ረመዳን ታላቁ የፆም ወር

Views: 315

በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ዘንድ በከፍተኛ ናፍቆት የሚጠበቀው የታላቁ ረመዳን ፆም ሰኞ፣ ሚያዚያ 28 መጀመሩ ይታወቃል። ረመዳን በየዓመቱ በዚህ ወቅት የሚካሔድበትም ዋነኛው ምክንያት ቅዱስ መፅሐፍ ወይም ቁራን ለነብዩ መሐመድ የተገለጠበት ወቅት ስለሆነ እንደሆነ የእምነቱ ምሁራን ይናገራሉ። ነገር ግን ከዓመት ዓመት የተወሰነ የቀናት መለዋወጥ የሚኖር ሲሆን ይህም የእስልምና የቀን መቁጠርያ የሚጠቀመው የጨረቃ አወጣጥን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ነው።

በእስልምና ውስጥ በዋናነት ከሚጠቀሰሱተ የእምነቱ ተግበራት ውስጥ ጸሎት፣ እምነት፣ መርዳትና ወደ መካ መንፈሳዊ ጉዞ ማድረግ ይገኙባቸዋል። ይሁን እንጂ በእምነቱ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው ፆም እንደሆነ የሃይማኖቱ አባቶች ይናገራሉ።

በእስልምና እምነት የሃይማኖት መምህር የሆኑት ዑስታዝ አቡበከር አሕመድ መሐመድ ለአዲስ ማለዳ ስለረመዳን እንዳስረዱት ፆም በእስልምና እምነት ተከታዮች መሰረታዊ ከሚባሉት መንገዶች አንዱ ሲሆን ሕፃናት፣ አዛውንቶች እንዲሁም ሕመም ላይ ያሉ ሰዎች ካልሆኑ በስተቀር ሁሉም ሰው የመፆም ግዴታ አለበት ብለዋል። ይህንንም ሲባል የረመዳን ፆም ዋና ዓላማው የፈጣሪን ትዕዛዝ መመሪያ በማድረግና በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ በመተግበር ፈጣሪ ከማይወዳቸው ነገሮች መታቀብ መሆኑን ይናገራሉ። ፈጣሪ የማይወዳቸው ድርጊቶችም የተለያዩ አልኮል መጠጦች ከመጠጣት መቆጠብ፣ ከመጥፎ አስተሳሰቦች ራስን ማጽዳት፤ ሲሆኑ አንድ ምዕመን ማድረግ ከሚገባቸው መካከል ደግሞ ስለሌሎች ታናናሽ ወገኖች ረሃብ እና ድካም ምንነት እንዲሰማን የሚያደርግ ትልቅ ፆም ነው። አማኙ እነዚህን ነገሮች በሕይወቱ ሲተረጉም የተሻለ የማንነትንና ጥሩ ባሕሪይን ለመቅረጽ ስለሆነ ጎህ ከመቀደዱ ጀምሮ ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ ሰዓቱ ተጠብቆ መፆም እንዳለበት ያስረዳሉ።

በተለምዶ አንዋር መስኪድ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኙ የጣፋጭ ነጋዴዎች አካባቢውን ቢያደምቁትም ከዚህ በፊት ይታይ ከነበረው ግርግር ጋር ሲነፃፀር የገበያው ሁኔታ መቀዛቀዙን አስተያየት ሰጪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናናረዋል።
በየዓመቱ የረመዳንን ፆም ስንቀበል የተለያዩ ቴምሮችን በመሸጥ መተዳደር ከጀመርኩ ዓመታትን አስቆጥሪያለሁ የሚለው ወጣት ሱልጣን ጀማል፥ ስለሚሸጣቸው ጣፋጭ ቴምሮች የዋጋ መናር አስከትሎ ያለውን የገቢያ ማሽቆልቆል ለስለስ ባለና ድካም በተሞላው አንደበት ይናገራል።

በእምነቱም በረመዳን ወቅት አብዛኛውን ማኅበረሰብ የሚያፈጥረው በቴምር ነው። ይህም በብዙዎች የሚስተዋለው የደከመ ሰውነትን ከማነቃቃት ባለፈ ጤነኛ የሆነ ስሜት እንዲሰማ ያደርጋል በሚል እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ። ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት የቴምር ዋጋ በዕጥፍ በሚባል ደረጃ በመጨመሩ የተነሳ ተጠቃሚ የለም ማለት ይቻላል።

ከዚህ ቀደም በፆም ወቅት ከአንድ ሺሕ እስከ 5 መቶ ግራም ቴምር ከስልሳ እስከ 30 ብር ድረስ ይሸጥ እንደነበር የሚናገረው ሱልጣን በቀን እስከ 3 ሺሕ ብር ድረስ የምሸጥበት ጊዜ ነበር ሲልም ቅሬታ በተሞላው አንደበት የቅርብ ሩቅ ትዝታውን ያወጋል። “በአሁኑ ወቅት ቴምር ከመቶ እስከ 50 ብር በኪሎ እየተሸጠ ነው። ነገር ግን በዋጋ ጭማሪ የተነሳ በቀን የምንሰራው 7 መቶ ብር ብቻ ድረስ ነው” በማለት ሱልጣን ይናገራል።

