እዮብ ተፈራ ይባላሉ የሚኖሩት አዲስ አበባ ነው፡፡ እዮብ አሜን እዮብ የምትባል አራት አመት ልጅ እንዳለቻቸው ይናገራሉ፡፡ አሜን በ2102 ኬጅ አንድ ተማሪ ነበረች፣ በአለም አቀፍ ደረጃ ድንገት ተከስቶ አለምን አንድ ያደረገው እና ያሽማቀቀው ኮቪድ-19 አሜንን እና መሰሎቿን ከሚወዱት ትምህርታቸው እና ጓደኞቻቸው ለሦስት ወራት ነጥሏቸው ቆይቷል፡፡ የዛሬን አያድርገው እና በኢትዮጵያ ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ለተማሪዎች ልዩ ጊዜ ነበር፣ እንዲህ እንደ ዘንድሮው ሳይማሩ እና በፈተና ሳይመዘኑ ከክፍል ወደ ክፍል ዘሎ መግባት ባይሆንም፡፡
ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ በተከሰተ በሳምንታት ልዩነት ነበር የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች እና ሌሎችም በትምህርት ላይ የነበሩ ከኬጅ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች ሳያስቡት ከትምህርት ቤት ቀርተው በቤታቸው ለመዋል የተገደዱበት ጊዜ ነበር፡፡ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችም ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ ግድ ሆኖባቸው ዩኒቨርስቲዎችን ለቀው ወጥተው በቤታቸው ይገኛሉ፡፡ የአስረኛ ክፍል ተማሪ ነበረችው ገንዘብ ቁምላቸው በዚሁ ጊዜ ነበር ከምትወደው ትምህርት ተለይታ በቤቷ አንድትቆይ የተገደደችው፡፡ ገንዘብ ትምህርት ሚኒስቴር ከሰምንትኛ እና ከ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በስተቀር ያለ ምንንም ፈተና ወደ ቀጣዩ ክፍል እንድተላለፉ በመደረጉ ደስተኛ እንዳልሆነች እና አንድ ዓመት ደግማ የቀረባትን ትምህረት ብታጠናቅቅ ምርጭዋ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ ትናገራልች፡፡
በሌላ በኩል አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ተማሪዎች እና ወላጆች ብብዛት ተማሪዎች ያለፈተና ወደ ቀጣዩ ክፍል ማለፋቸውን እንደሚጋሩ ያስረዳሉ፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት የሚቀርቡት ተማሪዎች አንድ ዓመት ደግመው ቢማሩ የአንድ ዓመት ጊዜ በከንቱ እንደሚልፍባቸው እና ለሌሎች አዲስ ተተኪ ተማሪዎች ሊማሩበት የሚችሉበት ቦታ መልቀቅ እንዳለባቸው በማመን ነው ይላሉ፡፡ የአሜን አባትም ይሄንኑ ሀሳብ ይጋራሉ ልጃቸው ገና የአራት ዓመት ህፃን ብትሆንም አንድ ዓመት እንዲያልፋት አይፈለጉም፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር ከትምህርት ውጭ በቤታቸው የሚገኙ ተማሪዎችን ቀጣይ እጣ ፋንታ ለመወሰን ከክልል እና ከራሱ ኪሚኒስቴሩ ከፍተኛ አመራሮች ጋር አደረኩት ባለው ወይይት፣ አስከ 7ኛ ከፍል እና ከ9ኛ አስከ 11ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን በቀጣይ 2013 ትምህርት ሲጀመር የ45 ቀን ማካካሻ ትምህርት ወስደው ያለ ምንም ፈተና ወደቀጣዩ ከፍል እንዲሸጋገሩ ወስኗል፡፡
