ሰው እንሁን …!?

Views: 185

የሰኔ 15ቱ ክስተት የተጣባን ዘውጋዊ ማንነት ዋልታ ረገጥነት አንዱ ማሳያ ነው የሚሉት ቁምላቸው አበበ፥ ይህም ዘረኝነት፣ ግዕብታዊነት፣ ኢአመክኖያዊነትና ድንቁር ምን ያክል ድንኳናቸውን እንደሰሩብን ግልጽ አመላካች ነው ይላሉ። በተለይ በዚህ አንድ ዓመት ከአመክኗዊነት ባፈነገጠ መልኩ በዘውግ ማንነት በመከፋፈል ምሽግ ያሲያዙ፣ አቋም ያስወስዱና ያሟገቱ ጥያቄዎችን፣ ሥጋቶችንና ፍላጎቶችን የዘውግ ማንነትን መካድ ሳያስፈልግ ወደ ሰውነት በመመለስ በአብርኆትና በአመክኖአዊነት መነጽር በመመርመር መፍትሔ ልናበጅላቸው እንችላለን ሲሉ ይሞግታሉ።

ያለፉት 27 ዓመታትም ሆኑ ከዚያ ቀደም ያሉት ዓመታት ያለፉት በዘውግ፣ በብሔር፣ በማንነት ፖለቲካ መሆኑ ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል። ብኩርናችንን፣ ቀደምትነታችንን አስቀምቶናል፤ አሰውቶናል፤ አስማርኮናል። በምክንያታዊነት ሳይሆን ሁሉን ነገር በዘውግ መነጽር እንድንመለከት አድርጎናል።

ሰሞነኛው የታሪካችን፣ የኢትዮጵያዊነታችን ጠባሳ መግፍኤም ይኸው ነው። ሰኔ 15 በባሕር ዳር እና በአዲስ አበባ የተፈጸመው ግፍ እና አገራችንን ወደለየለት የማያበራ እልቂት የመዝፈቅ እምቅ አቅም የነበረው ኹነት የጽንፈኛ ዘውጌያዊነት ቅርሻ ነው። ከጭፍን ጥላቻ፣ ከጎሰኝነት ይልቅ በተጠየቅ፣ በአመክንዮ በተመሰረተ ንግግር፣ ውይይት፣ ሙግት በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት ቢቻል ለዚህ ዘግናኝ ግፍ ባልተዳረግን፤ የሚያሳዝነው በአናቱ የደባ፣ የሴራ ኀልዮት ተጨምሮበት የተፈጠረው ውዥንብር ከሰማዕታቱ ይልቅ ነፍሰ ገዳዮችን በጀግንነት ሊያነብር መሞከሩ ዘውጌያዊነት ሕሊናችንን እንዴት እንደጋረደው ያሳያል። በሆነው ነገር ሙሾ ከማውረድ ይልቅ መውጫችን ላይ መነጋገር ይበጃል ብዬ ስለማምን፤ የመውጫችን በር ሰውነት ነው እላለሁ።

አዎ …! ዘውጋዊ ማንነት አገርን፣ ወገንን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን፣ መተሳሰብን፣ ምክንያታዊነትን፣ ተጠየቃዊነትን፣ እውቀትን፣ ሰብኣዊነትን፣ ታሪክን… ፤ አስገብሮን በምትኩ ጥላቻን፣ ቂም በቀልን፣ ጭፍን ድጋፍና ተቃውሞን፣ ዘረኝነትን፣ ግዕብታዊነትን፣ ኢአመክኖያዊነትን፣ ኢተጠየቃዊነትን፣ ድንቁርናን፤ አስታቅፎናል። የጥላቻን፣ የመጠራጠርን የጦር እቃ አስታጥቆናል፣ የቂምን የሾህ አክሊል፣ የበቀልን ጡሩር አስለብሶናል። የሦስት ሺሕም ሆነ ከዛ በላይ የሆነውን የታሪካችንን ቀለም አደብዝዞታል።