የቴምር ዋጋ ከሌላው ጊዜ በተለየ በእጥፍ ቢጨምርም ባለፉት ወራቶች በገበያው ላይ በመጥፋት የ1 ኪሎ ዋጋ እስከ 80 ብር ድረስ ሲሸጥ የነበረው ባሌንሺያ ጣፋጭ ብርቱካን በአሁኑ ወቅት በግማሽ ቅናሽ በማድረግ አንድ ኪሎ ከ40 እስከ 50 ብር ድረስ እየተሸጠ እንደሆነ በአካባቢው የሚገኙ ነጋዴዎች ይናገራሉ።

በረመዳን ወቅት የተለያዩ ጣፋጭ ምግቦች እንደየቤቱ ሁኔታ ሲቀርቡ ይስተዋላሉ። የተለያዩ ብስኩቶች፣ አፕል፣ ሀላዋ፣ ሙሸበክ፣ ፕሪም፣ ኩኪስ እና ሾርባ እንደሆኑ የእምነቱ ተከታዮች ይናገራሉ፤ ከምግብ በኋላ ለየት ባለ መንገድ እንደ ማንሸራሸሪያ ሀባብ መጠቀም የተለመደ ነው መሆነም ታውቋል።

በተለያዩ አገሮች በሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች በረመዳን ወቅት እንዲፆሙ የሚጠበቅባቸው ሲሆን በሳውዲ አረቢያ የእምነቱ ተከታይ የሆኑ ግለሰቦችም ሆነ የሌላ እምነት ተከታዮች ለሕዝቡ ተጋላጭ በሆነ ስፍራ ሲመገቡ ቢገኙ እስከ እስር የሚያደርስ ቅጣት ሊጠብቃቸው ይችላል። ተያይዞም የረመዳንን ፆም ለየት የሚያደርገው በረሀብ ለተጎዳ አካላቸውን ለማነቃቃት የሚጠቀሙበት ዋና ማፍጠሪያቸው ቴምር ይጠቀሳል።

እስልምና በኢትዮጵያ
የእስልምና ሃይማኖት በአክሱማዊ ግዛት በአርማህ ጊዜ በ7ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወይንም በ615 ወደ ኢትዮጵያ እንደገባ ይታመናል።

በመጀመሪያው ሂጅራ የተካሔደውን ከመካ ወደ ኢትዮጵያ ሲሆን በጊዜው ከፍተኛ የሆነ እንግልትና ስቃይ አልፎም ግድያ ይደርስባቸው የነበሩ የአዲሱ የእስልም እምነት ተከታዮች በነብዩ መሐመድ ትዕዛዝ ይደርስባቸው ከነበረው አሰቃቂ ጉዳት ሊተርፉ ወደ ሚችሉበት ስፍራ በአቢሲኒያ እንዲፈልጉ በተነገራቸው መሰረት ወደ ኢትዮጵያ ገቡ።

በዛ ጊዜ ኢትዮጵያን ያስተዳድሩ የነበሩት ንጉሥም ወደ አገሪቱ በስደት የመጡትን የእስልምና እምነት ተከታዮችን የሚያርፉበትን ምቹ ቦታ በማዘጋጀት በሰላም ከተቀበሏቸው በኋላ በአካባቢዋ ይኖሩ ከነበሩት የክርስትና እምነት ተከታዮች ጋር በስምምነት እንዲኖሩ ተፈቀደላቸው። ይህም ለዘመናት አብሮ በሰላምና በፍቅር ለኖረው የእስልናና የክርስትና እምነት ተከታዮች መነሻ እንደሆነ ይታወቃል።

እምነቱም ቀስ በቀስ ወደ ደቡባዊ ትግራይ በመስፋፋት ወሎ ክፍለ ሀገር ከፍተኛ የሆነ ተቀባይነትን ማግኘት የቻለ ሲሆን እስከ አሁንም ድረስ በአካባቢው የእስልምና ትምህርት እንዲሁም የባሕል ማዕከል ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። በተያያዘም እምነቱ ወደ ምሥራቃዊ የአገሪቱ ክፍል በመስፋፋት በተባበሩት መንግሥታት የትምርትና የባሕል ጥናት ተቋም መሰረት አራተኛዋ ቅድስት የእስልምና ከተማ በመባል ለተመዘገበችው የሐረር ከተማ ለመዳረስ ችሏል።

በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ ተከታይ ካሏቸው ሃይማኖቶች መካከል አንዱ እስልምና ሲሆን በ1999 የማዕከላዊ ስታስቲካል ኤጀንሲ ባካሔደው አጠቃላይ የሕዝብ ቆጠራ ከ25 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ 33.9 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ የእስልምና እምነት ተከታዮች እንደሆኑ ታውቋል። ይህም ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች በመቀጠል ከፍተኛውን ቁጥር የያዘ እምነት እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 27 ግንቦት 3 ቀን 2011

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com