ኢትዮጵያዊው የአረብኛ ቋንቋ ልሳን

0
1215

ኢትዮጵያ በተለያዩ የውስጥ ጉዳዩቿ ተጠምዳ የምትገኝበት ጊዜ ነው። ከወቅታዊ አለመረጋጋቶች ባሻገር በግንባታ ሂደት የቆየውና የውሃ ሙሌት ሥራው ይጀመራል የተባለው የሕዳሴ ግድብ ጉዳይም በብዙዎች ሐሳብና ልብ ይመላለሳል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታድያ የግብጽ መገናኛ ብዙኀን የኢትዮጵያን ሥም የሚያነሱበትን መንገድና የሚያሰራጩትን ሐሰተኛና ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ በመቋቋም በኩል፣ አረብኛ ቋንቋን የሚችሉ ኢትዮጵያውያን በያሉበት እየተዋጉት ያሉት ጉዳይ ሆኗል።

ዑመር መኮንን ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሊቢያ ትሪፖሊ በአረብኛ ቋንቋ ያጠናቀቁ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋ ጥናትና ምርምር ‹ፊሎሎጂ› (ጥንታዊ መዛግብትን የሚያጠና የትምህርት ክፍል) ኹለተኛ ዲግሪያቸውን ይዘዋል። ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ሥራ ዓለም ከገቡ በኋላ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሚታተመው ወርሃዊው የአል-ዓለም ጋዜጣ ከሪፖርተርነት እስከ አዘጋጅነት አገልግለዋል። በዚህም ለስድስት ዓመታት ቆይተዋል።

በጋዜጣው ባህልና ቱሪዝም የሚል አምድ እንደነበር የሚያወሱት ዑመር፣ በጋዜጣው በነበራቸው ቆይታ ከሦስት መቶ በላይ ጽሑፎችን እንዳበረከቱ ያስታውሳሉ። በመቀጠልም በአዲስ አበባ ዩኒሰርሲቲ የአረብኛ ቋንቋ መምህርነትን የተቀላቀሉ ሲሆን አሁንም ድረስ በማስተማር ላይ ይገኛሉ። በአዋሽ ኤፍኤም ላይም በሳምንት ሦስት ቀን (ሰኞ፣ ረቡዕ እና አርብ) ስለአባይ ምን ተባለ የሚል መሰናዶ አዘጋጅተው የሚያቀርቡ ሲሆን፣ በተጨማሪም በዛው የራድዮ ጣቢያ ቅዳሜ ከሰዓት የሚተላለፍ ‹ከአባይ ጓዳ› የተሰኘ በሕዳሴ ግድቡ ዙሪያ የአረብ መገናኛ ብዙንን የሚዳስስ መሰናዶን ከባልደረባቸው ኢብራሂም ሙሉሸዋ ጋር በመሆን ያቀርባሉ።
ጋዜጠኛ እንዲሁም መምህር ዑመር መኮንን የኢትዮጵያን የቋንቋ አጠቃቀም፣ የአረብኛ ቋንቋ በኢትዮጵያ ስላለው ገጽታና በጥቅሉ ምን ያህል ቋንቋውን ተጠቅመንበታል በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

ኢትዮጵያ እና አረብኛ ባላቸው ትስስር እንነሳ፣ ምን ያህል የጠበቀ ነው?
ቀድመን ማወቅ ያለብን እውነታዎችና መረጃዎች አሉ። አንደኛ አረብኛና ኢትዮጵያ በጣም የቆየ ስር የሰደደ ግንኙነት አላቸው። ይህን የሚያረጋግጥልን በርካታ ነገር ማንሳት እንችላለን። ለምሳሌ ከቋንቋ ትስስር አንጻር ስንመጣ ሴሜቲክ የሚባለው ቋንቋ ኢትዮጵያ ውስጥ አማርኛ፣ ትግረኛ፣ ግዕዝ፣ ሐረሪኛ፣ ጉራጊኛ የምንላቸው ቋንቋዎች አሉ። እነዚህ ከአረብኛ እና ከእስራኤል ቋንቋ ከሂብሪው ጋር አንድ ቤተሰብ ናቸው።