ከዚህ ከፍ ሲልም ምሽግ አስይዞናል። ጉድብ አስጎድቦናል። በዚህ ይዞታችን፣ አኳኋናችን ለአገራችን የምንመኘውን የምንፈልገውን ለውጥ ማምጣት አንችልም።
ሀቀኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ፍትሕንና እኩልነትን ለማስፈን፤ ሌብነትን ዘረፋን ከዚች አገር ለመንቀል የሕግ የበላይነትን ዘላቂና አስተማማኝ ሰላምን እውን ለማድረግ በእውነት ላይ የተመሰረተ ይቅርባይነትን ለመሻት ወዘተ. ባለፉት 27/50 ዓመታት በብሔር፣ በዘውግ ፖለቲካ የተዘረፍናቸውን የተነጠቅናቸውን ከላይ የተዘረዘሩትን ምርኮዎቻችንን ማስመለስ አለብን።

ምርኮዎቻችን የምናስመልሰው በዘውግ፣ በብሔር ግርዶሽ ተሸብበን ‘ውረድ እንውረድ. . .’ እየተባባልን የጥላቻ ጦራችንን በመስበቅ፤ የቂም በቀል ቀስታችንን ፍላጻዎቻችንን ለማንበልበል ለማስፈንጠር ደጋን በመወጠር አይደለም። በእውቀት፣ በሳይንስ፣ በተጠየቅ፣ በምክንያት ላይ በተመሰረተ የሰከነ የሐሳብ ፍጭት ሙግት በማድረግ ገዥ ሆኖ ልዕልና ያገኘውን ሐሳብ ፍኖተ ካርታ በመከተል ሲገባ እየሆነ ያለው ግን በብሔር በዘውግ የተቆፈረ ምሽግ ይዞ መጠዛጠዝ ነው። የውይይቱ፣ የንግግሩ፣ የሙግቱ መሰረት የሚገነባው በሳይንሳዊ እውቀት፣ በምክንያታዊነት፣ በተጠየቃዊነት፣ በእውነት፣ በሀቅ አለት …ሳይሆን፤ በዘር፣ በጎሳ፣ በማንነት፣ በዘውግ፣ በሃይማኖት፣ …፤ ድቡሽት ላይ በተቀለሰ ጎጆ ነው። ወገንተኝነት ታማኝነት ለሀቅ፣ ለአመክኖአዊነት፣ ለሕሊና ሳይሆን ለተገኘበት ጎሳ ወይም ዘውግ ነው። በዚህ አሰላለፍ አገራችንን ከገባችበት ቀውስ ማውጣት አይደለም እርስበርሳችን መቀባበል፣ መነጋገር፣ መደማመጥ አልቻልንም። ለጽንፈኝነት፣ ለአክራሪነት ተዳርገናል። እውቀት፣ ተጠየቅነት፣ ምክንያት፣ ሳይንስ በዘውጌአዊነት፣ በብሔርተኝነት ተደፍቀዋል።

በተለይ በዚህ አንድ ዓመት ከምክንያታዊነት፣ ከተጠያቂነት፣ ከአብርሆት ይልቅ በማንነት፣ በዘውግ ተከፋፍለን ምሽግ ይዘን፣ የተከላከልናቸውን፣ የተጠዛጠዝንባቸውን፣ አቋም የወሰድንባቸውን፣ የተሟገትንባቸውን፣ ጥያቄዎች፣ ሥጋቶች፣ ፍላጎቶች እንደ ክብደት ቅደም ተከተላቸው እንመልከት፦

