ኪራይ እየተከፈለ፣ በጠፋ ገበያ ለሠራተኞች ደሞዝ መክፈል ደግሞ ሌላ ችግር ራስ ላይ መጨመር ነው። የገበያው መቀዛቀዝ ግን በዚህ ከቀጠለ አስተናጋጆችን በመቀነስ ብቻ የምንቋቋመው ጉዳይ አይመስለኝም።›› ሲሉ አቡበከር ለአዲስ ማለዳ ጭንቀታቸውን ተንፍሰዋል።
ክሊኒኮች እና መድኃኒት መደብሮች
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ከተከሰቱ የንግድ መቀዛቀዞች በተቃራኒው ደግሞ የእስከዛሬውን እና ከዚህ ቀደም ያልሠሩባቸውንም ጊዜያት ያካካሱ የሚመስሉ የመድኃኒት መደብሮች ላይ አዲስ ማለዳ ቅኝት አድርጋለች። በዚህም መሰረት በከተማችን ያሉ መድኃኒት ቤቶች ደጅ ላይ ረጃጅም ሰልፎችን መመልከት የእለት ተዕለት ተግባር ሆኗል። አገልግሎት ለማግኘት የተሰለፉት ተገልጋዮችም የሚወስዱት መጠን ይለያይ እንጂ ፊት መሸፈኛ፣ እጅ ጓንት እና የእጅ ማጽጃ ኬሚካል መሆኑን አዲስ ማለዳ ከጠየቀቻቸው ሰዎች ተረድታለች።
ይህን ዓለም ዐቀፋዊ ወረርሽኝ እንደ ምክንያት በመጠቀም ከፍተኛ ፍላጎት በታየባቸው መገልገያ ዕቃዎች ላይ ታዲያ ከፍተኛ ጭማሪ በማድረግ መድኃኒት ቤቶች ሸጠዋል። የፊት መሸፈኛ ቀድሞ በዛ ከተባለ የአንዱ ዋጋ 10 ብር የነበረ ቢሆንም ወረርሽኙ አገር ውስጥ ከገባ በኋላ ግን እስከ 150 ብር ዋጋ ተቆርጦላቸው ለሽያጭ መቅረባቸው ታውቋል። አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ በታዘበችው የግል እና የመንግሥት መድኃኒት መደብሮች ላይ ከበርካታ ሰልፎች ባለፈ ሰፊ የዋጋ ልዮነቶችም ተስተውለዋል።
በተለይም ደግሞ እጅ ማጽጃ ኬሚካል ላይ የከተማ ነዋሪዎች ማኅበር (ከነማ) መድኃኒት መደብር ውስጥ እስከ 80 ብር ድረስ እየተሸጡ የሚገኙ ሲሆን፣ ተመሳሳይ መጠን ያለው የእጅ ማጽጃ ኬሚካል በአንዳንድ መድኃኒት ቤቶች ላይ እስከ 5 መቶ ብር ድረስ እንደሚሸጡ ተገልጋዮች ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። በዚህ ብቻ ሳይበቃ የእጅ ማጽጃዎች ለሚታወቁ ሰዎች ብቻ መሆናቸው ደግሞ እጅግ የሚያበሳጭ ጉዳይ እንደሆነ በአዲስ አበባ ሲኤምሲ ሚካኤል አካባቢ ያገኘናቸው ተገልጋይ ይናገራሉ።
ዘኪ ሙራ ይባላሉ። ለሦስት ተከታታይ ቀናት ለቤተሰብ የሚሆን የአፍ እና አፍንቻ መሸፈኛ እንዲሁም የእጅ ማጽጃ ለመግዛት ተመላልሰዋል። ይሁን እንጂ ከረጃጅም ሰልፍ በኋላ ማግኘት የቻሉት የአፍ መሸፈኛውን ብቻ ሲሆን እሱንም በነፍስ ወከፍ 100 ብር ሒሳብ ከፍለው እንደሆነ አስረድተዋል።
በመድኃኒት መደብሩ ውስጥ በፋርማሲ ቴክኒሻንነት የምታገለግለው ዕፀገነት አለበል የሚባለው ሁሉ ውሸት እንደሆነና በእቃዎች ላይ የታየው ከፍተኛ ፍላጎት ዕጥረቱ ቢከሰትም ድርጅታቸው ግን ምንም አይነት የዋጋ ጭማሪ እንዳላደረገ ትናገራለች።