ሌላው ከእስልምና በፊት ከየመን ጋር የነበረን የንግድ ግንኙነት በራሱ ከፍተኛ የሆነ ትስስር የሰጠን ነበር፣ በጊዜው። እንደውም በኢትዮጵያ ከእስልምና በፊት ክርስትና በነበረበት ጊዜ ኢትዮጵያ ነበረች ቀድማ ለተበደሉ የምትደርስ አገር። እናም የሚጻጻፉት የነበረውን በአረብኛ ቋንቋ ነው። አይሁዳውያን በየመን ክርስትያኖች ላይ ከፍተኛ የሆነ ኢሰብአዊ ድርጊት ሲፈጽሙባቸው፣ የመን ውስጥ ያሉ ክርስትያኖች በአረብኛ ጽፈው ወደ ኢትዮጵያ ይልኩ ነበር። ያኔ የአይሁዳውያን መሪ ዙናዋስን ይባል ነበርና፣ የኢትዮጵያ ነገሥታት ናቸው ከጥቃት የተከላከሉላቸው።

እና ከእስልምናም በፊት አረብኛ ቋንቋ ነበር። በተያያዘ፣ እኛ አገር አረብኛ ሲባል ከእስልምና ጋር፣ ግዕዝ ሲባል ደግሞ ከቤተክርስትያንና ክርስትና ጋር ማስተሳሰር አለ። ይህ መታረም ያለበትና ሁሉም ኢትዮጵያዊ በደንብ ማወቅ ያለበት ጉዳይ ነው። ቋንቋን ከሃይማኖት ጋር ማስተሳሰር ተገቢ አይደለም። ቋንቋ የሕዝብ ነው። እንደውም የክርስትና ሃይማኖት መጻሕፍት እንደ ስንክሳር፣ ሃይማኖተ አበው፣ ተአምረ ማርያም ወዘተ የሚባሉ ሃይማኖታዊ መጻሕፍት መሠረታቸው አረብኛ ነው። ተተርጉመው ነው የቀረቡት። ስለዚህ የኢትዮጵያንና የአረብኛ ቋንቋ ትስስር በቀላል የሚገለጽ አይደለም።

ነጃሺ የሚባል አንድ ፍትሐዊ መሪ እንደነበር ይታወቃል። በእስልምና እምነታቸው ምክንያት ተሰደው ወደ ኢትዮጵያ የመጡትን እንዳትነኳቸው ብሎ የከለከለላቸው፣ በእርሱ ምክንያት ኢትዮጵያ የእውነትና ፍትህ ያለባት ምድር ናት የተባለላት ነው። እርሱ ራሱ አረብኛን ያውቅ ነበር። ያም ብቻ ሳይሆን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጥናትና ምርምር ማእከል ባለው መረጃ መሠረት፣ እነ አጼ ምኒልክ፣ አጼ ዮሐንስ፣ አጼ ቴዎድሮስ ያሉ ነገሥታት አረብኛ በማኅተማቸው ላይ ይጠቀሙ እንደነበር የሚያሳይ ቅርስና መረጃ አለ።

ሌላው መታወቅ ያለበት የኢትዮጵያ ቋንቋና አረብኛ የተሳሰሩ ናቸው። ይህን የምታውቂው ከ26 በላይ የሚሆኑ የአማርኛ እና ትግረኛ ቃላት ቁርዓን ውስጥ አሉ። ይህ ማለት በፈጣሪ ቃል እንኳ የተነገሩ የእኛ ቅዱስ የሆኑ ቃላት አሉ። እንደውም ምሁራን እነዚህን የሀበሻ ናቸው የሚሏቸውና የሚለይዋቸው አሉ። በድምሩ አረብኛና ኢትዮጵያ እንዲህ የተሳሰሩ ነበሩ። ከእምነት እንዲሁም ከንግድ ጋር ተሳስሮ የነበረው ግንኙነት በጣም ጠንካራ ነው።

ታድያ ኢትዮጵያ ቋንቋውን ምን ያህል ተጠቅማለች?
በቅድሚያ የአረብኛ ፋይዳ ምንድን ነው ስንል፣ ብዙ ሰው በተለይ በኢትዮጵያ አረብኛን ከተከታታይ ድራማዎች ጋር ብቻ የተገናኘ አድርጎ ማሰብ ወይም የነጋዴ ቋንቋ የማስመሰል ነገር አለ። በታሪክ ግን ከ700 ዓመት በፊት ስለ ኢትዮጵያ ታላቅነት፣ የተከበረችና የተቀደሰች አገር ስለመሆኗ በአረብኛ ቋንቋ ነው የተጻፈው። አሁን ያሉ የታሪክ ጸሐፍት አሉ፣ እነዚህ ስለኢትዮጵያ ታላቅነት የጻፉ ናቸው። እኛ አረብኛ ብንችል ኖሮ ከመጀመሪያው ማጣቀሻ ታሪካችንን፣ በአረብኛ የተጻፈውን ማወቅ እንችል ነበር። በንግድም ከፍተኛ ትርፍ ማግኘት እንችላለን።