ሀ. የሕወሓት ተገፋን፣ ተከበብን ዋይታ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ጎልተው ከሚሰሙ አመክኖአዊ፣ ተጠየቃዊ ካልሆኑ ለቅሶዎች፣ ዋይታዎች፤ ቀዳሚው የሕወሓት ቡድን የትግራይ ሕዝብ ከማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣን ተገፋ፣ ተገለለ የሚለው ሀቲት፣ ትርክት ነው። እውነታው ግን የሕወሓት ልኂቃን ላለፉት 27 ዓመታት በበላይነትት፣ በብቸኝኝነት ይዞት የነበረውን የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሀብት፣ የደኅንነት፣ የመከላከያ የበላይነቱን በሕዝባዊ አመፅና በለውጥ ኀይሉ አጣ እንጅ የትግራይ ሕዝብ ፍትሐዊ ተጠቃሚነቱን አላጣም አያጣምም።

ትግራዋይ ልኂቃን ከእውነታው ይልቅ በመደበኛም ሆነ በማኅበራዊ ሚዲያው እያስተጋቡት ያለው ሕወሓት ሊያነብር የፈለገውን የተገፋን ሀቲት ነው። ልኂቃኑ ከማንነት ፈለፈላቸው ወጥተው በተጠይቅ፣ በአመክንዮ ማሰብ፣ ማንሰላሰል ቢፈቅዱ ኑሮ የሕወሓት ትርክት የተዛባ መሆኑን ገልፀው ከሀቁ ጎን ይቆሙ ነበር። የሚያሳዝነው ከአንዶም ገ/ስላሴ፣ ከአረጋዊ በርሔ (ዶ/ር)፣ መለስ ቀስ እያለ ቢሆንም ከአብርሃ ደስታ እና በጣት ከሚቆጠሩት ልኂቃን ውጭ ከእውነት ወገን የቆመ የለም ማለት ይቻላል፤

ለ. የመካድ አባዜ
ባለፉት 27 ዓመታት በአገሪቱ የተፈፀሙ ዘግናኝ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች፣ ስቃዮች እንዲያ በዘጋቢ ፊልም ሰለባዎች እየገለጹት አገር ጉድ እያለ፤ ከላይ ከጠቅስኋቸው የፖለቲካ ልኂቃን እና ጥቂቶች በስተቀር ብዙዎቹ ትግራዋይ ምሁራን ድርጊቱን ካለማውገዝ አልፈው ሕወሓትን ከሕዝብ ለመነጠል እንደተሠራ ደረቅ ፕሮፓጋንዳ መቁጠራቸው ተጠየቅ፣ አመክንዮ በማንነት እንደተጋረደ ያሳያል። እነዚሁ ምሁራን ባለፉት 27 ዓመታት የአንድ ቡድን ምጣኔ ሀብታዊ፣ ፖለቲካዊ እንዲሁም በደኅንነትና በመከላከያ መዋቅሩ ላይ ብቸኛ አዛዥና ናዛዥ እንደነበር ላለመቀበል የሚያደርጉት ጥረት የማንነት ፖለቲካ ምን ያህል ልባቸውን እንደደፈነው፣ አንገታቸውን እንዳደነደነው፤ እይታቸውን እንደጋረደው ያመለክታል። ለዚህ ነው ትግራዋይ የሕግ ልኂቃን ሳይቀሩ፤

“የወሰንና የማንነት ጉዳዮች አጣሪ ኮሚሽንን፤ ሕገ መንግሥቱን የጣሰ ነው” ብለው በአደባባይ ሲከራከሩ የማይሳቀቁት፤ በእርግጥ የኮሚሽኑ መቋቋም ኢሕገ መንግሥታዊ ቢሆን ከትግራዋይ ልኂቃን ውጭ ያሉ ምሁራን፣ የምክር ቤት አባላት ለምን አልተቃወሙትም? የእነሱን ያህል ዕውቀት፣ መረዳት ስለሌላቸው ነው? አይደለም። ኮሚሽኑ የተቋቋመበት ሒደት ሕገ መንግሥታዊ መሆኑንና አገሪቱም ከገባችነት ቅርቃር ያወጣታል ብለው ስለአመኑበት እንጅ የደገፉት፤ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕወሓት ተወካዮች የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት እና ትግራዋይ ልኂቃን ለምን ተቃወሙት!? የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ሲሳይ መንግሥቴ እንደሚሉት፤ የኮሚሽኑን መቋቋም የሚቃወሙት ከየክፍለ አገሩ ቆርሰው የወሰዱትን መሬት እና በጉልበት የጫኑትን ማንነት እንዳያሳጣቸው ስለሚፈሩ ነው። በተጠየቅ በአመክንዮ የሚመሩ ቢሆን ኖሮ ሀገሪቱን ቀስፎ ለያዛት የወሰን፣ የማንነት ችግር መፍትሔ ለማመላከት፣ ለማምጣት ያግዛል ብለው በቅንነት ይደግፉት ነበር።

