በኢትዮጵያ የሕግ ታሪክ በተለያዩ ጊዜያት የፍትህ ሥርዓትን ለማሻሻል ጥረቶች ቢደረጉም ከሕግ የበላይነት አንጻር ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጣ ሂደት ግን አልነበረም። የፍትህ ስርዓቱ ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ አሠራሮች ቢተገበሩም፣ ይህም ኢትዮጵያን በዴሞክራሲ ግንባታ ያሻሻላት እንዳልሆነ አባድር መሐመድ* እና ፋሲካ ዓለሙ** አንስተዋል። ባለፉት ኹለት ዓመታት በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የሕግና የፍትህ ስርዓት የለውጥ ሂደቶችን ይልቁንም በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ስር በተቋቋመው የሕግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔና በለውጥ ሂደቱ ላይ እየተከናወኑ ያሉ ውጤታማ ተግባራትን ዳስሰዋል።
‹እንቁላል ሰብሮ ሊወጣ ይችላል እንጂ ሰብሮ መግባት አይችልም› እንደሚባለው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ለውጦች ላይመለሱ መጥተዋል። ባለፉት ዐስርተ ዓመታት በኢትዮጵያ የተለያዩ የማኅበረሰቡ አካላት በተለያዩ ጊዜያት የተቃውሞና የለውጥ ጥሪ ይዘው ቢነሱም፤ በሐምሌ ወር 2006 የጀመረው ወጣት መር እንቅስቃሴ በመጨረሻ አዲስ የፖለቲካ ምህዋር እንዲፈጠር አድርጓል።
የዚህ ንቅናቄ ውጤት የሆነውና የለውጥ ጥያቄዎችን ለመመለስ የተነሳው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር በሚያዝያ 2010 ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ በቀደመው ጊዜ ለተፈፀሙ የሰብዓዊ የመብት ጥሰቶች ይቅርታ በመጠየቅ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን በይቅርታና ምህረት በመልቀቅ፣ በመገናኛ ብዙኀንና በበይነመረብ ላይ የነበሩ ገደቦችን በማንሳት፣ በሽብርተኝነት የተፈረጁ የፖለቲካ ድርጅቶችን ከሽብርተኝነት መዝገብ በማውጣት እንዲሁም በስደት የነበሩ ጋዜጠኞች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎችና የመገናኛ ብዙኀን ተቋማት ወደ አገራቸዉ እንዲገቡ በመፍቀድ አፋጣኝ የአጭር ጊዜ የመፍትሄ እርምጃችን ወስዷል።
ይህ ጽሑፍ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ኹለት ዓመታት ውስጥ እየተከናወኑ ያሉ የሕግና የፍትህ ስርዓት የለውጥ ሂደቶችን በተለይም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ስር በተቋቋመው የሕግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔ አማካኝነት እየተለወጡ ያሉ አሳሪና አፋኝ ሕጎችን በተለይም በለውጥ ሂደቱ ላይ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን የሚዳስስ ነው። ጽሑፉ ድርብ ዓላማ ያለው ሲሆን በአጠቃላይ በአማካሪ ጉባዔው ስር እየተከናወኑ ያሉ የሕግና የፍትህ ስርዓት የለውጥ ሂደቶች ለአንባቢያን መሰረታዊ የሆነ ፅንሰ ሐሳብ ከመስጠት አልፎ የሕግ ስርዓት ለውጥ ሂደቱ ውጤታማነት ላይ ትንታኔ ያቀርባል።
የ1987 የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥትና የሕግና የፍትህ ስርዓት ማሻሻል ሂደት