ሌላው ዲፕሎማሲ ነው። በፖለቲካውም በተመሳሳይ ፋይዳ አለው። በሥራው ዓለም በተመሳሳይ። ለምሳሌ አረብኛ ቋንቋ የአፍሪካ ኅብረት የሥራ ቋንቋ ነው። ኅብረቱ መቀመጫው እዚህ ኢትዮጵያ አዲስ አበባ ሲሆን፣ ለኢትዮጵያውያን ቅድሚያ የሚሰጥ ጥቅማ ጥቅም አለ። በተለይ አፍሪካ ኅብረት ላይ ለመቀጠርና የሥራ ኮታን በሚመለከት። እኛ ግን አረብኛ ባለመቻላችን ምክንያት የእኛን ኮታ ወይም ለኢትዮጵያውያን ተዘጋጅቶ የነበረውን የሥራ ኮታ ግብጻውያን እና ሱዳናውያን ናቸው አብዛኛውን የሚጠቀሙበት። የምንችል ቢሆን ኖሮ፣ በዚህም እንጠቀም ነበር።

ትልቁ ጥያቄም ቋንቋውን ተጠቅመንበታል ወይ የሚለው ነው። እውነት ለመናገር ተጠቅመንበታል ለማለት ይከብዳል። አንደኛ አስቀድሞ እንዳልኩት ከታሪክ ጋር በተያያዘ ስለኢትዮጵያ የተጻፉ መጻሕፍት አሁንም አልተተረጎሙም፣ አልተጠቀምንባቸውም ማለት ነው። በንግድና ዲፕሎማሲም እንደዛው። አሁን ከሕዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ለመጠቀም እየሞከርን ነው፣ እንጂ በዲፕሎማሲውም እየሠራንበት አይደለም።

እኛን ከአረብ ጋር ብዙ የሚያስተሳስረንና የቆየ ግንኙነት አለ። አሁን ግን አረቦች የኢትዮጵያን መልካምነት አይደለም የሚረዱት። አሁን ከሚድያ ጋር ተያይዞ እየሠራሁ ያለሁትም የግብጽን ሴራ ማጋለጥ ላይ ነው። እናም በግብጽ ጸሐፊዎች በፖለቲካው ዓለም ኢትዮጵያ ማለት ሌላ ናት። ደሃ እና የእርስ በእርስ ግጭት ያለባት ብለው ነው የሚጽፏት። እናም ይህን ስናይ በፖለቲካውም በሥራውም ዓለም እንዳልተጠቀምንበት ነው የሚያሳየን።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥስ ቋንቋን በተመለከተ ምን ያህል በትኩረት እየተሠራበት ነው ማለት ይቻላል?
ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይበል የሚያሰኝ ሙከራና የሚደነቅ ሥራ እየሠሩ ነው። አረብኛን በማስተማር ፈር ቀዳጅ የሆነው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው። ዩኒቨርሰቲው ከአምስት በላይ ጊዜ ተማሪዎችን በቀን መርሃ ግብር አስመርቋል። በማታ ደግሞ ከአምስት በላይ ፕሮግራሞች አሉት። በኹለተኛ ዲግሪም አረብኛን ለማሳደግ እየሠራ ነው።
የዓለማቀፍ ቋንቋዎች ከማስተዋወቅ ጋር በተገናኘ የሚሠራ አንድ ማኅበር (International language promotion Association) ነበር። በዛ በጎ ፈቃደኛ ሆኜ ሠርቻለሁ። ይህ ድርጅት በዋናነት የሚሠራው ዓለማቀፍ ቋንቋዎችን ማስተዋወቅ፣ ማሳደግና ለኢትዮጵያ ጥቅም የሚውልበትን መንገድ ማመቻቸት ላይ ነው። በዚህ ድርጅት ምክንያት ሰመራ ዩኒቨርሲቲ አረብኛ ማስተማሪያ ከፈተ።

በመንግሥት ደረጃ አሁን ቋንቋው ከአዲስ አበባ በተጨማሪ፣ ሰመራ፣ ጅግጅጋ፣ ወሎ፣ ሐረማያ፣ በሐረር መምህራን ማሠልጠኛ ውስጥ፣ መቀሌ ተከፍቷል። ባህርዳርም መከፈቱን አውቃለሁ፣ በደንብ እየተሠራበት ግን አይደለም። ሰመራ እና ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ እንደውም እያንዳንዳቸው አንድ ጊዜ አስመርቀዋል፣ ባለፈው ዓመት። ወሎ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስመርቃል። ስለዚህ በተቋማቱ ጥሩ መነቃቃት አለ። የአረብኛን ፋይዳ ከተረዱ በኋላ አሁን መንቀሳቀስ ጀምረዋል።

