የበዓል ድባብ የሳሳበት ፋሲካ

0
1067

ክርስትያኖች ከእሁድ ማለዳ ጀምረው ‹‹ክርስቶስ ተንስኣ እሙታን…በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን›› እያሉ የትንሣኤ በዓልን ለቀጣይ ሃምሳ ቀናት በደስታ ሲያስቡት ይከርማሉ። ምንም እንኳ በዓሉ የፍስኃና የደስታ ቢሆንም፣ ዘንድሮ በዓለም ላይ ባጠላው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት ግን ጭር ማለት ታይቷል። ገበያው፣ የአብያተ ክርስትያናት ውስጥ ምዕመናን ኅብረት፣ ኤግዚቢሽንና አውደ ርዕይ፣ ማስታወቂያውና ወዘተ አሁን ደብዝዘዋል። ሰሞነ ጾሙና ሰሞነ ሕማማቱም ለዓለም እውነተኛ ጾምና ሕማም የቀመሰችበት ይመስላል። ብዙዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፣ ብዙዎችም ዳግም ላይነቁ አሸልበዋል። ከዚህ የከፋው እንዳይመጣም ስጋቱ ይልቃል።

ታድያ በሽታውን ከመፍራት አንድም ለቤተሰብና ለታላላቆች በማሰብ፣ አንድም ስለራስ ጤንነት በመጨነቅም ቤታቸው መሆንና መጠንቀቅን የመረጡ ይታያሉ። በአንጻሩ የቤተክርስትያንን ትዕዛዝ ባለመቀበል፣ የመንግሥትን ሕግ ሰምተው ‹ጆሮ ዳባ ልበስ› በማለት በግዴለሽነት የሚንቀሳቀሱም ጥቂት አይደሉም። በዚህም ላይ የተለያዩ ሐሳብና አስተያየቶች ይነሳሉ።

የትንሣኤ በዓል አከባበርን ምክንያት በማድረግም ሰዎች አለመታዘዛቸው በርትቶ በዓሉን ለማክበር የእምነት ቦታዎችን እንዳያጨናንቁ ከወዲህ ማሳሰቢያው፣ ማስጠንቀቂያውና ተግሳጹ እየተሰማ ነው። ነገሬ ብሎ ከሰማው ይልቅ ግን በየመንገዱ የሚታየው መጨናነቅና ግርግር፣ ላይሳካ የደበዘዘውን በዓል ለማድመቅ የሚደረግ ግርግር ዋጋ እንዳያስከፍል ተሰግቷል።

የአዲስ ማለዳው ኤርምያስ ሙሉጌታ ይህን ጉዳይ በማንሳት የሚመለከታቸውን የሃይማኖት ሰዎች፣ የግለሰቦች አስተያየትና ምክረ ሐሳብን አካትቶ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

ፀደይ መዝሙር ባለ ትዳር እና የኹለት ልጆች እናት ናት። ዓመት በኣል ለፀደይ ትልቅ ትርጉም ካላቸው የሕይወት ኹነቶች ውስጥ ዋነኛው እና ትልቁ ነው። በተለይም ደግሞ በእርሷ አገላለጽ ‹‹ትላልቅ በዓላት›› ደግሞ እጅጉን አብልጣ የምትጠባበቃቸው እና የምታከብራቸው ቀናት ናቸው። ፀደይ ከልጅነቷ ጀምሮ ባደገችበት ቤተሰብ እና ማኅበረሰብ ውስጥ በዓላት ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው እና የቅርብ እና የሩቅ ቤተሰብ አንድ ላይ ሆኖ በኅብረት የሚከበር የወዳጅ ዘመድ መገናኛ ጊዜም እንደነበር ታወሳለች።

በዚህ መልኩ ላደገችው ፀደይ ታድያ የራሷን ጎጆ ይዛ ከትዳር አጋሯ ጋር መኖር ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ከወላጆቿ ቤት ይዛው ያደገችውን ተሰባስቦ በዓል ማክበር ልምዷን አጠናክራ ቀጠለች እንጂ ወደ ኋላ አላለችም።

‹‹ከቤተሰቦቼ ቤት ወጥቼ የመጀመሪያ ያከበርኩት በዓል እንቁጣጣሽ ነበር። በጣም ከመዘጋጀቴ የተነሳ በዓል የማከብር ሳይሆን ልጅ የምድር ነበር የምመስለው። ያላሟላሁት ነገር አልነበረም፣ ትልቅ ቤተሰብ እንዳለው ሰው እጅግ በጣም ብዙ የምግብ ዓይነት ነበር ያዘጋጀሁት። በጊዜው እኔ እና ባለቤቴ ብቻ ነን የነበርነው።›› ስትል ታስታውሳለች፤ ፀደይ።

