በሰው ዘር ጥናት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል የተባለ ቅሪተ አካል በአፋር ክልል ተገኘ

Views: 410

ባሳለፍነው ሳምንት ረቡዕ ነሐሴ 22 ቀን 2011 ይፋ የተደረገው 3.8 ሚሊዮን ዓመት ያስቆጠረው የወንድ የራስ ቅል እስከ አሁን ሉሲን ጨምሮ በአውስትራሎፒቴክስ ዝርያ ላይ ለሚደረጉ ጥናቶች ሙሉ የፊት ገፅታ ምስልን በመስጠት ምርምሩን እንደሚያግዝ ታወቀ።

በአፋር ክልል ሚሌ ወረዳ ሚሮ ዶራ በተባለ አካባቢ የተገኘው የራስቅሉ በ2008 የተገኘ ሲሆን ለሦስት ዓመታት ያህል ጥናት እና ምርምር ከተደረገበት በኋላ ይፋ በተደረገበት እለት ኔቸር (Nature) በተሰኝው ዓለም አቀፍ የሳይንስ መጽሔት ይፋ ተደርጓል።

ከአምስት ሀገራት የተወጣጣው የወራንሶ ሚሌ የቅድመ ታሪክ የጥናት ቡድን ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአሜሪካ፣ ፈረንሳይ ስፔን እና ስዊዲን ሃገር የመጡ ባለሞያዎችን በማሳተፍ ምርምሩን በቋሚነት ላለፉት 15 ዓመታት ሲያካሂድ ቆይቷል።

ግኝቱ በአውስትራሎፒቴክስ አፋሪንሰስ ሉሲ (ድንቅነሽ) ዝርያ ውስጥ የሚመደብ ሲሆን በተመራማሪዎቹ አውስትራሎፒቴክስ አናመንሲስ (MDR) የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። ሙሉ የራስቅል እና መንጋጋው መገኘቱ እስከ አሁን በዚህ ዝርያ ውስጥ ሊታወቁ ያልቻሉ የፊትና የጭንቅላት ቅርጾችን በስሪ ዲ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ለመጀመሪያ ጊዜ ፍንጭ የሰጠ መሆኑን የቡድኑ አባላት በብሔራዊ ሙዝየም በሰጡት መግለጫ ጠቅሰዋል።

‹‹የሉሲ ዝርያ እስከ አሁን ይታወቅ የነበረው ከ3.9 እስከ 4.2 ሚሊዮን ዓመት ድረስ ይኖር እንደነበር ሲሆን አዲሱ ግኝት ከ 3.6 እስከ 3.8 ሚሊዮን ዓመት ድረስ እንደነበር ያሳያል›› ያሉት ባለሞያዎቹ ‹‹በዚህ መሰረትም አዲሱ አውስትራሎ ፒቴክስ አናመንሲስ ከሉሲ በፊት የነበረ ዝርያ ነው›› ሲሉ ገልጸዋል።

በዚህ ግኝት መሰረትም ሁለቱ ዝርያዎች ቢያንስ ለ100 ሺ ዓመታት በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ መኖራቸው የታወቀ ሲሆን በዘርፉ የነበረውን የዕውቀት ክፍተት እንደሚሞላም የፕሮጀክቱ መሪ ዮሐንስ ኃይለሥላሴ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥነ ምድር ጥናት ተባባሪ ፕሮፌሰር ሙሉጌታ አለነ የቅሪተ አካሉን ዕድሜ ለማረጋገጥ በተገኘበት አካባቢ ያሉ የአለትና ሙናዎችን በመሰብሰብ ዘመኑ ባፈራው ቴክኖሎጂ በመጠቀም ትክክለኛ እድሜው 3.8 ሚሊዮን ዓመት መሆኑን ማረጋገጥ መቻሉን ጠቁመዋል።

በአፋር ክልል እና በሌሎች የስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች ባሉት መካነ ቅርሶች የሚገኙ እስከ 6ሚሊዮን ዐመት ዕድሜ ያስቆጠሩ የቅድመ ሰው ዝርያ ቅሪተ አካላት ኢትዮጵያ የሰው ዘር ምንጭ ስለመሆኗ በተደጋጋሚ ማረጋገጣቸውን የገለጹት ዮሐንስ፤ አዲሱ ግኝት ስለቅድመ ሰው ዝርያ አመጣጥ ጥናት ከሚሰጠው አዲስ መረጃ ባሻገር ኢትዮጵያ በርግጥም የሰው ዘር መገኛ ምንጭ ስለመሆኗ ተጨማሪ ማረጋገጫ መሆኑን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በመላው ዓለም ስሟ እንዲጠራ ከሚያደርጉ በርካታ የሀገሪቱ የቅርስ ዕሴቶች አንዱ እንደሚሆን ተናግረው፤ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ መሰንበቱ ለቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ ግብዓት እንደሚሆን እና ለሀገር መልካም ገፅታ ግንባታም ቀላል የማይባል ሚና እንደሚኖረው ዮሐንስ ተናግረዋል። መንግሥት የቱሪዝም መዋቅሩን በማስተካከል ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ መሥራት እንዳለበትም አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
እስከ አሁን ከሚታወቁ ከ20 የማያንሱ የቅድመ ሰው ዝርያዎች መካከል አስራ ሦስቱ በኢትዮጵያ የተገኙ ናቸው።

ቅጽ 1 ቁጥር 43 ነሐሴ 25 2011

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com