ኮሮና ቫይረስን በዘመናዊ መንገድ ከመከላከል ባለፈ በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ ባሕላዊ ቅመማ ቅመሞችን በስፋት የመጠቀም አዝማሚያ በመታየቱም በቅመሞች ላይ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል። ይህንም ተከትሎ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጉዳዮን የሚከታተል ግብረ ኃይል እስከ ማቋቋም እና የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉት ላይ እርምጃ እስከ መውሰድ ደርሷል። ወረርሽኙ በኢትዮጵያ በተከሰተ በሰዓታት ውስጥ የአንድ ኪሎ ነጭ ሽኩርት ዋጋ 250 ብር መድረሱ የተሰማ ሲሆን በሾላ ገበያ አንድ ኪሎ ነጭ ሽንኩርት 300 ብር ሲሸጥ ነበር። አንዳንድ ነጋዴዎችም በመደበቅ እና ለቁጥጥር ነው የመጣው ብለው ለሚያስቡት ሰው እስካለመሸጥም ይደርሳሉ።
አዲስ ማለዳ በዘውዲቱ ሆስፒታል እና በተወሰኑ የግል የሕክምና ተቋማትም ላይ ቅኝቷን አድርጋለች። በዘውዲቱ ሆስፒታል ቅጥር ጊቢ ውስጥ የሚገኘው የከነማ መድኃኒት ቤት በሰዎች ተሞልቶ በሽታው እንዲባባስ ከሚያደርጉ ኹነቶች አንዱ የሆነው እርስ በርስ መተገፋፈግ ሲከወን ይታያል። የበርካታ ሰዎች መሰለፍ ምክንያት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ዋጋ አውጥቶለት ለግልና መንግሥት መድኃኒት መደብሮች በተቆረጠለት ዋጋ እንዲከፋፈል ስላደረገው የእጅ ማጽጃ ኬሚካልን ለመግዛት ነው።
በዚሁ ሆስፒታል ቅጥር ገቢ ውስጥ በነጻ የሙቀት ልኬት የሚሰጥ ሲሆን፣ ሌሎች ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያያዥ ምልክቶችንም በነጻ ማረጋጋጥ እንደሚቻል የሆስፒታሉ ሐኪም ዶክተር ቴዎድሮስ ሽፈራው ለአዲስ ማለዳ ይናገራል።
በሌላ በኩል ደግሞ በቦሌ ሩዋንዳ አካባቢ በሚገኘው ዋሽግተን ሜዲካል ሴንተር ከተለመደው ጊዜ በላይ ደንበኞችን እያስተናገደ እንደሚገኝ የሜዲካል ሴንተሩ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ፋሲል ተፈራ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በዚህ ሕክምና ማእከል ውስጥ አንድ ሰው ለካርድ 300 ብር በማውጣት ወደ ቀጣዩ ምርመራ ይሄዳል። በቀን ከአንድ ሺሕ እስከ አንድ ሺሕ 500 ተገልጋዮችን ያስተናግድ የነበረው የሕክምና ማእከሉ፣ አሁን እጥፍ ቁጥር ያለውን ተገልጋይ ማስተናገድ መጀመሩን ዳይሬክተሩ ይናገራሉ።
‹‹24 ሰዓት እንሠራለን። ነገር ግን ሌሊት አልፎ አልፎ የሚመጡ ድንገተኛ ታማሚዎች ካልሆኑ በስተቀር ተኝተው የሚታከሙ ሰዎች አስታማሚዎች ናቸው ይመላለሱ የነበረው። አሁን ግን አዲስ ካርድ አውጥተው የሚታከሙ ተግልጋዮች ይመጣሉ። ትንሽ የሙቀት መጠናቸው ሲጨምር ለመለካት ሲሉ ብቻ የሚመጡ አሉ። ሌሎች ደግሞ ሕመም ስሜት ሲሰማቸው አዲስ ወረርሽኝ ይሆናል በሚል ፍራቻ ወደ ሕክምና ማእከሉ ይመጣሉ›› ሲሉ ፋሲል ያስረዳሉ።