ግን በቂ ነው ወይ የሚለው መታሰብ አለበት። ቋንቋ ራሱን የቻለ አውድ ይጠይቃል። ሳይንስና ሒሳብን አንድ ሲደምር አንድ ኹለት ብለን ልንማር እንችል ይሆናል። ቋንቋ ላይ ግን ቀልጣፋ መሆን ያስፈልጋል። አረብኛ ሲነገር የሚባለውን ነገር በደንብ ተረድተው የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስከብሩን ነው የምንፈልገው።

በዚህ በተያያዘ የማቀርበው ሐሳብ አለ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቻይንኛ ቋንቋ አለ። ቻይናዎች ከሌላው ቋንቋ በተለየ ሁኔታ፣ የገንዘብ አቅም ስላላቸውም ይሆናል፣ ቻይንኛን መርጦ ለመማር የተመዘገበ የዲግሪ ተማሪን፣ አንዱን ሴሚስተር ቻይና ሄዶ እንዲማር ያደርጋሉ። እዛም ተማሪው አውዱን በደንብ ይረዳል። የቻይንኛ ቋንቋን ገበያ ውስጥ ገብተው፣ የተለያዩ ስፍራዎችን ሲጎበኙ፣ ከሕዝብ ጋር ወዘተ ተቀላቅለው ለምደው ይመጣሉ። እኛ አገር በዚህ መልክ ቢሠራ።

ይህ ደግሞ እኛ በመንግሥት ደረጃ በደንብ ስላልተንቀሳቀስን እንጂ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ወጪ ሳያወጣ አረቦች ራሳቸው ስፖንሰር ሊያደርጉት የሚችሉት ነው። ከተለያዩ አገራት ጋር ተነጋግሮና ተስማምቶ ወደ ተለያዩ አረብኛ የሚነገርባቸው አገራት በመውሰድ ተማሪዎቻችን ቢያንስ የአንድ መንፈቅ ዓመት ትምህርታቸውን በዛ መልክ እንዲማሩ ማድረግ ይቻል ነበር።

የዲፕሎማሲ እውቀትና ችሎታ ያላቸው አሉ፣ ቋንቋውን ግን አይችሉም። በአንጻሩ ቋንቋውን የሚችሉ ዲፕሎማሲያዊ ሥራ ላይ በብዛት አይገኙም። ይህን ለማናበብ ምን መደረግ አለበት?
እኛ በደንብ መሥራት ያለብንም እዚህ ላይ ነው። አረብኛ ብቻ አይደለም። ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያን ወክለው፣ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበርና ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ አምባሳደር ሆነው የሚሾሙት፣ የትም አገር ቢሄዱ፣ የሚሄዱበትን አገር ቋንቋ ቢያውቁ ይመረጣል። ፈረንሳይ አገር የሚሄደው ፈረንሳይኛ፣ ኬንያና ታንዛንያ የሚሄደው ደግሞ ስዋሂሊ ቢችል፣ አረብ አገር የሚላከውም አረብኛ ቢችል፣ ይህ በጣም ጥሩ ነገር ነው።

ባለፈው ከግድቡ ጋር ተያይዞ ከግብጽ መገናኛ ብዙኀን ጋር ትንቅንቅ እያደረግን ያለን ሰዎች፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሪ አድርጎልን ስብሰባ አድርገን ነበር። እርሱ ላይ ቃል የገቡት ነገር፣ ለአረብኛ ትኩረት ባለመስጠት ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰብን ነው። እንደውም ወደ አረብ አገር አምባሳደር ተደርጎ ተሹሞ፣ ስለኢትዮጵያ ምን እየተባለ እንደሆነ የማያውቅ አምባሳደርም ሆነ ዲፕሎማት ከዚህ በኋላ መሾመም የለበትም የሚል ነው።

