“ያንዲት ምድር ልጆች” ታሪካዊ ልብወለድ መጽሐፍ

Views: 803

አማረ ተግባሩ (ዶ/ር) “ያንዲት ምድር ልጆች” በሚል ርዕስ ከዓመታት በፊት ያሳተሙትን ታሪካዊ ልብ ወለድ በድጋሜ ለአንባቢያን መቅረቡን መነሻ በማድረግ፥ ዮናስ አሽኔ (ዶ/ር) መጽሐፉ ምንም እንኳን ከፀረ ጣሊያን የአርበኞች ትግል እስከ አብዮቱ መንደርደሪያ ድረስ ያለውን ትግል የሚዳስስ ቢሆንም በትላንት እና በዛሬ መካከል ያለውን አንድምታ ቃኝተዋል።

 

ደራሲው አማረ በመቅድም ውስጥ “ምንም ዓይነት የጽሑፍ ሥራ መገምገም ያለበት በተፃፈበት የታሪክ ወቅት ውስጥ በመሆኑ” ከዚሁ መንፈስ አንጻር መጽሐፉ እንዲነበብ ይጠይቃሉ። እንደ “ያንዲት ምድር ልጆች” ዓይነት ታሪካዊ ልብ ወለድ እንዴት እናንብብ? በምናብ ተጉዘን የደራሲው ዘመን መንፈስ ተላብሰን እናንብብ ወይስ ከእኛ ዘመን ማማ ላይ ሆነን የመጽሐፉ ፋይዳ በእኛው ዘመን መነጽር እንመልከት? እንደነ አማረ ተግባሩ ዓይነት የ‘ያትውልድ’ አሳቢዎች መጻሕፍትን በእነሱ ዘመን መንፈስ ብቻ ማንበብ ይቻል ይሆን? ለእኔ መልሱ አሉታዊ ነው። ምክንያቱም የ‘ያ ትውልድ’ የሕይወት ተሞክሮ በታሪክ ላይ ያነሳቸው ጥያቄዎችና ተግባሮች ስህተቶችም ሆነ ስኬቶች ለመማር የዚህን ዘመን መንፈስ ተላብስን መመርመር ይጠይቃል። ምናልባትም ይህ ተፈጥሯዊ የትናንት እና የዛሬ መስተጋብር ነው።

የዘመን ጉዞ ዑደታዊ ነው ይባላል። ዑደቱ የሚከፋፈለው በተፈጥሮአዊ ኩነቶች በመሬት ዙረት ወይም በጨረቃ ዑደት ሳይሆን በማኅብረዊ እና በፖለቲካዊ ክንውኖች ዑደት ነው። ‘ያ ትውልድ’ ራሱን ከአብዮቱ ጋር በማስተሳሰር ይገልጻል። የቅድመ አብዮትም ሆነ የአብዮት ዘመን ከዚሁ ከእኛው የታሪክ ዘመን ጋር በታሪክ ሰንሰለት የተቆራኘ ነው። የታሪክ ዘመን ከዓውዱ ነጥለን በማውጣት መመልከት የምንችልም አይመስለኝም። ታሪክ የትናንት ቢሆንም ከዛሬ ጋር የተነጠለ አድርገን ማየት አይቻልም። በትናንት ውስጥ የተከናወኑ የዛሬ ሰዎች ከሚከውኗቸው ተግባራት ጋር የተገናኙ ናቸው። እኔም “ያንዲት ምድር ልጆች” በትናንት እና በዛሬ መካከል እንደሚደረግ ንግግር አነበዋለው፤ ማንበብ በአንባቢው ሜዳ ያለች የአንባቢ ኳስ እንጂ የደራሲው አይደለችም።