የገቢው መጨመር መልካም ነገር መሆኑን የሚገልጹት ፋሲል፣ ነገር ግን እንደ ሕክምና ባለሙያነታቸው ከመደናገጥ ይልቅ ሰው ከንክኪ እንዲታቀብ እና እጃቸውን በተደጋጋሚ እንዲታጠቡ መክረዋል። ‹‹በፍራቻ ምክንያት ለሚመጡ ሰዎች የሙቀት መጠናቸውን ለክተን አጠራጣሪ ጉዳይ ካለ ለይተን እንዲቆዩ ማድረግ ነው። እንጂ ልናደርግላቸው የምንችለው ነገር አለመኖሩ ሰዎች ሊገባቸው ይገባል›› ይላሉ።
ምሽት ቤቶች
በምሽት ቤቶች በኩል ሁኔታው ከምግብ ቤቶች እና ከካፊቴሪያዎች የተለየ ሁኔታ ነው ያለው። ቀን ከምግብ ቤቶች እና ከካፊቴሪያዎች ተሰውሮ የቆየው ሕዝብ ምሽት ላይ ወደ ጭፈራ ቤቶች ጎራ ማለቱን ግን የቀነሰ አይመስልም። አዲስ ማለዳ ማምሻ ቤቶች ናቸው በተባሉ እና ምሽቱ እየገፋ ሲሔድ በብዛት ሰዎች ይዝናኑባቸዋል በተባሉ ስፍራዎች ሁኔታውን ለመመልከት ችላለች።
አቫንቲ ላውንጅ ውስጥ በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው ሰዎች እንደተለመደው ሲስተናገዱ ለማየት ተችሏል። የላውንጁ ባለቤት ኤርሚያስ ዘውዴ ለአዲስ ማለዳ ሲናገር፣ ገቢው ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ እንደመጣ እና ወረርሽኙ በኢትዮጵያ ተከሰተ ከተባለበት ቀን ጀምሮ ደግሞ ይባሱኑ የደንበኞች ቁጥር እንደጨመረ ይናገራል። ‹‹እኔ እንኳን ብዙም ባላምንበትም ሰዎች ግን ጠንከር ያሉ አልኮሎችን ያለመበረዣ መጠጣት ኮሮናን ይከላከላል በሚል አዘውትረው ይመጣሉ። በእርግጥ እስካሁን ሲነገር አልሰማሁም። ለእኔ ግን ገቢዬ እንዲጨምር አድርጎልኛል።››
ኤርሚያስ እንደሚናገረው፣ በሥራ ቀናት ድርጅቱ እያስገባ የሚገኘው ገቢ በእረፍት ቀናት ያስገባ ከነበረው እየበለጠ እንደመጣ ያስረዳል። በጾም ወቅት ገበያ እምብዛም እንደሆነና አሁን ግን በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት ከፍ ያለ ገቢ ማስገባት መቻሉን ይናገራል። ከዚህ ባለፈ ደግሞ ወደ አንድ ምሽት ክበብ የተጓዘችው አዲስ ማለዳ፣ የምሽት ቤቱን ባለቤት ለማናገር ችላለች።
‹‹በቀን እስከ 200 ሺሕ ብር ሽያጭ የተካሔዱበት ቀናት ናቸው፤ የሰሞኑ ቀናት›› ሲል የሚናገረው የምሽት ቤቱ ባለቤት፤ በጾም ወቅት ብቻ ሳይሆን በፍስክ ወራትም እንዲህ ዓይነት ሽያጭ ተገኝቶ እንደማይታወቅ ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል። በጣም በዛ ከተባለ ከ100 ሺሕ ብር በላይ ዘሎ የማያውቀው የሽያጭ መጠኑ፣ እዚህ የመድረሱን ምክንያት አያውቀውም። በአብዛኛው የሚሰማው ነገር ገበያው መቀዛቀዝ እንዳሳየ ነው። በተባለው የምሽት ቤት ከቤቱ አቅም በላይ በሆነ የሰው ቁጥር ተጨናንቆ እና በውጪ በረንዳ ላይም ሰዎች አልኮል ሲጎነጩ ተስተውሏል።
የልብስ እና ጫማ መሸጫዎች
