በሙሉ ወንጌል ውስጥ ተከስቶ የነበረው አለመግባባት እንዲፈታ ውሳኔ ላይ ተደረሰ

Views: 980

ከወራት በፊት በኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተከስቶ የነበረው አለመግባባት በአስቸኳይ እልባት እንዲያገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ውሳኔ ማሳለፋቸውን ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ። በቅርቡ ቅሬታ አቅራቢዎችን በጽሕፈት ቤታቸው ጠርተው ያነጋገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተከሰተ የተባለው ነገር እጅግ አሳፋሪ እንደሆነና ጉዳዩ በአፋጣኝ ሊገታ እንደሚገባው ተናግረው እስካሁን ደሞዝ ያልተከፈላቸው አባላትም ደሞዛቸው እስከ እሁድ፣ ሐምሌ 14/2011 እንዲከፈላቸውና ታግደው የነበሩ ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያኗ እንዲመለሱ ውሳኔ አሳልፈዋል።

በኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን ጠቅላላ ጉባኤ ታኅሳስ 12 – 13/2011 ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ቤተ ክርስቲያኗ ከሐምሌ 2006 ጀምሮ ትጠቀምበት የነበረውን መተዳደሪያ ደንብ ማሻሻሉ ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ ተሻሻለ የተባለው መተዳደሪያ ደንብ አሠራር እና የሕግ ክፍተት እንዲሁም የአስተምሮ እና ሥነ ምግባር ችግሮች አሉበት በሚል ቅሬታዎች ቀርበውበት የነበረ ሲሆን ቅሬታዎችም ወደ ተካረረ አለመግባባቶች አምርተው በርካታ ግለሰቦች የተደበደቡበት ወደ ክስም የተሔደበት አጋጣሚዎች ተፈጥረው ነበር።

ቅሬታ አቅራቢዎች በተደጋጋሚ በሰላም ሚኒስቴር በኩል እልባት ለማግኘት በርካታ እንቅስቃሴዎችን እና አቤቱታዎችን በቃል እና በደብዳቤ በማስገባት ምላሽ በመጠባበቅ ላይ ነበሩ። ይሁን እንጂ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ከጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ ጋር በመወያየት እልባት እንዲሰጣቸው እና ክስ ተመስርቶ ከነበረም እንዲቋረጥ ስምምነት ላይ መደረሱን ምንጮች ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል። ምንጮች አያይዘውም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዳዮን በቅርበት እየተከታተሉ ተፈጠሩ የተባሉትን ችግሮች እንዲፈቱ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ኀላፊውን ሹመቴ ግዛው (ዶ/ር) እንደመደቡላቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ ባደረገችው ማጣራት በኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን ቀጠና ኹለት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰባት ሰዎች ከቤተክርስቲያን የሚከፈላቸው ደሞዝ ተቋርጦባቸው የነበረ ሲሆን ምዕመናን በግላቸው ከኪሳቸው በማዋጣት ደሞዛቸውን እንዲከፈላቸው እንደተደረገ ለማወቅ ተችሏል።

በሌላ በኬል ደግሞ በተጠቀሰው አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተሸሻለ በተባለው ደንብ ላይ ጥያቄ ያነሱ የተወሰኑ ግለሰቦች ተመርጠው ሥም ዝርዝራቸው ለቤተ ክርስቲያኗ የጥበቃ አባላት እንዲተላለፍ ከተደረገ በኋላ ከግንቦት 24 /2011 ጀምሮ እንዳይገቡ የሚል ክልከላ ተደርጎባቸው ነበር። ይሁን እንጂ ይህም ክልከላ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይት ከተደረገ በኋላ ክልከላው እንዲነሳ እንደተደረገ ተረጋግጧል። አዲስ ማለዳ በሰኔ 1/2011 ዕትሟ ባወጣችው ዘገባም ሆነ በዚህኛው ዕትም ስለ ጉዳዮ የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን ፕሬዘዳንት ፓስተር ይልማ ዋቄን ለማግኘት ያደረገችው ጥረት ቢሳካም ስለ ጉዳዩ ግን ተጨማሪ ማብራሪያ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 37 ሐምሌ 13 2011

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com