በ1983 የደርግ መንግሥትን የጣለው የኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ መራሹ ጥምረት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ በተለይም በኅብረተሰባዊ ፖለቲካ ቅኝት ስር የነበሩ ሕጎችን በተጨማሪም የሕገ-መንግሥት ስርዓት ለመገንባት የሚያስችሉ አንዳንድ የሕግና የፍትህ ስርዓት የለውጥ ሂደቶች ተከናውነዋል። በዚህም የአገሪቱ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ አቅጣጫ ለውጦች የታዩበት ነው ማለት የሚያስችል ነው።
በ1987 የተደነገገው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥት አገሪቱ የምትከተለው የፌዴራሊዝም ስርዓት መሆኑን በመደንገግ በስርዓቱ ውስጥም የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት በራሳቸው የሥልጣን እርከን ውስጥ ሕገ-መንግሥቱን የማይቃረኑ ሕጎች የማውጣት እና ተግባራዊ የማድረግ ሕገ-መንግሥታዊ መብት አጎናጽፎችዋል። የተዘረጋው ስርዓት በተግባር ፌዴራላዊ መሆኑ ላይ ብዙ ምሁራዊ ጥያቄና ሂስ ቢነሳም በአዲሱ መዋቅር የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት በየፈርጃቸው የየራሳቸውን የሕግና የፍትህ ስርዓት ለውጦችን አካሄደዋል።
ምንም እንኳን 1940 እና 50ዎቹ የኢትዮጵያ የሕግ ታሪክ እንደነበረው አንድ ግዙፍና ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጣ የሕግና የፍትህ ለውጥ ሂደት ያልተካሄደ ቢሆንም፣ በተለያዩ ጊዜያት የፍትሕ ስርዓቱን የሚያሻሽሉ ጥረቶች ተደርገዋል።
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥት መኖሩ ራሱ ከፍተኛ የሕግ ስርዓት ለውጥ ሥራ ሆኖ ሳለ፣ በሕገ መንግሥቱ ስር በመጀመርያ የተተገበረው ደርግ ያወጣቸውን በሶሻሊዝም የተቃኙ የመሬት ይዞታ ሕጎች ቀይሮ የመሬትን ይዞታ ሪፎርም ማካሄድ ነው። ይህ ሂደት በመንግሥትና ገበሬዎች መሃል የነበሩትን ግንኙነቶች እንዲሁም አዲስ የ‹አሸናፊና ተሸናፊ› ውቅሮችን በመፍጠሩ ከፍተኛ ውዝግብ አስነስቶ ነበር። ይህን ተከትለው የመጡት የሕግና ፍትሕ ስርዓት ማሻሻያ ሂደቶች ሰፋ ያለ ይዘት ያላቸው ሲሆን የተለያዩ የሲቪል ሰርቪስ፣ የሕግ አውጪ አካላት፣ የፍርድ ቤቶች እና የተለያዩ የሕግ አስፈጻሚ አካላት ማሻሻያ ሂደቶች በተዘበራረቀ መልኩ ተካሂደዋል።
ከ90ዎቹ ጀምሮ አቅም ግንባታ ሚኒስቴር እና በየፍትህና የሕግ ስርዓት ምርምር ኢንስቲትዩት መዋቅር ስር የሕግና ፍትሕ ስርዓት እንዲሁም የተለያዩ የለውጥና ማሻሻል ሥራዎች አጠቃላይ በሆነና በተቀናጀ መልኩ መጀመራቸው ይታወሳል።
በዚህ መዋቅር ስር የተለያዩ የፍትህ ሪፎርም፣ የአቅም ግንባታ፣ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን (GTP)፣ የፐብሊክ ሴክተር አቅም ግንባታ (PSCAP)፣ መሠረታዊ የሥራ ሂደት ለውጥ (BPR) እና የመሳሰሉት የፍትሕ ስርዓቱ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጽዕኖ የሚያሳርፉ ፕሮግራሞች ተተግብረዋል። እነዚህ ፕሮግራሞች በጥቅሉ ሲታይ በፍትህና በፍትህ ሴክተሩ ቴክኒካዊ መሻሻልና አገራዊ አቅምን ቢገነቡም፣ ፕሮግራሞቹ በጽሑፍ ቃል ከሚገቡት ከሕገ መንግሥታዊነት፣ ከሕግ የበላይነት ከሰብዓዊ መብቶችና ከዴሞክራሲ ግንባታ አንጻር ግን ኢትዮጵያ እየተሻሻለች አልነበረም።
የሕግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤ መቋቋም
ከላይ የተቀመጡት ሂደቶች በኢትዮጵያ የሕግና የፍትህ ስርዓት የለውጥ ሂደት ውስጥ አመርቂ የሚባሉና በአሁኑ ወቅት ላሉት የስርዓቱ ተዋናይ ተቋማት መሠረትን የጣሉ የሕግ ስርዓትና ማኅበራዊ ለውጦች ናቸው። ሆኖም የተቋማዊ መዋቅራቸውና የተቋቋሙበትን ዓላማ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከማረጋገጥ አንፃር መሰረታዊ ድክመቶች የነበሯቸው መሆኑ እሙን ነው።
ከእነዚህ ድክመቶች ዋነኛው በተለይም ከሰብዓዊ መብት አከባበር፣ ከሕግ የበላይነትና ከዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አንጻር ውስን ውጤቶች መኖራቸውን መካድ ባይቻልም፣ መንግሥት ለእነዚህ ውጤቶች በዋናነት ጣርያ ያበጀላቸው መሆኑ ነው። በሌላ አነጋገር መንግሥት ሰብዓዊ መብትን፣ የሕግ የበላይነትና ዴሞክራሲ ግንባታን የሚቀበለው አምባገነናዊ የፖለቲካ መዋቅሩን እስካልተቀናቀኑ በመሆኑ፣ የሚደረጉት የለውጥ ሙከራዎች ከተወሰነ ገደብ ማለፍ አለመቻላቸው የግድ ነበር።
ይህ አልበቃ ብሎ በተለይ ከምርጫ 97 በኋላ መንግሥት የሕግና ፍትሕ ስርዓቱን አገዛዝ ስርዓት ማጠናከሪያ አድርጎ በመንቀሳቀሱ ምክንያት የፍትህና የፍትህ ስርዓት ለውጥ ተቋማት በአብዛኛው የሰብዓዊ መብት፣ የሕግ የበላይነትና የዴሞክራሲ መከርከምያ ዋነኛ መሣርያ ሆነው አገልግለዋል።
በቅርቡ ከተካሄደው የፖለቲካ ለውጥ በፊት መንግሥት ሆን ብሎ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ ፍትህና የሕግ ምርምር እና ሥልጠና ኢንስቲትዩት እና የተለያዩ የክልል የፍትህ ተቋማት ነባራዊ ሕግጋትን ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ አንጻር እንዲቃኙና እንዲቀይሩ የማድረግ ሂደት ውስጥ እንደነበር ይታወቃል። የነበረው መንግሥት የአገሪቱን ቢሮክራሲ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲና ከፓርቲ አባልነት ማቆራኘቱ በአገሪቱ የረጅም ጊዜ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖረው የማያጠያይቅ ቢሆንም፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ በሕጎች ውስጥ እንዲሰርጽ የነበረው ተነሳሽነት ተሳክቶ ወደ ተግባር ቢቀየር ኖሮ የለውጥ ሂደቱ ፈታኝነት ከፍ ያለ ደረጃ ሊደርስ ይችል ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከመጀመሪያ የምክር ቤት ንግግራቸው ጀምሮ መንግሥት አሳሪና አፋኝ ሕጎችን ለመለወጥ ቃል የገቡበትና በሂደትም የፍትህና የሕግ ስርዓት ለውጥ በማካሄድ የአገሪቱን የዴሞክራሲ ስርዓትና የሕግ የበላይነት ብሎም የሰብአዊ መብት አከባበርን የሚያጠናክሩ ተቋማዊ የለውጥ ሂደቶች የጀመሩ መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ይህ ለህዝቡ የገቡትን ቃል ለመተግበር በማሰብ በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ስር በአገሪቱ ታዋቂ የሆኑ የሕግ ምሁራንን፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላትን፣ ጋዜጠኞችን፣ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾችን እና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችን ያካተተ የሕግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔ አቋቁመዋል።
የሕግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔው የተቋቋመበት ዋናው እሳቤ በአገሪቱ የሕግ ማውጣት እና የፍትህ ስርዓት ውስጥ ከሰብዓዊ መብቶችና የሕግ የበላይነት አንጻር የከሸፉትን ወሳኝ ነገሮች ለማስተካከልና በቀጣይም በሕግና ፍትህ ስርዓት ለውጥ ውስጥ መልካም የሆነ የሕግ አወጣጥ ስርዓትና ባህል እንዲዳብር የራሱን የሆነ አሰራር ለመንደፍ ነው። በኢትዮጵያ የሕግ ማውጣትና ፍትህ ስርዓት ግንባታ ከ1940 እና 50ዎቹ በኋላ እየላሸቀ የመጣበትና አንድና ወጥነት ያለው መሠረታዊ የሆኑ የሕግ አወጣጥ ስርዓቶችን ያልተከተለ፣ በተለይም የፖለቲካ ስርዓቱን ለመጥቀም ታስቦ ሕጎች የሚወጡበት፣ ሥልጣንን አላግባብ መገልገል የነገሠበት የሕግና የፍትህ ስርዓት የነበረ መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በአገራችን የሚወጡ ሕጎች ጥራታቸውን ያልጠበቁ እና የመንግሥትን ሥልጣን ሰይፍ የሞረዱ ከመሆናቸውን ባሻገር አሳሪና አፋኝ እንዲሁም ሰብአዊ መብቶችን ያደፈጠጡ ነበሩ። ለአብነት ያህል የፀረ-ሽብርተኝነት፣ የሲቪክ ማኅበረሰቦች እና የሚዲያ ሕጎች አንድም በሕግና ፍትህ ስርዓት ግንባታን የሚሸረሽሩ ሲሆኑ፣ በሌላ በኩልም የማኅብረሰቡን የማሰብና በነጻነት የመኖር መብት የሚረግጡ የነበሩ ለመሆናቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታዎች ናቸው።
የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በአዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 8/2/ሰ መሠረት የፍትህና የዴሞክራሲ ተቋማትን የማሻሻል ሂደት ውስጥ ሕዝብንና ባለሙያዎችን ባሳተፈ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግና ወጥነት ያለው የሕግና የፍትህ ስርዓት የለውጥ ሂደትን ለማጠናከር በማሰብ በመመሪያ ቁጥር 24/2010 ተጠሪነቱ ለፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሆነ የሕግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔ አቋቁመዋል።
በሕግና ፍትህ ጉዳዮች ዙሪያ መረጃና ጥናትን መሰረት በማድረግ ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሙያዊ ምክር መስጠት፣ የሚረቀቁ ሕጎች ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ተገቢውን እገዛ ማድረግ እና የሕግና የፍትህ ስርዓት ማሻሻያዎች ወጤታማ እንዲሆኑ የመፍትሄ ሐሳቦችንና አቅጣጫዎችን ማቅረብ መሰረታዊ የሆነው የአማካሪ ጉባዔው የተቋቋመበት ዓላማዎች መሆናቸውን የጉባዔው ማቋቋሚያ መመሪያ ቁጥር 24/2012 ውስጥ በግልጽ ተመልክቷል።
አማካሪ ጉባዔው ምን አዲስ ነገር ይዞ መጣ?