ባለቤቷም እንደ እርሷ ለበዓል ያለው አመለካከት እጅግ ከፍተኛ ነበርና የመጀመሪያው በዓላቸው በሰፊ ዝግጅት የተከናወነ እና እንደ ፀደይ አገላለጽ ለአዲስ ጎጆ ወጪዎች የማይመስል የበዓል አከባበር ነበር። ‹‹በዓል በጣም ነው የምወደው፤ በተለይ ደግሞ አዲስ ዓመት እና ፋሲካ ልዩ ትርጉም የምሰጣቸው በዓላት ናቸው። ከበዓልነታቸው በተጨማሪ በተለይ ፋሲካ የመጀመሪያ ልጄን የተገላገልኩበት ልዩ ቀን በመሆኑ ለእኔ እና ለቤተሰቤ ድርብ በዓል ነው›› ትላለች።

የፀደይ ቤተሰብ ከዓመታት በፊት የነበረው የባል እና የሚስት ብቻ ኑሮ አሁን ወደ ሦስት ጉልቻ አድጎ አራት ሆኗል። ልጅ በመጣ ቁጠር ደግሞ የበዓል አከባበሩ እና መጠኑ ከፍ ወደ ማለት መጥቷል። ዘወትር በበዓላት ቀን ፀደይ እና ቤተሰቧ ቁርስ ብቻ ነው ቤታቸው የሚመገቡት።

ውሏቸው እንዲህ ነው፤ መጀመሪያ ወደ ባለቤቷ ወላጆች ቤት ይሄዳሉ። ዘመድ ወዳጅ ተሰብስቦ ይጠብቃቸዋል። የፍቅር፣ የተድላ፣ የሳቅና የጨዋታ ጊዜ ያሳልፉ እና ወደ አደገችበት ወላጆቿ ቤት ደግሞ ያቀናሉ። በዚሁም እንደ ባለቤቷ ወላጆች ቤት ሁሉ ጨዋታ፣ ሳቅ እና አብሮነቱ ይቀጥላል። ምግቡ ይስተናገዳል፣ መጠጡ ይንቆረቆራል በዓሉም እንደዚህ ያልፍና አመሻሽ ላይ ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ።

በዚህ ዓመት ግን ፀደይ እና ቤተሰቧ አንድ እክል የገጠማቸው ይመስላል። በተለይ ደግሞ በዓልን በናፍቆት ለሚጠብቅ እና ለማክበር የረጅም ጊዜ ዝግጅት ለሚያደርግ ሰው የተፈጠረው ጉዳይ አሳሳቢም አሳዛኝም ነው። ለወትሮው ከቀናት ከፍ ሲልም ከሳምንታት አስቀድማ ለመጪው በዓል ዝግጅት የምታደርገው እና አስፈላጊውን የቤት ወጪ የምትከውነው ፀደይ በቅርቡ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተከሰተውን ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሽሽት ቤቷ ከከተመች ሰነባብታለች።

ይሄ ብቻ ሳይሆን በተለይም ደግሞ ከወዳጅ ዘመድ ተለይተው በዓልን አክብረው የማያውቁት ፀደይ እና ቤተሰቧ፣ ስለ መጪው በዓል ትልቅ ዝግጅት እና ውሳኔ ለማድረግ ተዘጋጅተዋል። በሽታው አንደኛው እና ዋነኛው የማይፈልገው ጉዳይ አካላዊ መቀራረብና ጥግግትን በመሆኑ፣ በበዓል ቀን ወደ ቤተዘመድ ቤት ለመሄድና እንደቀደመው ቀን ለመጫወት፣ በአብሮነት ለማክበር የሚፈቅድ አይደለም።

በተለይ ደግሞ ፀደይ እና ባለቤቷ በዓላትን በእድሜ ወደ ገፉት ወላጆቻቸው ቤት በመሄድ በመሆኑ ያከብሩት የነበረው፣ በሽታውም በእድሜ በገፉት ላይ ስለሚበረታ ትልቅ ውሳኔ መወሰን እንዳለባቸው አስበዋል።

በዚህም መሰረት ጸደይ እና ባለቤቷ ልጆቻቸውን ጨምረው በዓሉ 20 ቀን ሲቀረው ጀምረው ራሳቸውን በቤት ውስጥ ለይተው በማስቀመጥ እና ከውጪው አካባቢ ጋር ባለመገናኘት ጤንነታቸውን ከጠበቁ በኋላ ለበዓል ወደ ወላጆቻቸው ቤት ለመሔድ በማሰባቸው፣ ከሳምንታት በፊት በቤት ውስጥ ውሸባቸውን ቀጥለዋል። አዲስ ማለዳ ይህን ጽሑፍ በምታጠናቅርበት ወቅት ጸደይን ለማግኘት በተዘጋ በር ውስጥ ተቀምጣ ከጊቢ ውጪ በመሆን ነበር ቃለ ምልልሱ ያካሄደችው።

የፀደይ እና ባለቤቷ ለበዓል ወደ ወላጆቻቸው ቤት የመሔድ ውሳኔ ታዲያ በባህር ማዶ በምትኖረው እና የባለቤቷ ታላቅ እህት ትልቅ ተቃውሞ ገጥሞታል። ወረርሽኙን እንደ ቀልድ እንዳይመለከቱት እና በእድሜ የገፉትን ወላጆችን በቀላሉ የሚያጠቃ በመሆኑ የተለመደውን የበዓል የቤተ ዘመድ ጉብኝት ማስኬድ እንደሌለባቸው በአጽንኦት መናገሯ ሌላኛው ተግዳሮት ሆኖባቸው እንዳለ ፀደይ ለአዲስ ማለዳ ትናገራለች።