መጽሐፉ በዘመኑ ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግበት ወህኒ ቤት ከተፃፉ መጻሕፍት አንዱ ሲሆን በአምስት ክፍሎች የተከፋፈሉ እያንዳንዳቸው ከአራት እስከ 13 ምዕራፎች ያሉት ሆኖ በ438 ገጾች ተቀንብቧል። የታሪኩ አብዛኛው ዑደት አዲስ አበባ ዙሪያ ቢያደርግም ሌሎች ከተሞችን ለምሳሌ እንደ ጎሬ፣ ጅማ፣ ጎጃም፣ ጎንደር፣ ኡመራ የመሳሰሉት በትረካው በተለያየ ደረጃ አካትቷል። የአዲስ አበባ ሰፈሮች በተለይም የድሆች መኖሪያዎች የታሪኩ ዓውዶች ናቸው። ታሪኩ ከፀረ ጣሊያን የአርበኞች ትግል እስከ አብዮቱ መንደርደርያ ይወስደናል። ኹለቱን የነፃነት ትግሎች ትሰስር በማሳየትም የተዋጣለት መጽሐፍ ነው። አማረ የመጽሐፉን ታሪክ በምናብ በምዕራብ ኢትዮጵያ በጎሬ እና ሱዳን ስለተዋወ ቋቸው ኹለት አርበኞች ጀምረው ኢትዮጵያን እየዞሩ አዲስ አበባን ዋና የታሪክ መከናወኛ አድርገዋታል።

የዚህ ታሪካዊ ልብ ወለድ ገፀ ባሕርያት በጣም ብዙ ናቸው። ዋነኞቹ ብላታ ጎበዝ አየሁ ከላይኛው መደብ የሚመደቡ ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ በመሔድ ጣሊያንን ከተዋጉ አርበኞች አንዱ ሲሆኑ በድኅረ ጣሊያን ጊዜ ለውጥ ፈላጊ አርበኛ የነበሩ የቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ቀንደኛ ተቃዋሚ፤ ብዙ ጊዜ በግዞት የሚቀጡ የነ ታከለ ወልደ ሐዋርያት፣ በላይ ዘለቀ እና በጀሮንድ ተክለ ሐዋርያት ዓይነት የለውጥ አራማጆችን የሚወክሉ ናቸው።

ሌላው በአርበኝነታቸው ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ ውስጥ የጭቁኖችን ጥያቄ ያነሱ ለፍትሕ፣ ለእኩልነት እና ለነፃነት የታገሉ ተራማጆችን የሚወክሉት ባሻ ቢተው የተባሉ አርበኛ ናቸው። የባሻ ቢተው በወጣትነት ጣሊያንን የወጉ፣ የቆሰሉ አገር ወዳድ አርበኛ በስተርጅና ከወጣት እና ከልጆች ጋር መዋል የሚወዱ የአርበኝነት ታሪክን ለአዲስ ትውልድ በታሪክ ፋይዳው ብቻ ሳይሆን ለአዲሰ የነፃነት ትግል እርሾ እንዲሆን የሚተረኩ የተለየ ባሕርይ ያለቸው ተራማጅ ነገር ግን በዘመኑ በነበረው አገዛዝ የተረሱ እና የተገለሉ አርበኞችን የሚወክሉ ናቸው። ባሻ ቢተው የአባት አርበኞች እና የአብዮተኞች ድልድይ የሆነ ትውልድን የሚውክሉም ይመስለል።

ባለቤታቸው እመት ጌጤነሽ ብዙ መስዋዕትነትን በአደባባይ ከከፈሉ ባሎች ጀርባ ሆነው የታሪክ መነጽር ከማይመለከታቸው የብዙ ሚስቶችንና እናቶችን ታሪክ ይወክላሉ። በ“ያንዲት ምድር ልጆች” ከታሰሩ፣ ከተገደሉ እና ከተሰደዱ ወንዶች ጀርባ ቤተሰብ ያጸኑ፣ ትውልድ የቀረፁ እና የማኅበረስብ ቀጣይነትን ያረጋገጡ በእመት ጌጤነሽ ይወከላሉ።