አማካሪ ጉባዔው በአገሪቱ ውስጥ ቀድመው ከተዋቀሩና በአሁንም ወቅት ካሉ የሕግና የፍትህ ስርዓት ማሻሻያ ተቋማት አንፃር ልዩ የሆኑ መሠረታዊ ባህሪያት አሉት። ጉባዔው ኢትዮጵያ የተያያዘችውን በሕግና ፍትህ መሰረት ተቋማትን የማዋቀር ተግባር በሰፊው ከመደገፍ ባለፈ፣ በአገሪቱ ውስጥ የሕግ የበላይነትን፣ የሰብአዊ መብቶችን የማክበርና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን በትክክለኛው መስመር ማቃናት ያስችል ዘንድ አሳሪና አፋኝ የሆኑ ሕጎችና ተቋማዊ መዋቅሮችን መቀየርና በሂደትም ጠንካራና ተአማኒነት ያላቸው ማድረግ ዋነኛ ዓላማው ነው።
የአማካሪ ጉባዔው አባላትና በስሩ ባዋቀራቸው ተቋማት ውስጥ ያሉት ባለሙያዎች ፍፁም ሙያዊ በሆነ መልኩ በተለይም ሕሊናንና የሰብዓዊ መብትና ሕጋዊነትን በሚያስቀድም ሁኔታ፣ የሕግና የፍትህ ስርዓት የለውጥ ሂደቱን የሚደግፉ ናቸው። በፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ ሰብሳቢነት የሚመራ የ13 ታዋቂ የሕግ ምሁራን ያሉት ጉባዔው፣ በውስጡ በተዋቀሩ የሥራ ቡድኖችም ውስጥ ከየትኛውም አካል ተፅዕኖ ነፃ የሆኑ የሕግ ምሁራን፣ ጋዜጠኞች፣ የዩኒቨርስቲ መምህራን፣ ጠበቆችን፣ በተለያየ በዓለም ዐቀፍ ተቋማት ውስጥ የሚያገለግሉ ኢትዮጵያዊ የሕግ አማካሪዎች እና የተፎካካሪ ፓለታካ ፓርቲ አባላት የያዘ ነው።
ይህም ጉባዔው በአጠቃላይ በማኅበረሰቡ ውስጥ ሁሉን ዐቀፍ የሆነ የለውጥ ችቦ በመለኮስ የአገሪቱ የሕግና የፍትህ ስርዓት ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን መያዙ፣ የአገራዊ የለውጥ ሂደቱ በመደግፍ ላይ መገኝቱና አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡ እሰየው የሚያስብለው ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ዓመታት የተቋቋሙ የሕግና የፍትህ ስርዓት ማሻሻያ ተቋማት ዋነኛ ድክመት በአንድ ፓርቲ ስር በመተብተብ የጥቂት ቡድኖች መሣሪያ መሆን ነው። በዚህ ረገድ አማካሪ ጉባዔው በመርህ ደረጃም ሆነ በተግባር ከመንግሥት ተቋማትና ከገዥ ፓርቲ ተፅዕኖ ነፃ የሆኑና ባላቸው ሙያዊ ክህሎቶች ለማገልገል ቁርጠኛ የሆኑ ምሁራንን የያዘ መሆኑ ነው። ጉባዔው የሚያከናውናቸውን ተግባራት በተመለከተ የራሱን እቅድ ከማውጣት ጀምሮ ተቋማዊ ገለልተኛነቱን በመጠበቅ የሚመራ ሲሆን፣ በተግባርም በተለያዩ አጋጣሚዎች የጉባዔ ገለልተኝነት የሚያመለክቱ ሁኔታዊች ተፈጥረዋል።
ለአብነት ያህል ቀድሞ በጉባዔው ስር ተቋቁሞ የነበረው የዳኝነትና የዳኝነት ስርዓት የለውጥ የሥራ ቡድን ከፍርድ ቤቶች ነጻነት መርህ አንጻር በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ስር መኖር የለበትም ወደሚል ድምዳሜ ስለተደረስ፣ ቡድኑ በጉባዔው ውስጥ የነበረውን የሰው ኃይልና አስፈላጊ ግብአቶችን በመያዝ ለፍርድ ቤት ተጠሪ እንዲደረግ ተደርጓል።
ይህ የሚያመላክተው ጉባዔው እውነተኛ የሆነ ተቋማዊ ገለልተኝነት ያለውና ዋና አዓላማው የአገሪቱን የፍትህና የሕግ ስርዓት በተገቢው መስመር ማስያዝና ማቃናት መሆኑን ነው። መንግሥትም ለዐስርት ዓመታት ተቃዋሚ ፓርቲ፣ መስጂድና ቤተክርስትያን ሳይቀር በአገሪቱ ያለ ማንኛውንም የተደራጀ ሕያው ነገር ከመቆጣጠር አልፎ በስሩ የማጠቃለል አሰራርን ትቶ፣ በስሩ ለሚቋቋም አማካሪ ጉባኤ ሙያዊ ገለልተኝነት መፍቀዱ ብቻ ትልቅ እመርታ ነው።