‹‹ልጆችን ለበዓል አያቶቻቸው ጋር ይዘናቸው እንደምንሄድ ቃል ገብተንላቸዋል። እነርሱም በጉጉት እየተጠባበቁ ይገኛሉ። አሁን በዚህ ጉጉት ላይ ያሉትን ልጆች አትሄዱም ማለት አስቸጋሪ ነው። ከእነርሱም ባለፈ እኔም ሆንኩኝ ባለቤቴ ከዚህ ቀደም በዓላትን ብቻችንን አሳልፈን አናውቅም። በጣም ፈታኝ ጊዜ ላይ ነው ያለነው›› ስትል ሐሳቧን ትገልጻለች።

ለወትሮው በዓል በመጣ ቁጥር አስቀድመው መደረግ ያለበትን ለበዓል የሚያስፈልገውን አስቤዛ በመግዛት ዝግጅታቸውን የሚጀምሩት ፀደይ እና ባለቤቷ፣ በዚህ በዓል ግን አስቀድመው ራሳቸውን በቤት ውስጥ ለይተው በማስቀመጣቸው ግብዓት ግዢው ላይ እንኳን እየተንቀሳቀሱ አይመስልም። ‹‹እኔም ሆንኩኝ ባለቤቴ ከቤት ስለማንወጣ የቤት ሠራተኛችን ናት ወደ ገበያ እና ሱፐርማርኬት በመሄድ ለበዓል የሚሆኑትን አስቤዛ የምትገዛዛው። ግን እውነት ለመናገር እንደራሴ ስለማይሆንልኝ ከፍቶኛል። ዘንድሮ በዓል ጣዕሙን ሳላውቀው ሊያልፍ እየመሰለኝ ከወዲሁ እየከፋኝ ነው›› ትላለች ፀደይ።

በዓለም እንዲሁም ከአንድ ወር ገደማ በፊት በኢትዮጵያ የተከሰተውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተከትሎ፣ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገግ በርከት ያሉ ክልከላዎችን እና አስገዳጅ ሁኔታዎችን በማውጣት ወረርሽኙን እንደ አገር መቆጣጠር የሚቻልበትን ሁኔታ እየተገበረ ይገኛል። ከድንጋጌዎች አንዱ ደግሞ አራት እና ከዛ በላይ ከሆኑ የቤተሰብ አባላት ውጪ በአንድ ስፍራ መገኘት የተከለከለ ነው ሲል የሚለው ይገኝበታል። ይህ ታዲያ በኢትዮጵያ የአኗኗር ዘይቤ እና በተለይም ደግሞ የበዓል አከባበር ባህል ጋር የሚቃረን እንደሆነ የባለታሪካችንን ነባራዊ ሁኔታ አንደኛው ማሳያችን ነው።

መንግሥት ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ የተደነገገውን የአካላዊ ርቀትን በሚመለከት ምን አስተያየት እንዳላት አዲስ ማለዳ ባለታሪካችን ፀደይን ጠይቃት ነበር።

መልሷ እንዲህ ነው፤ ‹‹ሕጉ ጋር ምንም አይነት ተቃውሞ አይኖረኝም። ነገር ግን በቤተሰብ መካከል ከአራት ሰው በላይ አንድ ላይ መቀመጥ እንደ ሌለበት ያውም በኹለት ሜትር ልዩነት የሚለው እጅግ የተጋነነ እርምጃ ይመስለኛል። አውቃለሁ ጉዳዩ አሳሳቢ ነው። በዓለም ዐቀፍ ደረጃም እያደረሰ ያለውን ጉዳይም አውቃለሁ። ግን ኹሉም ለቤተሰቡ ሲል መጠንቀቁ ስለማይቀር በቤተሰብ መካከል የሚኖረውን መራራቅ ትንሽ ቢያለዝበው እላለሁ። ምክንያቱም በእኔ ቤተሰብ እንኳን ባይሆን በሌሎች ሰዎች ቤተሰብ ውስጥ የላላ የቤተሰባዊ ግንኙነት በመኖሩ ይባሰ ማኀበራዊ ግንኙነቱን ሊበጥሰው ስለሚችል እና ከወረርሽኞች በኋላ ደግሞ ሌላ ማኅበራዊ ቀውስ ውስጥ እንዳንገባ የሚል ሐሳብ አለኝ››