ካፌ ውስጥ ገብተሸ ስለአገርሽ ምን እየተወራ እንደሆነ ሰምተሸ መውጣት አለብሽ። ይህን አናውቅም። ጋዜጦች ምን እየጻፉ ነው? አምባሳርድ ሆነሽ ተሾመሽ በዛው አገር በአረብኛ የሚታተሙ ጋዜጦች ስለኢትዮጵያ ምን እንዳሉ ማወቅ አለብሽ። ከዚህ ጋር በተያያዘ ሥልጠና ተጀምሯል። ይህም ግን በቂ አይደለም። ሥልጠናውም ቋንቋው ነው። ሥልጠና ወስደው ሲወጡ የሚገቡበት ከባቢ አረብኛ የሚነገርበት ስላልሆነ፣ እንደወጡ በአማርኛ ነው የሚያወሩት። ስለዚህ ቢያንስ የኹለት ዓመት ሥልጠና ከአረቦች ጋር በመነጋገር ውጪ ተምረው ቢመለሱ ጥሩ ነው የሚሆነው። አገር ውስጥ የሚሰጥ ሥልጠናም መኖር አለበት። ይህ ለእኛ ጥቅም ነው።

ከዚህ ጋር በተያያዘ እኔ ጋዜጠኛ በነበርኩኝ ጊዜ ሁሌ የማነሳው አንድ ቅሬታ ነበረኝ። ትልልቅ የመንግሥት ባለሥልጣናት ለሥራ ጉብኝት ወደ ተለያዩ አገራት ለጉብኝት ይሄዳሉ። ለምሳሌ ወደ አረብ አገራት ሲሄዱ፣ አብሮ ቋንቋውን የማያውቅ ጋዜጠኛ ይሄዳል። ይህ ለምን ይሆናል? ጋዜጠኛውኮ ሕዝብ ጋር ወርዶ ስለኢትዮጵያ ምን ታውቃላችሁ ብሎ ሊጠይቅ ይችላል። ጋዜጠኛው በአረብኛ ቢያወራ የበለጠ ተሰሚነት ይኖረዋል። ቋንቋ ሀብት ነውና በዚህ መሠረት ነው መሄድ ያለበት። እናም ሥልጠና መሰጠት አለበት። ጥቅማችንን ማስከበር የምንችለው በዚህ መልክ ስለሆነ፣ ዲፕሎማሲ ላይ በደንብ መሠራት አለበት።

ቋንቋን በሚመለከት አስቀድሞ እንዳነሱት ከሃይማኖት ጋር ማስተሳሰር አለ። በተጨማሪም በአገር ውስጥ ሰላም ማጣት የብሔር ጉዳይ ሲነሳም ቋንቋ ድርሻ አለው። ቋንቋ የመግባቢያ መሣሪያ መሆኑ ላይ ግንዛቤ እንዲኖርና ከእነዚህ ሐሳቦች ለማላቀቅ ምን መሥራት ይጠበቃል?
ቋንቋ ሀብት ነው። ድልድይና መገናኛም ነው። ቋንቋን አንዳንድ ሰዎች ከብሔር ጋር ያስተሳስሩታል። አይደለም። ቋንቋ ቀድሞ ነበር፣ ሁሌም አለ። ቋንቋ መግባቢያና መገናኛ ብቻ ነው። ሌላው የሌሎችን ሥነልቦና እና ታሪክ የምንረዳበት ትልቁ መሣሪያችን ነው። እንደ አገር ስንኖር፣ እንደ ኢትዮጵያ ስታስቢ የጎረቤትን ቋንቋ ማወቅ ትያለሽ። እንደ አገር ውስጥ ደግሞ፣ አማራው አፋን ኦሮሞ ቢለምድ፣ ኦሮሞው አማርኛ ቢለምድ፣ ጉራጌው ትግረኛ፣ ትግሬው ጉራጌኛ ቢያውቅ፣ ይህ ትልቅ ሀብት ነው። በደንብ መለመድ ያለበት ነገር ነው።

በተጨማሪም ስለእኛ ምን እንደተባለ ለማወቅም ያግዘናል። ሱዳን ኹለት ዓመት ተኩል ቆይቻለሁ። ያኔ ስለኢትዮጵያ ምን እየተባለ እንደሆነ በደንብ እንሰማለን። ይህ ነው መሆንም ያለበት። ሠርተንበታል ወይ ነው ትልቁ ነገር። ሙከራ እንዳለ ግልጽ ነው። ከሕዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘም የአቅማችንን እየተፍጨረጨርን ነው። ለግብጽ ምላሽ ለመስጠት ሱዳኖችና የአረብ ጋዜጦች ምን አሉ የሚለውን፣ አገራዊ ግዴታም ስላለብን እያየን ነው። ግን ይህ በቂ አይደለም።

