የአገሪቱ የሰብኣዊ መብት አያያዝ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው ተባለ

Views: 471

በቅርቡ በባሕር ዳርና በአዲስ አበባ የተፈጠረውን አሳዛኝ ክስተት ተከትሎ ከሰባት መቶ በላይ ሰዎች በፖሊስ ተጠርጥረው መታሰራቸው በመንግሥት ተገልጿል። ከታሳሪዎቹ መካከል የፖለቲካ ፓርቲ አባላት፣ የመብት አቀንቃኞች፣ ጋዜጠኞች እና የሕግ ባለሙያዎችም ይገኙበታል። የታሳሪዎቹ ቤተሰቦች እና የሕግ አማካሪዎቻቸው እንደሚናገሩት የተወሰኑት ታሳሪዎች በቤተሰብ እንዳይጎበኙ እና አንዳንዶቹም በጨለማ እና ቀዝቃዛ ክፍሎች ውስጥ እንዲቆዩ መደረጉ እየተገለጸ ነው።

ከእነዚህ ውስጥ በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ከታሰሩት ሦስት ዐቃቤ ሕግ መካከል የወግሰው በቀለ ከምሌ 20/2011 ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት በታሰረበት አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አካባቢ በሚመጣው ሽታ ሳቢያ እሱና አብረውት የታሰሩት ሰባት ሰዎች ለችግር መዳረጋቸውን፣ ቤተሰብና ጠበቃቸውንም ማየት እንዳይችሉ መደረጋቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። የአስም በሽተኛ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ ያስታወቁት የወግሰው፣ በቂ አየር ሊያገኙ ወደሚችሉበት ቦታ እንዲዛወሩ፣ በጠበቆቻቸውና ቤተሰባቸው እንዲጎበኙ መጠየቃቸውን የግል ጠበቃቸው ይድነቃቸው ኀይሌ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ይድነቃቸው፣ ለረጅም ጊዜ ደንበኛቸውን መጠየቅ እንዳይችሉ መከልከላቸውንና ስለደረሰባቸው ነገር ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ሳይችሉ 15 ቀን መቆየታቸውን ተናግረው፣ ደንበኛቸው ያሉበትን ችግሮች አስመልክቶ ለፍርድ ቤቱ ማቅረቡንና ፍርድ ቤቱም የሚፈልጉት ነገር እንዲሟላላቸው ማዘዙን ተከትሎ ሐሙስ ደንበኛቸው ከቤተሰብ ጋር ሊገናኝ መቻሉን ገልጸዋል።

ጌታቸው ሽፈራው በሳተናው የዜና ድረ ገጽ ላይ “ጌታቸው አምባቸው በጨለማ ቤት” በሚል ርዕስ ባስነበበው ጽሁፍ፣ እነጌታቸው አምባቸው የታሰሩበት አዲስ አበባ ፖሊስ ኮምሽን (3ኛ) ጨለማ ቤት ነው። ቤተሰብ የላከላቸውን ምግብ እንኳን ከታሰሩበት ክፍል ወጥተው መቀበል አይችሉም፤ ፖሊስ ነው የሚያደርስላቸው። አየር ለማግኘት፣ ወደ ሽንት ቤት ለመሄድ የፖሊስን ይሁንታ ጠይቀው ነው። በቀን አንድ ጊዜ ወይንም ኹለቴ ከጠባብና ቀዝቃዛዋ ክፍል መውጣት ቢችሉ ነው።
የሰኔ 15ቱን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል፣ በአዲስ አበባና በቤኒሻንጉል ኹለት መቶ ዘጠና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራሮችና አባላት መታሰራቸውን ፓርቲው ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል። የአማራ ተወላጆች ብቻ በመሆናቸው 332 ሰዎች መታሰራቸውንም አክሎ ገልጿል።

