የችግኝ ተከላ ዘመቻ ወጎች

Views: 189

ሰኞ፣ ሐምሌ 22 በአገር ዐቀፍ ደረጃ የታቀደውና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጠራው “የአረንጓዴ አሻራ” ቀን በተሳካ ሁኔታ መካሔዱ በርካታ ማኅበራዊም ሆነ መደበኛ የመገናኛ ብዙኀንን ቀልብ ስቦ አልፏል። በአንድ ቀን 200 ሚሊየን ችግኞች ሊተከሉበት ከታሰበለት የችግኝ ተከላ ዘመቻ ቀን በኋላም ግን መነጋገሪያነቱ ቀጥሏል።

ሙሽሮች በደመቀ የሰርግ በዐል ልብሳቸው፤ አራስ ከነጨቅላ ልጇ፤ እርጉዝ እንዲሁም የ91 ዓመት አዛውንትም በችግኝ ተከላ ዘመቻው ጋር በተገናኘ ትኩረት አግኝተው በተለየ መነጋገሪያ ሆነዋል። ሌላው ከዚሁ ጋር በተያያዘ መነጋገሪያ የሆነው የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመሰራጨት ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን የችግኝ ተከላው አካል መሆናቸው ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ደቡብ ክልል በማቅናት ‘በአንድ ድንጋይ ኹለት ወፍ’ እንዲሉ፤ አንድም በአርባ ምንጭና በወላይታ በመገኘት ችግኝ የተከሉ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ በወላይታ ፖለቲከኞችና ከኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አድርገዋል።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ወደ አማራ ክልል በማቅናት በጎንደር የችግኝ ተከላ ከማድረጋቸው በተጨማሪ ጎንደር ዙሪያ ገባውን ጎብኝተዋል፤ የባሕላዊ አልባሳት ሽልማትም ተበርክቶላቸዋል። የብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የአፋርን ባሕላዊ ልብስ በመልበስ የዘመቻው ተካፋይ ከመሆን ባሻገር ልዩ ትኩረት አግኝተዋል።
ሌላው ከችግኝ ተከላ ዘመቻው ጎን ለጎን ምፀት አዘል ምስሎችም በሰፊው በተለይም ማኅበራዊ ትስስር መድረኮችን አጨናንቀው ነበር። “የወደፊቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ” በማለት በጫካ መካከል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወንበር ላይ ተቀምጠው የሚያሳይ ፎቶ በሰፊው ብዙዎች ተቀባብለውታል።

ምፀታዊ ቀልዶችም እንዲሁ የብዙዎች መነጋገሪያ ከሆኑት መካክል የሚገኙ ሲሆን ከዚህም መካከል “ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሩን ጫካ በጫካ በማድረግ የሽፍቶች መናኸሪያ እንዳንሆን” የሚል ይገኝበታል።

በአጠቃላይ ይኽ የችግኝ ተከላ ዘመቻ ብዙኀኑን የማኅበረሰብ ክፍል ያስማማ ሆኖ አልፏል ሊባል ይችላል፤ ሲሉ አንዳንዶች ተደምጠዋል። ከታቀደውም በላይ ከ353 ሚሊዮን ችግኞች በላይም በመትከል የስኬታማ ድርብ ድል ተዳጅቷል ቢባል ብዙዎች ያስማማል።

ቅጽ 1 ቁጥር 39 ሐምሌ 27 2011

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com