ሐ. የውለታ፣ የውርስ ሽሚያ፤ የተረኝነት
ከአንድ ዓመት ወዲህ የለውጡን መባት ተከትሎ በመደበኛም በማኅበራዊ ሚዲያዎች፤ ከተስተዋሉ ተጠየቅ፣ አመክንዮ ከጎደላቸው እሰጥ አገባ፣ ሽሚያና ውርክቦች፤ ቀዳሚው፤ ለውጡን ያመጣሁት “እኔ ነኝ፣ እኔ ነኝ” የሚለው ንጥቂያ ነው። በአገሪቱ ፖለቲካ ታሪክ አይደለም በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአፄዎች አገዛዝም እንዲህ ያለ የግዳይ፣ የድል፣ የውለታ ሽሚያ ታይቶ አያውቅም። አገሪቱ በምንም ዓይነት የማኅበራዊ ቀውስ ተዘፍቃ እንኳን እረኛው፣ አዝማሪው ጀግንነቱን በዜማው ለሚገባው ያደላድላል ዕውቅና ይሰጣል እንጅ ጀግናው ራሱ ተነስቶ ጀግና ነኝ ይህን ድል ያመጣሁት እኔ ነኝ አይልም። መናገር ግድ ቢሆን እንኳ የእናት የአባቴ አምላክ ረድቶኝ ለዚህ በቃሁ ይላል እንጅ እንዲህ እንደዛሬዎቹ ጉዶች ለውጡን እኛ ነን እኛ ነን ያመጣነው በሚል እብሪት አይታበይም። አዎ! ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋግመው እንደሚሉት፤ ለውጡን ያመጣው ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንጅ አንድ ቡድን ወይም ግለሰብ አይደለም። ለውጡ ግፍ፣ በደልና ጭቆና አምጦ የወለደው ነው።
“እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና።” (የማቲዎስ ወንጌል 7 ÷ 12)
በሚለው የታላቁን መፅሐፍ ሐረግ ተንጠላጥሎ፤ “በራስህ ላይ እንዲደረግ የማትፈልገውን፤ በሌሎች ላይ አታድርግ” በሚል የሜጫ ቱለማ ዘር የበቀለው ኦነግም ሆነ የእርሱ ቅርሻ የሆኑ ድርጅቶችና ልኂቃን በእነሱ ላይ እንዳይፈፀም የታገሉትን አድልዎ፣ ኢፍትሐዊነት፣ ተረኛነት በሌሎች ለመጫን መሞከሩ የገዳ ስርዓትን አቃፊነት፣ ሰብሳቢነት፣ እንዲሁም ከላይ የተጠቀሰውን መንፈሳዊ መርሃ የሚጥስ ከመሆኑ ባሻገር አመክኖአዊነት፣ ተጠየቃዊነት፣ አብርሆት የጎደለው ሐቲት ነው። የአገሪቱ ከ70 በመቶ በላይ ኢንዱስትሪ ወደ 80 በመቶ የሚጠጋ ኢኮኖሚ የሚገኝበት ሁሉም በደሙ በላቡ የገነባት መኖሪያው የአፍሪካ መናኽሪያ የሁሉም ኢትዮጵያዊ መዲና ናት አዲስ አበባ፤ መጤም ባዕድም የላትም። አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የሕሊና የእጅ ሥራ ናት።