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ መከሰቱን ተከትሎ በርካታ ሕጎች እና ተፈጸሚነት ያላቸው መመሪያዎች በመንግሥት በኩል ሲተላለፉ ሰነባብተዋል። በተለይም ደግሞ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በይፋ ከመታወጁ በፊት የወጡት እና በኋላ ላይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውስጥ የተካተቱት ሕገ ደንቦች በብዛት ሕዝብ በተሰበሰበባቸው አካባቢዎች መገኘት እንደማይቻል እና ገበያዎች አካባቢም ሰዎች ሲገበያዩ አካላዊ ርቀታቸውን ጠብቀው ንክኪ በሌለበት መልኩ እንዲከውኑ የሚያሳስበ ነው።
ይህንንም ለመተግበር ከሳምንታት በፊት በአዲስ አበባ ትልቁ አትክልት ገበያ በተለምዶ አትክልት ተራ ተብሎ የሚጠራው ስፍራ ቀድሞ ከነበረበት ፒያሳ እና መርካቶ አካፋይ ቦታ በከተማ አስተዳደሩ እንዲነሳ በመደረግ ወደ ጃን ሜዳ እንዲዛወር ተደርጎ ነበር። ይሁን እንጂ ይህም አዲስ ማለዳ በስፍራው ባደረገችው ቅኝት የሰው አካላዊ ጥግግት ከመቼውም በላይ እንደጨመረ እና ለግብይት አመቺ አለመሆኑን ለመታዘብ ችላለች።

በሌላ በኩል ደግሞ በበዓላት ወቅት ይደረጋል ተብሎ ከሚጠበቀው የገበያ ዓይነት አንዱ የቁም እንስሳት ግብይት ሲሆን፣ በዚህ በዓል እምብዛም አይስተዋልም። በተለይ ደግሞ ለወትሮው በፋሲካ በዓል በሰሞነ ሕማማት ሳምንቱን ሙሉ የከተማውን ዋና ዋና መንገዶች ዘግተው አላሳልፍ የሚሉት በግ እና የፍየል እንዲሁም የበሬ መንጋዎች በዘንድሮው በዓል አይታዩም ወይም የሉም ቢባል ይቀላል።

‹‹በዓልን ከለመድከት ውጪ አላከብርም። ብኖርም ብሞትም ተደስቼ መሆን ይኖርበታል›› በሚል አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ የሰጡት ሳሙኤል ዘለቀ፤ ከሳምንት አስቀድመው ከደብረ ብርሃን ከተማ ትልቅ ሙክት ገዝተው መምጣታቸውን እና ስለ ወረርሽኙ እምብዛም እንደማይጨነቁ ያስረዳሉ። ‹‹የበሽታውን ጉዳይ እኮ አለመስማት አይቻልም። ቴሌቪዥኑ ሁሉ የሚያወራው ስለዚሁ አይደል?!

ግን እኔ አልጨነቅም። ከሞትኩም ሆነ ከኖርኩም መደሰት ይኖርብኛል። ተጨንቄ የማመጣው ነገር ባለመኖሩ የተለመደው ሕይወቴን እና የበዓል አከባበሬን እቀጥላለሁ። ግን ትንሽ የሚከብደው እኔ እንኳን ባልጨነቅ ሌላው ሰው ስለተጨነቀ እና መንግሥትም ትዕዛዝ ስላስተላለፈ ለበዓል የሚሆኑ ነገሮችን ለመግዛት እንደልብ አይገኝም›› ሲሉ ይናገራሉ።

አዲስ ማለዳ በተዘዋወረችባቸው አካባቢዎች የበዓል ግብይቱን በሚመለከት ለመታዘብ ሞክራለች። በተለይም ደግሞ ከዚህ ቀደም በበዓል ሰሞን ሞቅ ደመቅ የሚሉ አካባቢዎች ላይ ዳሰሳዋን አካሂዳለች። በቦሌ እና አካባቢው ለወትሮው የበዓል ሰሞን ንግድ ቤቶች ትላልቅ ድምጽ ማጉያዎችን በመጠቀም እና በተለያዩ ጌጣጌጦች ሕንጻዎቻቸውን በማስጌጥ ገበያ የመሳብ ሽር ጉዳቸውን ያሰሙ ነበር። በዘንድሮ ፋሲካ ግን እነዚሁ የገበያ ማእከላት ከአዘቦት ቀናት በቀዘቀዘ ድባብ በዓሉን ለመቀበል የተዘጋጁ ይመስላሉ።

ከቦሌ መድኃኒዓለም ወደ 22 ማዞሪያ የሚወስደውን መንገድ ተከትለን ስንጓዝ በመንገዱ ግራ በኩል ተሰድረው የሚታዩት በአብዛኛው የሴቶች የልብስ መሸጫ መደብሮች በመብራቶች ደምቀው እና በደንበኞቻቸው ተጨናንቀው ቀናትን በተለይም ደግሞ በዓላትን እንዳላሳለፉ፣ አሁን ግን በቀን እንኳን ገብቶ የሚጎበኛቸው ሰው በማጣት የደንበኛ ናፍቆት ላይ ይገኛሉ።

