የአዲሱ የትምህርትና ሥልጣና ፍኖተ ካርታ ጉዳይ

Views: 557

ትምህርት ሚኒስቴር ረቡዕ፣ ነሐሴ 15 ከዚህ ቀደም ለበርካታ ዓመታት ሲተገበር የነበረውን 8-2-2 የትምህርት መዋቅርን በማስተካከል 6-2-4 በሚል እንዲቀየር መወሰኑን በይፋ ማስታወቁን ተከትሎ የሰሞኑ መነጋገሪያ ጉዳይ ሆኗል። በዚህ ትምህርት መዋቅር መሰረት እስከ 8ኛ ክፍል የነበረው የመጀመሪያ ሳይክል በ6ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና እንዲጠናቀቅ ውሳኔ ላይ ተደረሰ ሲሆን ከ1993 ጀምሮ በሥራ ላይ የነበረውን የ10ኛ ክፍል የኹለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናንም አስቀርቶ በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና እንዲደመደም አውጇል።

ከዚሁ በተጓዳኝም የከፍተኛ ትምህርት እና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርም ከቀጣዩ ዓመት 2012 ጀምሮ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎች ሦስት ዓመት የነበረው የቆይታ ጊዜያቸው ወደ አራት ዓመታት ከፍ እንዲል መደረጉንም አስታውቋል።

በቀጣዩ ዓመት ተግባራዊ እንዲሆን የተደረገው አዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ታዲያ በበርካቶች ዘንድ የተለያዩ አስተያየቶች እና ምክረ ሐሳቦች ሲሰነዘሩበት ሰንብቷል። አንዳንዶቹ እንደ ከዚህ ቀደም ሁሉ ግብታዊ ውሳኔዎችና በደምብ ዳሰሳ ጥናት ሳይካሔድበት እንዲሁ በለብ ለብ ተግባራዊ እንዲሆን የታሰበ ከመሆኑም በላይ ሩቅ የማያስኬድ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። አያይዘውም በአገራዊ ትምህርት ጥራት ስትታማ ለኖረችው ኢትዮጵያም ዘላቂ መፍትሔ የማያመጣ ነው ሲሉም ተችተዋል።

በሌላ አመክንዮ ብቅ ያሉት ቡድኖች ደግሞ የለም ከሦስትና አራት ዓመታት በፊት ጥናት ይደረግበት የነበረ ጉዳይ እንደሆነና መደረግ ከነበረበት ጊዜ ዘገየ እንጂ እንዲያውም በቂ የዝግጅትና የዳሰሳ ጥናትን አልፎ ለሕዝብ የደረሰ ነው ሲሉም ይሞግታሉ። ከዚህም ጋር አያይዘው አዲሱ ፍኖተ ካርታ ሲተገበር ከዚህ ቀደም ይታዩ የነበሩትን ተግዳሮቶችና ጉድለቶች ማስወገድና መሙላት እንደሚኖርበትም ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል። ከዚህም ውስጥ በየደረጃው ያሉትን መምህራን ብቃት እንዲሻሻል፣ የሚሰጠው ትምህርት በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ተመሳሳይነት እንዲኖረው እና የመሳሰሉት ከቀረቡት ምክረ ሐሳቦች ቀዳሚዎች ነበሩ።
የአዲሱ የትምህርትና ሥልጣና ፍኖተ ካርታ የታለመለትን ግብ ይመታ እንደሆነ ይዋል ይደር እንጂ ጊዜ ምላሽ መስጠቱ አይቀርም።

ቅጽ 1 ቁጥር 42 ነሐሴ 18 2011

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com