አማካሪ ጉባዔው ኢትዮጵያ የተያያዘችውን የለውጥ አቅጣጫ የሚደግፍበት ሂደትና የአሰራር ስርዓቶች በ1950ዎቹ የአርቃቂ ኮሚሽኑ አመርቂ የሚባሉ የአሰራር ስልቶችን በአርአያነት በመውሰድ በተለያዩ የሕግ ሙያ ዘርፍ ውስጥ ያሉ ምሁራንን በመያዝ ተግባሩን የሚከውን ነው። ጉባዔው የሕግ ረቂቅ ከማቅረቡ በፊት የተለያዩ ቅድመ-ጥናቶችን የሚያካሄድ ሲሆን፣ እነዚህ ጥናቶች በሂደት የሕግ አውጪው ሐሳብ ሊያንፀባርቅ የሚችሉ ቅድመ-ሥራዎች (Travaux Preparatoires) እና እንደ ሁኔታው የሕግ አውጪውን ሐተታ ዘምክንያት (Expose de Motifs) ሊሆኑ የሚችሉ ጥናቶችን የሚያደርግና በውጤቱም በሕግና ተቋማዊ መዋቅር ረገድ ያለውን የችግሮች ለይቶ የረቂቅ ሕግ የሚያቀርብ ይሆናል።
ያሁኑን አማካሪ ጉባዔ ከ1950ዎቹ የአርቃቂ ኮሚሽን የሚለየው የድሮው ኮሚሽን ሥራ በዋናነት ከውጭ አገር በመጡ ባለሙያዎች የሚመራ ነበር። የአማካሪ ጉባኤው የሥራ ውጤቶች ግን ሙሉ በሙሉ ሊያስብል በሚችል ደረጃ በኢትዮጵያውያን እየተሠራ መገኘቱ ነው። የአማካሪ ጉባኤው የሥራ ቡድን አባላት አልፎ አልፎ የአገር ውስጥ ሙያተኞች በበቂ ደረጃ ያላጠኑት ንዑስ ርዕሰ-ጉዳይ ሲያጋጥማቸው የውጭ ባለሙያዎችን የሚያማክሩ ወይም የሥራ ውጤታቸውን ለሙያዊ ሂስ የሚያቀርቡ ቢሆንም፣ በዋናነት የለውጥ ሥራው ሽክምም ባለቤትነትም በአገር ባለሙያዎች ላይ ነው የተጣለው።
በአገሪቱ የሕግና የፍትህ ስርዓት የለውጥ ሂደት ላይ አመርቂ ሊባል በሚችል መልኩ በጥናቱና ሕግ ረቂቅ በማዘጋጀት ከሚሳተፉት በሙያው ከፍተኛ ብቃት ያላቸው ከመሆኑ ባሻገር፣ ጉዳዩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር ሕዝባዊ ውይይቶችን በማድረግ ሁለንተናዊና ማኅበረሰባዊ ተሳትፎ ያለው የሕግ ማውጣት ሂደቶች መከተሉ ልዩ የሚያደርጉት የአሰራር ሂደቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነው። በአጠቃላይ በጉባዔው በተሠሩ ረቂቅ ሕጎች እና ቅድመ ሥራዎች ዙሪያ ከተለያዩ የማኅበረሰብ አካላት ጋር አዲስ አበባንና ድሬዳዋ ከተማ መስተዳድሮችን ጨምሮ በክልል ዋና ዋና ከተሞች ላይ ሕዝባዊ ውይይቶችን በማድረግ ግብአቶችን በመሰብሰብ በዚሁ መሰረት በረቂቅ ሕጎቹ ላይ ማስተካከያዎች አድርጓል።
አማካሪ ጉባዔው ተቋማዊ መዋቅሩም በሕግ የተጣለበትን ግዴታ ለመወጣት የሚያስችል ነው። ተጠሪነታቸው ለራሱ ለጉባዔው የሆኑ የጉባኤው ጽሕፈት ቤት እና በተለያዩ የሕግና የፍትህ ስርዓት ማሻሻያ ሂደቶችን የሚያጠኑ የሥራ ቡድኖች አሉት። የጉባዔው ጽሕፈት ቤት በአማካሪ ጉባዔ እና በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መካከል እንደ ድልድይ ሆኖ የሚያገለግል ለተቋሙ በሕግ የተጣሉበትን ተግባራት ለማከናወን የአስተዳደራዊና ሙያዊ እገዛ የሚያደርግ ነው።
በጉባዔው የሚደራጁ የተለያዩ የሥራ ቡድኖች ጉባዔው በሚተዳደርበት የአሰራር ስልትና ሂደት መሰረት ጥናታዊ ጽሑፎችንና ረቂቅ ሕጎችን በማዘጋጅት ሙያዊ አበርክቶዎችን የሚሰጥ ነው።
ከላይ ከተመለከቱት ነጥቦች በተጨማሪ አማካሪ ጉባዔውን ልዩ ከሚያደርጉት መሃል የበጎ ፈቃደኝነት ባህል ዋነኛ ነው። ጉባዔው ባዋቀራቸው የሥራ ቡድኞች ውስጥ ከ180 በላይ የሆኑ በጎ ፍቃደኛ ባለሙያዎች ያሉት ሲሆን፣ እነዚህ የሙያ ሥነ-ምግባር፣ አገራዊ ፍቅርና ታማኝነት የለውጥ ሂደቱን በመደገፍ በሕግ የበላይነት፣ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና በሰብአዊ መብቶች መከበር ዙሪያ ሙያዊ አበርክቶዋቸውን እየሰጡ ይገኛሉ።
አዲስ ጅማሬ ወይስ የሐሰት ተስፋ?