የሰዎች እንቅስቃሴን መገታት ተከትሎ በበዓል ድባቡ ላይ መቀዛቀዝ እንደሚኖር የሚናገሩት የምጣኔ ሀብት ምሁሩ አጥላው ዓለሙ (ዶ/ር)፣ በአንድ አገር ምጣኔ ሀብት ላይ ትንሽ የንግድ አንቅስቃሴ ወይም ትልቅ የንግድ እንቅስቃሴ ብለን ብንከፍለው እንኳን የአንዱ መቀዛቀዝ ለሌላኛው መፍዘዝ ምክንያት ይሆናል ሲሉ ይናገራሉ። በመጪው በዓልም በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተከሰተው የምጣኔ ሀብት ድቀት ኢትዮጵያንም የማይነካበት ምንም ምክንያት ባለመኖሩ፣ በእርግጥም የተቀዛቀዘ አውደ ዓመት ይሆናል ብለው እንደሚያምኑ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ ከበዓል አከባበሩ እና ከኢትዮጵያውያን አኗኗር ዘይቤ በመነሳት በመንግሥት በኩል የተላለፈውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተመለከተ ምን ያህል ተግባራዊ ይሆናል የሚለውን ጉዳይም አንስተናል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሥነ ሰብእ ትምህርት ክፍል ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት የራስወርቅ አድማሱ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ሐሳባቸውን ይገልጸሉ።

‹‹ሲጀመር በአንድ ጊዜ ሰውን የለመድከውን ነገር አቁም ሲባል ግራ መጋባት እና መሸበር ሊሰማው ይችላል። ሆኖም ግን ሁኔታው አስገዳጅ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ በመንግሥት የተላለፈው ጉዳይ እጅግ አስፈላጊ ነው፤ መተግበርም ይኖርበታል። በእርግጥ እኛ ኢትዮጵያውያን ከአኗኗራችን ተነስተን አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የደነገጋቸው ሕግጋት በበዓል ላይ ይተገበራሉ ወይ ብሎ ማሰብ ትንሽ የሚከብድ ነው።›› ሲሉ አስተያየታቸውን ይሰነዝራሉ።

የራስወርቅ በተደጋጋሚ ከሚያነሷቸው ጉዳዮች አንዱ እና ዋነኛው ደግሞ በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለው የመረዳዳት ባህሉ በረጅም ዘመናት የተገነባ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በአንድ ጊዜ ያውም በሳምንታት ደረጃ አቁመው ሲባል ሊሰማው የሚችለውን ሥነ ልቦናዊ ችግር መገመት አያዳግትም ሲሉ ያስረዳሉ። ቀጥለውም በበዓል ወቅት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በተለይም ደግሞ ቤተ ዘመድ ጋር ያለውን አብሮ ተካፍሎ፤ ተደስቶ ለሚውል ማኅበረሰብ ቤት ቆይ ሲባል አሻፈረኝ ማለቱ እና መንቀሳቀሱ እምብዛም የሚደንቅ ነገር እንዳልሆነም ያስረዳሉ።

የራስወርቅ በዚህ በዓል ኅብረተሰቡ ለጥቂት ጊዜ በመንግሥት የወጣውን ሕግ የማክበር ግዴታ ያለበት ቢሆንም ነገር ግን በአመዛኙ ይተገብረዋል ብለው እንደማያስቡ ለአዲስ ማለዳ ይናገራሉ። ‹‹እኔ በበኩሌ ሰው ወይም ወዳጅ ዘመድ ወደ መኖሪያዬ እንዳይመጣ እፈልጋለሁ። ጥላቻም አይደለም። ግን ለኹላችን በመልካም ጤንነት መኖርና ደኅንነት ሲባል መራራቁን ለትንሽ ጊዜ መተግበሩ ጠቃሚ ነው ብዬ አስባለሁ። ነገር ግን አብዛኛው ሰው ዘመዱ ወይም የቅርብም ሆነ የሩቅ ወዳጁ በወረርሽኙ የሚጠቃ ስለማይመስለው መገናኘቱን እና አብሮ በዓል ማሰላፉ የማይቀር ነው›› ሲሉ ይናገራሉ።

አዲስ ማለዳ ከሰሞነ ሕማማት መጀመሪያ ቀን ዋዜማ ላይ በሚከበረው የሆሳዕና በዓል ላይ ቁጥሩ በርከት ያለ ምዕመን በተለያዩ ደጀ ሰላሞች ላይ ተሰድሮ ጸሎት ሲያደርስ አስተውላለች። በተዘዋወረችባቸው ቦሌ መድኃኒዓለም እና ሰኣሊተ ምህረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስትያን ቁጥሩ የበዛ ምዕመን ሃይማኖታዊ ስርዓቱን ሲፈጽምም ታዝባለች።

በእርግጥ የአብያተ ክርስትያናት ደጅ ዝግ ከመሆኑ እና ወደ ውስጥ ለመግባት የማይቻል መሆኑን ለመታዘብ ቢቻልም፣ የተጠቀሱትን አብያተ ክርስትያናት አጥር ተከትሎ በርካታ ሕዝበ ክርስትያን ማኅበራዊ ጥግግት በታየበት መልኩ ሲመላለስ ይታይ ነበር። ከዚህም ባለፈ እንደ ቀደመው እና መደበኛው ጊዜ በአካባቢው ጥቃቅን ዕቃዎችን የሚቸረችሩ ግለሰቦችንም ለማየት ችላለች።