ልጃቸው በላይነሽ የብዙ ምስኪን ሴቶች፤ እናቶች፤ ሚስቶች፤ ፈቶች፤ የቡና አበጣሪ ሴቶች፤ ቡና ቤት አስተናጋጆች፤ ሴተኛ አዳሪዎች ከማጀት እሰከ አደባባይ በማኅረሰብ ጭቆና የታሰሩ፤ የተንገላቱ እና የተበዘብዙ እንሰቶችን ትወክላለች። የባሻ የልጅ ልጅ ከስኬታማ አያቶች የነጻነት፣ የእኩልነት እና የፍትሐዊነት ትግሉን ተቀብለው ያቀጣጠሉትን ብዙ ታሪክ ያልተፃፈለቸውን የተራማጅ ሴት ሠራተኞችን ትወክላለች። ደብሪቱ ስብሐት ሌላዋ ከቤት ሠራተኝነት ሕግ የማያውቀው ሚስትነትና እናትነት እስከ ሴት አዳሪነት በሚቀያየር የከተማ የጉስቁልና ሕይወት የሚኖሩ ምሰኪን ሴቶች ተምሣሌት ናት፤ ከቀጠሪዋ የወለደችው ፈጠነ ለማይረባ ክፍያ ጉልበታቸውን የተበዘበዙ ነገር ግን የአብዮቱን ዋዜማ እምቢተኝነት ችቦ ያቀጣጠሉ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችን ይወክላል።

በአጠቃላይ በመጽሐፉ የባሻ ቢተው የቤተሰባቸው እና የብዙ ጓደኞቻቸው ሕይወት የቅኝ ግዛት ትግልን ከደኅረ ቅኝ ግዛት ዘመን ከተስተዋሉ ከእምቢተኝነት እና የአብዮት እንቅስቃሴ ጋር የሚያያይዙ ተረኮች ናቸው።

የመጽሐፉ ዋና ገፀ ባሕሪያት ከምዕራፍ ምዕራፍ እየተቀየሩ ከባሻ ቢተው አርበኝነት ተጋድሎ በድኅረ ጣሊያን ዘመን አርበኝነት ለእኩልነት እና ለፍትሕ ያደረጉት ትግል እስከ ሠራተኞች እንቅስቃሴ አመፅ በእነ ፈጠነና በልጅ ልጃችው ሙሉነሽ በመሳሰሉ ሲቀጣጠል ያሣየናል። የነፃነት፣ የፍትሕ እና የእኩልነት ትግል እንደወራጅ ውሃ ሁሉም ትውልድ አሰተዋጽዖ እያደረገ ከዘመን ዘመን የሚሻገር “ያንዲት ምድር ልጆች” መነሻ እና መድረሻ ይመስላል።

“ያንዲት ምድር ልጆች” የአንድ ዓለም ልጆች አለመሆናችውን በመደቦች መካከል ባለው የጭቆና ግንኙነትና በተለይ በጭቁኖች ላይ በሚደርሰው እንግልት፣ ስቃይና ሞት ይተርካል። ይህ የጉስቁልና ሕይወት የዛሬም የአዲስ አበባ ጭቁኖች ታሪክ ነው። በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ከተሞች ፋብሪካዎች፣ ጎዳናዎች፣ መጠጥ ቤቶች የምንዱባን አጭር የሕይወት ታሪክ ማካሔጃ መድረኮች አይደሉምን። ምንም እንኳን የመደብ ጥያቄ ቋንቋ በየቀኑ ባንሰማውም ጥያቄው የለም የምንልበት ዘመን ላይ አልደረስንም።