የሕግና የፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔው አሁን ያሉት የለውጥ ሂደት አዎንታዊ መገለጫዎች መሃል አንዱ ሲሆን ጉባዔው ከተቋቋመ በኋላ የራሱን የአሰራር ሂደቶች በመንደፍ በአገሪቱ የሕግና የፍትህ ስርዓት ውስጥ አፋኝና አሳሪ የሆኑ ሕጎችና ተቋማት እንዲሻሻሉ የተለያዩ የመፍትሄ ሀሳቦችን ለመንግሥት በማቅረብ ውጤቶችን አስመዝግቧል። እነዚህ ውጤቶች ትውልድ ተሻጋሪ ዝግመተ ለውጥ እይታ ካየናቸው ባለፉት ሰማንያና ከዚያ በላይ ዓመታት ከተገኙት እመርታዎች አንድ ተጨማሪ ወይም ተደራቢ ድል ተደርገው ሊወሰዱ የሚችሉ ቢሆንም፣ አሁን ያለው ለውጥ ከዚያ በላይ ምናልባትም ዘላቂ የሆነ የዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብቶችና የሕግ የበላይነት ስኬት ሊያስመዘግብ የመቻል ከፍተኛ እድል አለው።
መንግሥት አማካሪ ጉባዔው ባስቀመጣቸው አሰራሮችና ምክረ ሐሳቦች በመመራት ባለፈው ዓመት ያስመዘገበውን ውጤት ብናይ ከዚህ በፊት ከነበሩት ጋር የሚመሳሰል የሐሰት ተስፋ ብቻ እንደማያቀርብ እርግጠኛ መሆን ይቻላል። አማካሪ ጉባኤው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በአጭር ጊዜ ውስጥ 14 የሕግ ዘርፎች ላይ የሕግ ስርዓት ብቃት መመዘኛ ዳሰሳ ጥናቶችን በማከናወንና እነዚህን ዘርፎች ለማሻሻል የሚያስችሉ ረቂቅ ሕጎችን ከሞላ ጎደል አዘጋጅቷል።
ከእነዚህ ውስጥ ስድስቱ አግባብነት ባለው መንግሥታዊ መዋቅር በማለፍ ለአቅመ ሕግ ደርሰዋል። የጥናትና የማርቀቅ ሥራቸው ተጠናቆ በነጋሪት ጋዜጣ የታተሙት ሕጎች የሚሸፍኗቸውን የሕግ ዘርፎች የሲቪል ማኅበረሰብ፣ የሽብር ወንጀል፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ማረሚያ ቤቶች፣ እና አስተዳደር ስነ-ስርዓት ሕጎችን ያካትታሉ። በነዚህ የሕግ ዘርፎች ኢትዮጵያ ዓለማቀፍ ደረጃ የጠበቁ ሕጎች እንዳሏት ብቻ ብንመለከት፣ የሕግ ስርዓት ላይ ከፍተኛ መሻሻል መኖሩን የሚያሳይ ሲሆን ከዚህም በላይ ተስፋ የሚያሰጡ ተጨማሪ አዝማሚያዎች አሉ።
ለዚህ ተስፈኛ አመለካከት ተጨማሪ አመላካች አሁን ያለው ለውጥ በ1940 እና 50ዎቹ እንደነበረው ሂደት አዲስ የሕግ ፖለቲካና ማኅበረሰባዊ እሴቶችን እያስተዋወቀ ሳይሆን፣ በብዙ መንገድ ስር የሰደዱ እሴቶች በሕግ እንዲጠበቁ ለማድረግ እየጣረ መሆኑ ነው። ለውጡ የመጣው ባልታጠቁና የመብት ጥያቄ ባነሱ ወጣቶች መሆኑ፤ እንዲሁም ከዚህ በፊት ከነበሩት የለውጥ ሂደቶች በተለየ መልኩ ከፍተኛ የሆነ የትምህርት ስርጭት ጋር በተያያዘም ቅሬታውን በዴሞክራሲና መብት ቋንቋ የሚገልጽ ሕዝብ መብዛቱም ተስፋኝትን የሚደግፍ ተጨማሪ ጉዳይ ነው።
በአማካሪ ጉባዔው መዋቅር እየተሠሩ ያሉት የሕግ ለውጥ ሥራዎች በዋናነት ከፍተኛ ቁጥር ባላቸውና አስተዋጾአቸውን ክፍያ ሳይጠይቁ በሚያበረክቱ ኢትዮጵያዊ ባለሙያዎች መካሄዱ ሌላ ተስፋ የሚያሰንቅ ጉዳይ ነው። በተጨማሪም የዴሞክራሲ፣ ሰብዓዊ መብትና የሕግ የበላይነት ሥራዎችን ያለ ውጭ እገዛ ለመሥራት የሚያስችል አቅም በአገር ውስጥ መኖሩ እንዲሁም የእነዚህ ባለሙያዎች የእድሜ ስብጥርም አፄ ኃይለሥላሴ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጊዜ የተወለዱ ባለሙያዎችን ማካተቱ፣ ምን ያህል እነዚህ መርሆች ትውልድ ተሻጋሪ በሆነ መንገድ ስር እንደሰደዱ ያሳያል።