እንዲሁም የ8ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች በ2013 የማካካሻ ትምህርት ከወሰዱ ብኃላ ወደቀጣዩ ክፍል የሚልፉበትን እና ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገቡበትን የመመዘኛ ፈተና እንደሚፈተኑ ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡ የ12ኛ ከፍል ተፈታኝ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርስቲ ለመግባት የሚወስዱት ፈተና በበይነ መረብ ለመስጠት መታሰቡን እና ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስቴሩ ጌታሁን መኩሪያ(ዶ/ር) ሀምሌ 3/2012 በዚሁ ጉዳይ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ጠቁመዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔ ተገቢነት እና አላማ
ትምህርት ሚኒስቴር የወሰነውን ውሳኔ በተመለከተ አዲስ ማለዳ በተለያዩ የትምህርት ደረጃ ያሉ ተማሪዎችን እና የተማሪ ወላጆችን አነጋግራ ያገኘችው ምላሽ ብዛት በውሳኔው እንደሚስማሙ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ እንደምክንያት የሚነሱት ደግሞ አሁን በትምህርት ላይ የነበሩ ተማሪዎች አንድ ዓመት ቢያልፋቸው ከእድሜቸው አንድ ዓመት እንደመቀነስ ነው ይላሉ፡፡ ሁለተኛው ያቀረቡት ምክንያት ደግሞ አዲስ ተከታይ የሆኑ ትውልዶችን(አንድ አዲስ ትውልድ) ወደ ኃላ እንደሚጎትት በማመን ነው፡፡
የአዲሱ ኢትዮጵያ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ዋና አስተባባሪ ፕሮፌሰር ጥሩሰው ተፈሪ የትምህርት ሚኒስቴር በተማሪዎች የቀጣይ ዓመት ትምህርት ዘመን እጣ ፋንታ ላይ ያሳለፈው ውሳኔ የተፈጠረውን የትምህርት ክፍተት ተከትሎ ወደፊት ሊፈጠር የሚችለውን ብሔራዊ የትምህርት ቀውስ ለመመከት ያለመ መሆኑን በመግለጽ፣ በውሳኔው ተገቢነት እንደሚስማሙ ይናገራሉ፡፡
ፕሮፌሰር እንደሚሉት አሁን በተፈጠረው አለም አቀፍ ችግር ተማሪዎችን እንዲደግሙ ማድረግ ወይም አንድ ዓመት እንዲያልፋቸው ማድረግ በትምህርት ስርዓቱ ላይ ብሔራዊ ቀውስ እንደሚፈጥሩ ይናገራሉ፡፡ እንደ ፕሮፌሰሩ እምነት አሁን በትምህርት ላይ የሚገኙት ተማሪዎች ለሚቀጥለው አዲስ ተተኪ ትውልድ ቦታ መልቀቅ እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዜዳንት ዮሀንስ በንቲ(ደ/ር) የፕሮፌሰር ጥሩሰውን ሀሳብ በመጋራት አለም አቀፉ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአለም አቀፍ ደረጃ የትምህርት ቀውስ እንደፈጠረ በማንሳት፣ ተማሪዎች አሁን ያሉበትን ክፍል እንዲደግሙ ማድረግ የረጅም ጊዜ ቀውስ(Long term crisis) እንደሚፈጥር እና አንድ ትውልድ(one generation) ትምህርት ቀውስ እንደሚፈጥር ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡
ዮንኒስ(ደ/ር) የአለም አቀፉ የመምህራን ማህበር አባል ናቸው፡፡ አለም አቀፉ የመምህራን ማህበሩ ኮቪድ-19 በአለም አቀፉ የትምህርት ስርዓት ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖ በተመለከተ በተደጋጋሚ ውይይቶች ማድረጉን የጠቆሙት ዮሀኒስ(ዶ/ር)፣ የተፈጠረውን የትምህርት ጉድለት ለመሙላት፣ እንደየ አገራቱ ትምህርት ሲጀመር በቅድሚያ ተማሪዎች ያልተማሯቸውን መሰረታዊ ትምህርቶች መማር እንዳለባቸው ማህበሩ አቅጣጫ መጠቆሙን ጠቁመዋል፡፡ ማህበሩ በአለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው ኮቪድ-19 የትምህርት ቀውስ(Education crisis) እንደሆነ መግለጹን እና ሀገራት መውሰድ ያለባቸውን እርምጃ ማመላከቱን ዮሀኒስ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