በነገራችን ላይ ግብጾች እኛን በደንብ አጥንተውናል። እኛን ያላጠኑበት መስክ የለም። እንደውም የደረሱበትን ደረጃ ስናይ፣ ካይሮ ባለ ቤተመጻሕፍት አንድ ወዳጄ ያየውን ጽሑፍ ሲነግረኝ፣ ርዕሱ ‹የፖለቲካ አገላለጾች በኢትዮጵያ ጋዜጦች› የሚል ነው። እነርሱ የእኛን ፖለቲካ ማወቅ ስለሚፈልጉ፣ ኢትዮጵያውያን ስለ ፖለቲካ መናገር ሲፈልጉ ምን ዓይነት አገላለጽ ይጠቀማሉ የሚለውን ለማወቅ እንዲመቻቸው ነው። አንድ ግብጻዊ ነው የመመረቂያ ጥናታዊ ወረቀት የሠራበት።

ግብጾች አማርኛ ይችላሉ። በተለይ ዲፕሎማትና የምርምር ባለሞያዎች ግዕዝና አማርኛ ይችላሉ። ግዕዝ እንደውም በካይሮ በዲግሪና በማስተርስ ደረጃ ይሰጣል። እነርሱ የእኛ ቋንቋዎች በዩኒቨርስቲ ደረጃ ሳይቀር ይሰጣሉ። አንደኛ ፍላጎትም ስላላቸው ነው። ከኢትዮጵያና ከሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ አባይን እንዳንጠቀም፣ በነጻና በብቸኝነት ሲጠቀሙ የእኛ እናቶች ግን እስከ አሁን የኃይል አማራጭ አጥተው በጭስ ዐይናቸው እየተጎዳ ነው።

ይህን ያደረጉት እኛ እንዳንጠቀም የፖለቲካ ሴራ ሲሠሩ ቆይተዋል። ይህ እንዲሳካለቸው ያደረገው ደግሞ የእኛን ሥነልቦና በእኛ ቋንቋ ስለተረዱ ነው። እኛ ግን አልተጠቀምንበትም። ቋንቋ ላይ በደንብ መሥራት አለብን። በተለይ አረብኛ ላይ፣ አንደኛ አዲስ አይደለም። የሃይማኖት ቋንቋ ነው ካልንም የክርስትና እንደሆነ ነው ታሪክ የሚያሳየው። ምክንያቱም በአገራችን ቀድሞ የነበረው ክርስትና ነው። እንዳልኩት የቤተክርስትያን መጻሕፍት አብዛኞቹ አረብኛ ነው ምንጫቸው።

ስለዚህ እኛ በሃይማኖት እንኳ እንደልድለው ካልን ክርስትናም ውስጥ አለ። ቤተክርስትያንም በይፋ ትጠቀምበት ነበር። እና ስሱ መሆን የለብንም። ግብጽ ውስጥ ኮፕቲክ ቤተክርስትያን አለ። ቋንቋቸው አረብኛ ነው። ‹ቢስሚላሂ ራህመን ራሂም› ብለው ነው የሚባርኩት። ቋንቋቸው ስለሆነ ነው። በነገራችን ላይ ግዕዝ የሚናገርና አረብኛ የሚናገር ሰው እንደሚግባቡ ማወቅ አለብን። ግዕዝ የሚያወራ ሰው አረብኛ የሚያወራ ይመስላል፣ አረብኛ የሚያወራም ግዕዝ የሚያወራ ነው የሚመስለው።

መገናኛ ብዙኀንስ ምን ያህል ሠርተዋል ማለት ይቻላል? እርስዎም አል ዓለም ጋዜጣ ላይ ሠርተዋልና፣ በዚሁ ቆይታዎ እንዴት ነበር?
ከሚድያ ጋር ተያይዞ ጥሩ ሙከራ አለ። እንዳልኩት ስድስት ዓመት በአል ዓለም ጋዜጣ ሠርቻለሁ። የተለያዩ ኢትዮጵያን የሚያስተዋውቁ አምዶች አሉ። ባህልና ቱሪዝም አምድ ላይ ነበር እኔም የምሠራውና፣ እሱ ላይ ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ ተሞክሯል። ግን ማደግ ባለበት መጠን አላደገም፤ አልተሠራበትም። ሌሎች አፍሪካ አገራት ኬንያም ሆነ ኡጋንዳ፣ ማሊ ወይም ኒጀርና ናይጄሪያ ብትሄጂ፣ እነዚህ አረብ ያልሆኑ አገራት፣ በአረብኛ ብዙ ሚድያ አላቸው። እኛ ግን በጋዜጣ ደረጃ እንኳ ያለን አንድ ጋዜጣ አል ዓለም ነው።