በመጨረሻም ያሁኑ የለውጥ ሂደት ዘላቂ መሆኑን ከሚደግፉ ሁኔታዎች ሌላኛው በአማካሪ ጉባኤው የለውጥ ሂደቱን ከዚህ በፊት በኢትዮጵያም ይሁን በብዙ አገራት ባልተለመደ መልኩ የተራቀቁና ጠንካራ አሰራር ዘዴዎችን መዘርጋቱ ነው። በአማካሪ ጉባኤው ሂደቶች ውስጥ የተሳተፉና እየተሳተፉ ያሉ ባለሙያዎች፣ በቀጣይ በአገሪቱ ለሚከናወኑ የሕግና የፍትህ ስርዓት የለውጥ ሂደቶች አስተምህሮታቸው የጎላ፣ ያሏቸውን ዘመናዊ አሰራሮች ተግባራዊ ለማድረግ እየጣሩ ሲሆን ሥራቸው በአገር ውስጥ ብቻ አይደለም፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኘ ነው።
እንደ ኒው ዮርክ ዩኒቨርሲቲ፣ ፓዝፋይንደር ኢንተርናቲኦናል፣ ዓለም ዐቀፍ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር እና የተባበሩት መንግሥታት የአስተያየት እና ሐሳብን የመግለጽ መብት ልዩ ዘጋቢ ያሉ አካላት የአማካሪ ጉባኤውን አሰራሮችና አወቃቀር በሚመለከት ባደረጓቸው መግለጫዎች ‹መሪ ብርሃን› (Beacon)፣ ‹አስደናቂ›፣ ‹ግሩም›፣ ‹ያልተጠበቀ አካታችነት የሚታይበት› ሲሉ አወድሰዋቸዋል። የአማካሪ ጉባኤው አባላት ቁርጠኝነት ያላቸው ባለሙያዎች መሆናቸውን መስክረውላቸዋል።
ከሦስት ዓመት በፊት ኢትዮጵያ በዓለማቀፍ ሚዲያ አውታሮችና በተባበሩት መንግሥታትና የአፍሪካ ኅብረት የሰብዓዊ መብት ስብሰባዎች ላይ በዋናነት በአሉታዊ መንገድ ብቻ ትነሳ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ኢትዮጵያ “የዓለም 10 በጣም መጥፎ የጋዜጠኛ አሳሪዎች”፣ የበጎ አድራጊ ድርጅቶችን በገፍ የሚዘጋ አገር፣ የሃይማኖት አባቶችን ሳታስቀር በዜጎቿ ላይ የተቀናጀ የማሰቃየት ተግባር የምትፈጽም አገር፣ አልፎ አልፎም በጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በዜጎቿ ላይ ፈጽማለች ተብላ ትወነጀል ነበር።
ይህቺው አገር በአጭር ጊዜ ውስጥ መሪዋ ኖቤል ሽልማት የሚሰጠው እና የተባበሩት መንግሥታት አካላት የሕግ ማሻሻል ዘዴዎቿ “በዓለም ዙሪያ ላሉ ዴሞክራሲያዊ ሂደቶች አርአያ መሆን ያለበት አሰራር” ብለው የሚጠቅሷት አገር መሆኗ በእግጥም ተስፋ ያሰንቃል። የሕግና የፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔው ጥንካሬዎች በብሩህ አመለካከትና ተስፋው ላይ ቢጨምሩ እንጂ እንደማይቀንሱ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሻው ውጤት እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን።
*አባድር መሐመድ በሕግ ሳይንስ ዶክትሬት (J.S.D.)፣ የሰብዓዊ መብት ጠበቃና መምህር፣ የሕግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ።
**ፋሲካ ዓለሙ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሰብዓዊ መብቶች ትምህርት የኹለተኛ ዲግሪ ተማሪ እና በሕግና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት የሕግ ባለሙያ።
ቅጽ 2 ቁጥር 79 ግንቦት 1 2012