ከታሰሩት ሰዎች መካከል የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መምህራኖች፣ የሕክምና ባለሙያዎች፣ ነጋዴዎችና ፖሊሶች እንደሚገኙበት ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁት የአብን ጽሕፈት ቤት ኀላፊ በለጠ ካሳ፣ የአብን አባላቶች ናችሁ በሚል በተለያዩ አባላቶቻቸው ላይ እስርና እንግልት እየገጠማቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በርካቶቹ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ የተያዙ መሆናቸው ደግሞ በርካታ ዓለም ዐቀፍ የሰብኣዊ መብት ተቋማትን ትኩረት እንዲስብ አድርጓል።

ይህንንም ተከትሎ ዓለም ዐቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን ድርጊቱን ተቃውሞታል። ላለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኞችና የመብት ተማጋቾች በነጻነት ሐሳባቸውን ስለገለጹ ብቻ ያለምንም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሲታሰሩ፤ ሲገረፉ፤ ሲገደሉ እና ሲስቃዩ ያሳለፉት ዘመናት ገና ሳይረሳ፣ በተለይም በአሁኑ ወቅት በአገራችን በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ መጥቷል በሚባልበት ጊዜ እና አገሪቱን የሚመሩት ጠቅላይ ሚንስትር “በኢትዮጵያ ውስጥ ማንም ይሁን ማን አስቀድሞ ማጣራት ሳይደረግና የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሳይወጣ፣ አንድም ሰው እንዲታሰር አንፈቅድም” በማለታችው ምክንያት ከዓለም ዐቀፍ ተቋማት አምነስቲ ኢንተርናሽናልና የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ዕውቅና በተሰጣቸው አንድ ወር በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ፤ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከኹለት መቶ ሰባ በላይ የሚሆኑ የአዲስ አበባና የሌሎች ነዋሪዎች ታፍነው ወደ እስር ቤት ተወርውረዋል። እየተገረፉ ነው። በሽብርተኛነት እየተከሰሱ ነው ሲል ድርጊቱን አውግዟል።

መግለጫው አክሎም፣ የሕወሓት መራሹን አፋኝና ጨቋኝ መንግሥት ሥራ የሚያስታውሰንና የሚመስል አድራጎት በአገሪቷ ውስጥ መጥቷል የሚባለውን ለውጥ ተስፋ ሰጪ መሆኑ ቀርቶ ኢትዮጵያዊያኖች መጪውን ጊዜ በጭንቀትና በፍርሃት እንዲመለከቱት ከማድረጉም ባሻገር፣ ያለፈው የመከራና የአፈና ዘመን መልሶ መምጣቱን ከወዲሁ አመላካች እንደሆነ ያሳያል ነው ያለው።

የሰብኣዊ መብት ተሟጋችና ጠበቃ የነበሩትና በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽነር ተደርገው የተሾሙት ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ሰኔ 30/2011 ከቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ በኢትዮጵያ የሰብኣዊ መብት ችግሮች በሙሉ ተፈትተዋል ማለት እንደማይቻል ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ ሰፊ፣ ውስብስብ፣ ጥልቅ፣ የሆኑ የሰብኣዊ መብት ችግሮችም፤ የፖለቲካ ቀውስም፣ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥም የምንገኝ መሆኑ ሊካድ አይችልም ሲሉም ስላለው ነባራዊ ሁኔታ ተናግረዋል።

ዳንኤል ምክንያቱን ሲያስረዱ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ጠንካራ ተቋማት አለመኖራቸው በጣም ትልቅ ችግር ነው፤ ምክንያቱም በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር፣ በዳኝነት ሥራ፣ በፖሊስና በፀጥታ ኀይሎች ብዙ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች ሊፈፀሙ የሚችሉበት ሁኔታ አለ።