መ. ሁሉም ጥያቄዎች አሁኑኑ መልስ ያግኙ
የሽግግር መንግሥት ይቋቋም፤ አሁኑኑ ምርጫ ይካሔደ፤ ሕዝበ ውሳኔ ተካሒዶ የማንነት ጥያቄያችን ዛሬ መልስ ካላገኘ፤ አዲስ ሕገ መንግሥት ካልተረቀቀ፤ የፌደራል ስርዓቱ ካልፈረስ፤ ባንዲራው ካልተቀየረ ብለው ‘ሱሪ ባንገት’ የሚሉ ጉምቱ “ምሁራን”፣ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያን፣ የመብት ወትዋቾች መኖራቸው ምን ያህል ከአገሪቱ ነባራዊ ተጨባጭ ሁኔታ እንደተነጠሉ ያሳያል። ከዚህ አልፎም ሌላ ስውር ደባ፣ ሴራ ቢያሴሩ እንጂ ነባራዊ ሁኔታስ እንኳን ለእነሱ ትላንት ለተወለደ ብላቴና እንኳን የተሰወረ አይደለም። ነፃ ተቋማት በሌሉበትና አንድ ፓርቲ በሚያገለግሉበት በዚያ ወቅት የሽግግር መንግሥት እንዴት ብሎ ይቋቋም ነበር!? ገለልተኛ የምርጫ ቦርድና አስፈጻሚስ በሌለበት እንዴትስ ነፃና ገለልተኛ ሕዝበ ውሳኔስ እንዴት ሊካሔድ ይችላል!? ዛሬ ካልተካሔደ ሞቼ እገኛለሁ የሚባለው፤
ወላድ በድባብ ትሒድና ከምርጫ በፊት መረጋጋት፣ ሰላም ይስፈን፤ የዴሞክራሲ ተቋማት ይቋቋሙ፤ ከሥልጣን በፊት አገር ይቅደም፤ ወቅቱ ለሥልጣን የምንራኮትበት ሳይሆን አገርን የምንታደግበት ነው የሚሉ ሀቀኛ፣ የቁርጥ ቀን ልጆች መኖራቸው ያፅናናኛል። ብርሀኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)፣ ሙስጠፌ አሕመድ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ፣ ብርሃነ መስቀል አበበ (ዶ/ር)፣ አንዳርጋቸው ፅጌ፣ ኤፍሬም ማንዴቦ፣ መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር)፣ አንዷለም አራጌ፣ የሽዋስ አሰፋ፣ አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) አገሪቱ የምትገኝበትን ነባራዊ ሁኔታ ተንትነው ዘመኑን የሚዋጅ አቋም መያዛቸው አርዓያነት ያለው ተግባር ነው ። ዛሬ ድረስ የአገራችን ምሁራን፣ የፖለቲካ፣ የታሪክ ልኂቃንን ዘወጌ ጎራ አስለይተው የሚያጨቃጭቋቸው ግን ሳያግባቡ ለመጭው ትውልድም በዕዳነት ሊተላለፉ ይችላሉ የምላቸውን መከራከሪያቸውን ደግሞ እንመልከት፦