ከዚህም ባሻገር በተለይ በተለይ ምዕመናን በተለያዩ የመገናኛ ብዙኀን ሲነገር የነበረውን እና መልዕክትም ሲተላለፍበት የነበረውን የአብያተ ክርስትያናትን ደጅ መሳለም ባልተፈቀደ መልኩ እና በመንግሥትም በሃይማኖት አባቶች በኩል የተላለፈውን መልእክት ችላ ባለ መልኩ ነው ሲከውኑ የነበረው። ለወረርሽኙ መስፋፋት እጅግ ምቹ ሁኔታን በፈጠረ መንገድ ሲከበር የነበረው ሆሳዕና፣ በቀጣይ እስከ ዳግማዊ ትንሣኤ ባሉት ቀናትም ቀጣይነት ይኖረዋል የሚሉ ስጋቶች ከአስተያየት ሰጪዎች ዘንድ ይደመጣል።

በሰዓሊተ ምህረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስትያን ከበዛው ምዕመን ራሷን ገለል አድርጋ በቅርብ ርቀት ጸሎት ስታደርስ ወደነበረች ወጣት አዲስ ማለዳ በመቅረብ አስተያየቷን ተቀብላለች። ልዋም ኃይሉ ትባላለች። ‹‹ሰው ይኖራል ብዬ አልገመትኩም፤ እንዲህ መሆኑን ባውቅ አልመጣም ነበር። ሰው ጭራሽ እየተነገረው ያለውን ነገር ከግምት ውስጥ ያስገባ አይመስልም። በተለይ ደግሞ በመግቢያ በሮች ላይ ተጠጋግቶ ጸሎት የሚያደርጉት ለበሽታው ግዴለሽነታቸውን እንጂ እምነታቸውን እያየሁ አይደለም።›› ስትል አስተያየቷን ትሰጣለች።

ልዋም በተለይም ደግሞ ሕዝቡ በቀጣይ ለሚኖሩት በዓላት ማኅበራዊ ርቀቱን ጠብቆ እና ወረርሽኙን ተከላክሎ ያከብራል ብላ ለማሰብ እንደምትቸገርም ለአዲስ ማለዳ አልሸሸገችም። መጪውን የትንሣኤ በዓል ከቤተሰቧ ጋር ከቤት ሳትወጣ እንደምታከብረው ከወዲሁ ወስናለች። በተለይም ደግሞ በዕድሜ ወደ ገፉት እናት እና አባቷ ቤት ላለመሄድ እንደወሰነች ትናገራለች።

‹‹ወላጆቼ ዕድሜያቸው ገፍቷል። በተለይ አባቴ ደግሞ የስኳር በሽተኛ ነው።

ለዚህ በእኔ ምክንያት በሽታው ይዞት ለከፋ አደጋ እንዲጋለጥ ስለማልፈልግ ከባለቤቴ ጋር ተስማምተን ቤታችን ውስጥ ለማክበር ወስነናል። በተለይ ደግሞ ባለቤቴ ከብዙ ሰዎች ጋር የሚያገናኘው የሥራ ዘርፍ ላይ በመሰማራቱ በበሽታው ቢጠቃ እንኳን በመጀመሪያ ደረጃ እሱን ከፍ ካለም እኔንም ጨምሮ ሊያጠቃ እና እኛ ላይ ብቻ ሊቆም ይችላል። ነገር ግን በዓል እና አውደ ዓመት በሚል ሰበብ ከወዳጅ ዘመድ ጋር በተገናኘን ቁጥር ግን ልናበዛው እንችላለን›› በሚል አፍ እና አፍንጫዋን አፍና በለሆሳስ በሚሰማ አነጋገሯ ለአዲስ ማለዳ አስተያየቷን ሰጥታለች።

የሥነ ልቦና ባለሙያዋ ዶክተር ኢየሩሳሌም ኃይሌ ለአዲስ ማለዳ ሲናገሩ፤ በኅብረተሰቡ ዘንድ ይፈጠራል ተብሎ የሚገመተው እና የወጣውን የመንግሥት አዋጅ ያለማክበር ሂደት ጤነኝነት ነው ሲሉ ይጅመራሉ። ‹‹ሰው ማኅበራዊ እና አእምሯዊ መረጋጋቱ የሚጠበቀው እኮ ከማኅበረሰቡ ጋር በሚኖረው መስተጋብር እና የስምምነት ኑሮ ነው። ስለዚህ ይህን ኹሉ በገነባበት እና ለመኖሩ ሕልውናው የሆነውን ማኅበራዊ መሰረት በአንድ አዳር ልናድብህ ስትለው አሻፈረኝ ማለቱ ጤነኝነቱ ነው። ነገር ግን የበዛው አለመታዘዝ ከጤነኝነት ያልፋል። ቢሆንም ግን በመንግሥት ደረጃ ታውጇል እና መታዘዝ ተገቢ ነው።