መጽሐፉ ይህን የጉስቁልና ሕይወት ከአደባባይ እስከ ማጀት፤ ከሥራ ቦታ እስከ እስር ቤት፤ ከመኖሪያ ሰፈር እስከ አዲስ አበባ ጎዳናዎች እየወሰደ ይተርክልናል። በሚያስደነግጥ ሁኔታ ገፀ ባሕሪያቱ ከሕይወት ትንቅንቅ ድንገተኛ ሞት ሲወስዳቸው ያሳየናል። ድንገተኛ ሞት በየገፀ ባሕሪያቱ ላይ እየተከሰተ ሲወስዳቸው ከመጽሐፉ አንድ የተለየ አሸናፊ ጀግና ብዙም አናይም። አንዳንድ ገፀ ባሕርያት ከሥራም ሲባረሩና ከታሪኩ ሲክስሙ ስንመለከት መጽሐፉ የብዙኀን ታሪክ እንጂ የግለሰብ ግለ ታሪክ አይደለም ያስብላሉ።

“ያንዲት ምድር ልጆች” ከልብ ወለድ ይልቅ የብዙኀን የሕይወት ተረክ ይመስላል። ይህ ሲባል በውስጡ በምናየው ዝብርቅርቅ የሕይወት ጉዞ ነው። ታታሪ ሠራተኛ ድንገት ሲባረር፤ ሰው በሰቃይ ተወልዶ በጉስልቁልና ኖሮ ድንገት ሞት ሲወስደው እናነባለን። ታጎር “ፈጣሪ የአጭር ሕይወት ታሪክ ደረሲ ነው” እንዳለ፤ በድንገት የሚሞቱት ምንዱባን በመመልከት ፈጣሪ ብቻ ሳይሆን አማረም ብዙ አሳዛኝ አጭር የሕይወት ታሪኮች በመጽሐፋቸው እንደደረሱ መመልከት እንችላለን። ምነው ይቺ ሴት በኖረች ብለን እንቆጫለን። አብዮት ቶሎ እንዲፈነዳ ሕይወት እንድትለወጥ በየምዕራፉ እንመኛለን።

“ያንዲት ምድር ልጆች” የጉስቁሎችን ሕይወት የተሸናፊዎች፤ የተጎጂዎችና የረዳት የለሾች ብቻ ታሪክ አያደርገውም። ተስፋ ቢስነት የሚተርክ መጽሐፍ ባይሆንም ተስፋን ግን በፌሽታ አይገልፃትም። አሸናፊነት ቢኖርም ዘላለማዊ ወይም ቅጽበታዊም ድል አያደርገውም። ተስፋና አሸናፊነት በማኅብራዊ ግንኙነት ውስጥ እንደ ዥዋዥዌ ከተሸናፊነት ጋር ይታያሉ።

ከጭቁኖች የማኅብረስብ ታሪክ ብዙ የሚያስንቅ እንዳለ ያሳየናል። ምናልባትም ሰብኣዊነት መኖሪያው በድሆች መንደር ነው ሊያስብሉ የሚያስችሉ ተረኮችን እናነባለን። ስብኣዊ መረዳዳት በየጋራዡ፣ በየፋብሪካው፣ በየኪራይ ቤቱ፣ ይተርክልናል። ጭቁኖች ታሪክ አልባዎች እንዳልሆኑ በየራሳቸው መንገድ በሚታዩ ሰብኣዊ የመረዳዳት የመተሳሰብ የአብሮነት ተሞክሮዎች ያሳየናል። የገበያ አመክንዮን የሚሻገሩ ብዙ ስጦታዎች እና መረዳዳቶች ምናልባትም የመጽሐፉ ትውራዊ መዋቅር የመደብ ትንተናና ኢኮኖሚዝም በሚፈታተን መልኩ ሲካሔዱ እናነባለን። የብላታ ለባሻ ያደረጉት ስጦታ፤ እነ ባሻ ለደብሪቱ የዋሉት ውለታ በሠራተኞች መካከል ያለው መረዳዳት እቁብን እንኳን ከኢኮኖሚያዊ ትርጉሙ በላይ የማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ትብብር ዓውድ ሲሆን በየምዕራፉ እናነባለን። ሰው ኢኮኖሚያዊ እንስሳ ታሪኩም በቁሳካላዊነት ብቻ የሚተነተን ሳይሆን የሞራል ማንነቱም ጎልቶ የሚወጣ ታሪኩም ሰብኣዊ ጓዳዊ ትብብር የሚታይበት መሆኑን እንመለከታለን።