የፖለቲካ ሒደቱ ብሔርን መሰረት ያደረገ፣ የተካረረ የፖለቲካ ውጥረት መኖሩ ያስከተለው ግጭት፣ የፈጠረው የብዙ ሕዝብ መፈናቀል፣ መሞትና ከኑሮው መስተጓጎል ኢትዮጵያ ውስጥ ከተፈጠረው ለውጥ ጋር ተያይዞ በርካታ የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ የደኅንነት ክፍተት መፈጠሩ ማለትም ሕግና ሥርዓትን ማስከበርን አለመቻልን ጨምሮ ማለት ነው። አንዳንድ አካባቢዎች ሕግና ሥርዓትን ማስከበሪያ ተቋማት በመዳከማቸው ወይም በመጥፋታቸው የተነሳ የደኅንነት ክፍተት ተፈጥሯል። በዚህም ሳቢያ ሰብኣዊ መብቶች ሲጣሱ ይስተዋላል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር የሆኑት ደረጀ ዘለቀ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ መንግሥት አምባገነን ሆኗል ይላሉ። ወደ ቀደመው አምባገነናዊ ሥርዓት እየተመለስን ነው የሚሉት ደረጀ፣ በየጊዜው ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰዎች ታሰሩ የሚሉ ወሬዎችን መስማት የተለመደ ሆኗል በማለት።

ዓለም ዐቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን እንደሚለው፣ አሁንም ቁጥራቸው የማይታወቅ ወጣቶች ወደ ሰንዳፋ ተወስደው ርህራሄ የጎደለው ግርፋትና እንግልት እየተፈጸመባቸው ነው፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ኢንተርኔት እንዳይተላለፍ ስለከለከለ ሃቁን ለመከታተል አልተቻለም የሚለው ተቋሙ፣ የኢንተርኔት መገናኛ መቋረጥ ዋናው ዓላማ ለአፈናው አመች እንዲሆን ነው ሲል አስታውቋል።

በአሁኑ ወቅት በማንኛውም ሥልጣን ደረጃ ላይ ያሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት የፍትሕ አካላት እና የፖሊስ ኀይል ልብ ሊሉት የሚገባው ያለምንም የፍርድ ቤት ትዕዛዝና የወንጀል ድርጊት ማስረጃ ሳይቀርብባቸው ዜጎችን በድንገት አፍኖ እስር ቤት ማጎር ዓለም ዐቀፍ ሕግጋትን የጣሰና የግለሰብን ስብኣዊ መብት በእጅጉ የሚጎዳ ከመሆኑ ባሻገር ይህንን ሕገወጥ አድራጎት የሚፈጽሙትንም የመንግሥት አካላት ተጠያቂ እንደሚያደርግ አሳስቧል።

እንደ መፍትሔ
ዳንኤል፣ የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን መዋቅራዊም ሆነ አሠራራዊ የለውጥ ማሻሻያ ሊያደርግ ይገባዋል የሚል እምነት አላቸው። ነገር ግን ወደ እንደዚህ ዓይነት የተቋም ማሻሻል፣ ማጠናከር፣ ማደስና የአሠራር ለውጥ ጉዳዮች ውስጥ ከመገባቱ በፊት ትንሽ በጥሞና ማድመጥ፣ ማጥናትና መጠየቅ ያስፈልጋል።

የሕግ መምህሩ ደረጀ በበኩላቸው መንግሥት በመደንበሩ አውቆትም ይሁን ሳያውቀው የሰብኣዊ መብት ጥሰት እየፈጸም መሆኑን ይገልጻሉ። በዚሁ ከቀጠለ ወደ ባሰ ችግር አገሪቷን ሊከታት ስለሚችል የሚመለከታቸው አካላት በጉዳዩ ላይ መምከር እንዳለባቸው ያሳስባሉ። በተለይ በክልል አመራሮች መካከል የሚታዩትን የቃላት ጦርነቶች ገደብ እንዲኖራቸው በማድረግና የክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብሳቢነት ተገናኝተው በሰከነ መንፈስ በመነጋገር ለአገር መረጋጋት ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት ሲሉ ይመክራሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 36 ሐምሌ 6 2011

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com