በተለይም ደግሞ ዓለምን ባሸበረው እና የብዙዎችን ሕይወት እየቀጠፈ ባለው ወረርሽኝ እንኳን በአገራችን ታይቶ እና ሰዎችን ለኅልፈት ዳርጎ ይቅርና ባይሆንም እንኳን በአካላዊ መራራቅ ልንፋለመው ይገባል። በእርግጥ እንደ ማኅበረሰብ ሊከብድ ቢችልም ከአኗኗር አንጻር ግን ግድ ሊተገበር የሚገባው ተግባር ነው›› ብለዋል።

በተለይ በኅብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸው ሰዎች፣ የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦች በተደጋጋሚ የሚያስተላልፉት መልዕክት እጅግ ጠቃሚ እንደሆነና ኅብረተሰቡን ከማንቃትና ከማስተማር አንጻር ከፍተኛ የሆነ ጠቀሜታ እንዳለው ዶክተር ኢየሩሳሌም ያስረዳሉ።

በበሽታው በኩል የሕዝቡን ንቃተ ሕሊና ከፍ ለማድረግ በሌሎች አገራት እንደምንሰማው ዘግናኝ ቁጥር ያለው ሞት ቁጥር መመዝገብ የለበትም የሚሉት ኢየሩሳሌም፤ ከሌሎች ልምድ ወስደን ለመጠንቀቅ ጊዜ መፍጀት የለብንም ሲሉም ያስገነዝባሉ። በሙያቸው እጅግ ከባድ የሥነ ልቦና ችግር አጋጥሟቸው የሚመጡ ሰዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ መብዛታቸው የታዘቡት ባለሞያዋ፣ አብዛኞቹ ከሰው ተገልለው መቀመጣቸው ራሱን የቻለ የድብርት ስሜት ውስጥ እንደከተታቸው አረጋግጠዋል።

አዲስ ማለዳ በ75ኛ ዕትሟ እንግዳ አድርጋ ካቀረበቻቸው የሥነ አዕምሮ ረዳት ፕሮፌሰር ማጂ ኃይለማሪያም አስተያየት ለመረዳት እንደተቻለው፤ በቤት ውስጥ ሰዎች ሲቀመጡ ጭንቀት እና ድባቴ ሊሰማቸው እንደሚችል የታመነ በመሆኑ፤ በጠዋት ሌላ ጊዜ ወደ ሥራ በሚሄዱበት ወቅት በሚነሱበት ሰዓት መነሳትና ፒጃማቸውን ቀይረው በቤት ውስጥ የሚሠሩ ሥራዎችን በመሥራት ጊዜያቸውን ማሳለፍ እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።

አዕምሯቸውንም ለማሳረፍ በሥራ መጥመድ እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል። ከዚህም ባለፈ ለምን ድባቴ ወይም ጭንቀት ተሰማኝ ማለት ለበለጠ ችግር ሊያጋልጥ የሚችል ሌላኛው ጉዳይ ነው ያሉት ማጂ፤ ድባቴ መሰማቱ ትክክል እንደሆነ እና ሰው የለመደው ሲቀርበት ሊደብተው፣ ሊነጫነጭ እና አዳዲስ ፀባይን ሊያሳይ እንደሚችል የሚገመት እንደሆነ ያስረግጣሉ።

በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለውን የበዓል አከባበር እና መደረግ ያለባቸውን ተግባራት ከመንፈሳዊ ጉዳዮች አንጻር በማየት አስተያየታቸውን የሰጡት ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን የውጪ ጉዳዮች አማካሪ መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል ናቸው። መምህር ዳንኤል እንደሚሉት፣ ሃይማኖት ጠንካራ እና የማይለወጡ ተግባራት ቢኖሩትም ሃይማኖትን መሰረት አድርገው ባህል የሆኑ ነገሮች ግን እንደየ ሁኔታው እና እንደ አጋጣሚዎች ሊለዋወጡ ይችላሉ ይላሉ።
‹‹በሃይማኖት ስርዓት ውስጥ በወጀብ፣ በአውሎ ንፋስ እንዲሁም አሁን ባለንበት ቸነፈር እና ወረርሽኝ ወቅት ያለ ምንም ማጓደል የሚፈጸሙ ተግባራት አሉ። እነዚህ ስርዓቶች ታዲያ የአተገባበራቸው ሁኔታ ይለወጥ እንደሆነ እንጂ በምንም ተአምር አይተዉም። ቅዳሴ፣ ጸሎት እና የመሳሰሉት በየትኛውም ሁኔታ እና ዘመን ተሁኖ ለአምላክ የሚደርሱ መስዋዕቶች በመሆናቸው ሁኔታዎች አያግዷቸውም።

ነገር ግን አሁን በአውደ ዓመት ከወዳጅ ዘመድ ጋር በኅብረት መብላት እና መደሰት አመቺ ባልሆኑ ሁኔታዎች ሊቀሩ ይችላሉ። በእርግጥ የተቸገረን መርዳት እና ያለው ከሌለው ጋር ተካፍሎ መብላት ፈጣሪን ደስ የሚያሰኝ ተግባር ነው። ይህንም በጥንቃቄ እና አሁን በዓለም ላይ የተከሰተውን ወረርሽኝ በማያባብስ መልኩ መከወን ይቻላል›› ሲሉ ሐሳባቸውን ይሰነዝራሉ።