የበላዮቻቸው፤ ያከራዮች፤ የአዛዦች የገዢዎቻቸው ኢሰብኣዊነት ጭካኔ ተስፋ ቢስነት በምስኪኖች መንደር አይታይም። የጎስቋሎቹ መንደር የሞራል ልዕልና ጎልቶ ይታያል። ይህም የዛሬዋ የአዲስ አበባ ታሪክ ነው። ስብዕና ሞራል በስርቆት በብዝበዛ በፖለቲካ አሽቃባጭነት ከከበሩ ሰዎች አይገኝም። ይህን ለመለየት “ያንዲት ምድር ልጆች” እያነበብን በአዲስ አበባ መስሪያ ቤቶች፤ ቢሮዎች፤ እስር ቤቶችና ፋብሪካዎች እንሒድ። ለዚህ ነው “ያንዲት ምድር ልጆች” የዛሬ ታሪክ ናት የምለው። ነገሮች የተለወጡ ይመስላሉ ግን ብዙ ነገሮች ዛሬም የትናንት ናቸው።

አማረ በ“ያንዲት ምድር ልጆች” በአብዮት ዋዜማ የነበረው የከተማ ኑሮ የጉስቁልና ሕይወት ከአብዮታዊ ማንነት ግንባታ ጋር አያይዞ ይተርካል። ይህ የታችኛው መደብ አባላት የጋራዥ ሠራተኛ፤ የፋብሪካ ወዛደር ቡና አበጣሪ ሴቶች፤ የሴተኛ አዳሪ የጠላ ጠማቂዎች እና የልጆቻችው፤ የሕፃናት ሠራተኞች በአጠቃላይ የታችኛው መደብ አባላት ከሥራ ባሕርያቸው ወይም ከቀጣሪዎች ኪራይ ስብሳቢዎች ጋር ባላቸው መስትጋብር ማንነታቸው በተለይም የፖለቲካ ማንነታችው እንዴት እንደሚገነባ ይተርካል። በዚህ የማንነት ግንባታ የሥራ ቦታ ወሳኝ ሚና በግለጽ ያሳየናል። በተለይም የአብዮተኛ እምቢተኛ ማንነት ግንባታ ከቤተሰብ ጀምሮ በማኅበረሰብ ውስጥ በሚካሔዱ መስተጋብሮች እንደሚመሰረት እያነበብን ጭቆና አምቢተኝነትን እንዴት እንደሚጠነሰስ ለመመልከት እንችላለን።

መጽሐፉ የወዛደሮች፣ የሴተኛ አዳሪዎች፣ የቡና ለቃሚዎች፣ የሕፃናቶች የአርበኞች የእምቢተኞች ታሪክ ነው። ‘ያ የትውልድ’ የማንነት ግንባታ ከማርክሲስት ሥነ ጽሑፎች ብቻ ሳይሆን ከሕይወት ትግል ንቃተ ሕሊናቸው ከበለፀጉ ምስኪኖች ጋር የተሳሰረ እንደሆነ ደራሲው ያሳዩናል። የተማሪዎች እና የወታደሮች አብዮት የሚባለውን አብዮት የ‘ያ ትውልድ’ን አብዮት ለሰፊው ማኅብረሰብ በማድረግ ትርክቱን ዲሞክራሲያዊ ያደርገዋል። እንቢተኝነትን ሰዋዊ ያደርገዋል።