ተማሪዎች ቀጣዩን ከፍል ትምህርት ከመጀመራቸው በፊት ያለፋቸውን ትምህርት ሳይወስዱ አዲሱን ክፍል ትምህርት እንደማዩጀምሩ ዮሀኒስ(ዶ/ር) ለዲስ ማለዳ አስረድተዋል፡፡ ዮሀንስ አክለውም የመምህራን ማህበሩ ተማሪዎች ትምህት ሲጀምሩ ፈተና አይፈተኑ እንጅ ያለፋቸውን ትምህርት እንደሚማሩ አረጋግጠዋል፡፡ ሆኖም ግን በትምህርት ስርዓቱ ላይ ተጽኖ ማሳደሩ አይቀርም በሚለው ዮሀኒስ ይስማማሉ፡፡
ፕሮፌሰር ጥሩሰውም እንደ ዮሀኒስ(ዶ/ር) አሁን የሚኖረው ትምህርት አሰጣጥ ከዚህ በፊት ከነበረው የተለየ ሊሆን እንደሚችል ይናግራሉ፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ተማሪዎች ትምህርት ትተው በቤታቸው መቀመጣቸው የፈጠረባቸው የስነ ልቦናና የመዘናጋት ተጽኖ ሊኖር እንደሚችል በማመላከት ነው፡፡
የማካካሻ ትምህርትና ትኩረት
ትምህርት ሚኒስቴር ማስቀመጠው መስፈርት መሰረት ያለ ፈተና ወደ ቀጣዩ ክፍል የሚሸጋገሩትም ሆነ ለፈተና የሚቀመጡ ተማሪዎች በቅድሚያ ማካካሻ ትምህርት እንደሚሰጣቸው አስቀምጧል፡፡ ዮሀንስ(ዶ/ር) ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ያለፈተና ወደ ቀጣዩ ክፍል የሚሽጋገሩ ተማሪዎች በምንም መልኩ ቢሆን ያለተማሩትን ትምህርት ሳይማሩ ቀጣዩን ክፍል ትምህርት መማር እንደሌለባቸው ይገልጻሉ፡፡ ይሄ ካልሆነ የሚፈጠረው ክፍተት በአገሪቱ በነበረው የትምህርት ጥራት ጉድለት ላይ ሌላ ፈተና እንደሚሆን ስጋት አላቸው፡፡
ፕሮፌሰር ጥሩሰው በበኩላቸው ተማሪዎች የማካካሻ ትምህርት ሲሰጣቸው ከፍተኛ ስልታዊ አካሄድና ጥንቃቄ እንደሚሻው ይናገራሉ፡፡ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ስልታዊ የማካካሻ ትምህርት አሰጣጦች ጥራትን መሰረት ያደረጉና የተመረጡ መሆን እንደሚገባቸው የፕሮፌሰር ጥሩሰው እምንት ነው፡፡ እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ አሁን በሚኖረው ትምህርት አሰጣጥ ስርዓት እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉንም ትምህርት አግበስብሶና አድበስብሶ ከማለፍ ይልቅ፣ የተመረጡ መሰረታዊ የሆኑ ትምህርቶችን በጥራት መስጠቱ ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ይላሉ፡፡
የተመረጡ መሰረታዊ ትምህርቶች ሲባል ተማሪዎች ቀጣይ ክፍል ላይ ለሚማሩት ትምህርት በበቂ ሁኔታ ለዘጋጅ የሚችልና መሰረታዊ እውቀት ሊሰጥ የሚችሉ መሆን እንደሚገበቸው ፕሮፌሰር አመላክተዋል፡፡ ለዚህም ርዕሰ መምህራን በትኩረት መስራት እንዳለባቸው ፕሮፌሰር ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም ተማሪዎች እኩል ትምህርትን የመረዳትና የመቀበል አቅም ስሌላቸው፣ በልዩ ሁኔታ የተማሪዎችን ብቃት ደረጃ በማመዛዘን እኩል ደረጀ ላይ አስከሚደርሱ ማብቃት የግድ እንደሚል ፕሮፌሰር ይናገራሉ፡፡
የበይነ መረብ ፈተና ፍትሐዊነት
ትምህርት ሚኒስቴር በወሰነው ውሳኔ መሰረት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የ45 ቀን ማካካሻ ትምህርት ወስደው ፈተና ወስደው ወደ ቀጣዩ ክፍል(ወደ ዩኒቨርሲቲ) እንዲዘዋወሩ በወሰነው ውሳኔ መሰረት፣ ፈተናው የሚሰጠው በበይነ መረብ መሆኑ ተገለጿል፡፡ ለዚህም ትምህርት ሚኒስቴር ዝግጅት እያደረግሁ ነው ብሏል፡፡