በልብስ እና ጫማ መሸጫዎች ውስጥ ገበያ መቀዛቀዝ ብቻ ሳይሆን የእቃ ዕጥረትም አጋጥሟል። ይህንም ተከትሎ በልብሶች እና ጫማዎች ላይ ከ200 እስከ 300 ብር የሚደርስ የዋጋ ጭማሪዎች ታይተዋል። ከወር እና ከዛ በፊት 1500 ብር ይሸጡ የነበሩ የወንድ ጫማዎች፣ አዲስ ማለዳ በተዘዋወረችባቸው አካባቢዎች 1800 ብር ድረስ ይሸጣሉ። ለዚህ ደግሞ እንደምክንያት የሚጠቀሱት ወደ ቻይና እና ወደ መካከለኛው ምሥራቅ በተለይም ደግሞ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እንዲሁም ሩቅ ምሥራቅ ታይላንድ የሚደረጉ የነጋዴዎች ጉዞ መገታቱን ተከትሎ፣ እቃዎችን የሚያመጡ ሰዎች በመጥፋታቸው እንደሆነ ያስረዳሉ።
የወንዶች አልባሳት መሸጫ ባለቤት የሆነው መሐመድ ሲራጅ፣ ከዚህ ቀደም 500 ብር ይሸጡ የነበሩ ሱሪዎች 700 ብር እንደገቡና ከዚህም በላይ ሊጨምሩ እንደሚችሉ ያስረዳል። ‹‹ከምንረከብበት ቦታ አስመጪዎች የእቃ ዋጋ ይጨምራል በሚል ደብቀው አስቀምጠዋል። ደንበኞቻቸው ስለሆንን ከሸጡልንም በጭማሪ ዋጋ ነው የሚሸጡልን። ስለዚህ እኛም ተጠቃሚ ላይ እንጨምራለን። አሁን የመጣውን በሽታ ሳይፈሩ ወደ ቻይና ሔደው ዕቃ ያመጡ ሰዎች እንዳሉ እሰማለሁ። ግን ዕቃውን እስካሁን አልሸጡም፤ ደብቀው ይዘውታል›› ሲል መሐመድ ይናገራል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ወረርሽኝ የሆነውን እና በአገራችንም አሉታዊ ተጽዕኖዎችን እያሳደረ የሚገኘውን ኮቪድ-19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና በምጣኔ ሃብት እንዲሁም በንግድ እንቅስቃሴ ላይ የሚያሳድረውን ተግዳሮት በተመለከተ፣ በዓለም ዐቀፉ የገንዘብ ተቋም ውስጥ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት እና ሥማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ግለሰብ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
‹‹የተከሰተው ዓለም ዐቀፋዊ ችግር ነው። ባይሆን እንኳን በቻይና ብቻ ተወስኖ የሚቀር ቢሆን እንኳን በዓለም የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም ነበር። ለዚህ ደግሞ ማሳያው ከዓመታት በፊት በቻይና ተከስቶ የነበረው የሳርስ ወረርሽኝ በዓለም ዐቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ መቀዛቀዝን አድርሶ ነበር። በእርግጥ ኢትዮጵያ ላይ ይህን ያህል ተጽዕኖ በተለይም ደግሞ በምግብ ላይ ይኖራል የሚል ግምት የለኝም። ምክንያቱ ደግሞ በዋናነት ኢትዮጵያውያን የምንመገበው እንጀራ በአገር ውስጥ በሚገኝ የጤፍ ምርት በመሆኑ፣ የእለት እንጀራ ላይ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብዬ አላምንም›› ይላሉ።
ከዚህ ባሻገር ግን የወጪም ሆነ የገቢ ምርቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ ችግር እንደሚፈጠር የማያጠራጥር ጉዳይ እንደሆነ ባለሙያው ያስረዳሉ።
ቅጽ 2 ቁጥር 72 መጋቢት 12 2012