ሠ. የብሔር ወይስ የመደብ ጭቆና!?
በተማሪዎች የ1960ዎች እንቅስቃሴ ከእነግርማቸው ለማ፣ መለስ ተክሌ (የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሥሙን የወረሱት)፣ ሰለሞን ዋዳ፣ ጥላሁን ግዛው ይልቅ ዛሬ ድረስ በበጎም፣ በክፉም ሥሙ ከፍ ብሎ የሚወሳው የደሴው ዋለልኝ መኮንን ነው። ከእነ ሌኒን ማንፌስቶ እንዳለ ገልብጦ፣ ኮሩጆ ማታገያውን ከመደብ ጭቆና ወደ ጠባቡ የብሔር ጭቆና በማውረዱ፤ አገራችን ዛሬ ድረስ ለምትገኝበት ምስቅልቅል መግፍኤ ከመሆኑ ባሻጋር፤ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ልሒቃኑን በኹለት ጎራ ከፍሎ ይገኛል። በአገራችን ተንሰራፍቶ የነበረው ጭቆና የመደብ ነው አይደለም የብሔር ጭቆና ነው በሚሉ ኹለት የማይታረቁ ቅራኔዎች የብሔር ጭቆና በተጠየቃዊነት በምክንያታዊነት የሚተነተን ሳይሆን በማንነት በስሜት የሚቀነቀን የሚራገብ መሆኑ ልዩነቱን የማጥበብ ሒደቱን አዳጋች አድርጎታል። እዚህ ላይ በሕወሓት፣ በኦነግ እና የኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትን በሚያራምዱ ወገኖች መካከል ያለውን ልዩነት በአብነት ማንሳት ይቻላል።

ረ .የቅኝ ግዛት ወይስ የአገረ መንግሥት ግንባታ!?
የታሪክ የፖለቲካ ሐቲቱ በማንነት በዘውግ በጎሳ ኀልዮት መመስረቱ ከ123 ዓመታትና ከዚያ በላይ የአፄ ምኒልክ የማስገበር የአገረ መንግሥት ዘመቻ የቅኝ ግዛት ዘመቻ ነው እስከ ማለት ከመደረሱ አልፎ በታላቁ የኢትዮጵያውያን የጥቁር የሰው ዘር ድል አድዋ ላይ ዛሬ ድረስ ልዩነቱ ቀጥሏል። እነማንዴላ፣ ስቲቭ ቢኮ፣ ማርከስ ጋርቬ ያመለኩትን ድል መዘባበቻ እስከ ማድረግ ተደርሷል። ስለ ብርሀነ ዘኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱ ውርስ መግባባት ያልተቻለው ሚዛኑ ዘውግ ማንነት በመሆኑ ነው።

እንደ መውጫ
ልዩነቶቻችንን አቆይተን እስኪ መጀመሪያ ወደ ቀደመው ማንነት ማለትም ወደ ሰውነት፣ አዳምነት፣ ሔዋንነት አልያም ዳርዊናዊነት እንመለስ፤ በማሰከተል በይደር ያቆየናቸውን ልዩነቶች እንደ አንገብጋቢነታቸውና ቅደም ተከተላቸው በአብርኆት (enlightenment) በተጠየቃዊነት፣ በአመክኖአዊነት፣ በገለልተኝነት፣ …፤ መነጽር እንመርምራቸው፣ እንተንትናቸው ከዚያ መቋጫ መውጫ መፍትሔ እናብጅላቸው፤ የዛን ጊዜ ሁላችንንም ሊያግባቡ፣ ሊያቀባብሉ፣ ሊያቀራርቡ የሚችሉ መፍትሔዎች ላይ እንደርሳለን።

እዚህ ላይ ማንነቶቻችንን እንተዋቸው እንርሳቸው እያልሁ አይደለም፤ እነሱን መካድ አይቻለንም። ሆኖም ከዘራችን፣ ከመደባችን፣ ከሃይማኖታችን፣ ከአመለካከታችን፣ ከፆታችን ከእነዚህ ማንነቶች ቀድሞ ወደ ነበረው ወደ መጀመሪያዊ የጋራ ማንነት ወደ ሰውነት እንመለስ የዛን ጊዜ ከመጀመሪያው ጀመርን ማለት ነው። በተራው ሰው የመሆን ልምምድ እንኳን ከመጀመሪያው ስንጀምር ያለፍንበትን ስህተት እየነቀስን እያረምን ስለምንመጣ ስህተትን የመድገም ፈተናን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ እንኳን ባንችል መቀነስ ግን እንችላለን፤ ለዚህ ነው ከመጀመሪያው እንደገና መጀመርም የመፍትሔ አካል የሚሆነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 35 ሰኔ 29 2011

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com