ፕሮፌሰር ጥሩሰው በኦንላይን ፈተናው ፍትሐዊነት እና ውጤታማነት ላይ ከአገሪቱ የቴክኖሎጂ ልምምድና የተማሪዎች እውቀት አንጻር አስቸጋሪ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ተደራሽነትና ልምምድ በተማሪዎች ዘንድ ከዚህ በፊት የዳበረ ካለመሆኑ ባሻገር በሁሉም ቦታ ተመሳሳይ የበይነ መረብ ፈተና አወሳሰድና ኮምፒተር አጠቃቀም ልምድ ስለማይኖር ተማሪዎች አውቀቱ ቢኖራቸውም መደናገር እንደሚፈጠር ፐሮፈሰር ጥሩሰው ለአዲስ ማለዳ አመላክተዋል፡፡ ተማሪዎች እውቀቱ ኖሯቸው በልምድና እና አጠቃቀም ጉድለት ለሚፈጠሩ ክፍተቶች ትምህርት ሚኒስቴር ከወድሁ ሊስብብት እንደሚገባ ፕሮፌሰር አመላክተዋል፡፡ በተጨማሪም ትምህርት ሚኒስቴር ተማሪዎችን በደፈናው ኦንላይን ፈተና ላይ እንድቀመጡ ከማድረግ ይልቅ ከወድሁ ለሁሉም ተማሪዎች በቂ ስልጠናና ልምምድ መስጠት እንዳለበት ፕሮፌሰር ተናግረዋል፡፡
በተለይም በገጠራማ አካባቢ የሚማሩ ተማሪዎች የኮምፒተር አጠቃቀማቸው በከተማ አካባቢ ከሚማሩ ከሚማሩ ተማሪዎች በእጅጉ ልዩነት እንደሚኖረው የጠቆሙት ፕሮፈሰር ጥሩሰው፣ በሁሉም ተማሪዎች በኩል በቂና ተመጣጣኝ የኮምፒተር ችሎታ መፈጠሩን በሚገባ ማረጋገጥ እንደሚገባ ፕሮፌሰር አጥብቀው ተናግረዋል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች በኦንላይን ፈተኛ የሚፈተኑበትን ስርዓት በተመለከተ ግንዛቤ ስራ እንደሚሰራ አመላክቷል፡፡
ኮቪድ-19 የፈጠረው የትምህርት ክፍተት እንደት ይሞላ
ፕሮፌሰር ጥሩሰው ኮቪድ-19 በትምህርት ስርዓቱ ላይ እና በተማሪዎች ላይ እስካሁን የፈጠረው እና ወደፊትም የሚፈጥረው ስነ-ልቦና እና መዘናጋት ችግር እንደሚኖር ያምናሉ፡፡ ለዚህም የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት ቅድም ዝግጅት እና ልዩ ትኩረት እንደሚሻ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው ይላሉ ፕሮፌሰር፡፡ እንደ ፕሮፌሰር ጥሩሰው ገለጻ የትምህርት በቤት አስተዳደር ስራተኛች፣ መምህራን፣ በተለይም ርዕሰ መምህራን ወላጆች እንድሁም የሚመለከታቸው አካላት ተማሪዎቹን ወደ ትምህርት ሲመለሱ ከወትሮው በተለየ ሁሌታ በትኩረት በመስራት የተማሪዎችን ስነ-ልቦና ማስተካከልና ዝግጁ ማድረግ ቅድሚያ ሊሰጠው ይእንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
በተለይም ርዕሰ መምህራን ትምህርት ቤታቸውን የትምህርት ስርዓት ጊዜው በሚፈልገው ልክ ለማሳለጥ ከወዲሁ ትልቅ ስራ መስራት አለባቸው ይላሉ ፕሮፌሰር ጥሩሰው፡፡ በተለይም ቅድሚያ ትኩረት የሚሹ ነገሮች ኮቪድ-19 መቸ እንደሚጠፋ ስለማይታወቅ የተማሪዎችን ጤንነትና ስነ-ልቦና ሊጠብቅ የሚችል የትምህርት አካባቢ(Education enviromenet) መፍጠር እንደሚገባ ፕሮፌሰር ገልጸዋል፡፡ ወቅቱን የሚመጥን የትምህርት አካባቢ ከመፍጠር በተጨማሪ ሁሉም ተማሪ እኩል ትምህርትን የመረዳት አቅም ስለማይኖረው በልዩ ሁኔታ ልዩ ክትትልና ሚፈልጉ ተማሪዎችን ተከታትሎ የመረዳት ደረጃቸውን ማመጣጠን ይገባል ብለዋል ፕሮፌሰር፡፡
ምናልባትም ኮቪድ-19 መቼ እንደሚጠፋ እና ወደፊት ምን እንደሚፈጠር ሰለማይታወቅ ትምህርት ቤቶች ተጨማሪ መማሪያ ክላሶችን ቀድም በማዘጋጀት የተማሪዎች ርቀት አስጠብቀው የትምህርት ሂደቱን ለማስቀጠል መዘጋጀት አለባቸው ሲሉ ፕሮፌሰር አመላክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዜዳንት ዮሀኒስ(ዶ/ር) በበኩላቸው ክፍተቱን ለመሙላት የየአንዳንዱ ባለድርሻ አካላት ትብብር የሚጠይቅ መሆኑን በማንሳት፡፡ የኦንላይን ትምህርት ስርዓትን በማሰፋት ተማሪዎች የጎደላቸውን እውቀት እንዲሞሉ ማድረግ አንዱ አማራጭ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በጠቅሉ የሀገሪቱ የትምህርት ጥራት ወደፊትም ቢሆን ትኩረት የሚሻ መሆኑን እና ለማሻሻል ትልቅ ትኩረት መደረግ እንዳለበት የሚናገሩት ፕሮፌሰር ጥሩሰው፣ “የትምህርት ጉዳይ፣ የልማት ጉዳይ ነው፡፡” ሲሉ ይገልጹታል፡፡
ቅጽ 2 ቁጥር 89 ሐምሌ 11 2012