በተለያዩ ዓለማት ከቀናት አስቀድሞ ፋሲካ በዓል ተከብሯል። በተለይም ደግሞ በምዕራባውያን በድምቀት የሚከበረው ፋሲካ በዘንድሮ ዓመት ጭር ባለ አኳኋን ነበር የተከበረው። ፋሲካ ወይም በምእራባዊያን ሥያሜ ‹‹ኢስተር›› በምዕመናን በተሞላ ቤተ መቅደስ ውስጥ ነበር ከዚህ ቀደም የሚከበረው። ይሁን እንጂ በዚህ ዓመት በጣት ከሚቆጠሩ ጥቂት የአብያተ ክርስትያናቱ አገልጋዮች ውጪ ምንም ምእመን በሌለበት ሁኔታ ነው የተከበረው።

አዲስ ማለዳ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ፓትርያርክ ጽሕፈት ቤት ባገኘችው መረጃ ዘንድሮ ፋሲካም እንደ ከዚህ ቀደሙ በምዕመናን ታጅቦ የሚከበር እንዳልሆነ እና አካላዊ ርቀትን በጠበቀ መልኩ በጥቂት ሰዎች የሚከወን እንደሚሆን ታውቋል። ይህ ደግሞ በመንግሥት እና በቤተ ክርስትያኒቷ አማካኝነት ወረርሽኙን ለመግታት ከወጣው እርምጃ አንጻር ተገቢ ነው ብለው እንደሚያምኑም ከጽሕፈት ቤቱ ለአዲስ ማለዳ የደረሰው መልዕክት ያመላክታል።

በተመሳሳይም የወንጌላውያን አብያተ ኅብረት ፕሬዘዳንት ፓስተር ጻዲቁ አብዶ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ሕዝበ ክርስትያኑ ከዚህ ቀደም በየአጥቢያ ቤተ ክርስትያኑ ፈጣሪውን በማመስገን የአዳር መርሃ ግብር እንደሚያደርግ ጠቁመዋል። በዚህ ወቅት ግን ፈጽሞ እንደማይቻል እና በየቤቱ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ማክበር እንደሚገባ አሳስበዋል።

ይህ ሲሆን ግን ከእምነት ጋር የሚጋጭ ምንም ነገር እንደሌለ እና አማኞችም ይህን ተገንዝበው በመንግሥት ለወጣው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተገዢ እንዲሆኑ አሳስበዋል። በምድራዊ ሕግ መታዘዝን እግዚአብሔር የሚወደው ጉዳይ እንደሆነ እና ቤት አትውጡ፣ አካላዊ ርቀታችሁን ጠብቁ እና የመሳሰሉትን ትዕዘዛት ከመንግሥት የተሰጡትን መጠበቅ ይኖርብናል ሲሉ ያስገነዝባሉ።

በጉርድ ሾላ ሰዓሊተ ምህረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስትያን ደጅ ላይ ያገኘናት ልዋምን እዚህ ላይ እናምጣ እና በዚህ ዓመት የሚከበረው በዓል እንደ ቀደሙት ጊዜያት ደምቆ ሊከበር ይችላል የሚል እምነት እንደሌላት ጠቅሳለች። ነገር ግን በአገር ብቻ ሳይሆን በዓለም ሁሉ ላይ የመጣ መከራ በመሆኑ ኹሉም በየዕምነቱ ፈጣሪውን በመፈለግ እና ምህረትን በመፈለግ ሊያሳልፈው እንደሚገባ ታስገነዝባለች።

‹‹በእርግጥ እንደዚህ አይነት ሁኔታ ሲፈጠር ሰው ምን እንደሚያደርግ ግራ ሊገባው ይችላል። ግን በቃ! አድርጉ የተባለውን ማድረግ ምንም ኹለተኛ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው›› ስትል ትገልጻለች።

እንደ ልዋም ሁሉ አዲስ ማለዳ በገበያ ስፍራዎች እና በቀደሙት ዓመታት አውደ ዓመት ሲመጣ ሞቅ ደመቅ ወደሚሉ አካባቢዎች ተንቀሳቅሳ ነበር። ያነጋገራቻቸውም ሰዎች ተመሳሳይ ሐሳብ ነው የሚያንጸባርቁት። ዘንድሮ የተለየ በዓል እንደሆነ እና ምናልባትም በሕይወት ዘመናቸው እንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች እንደሌሉ ጠቅሰዋል። ካሉም ከአንድ ወይም ኹለት ጊዜ እንደማይበልጡ ይናገራሉ።

የቀደመው ትዝታቸው እና የበዓል አከባበር ጀብዳቸውን በዐይነ ሕሊናቸው እየቃኙ ‹ቀዝቅዟል› ያሉትን በዓል ለመቀበል እንደ አቅማቸው በተፈቀደላቸው እንቅስቃሴ እና አካላዊ ርቀት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 76 ሚያዝያ 10 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here