በ2000 የኢትዮጵያ ሚሊኒየም ላይ እንደሚታወሰው ሚዲያዎች መነቃቃት ነበራቸው። በከፍተኛ ጉልበትም ስለኢትዮጵያ ታላቅነት ይጽፉ ነበር። ያኔ ለዛ ተብሎ አልዓለም ጋዜጣ ወደ ኻያ ገጽ አድጎ ነበር። ነገር ግን መልሰው ወደ ስምንት ገጽ አወረዱት። እኔ በጣም እቃወም ነበር። ለምንድን ነው ገጽ የተቀነሰው ብለን በጊዜው የነበሩትን ዋና ሥራ አስኪያጅ ስንጠይቃቸው፣ አዋጪ ስላልሆነ ነው አሉን።

እኛ ያልነው፣ እነዚህ ሚድያዎች ለትርፍ የተቋቋሙ አይደሉም ነው። ይልቁንም የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለማሳየትና ገጽታ ለመገንባት፣ ኢትዮጵያን የምናተስተዋውቅበት፣ ታሪኳን የምናሳውቅበትና የኢንቨስትመንት አማራጭ የምናሳይበት ስለሆነ፣ መንግሥት ደጉሞም ቢሆን ማስቀጠል እንጂ ትርፋማ አይደለም አይባልም። ጋዜጣው አስቀድሞ የተጀመረው ኢትዮጵያውያን ይገዙታል ተብሎ አይደለም። አረቦች እዚህ ያሉ ዲፕሎማቶች ናቸው ሊገዙት የሚችሉት። ዋና ዓላማው ይህ አይደለም ብለን ሞግተናል። ጋዜጣው ከ78 ዓመታት በላይ ታሪክ ያለው ጋዜጣ ነው።
በተጨማሪ ኢቲቪ አረብኛ ዝግጅት አለው። በኢትዮጵያ ራድዮንም እንደዛው። ሌላው የማይታወቀው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በዌብሳይት አረብኛ ዜና አለው። ይህም ጥሩ ጅምር ነው። ዋልታም እንደዚሁ። ከህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ‹ፕራይም ሚድያ› የሚባል አንድ ተቋም ተቋቁሟል። ግብጽ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የማሳሳት ዘመቻ ከፍታብናለች። ግድቡን የሚሠሩት ኢትዮጵያውያን ሳይሆኑ እስራኤል ናት እያሉ ከአረቡ ዓለም ጋር ለማጋጨት የሚሠሩት ሥራ አለ። ፕራይም ሚድያ ሙሉ ለሙሉ በአረብኛ የሚተላለፍ ነው። ስለዚህ ይህም አንድ ጅምር አለ። እና በሚድያው በኩል ጥሩ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።

ራስን ማጋነን ካልሆነ፣ እውነት ለመናገር የጋዜጠኝነት ሙያውን በጣም እፈልገው ስለነበር፣ በዛም ላይ ሰባት ዓመት ከ6 ወር አካባቢ ከኢትዮጵያ ውጪ አረብ አገር ስለኖርኩኝ፣ አገሬን በጣም ነው የምወዳት። ውስጤ ተከፍቶ ቢታይ ከሁሉም ኢትዮጵያዊ በላይ አብልጬ የምወዳት ይመስለኛል። እናም የቻልኩትን ያህል ለማገልገል ሞክሬአለሁ። በጋዜጣው በነበረኝ የስድስት ዓመት ቆይታም፣የጻፍኳቸውን ርዕሶች ስንመለከት የኢትዮጵያን ባህል፣ ታሪክና ወግ፣ ጋብቻና የእርቅ ስነስርዓት ወዘተ የሚሉ የተለያዩ ነገሮችን ለመጻፍ ነው የሞከርኩት። ሦስት ጊዜም ተሸልሜአለሁ፣ ጋዜጠኞችን ለማበረታታት የሚደረግ ሽልማት ነበር።

እንዳልኩት በተቻለኝ መጠን ለመሥራት ሞክሬአለሁ። ግን ኋላ ያኮረፍኩት ሚሊንየም ላይ ኻያ ገጽ የደረሰን ጋዜጣ ለምን እናወርደዋለን ነው። ምክንያቱም ብዙ የሚጻፉ ነገሮች አሉን፣ አረቦች ሊያውቁት የሚገባም ብዙ ነገር አለን። ስለታሪካችን መጻፍ አለበት። ግብጽ ብዙ ጸሐፊዎች አሏት፣ ብዙ ሚድያ አላቸው። ስለኢትዮጵያ መልካምነት የሚጽፉ ግን ጥቂት ናቸው። ስለእኛ የውስጥ ችግር ነው የሚጽፉት።