“ያንዲት ምድር ልጆች” አብዮት የፀረ ቅኝ ግዛት እንቅስቃሴ ውልድ መሆኑን ያሳየናል። አብዮት በድኅረ ጣሊያን አሳቢ ከነበሩ የእምቢተኝነት እንቅስቃሴዎች ጋር አዋሕዶ ያቀርበዋል፤ የአብዮቱ ቅድመ ታሪክ ተረክ ይመስላል። ይህን ታሪክ እንደ ረጅም የማኅበራዊ ለውጥ ታሪክ አድርጎ በመተንተኑ አብዮቱን ራሱ የሰፊው ታሪካዊ የለውጥ ሒደት አድርገን እንድንመለከት ይጋብዘናል። ይህን በማድርጉ የዚህ ዘመንም የእምቢተኝነት ታሪክ ከዚሁ ከረጅሙ የእምቢተኝነት ታሪክ ውስጥ መመልከታችን አይቀሬ ይሆናል። ታሪኩ የዛሬ ነው የምለውም በዚህ የተነሳ ነው።

መጽሐፉ በኢትዮጵያ አብዮት ታሪክ ውስጥ ባለው ክርክር የራሱን አሻራ ሊጥል ይችላል። የአብዮቱ ተቺዎች ሒደቱን የባሕል ነቀላና በመጤ የማርክሲዝም ትንተና የተካሔደ ሲሉት በተቃራኒው ዓለማቀፋዊ ዓውዱ የፈጠረውን ሰዋዊ ተምኔትና ተስፋ ፍለጋ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ያለመ በማለት አብዮቱን ያሞካሻሉ። “ያንዲት ምድር ልጆች” አብዮቱን ከአርብኝነት እና ከሕይወት የዕለት ተለት ጥበብ ከበለፀጉ ሊቃውንት የፋብሪካ ሠራተኞች እምቢተኝነት ጋር ማስተሳሰሩ በክርክሩ ሦስትኛ ትርክት ሊሰጠን ይችለል።

ድርሰቱ በብዙ መልኩ ተራማጅ ከመሆኑም ባሻገር በተለይ የሴቶችን ታሪክ በመተረክ በኩል ተዋጥቶለታል። ነገር ግን ሙሉነሽ ወንዳወንድ ተደርጋ መሳሏ ለፍቅር ግድ ያልነበራት የተለየች ተደርጋ ከመጽሐፉ ጉዱ ካሶች አንዷ ተደርጋ ተስላለች። ተራማጅነት እብድነት ነው ወይ? እንድንል ይጋብዘናል።

“ያንዲት ምድር ልጆች” ምንም እንኩዋ የሰፊው የሠራተኛና የከተማ ጭቁኖች ታሪክ ቢሆንም እንደውም የተማረው ክፍል አድርባይነት በብላታም ሆነ በባሻ ትችት በከበደ ሕይወት ያሳየን ቢሆንም የተማረ ይግደለኝ ዓይነት ማሰሪያዎች መደመደሚያዎች በየቦታው በሚያበሳጭ መልኩ ሲገቡ እናየለን። ለምሳሌ የሙሉነሽን ተራማጅነት ከአራተኛ ክፍል ደርጃዋ የፈጠነን ንቃት ከተማሩ ሰዎች ጋር ከመዋሉ ጋር ለማዛመድ ይሞክራል። ግን ፈጠን ሙሉ ሰዓቱን ከቢጤዎች ጋር ብቻ ሲያሳልፍ ነው በመጽሐፉ የምናነበው። አማረ የሰጠውን መልሶ መውሰድ ይሞክራል። ተማሪነቱ በዚህ አድሎ ይታያል። መጽሐፉ ጥቅጥቅ ያለ አንዳንዴ ንድፈ ሐሳብ ሰባኪ ቢሆንም ታሪኩ ስለሚመስጥ ለማንበብ አያዳግትም።

ዮናስ አሽኔ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ ሳይነስ ኮሌጅ ቅድመ ምረቃ ተባባሪ ዲን ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው yonniashine2010@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 42 ነሐሴ 18 2011

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com