አሁን በቅርቡ እንኳ የተወዳጁን አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ሞት አስመልክተው በሠሩት ዘገባ፣ ኢትዮጵያ ልትፈርስ ነው፣ ወደ ብሔር ግጭት ልትገባ ነው ዓይነት ዜና ሲሠራ ሳይ ያመኛል።
እናም አል ዓለም አሁን ምን ሆኖ ማየት ትፈልጋለህ ካልሽኝ፣ ጋዜጣው እንዲህ ላሉ የግብጽ ዕይታዎች ምላሽ የሚሰጥ፣ ስለኢትዮጵያ የተሳሳተ አመለካከት ያላቸው ጸሐፍያን ለጻፉት ምላሽ የሚሰጥ፣ የኢትዮጵያን ገጽታ ግንባታ የሚሠራ፣ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ያሉበትና ልዩነት ውበት የሆነባት አገር መሆኗን ወዘተ ይህን ነው ለሌሎች ማሳየት ያለበን። ይህ አል ዓለም ጋዜጣ ላይ ተሠርቶና ጠንካራ ሆኖ ባየው ደስ ይለኛል። ወደፊት ሌሎች እንደሚወጡም እርግጠኛ ነኝ። በደንብ ከተሠራ የኢትዮጵያን መልካም ሥም ከፍ የምናደርግበትና ታላቅነቷን የምናሳይት አጋጣሚ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።

በአገራዊና ቀጠናዊ ትስስር ጥናት ማእከል ማእከሉ የወሰደው ድርሻና ርዕይ?
ወደ ሴንሪስ የተቀላቀልኩት በቅርቡ ነው። ምክንያቱም ከህዳሴ ግድቡ እንዲሁም ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምሥራቅና ከአረብ አገራት ጋር ምን ዓይነት እቅድ ይኑራት የሚለውን ነገር ለማየት ነው። ድርጅቱ ለትርፍ የተቋቋመ አይደለም፣ ከፖለቲካ ነጻ ነው። ጥናታዊ ሥራዎችን፣ ሴሚናሮችን ለማከናወንና ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ለማድረግ የተቋቋመ ነው። አገራችን ኢትዮጵያ በመካከለኛው ምሥራቅና ቀይ ባህር አካባቢ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ጥቅሟ የሚከበርበትን መንገድ ለማፈላለግ ታስቦ የተመሠረተ ነው።

ኢትዮጵያ በአፍሪካና በምሥራቅ የነበራት ግንኙነት አለ። ታላቋን ኢትዮጵያ ወደ ነበረችበት የመመለስና ታሪኳን የማስተዋወቅ ሁኔታ ነው። አንዳንዴ በቀጠናችን አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነቶች ይኖራሉ፣ ሰላምን የሚያደፈርሱ። እነዚህን በጥናትና ምርምር የተደገፈ ሥራ በመሥራት ጣልቃ ገብነቶችን የማስቆም፣ ከመንግሥት ጋር በመተባበር መከላከል ነው። ዋናውም ትስስር ላይ ነው የሚሠራው።
አንድ ሰው ብቻውን ጎዶሎ ነው። እኔ የተሰጠኝ ተሰጥኦ አለ፣ አንቺ የራስሽ ተሰጥኦ አለሽ። እኔ እና አንቺ ከሌሎች ጋር አንድ ላይ ስንሆን ነው የተሟላ ነገር የሚገኘው። እንደውም የሳበኝ ይህ ትስስር የሚለው ቃል ነው። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ታላቅ ነበረች፣ እስከ ሕንድ ድረስ የእኛ ግዛት ነው፣ ሶማሌ እና ጅቡቲ የእኛ ነበሩ እንላለን። አሁን ይህ ትስስር ግን የለም። ያ እንዲመጣ የሕዝቦች አንድነትና ፍቅር እያደገ፣ እየተዋሀደና መስተጋብር ይኖረው ነበር። ከዚህ አንጻር ነው የተቋቋመው። ወደፊት የማስበው ጥናታዊ ሥራዎችን ለማዘጋጀት ነው። ለዚህም ባለሞያዎች ጋር ሆኖ መሥራት፣ የታሪክ ምሁራንን በመጋበዝ አውደ ጥናቶች እንዲኖሩ ማድረግ ነው የታሰበው።

ቅጽ 2 ቁጥር 88 ሐምሌ 4 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here