በማዕድን ሀብት የበለፀገችው ዋግ ኽምራ ድህነት ውስጥ ገብታለች ተባለ

Views: 409

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳድር በዓመት እስከ 10 ሺሕ ቶን ምርት የሚገኝበት፣ 18 ዓይነት የዓሳ ዝርያ፣ የሲሚንቶ ጥሬ እቃ፣ የወርቅና ብረት ማዕድን፣ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ተመራጭ የሆነ የማር ምርት ቢኖረኝም ምርቱን የሚያንቀሳቅሱ ተቋማት ባለመኖራቸው ሊሠራበት አልቻለም ሲል አስታወቀ።

ከላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በ600 ዓመታት ቀድሞ እንደተገነባ የሚነገርለት ውቅር መስቀለ ክርስቶስ በብሔረሰብ አስተዳደሩ እንደሚገኝ ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳድር በርይሁን ኪዳነ ማርያም፣ እነዚህን ያልተነኩ ሀብቶች ተጠቅሞ ለማምረት ወደ አስተዳደሩ የሚመጣ ባለሀብትና ተቋም እምብዛም ባለመታየቱ ብሔረሰብ አስተዳደሩ ያለውን ሀብት ታቅፎ እንዲቀመጥ ምክንያት ሆኖታል ነው ያሉት።

በርይሁን እንዳስታወቁት፣ ከላይ ከተጠቀሱት ምርቶች በተጨማሪ ሙጫ፣ እጣን፣ ግራናይት፣ ኦፓል፣ ሴራሚክና የእንስሣት ተዋጽኦ በአካባቢው በስፋት ሊመረቱ የሚችሉ ሀብቶች ቢሆኑም፣ በአስተዳድሩ ያለው ሕዝብ በድኅነት ውስጥ ያለ ነው። ለግንባታ መሰረተ ልማት የሚያገለግሉ የተትረፈረፈ ማዕድናት ቢኖርም፣ በርካታ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የዳስ ናቸው። በቂ የሕክምና አገልግሎት ተቋማት ባለመኖራቸው ከ30 ከመቶ በላይ የሚሆነው የአስተዳደሩ ነዋሪ የትራኮማ በሽተኛ ነው።

አስተዳድሩ ነሐሴ 26/2011 የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለባለሀብቶች አስጎብኝቷል፡፡ በብሔረሰብ አስተዳድሩ እስካሁን ያልተነኩ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች አሉ ያሉት በሪሁን፣ ተከዜን ተገን ባደረገው አካባቢ በዓመት እስከ 10 ሺህ ቶን ምርት የሚገኝበት 18 አይነት የአሳ ዝርያ መኖሩን፣ በአካባቢው ደረጃውን የጠበቀ ሎጂ መገንባት እንደሚቻልም አስገንዝበዋል፡፡

ለኢንቨስትመንት አማራጭ ችግሮች ናቸው የሚባሉት የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች እየተፈቱ ነው ያሉት በሪሁን፣ ከሁሉም በላይ ግን ወደ አካባቢው መጥተው መዋዕለ ንዋያቸውን ለሚያፈሱ ባለሃብቶች ንብረታቸውን መንግስት ሳይሆን ሕዝብ ይጠብቅላቸዋል፤ አስተዳደሩ ውስጥ ያለው ነዋሪ ኢንቨስትመንቶችን አጥቅቶ አያውቅም ባለሃብት አጣ እንጂ ብለዋል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገረቻቸው የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ አምሳሉ እንየው፣ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳድር ወርቅን ጨምሮ በርካታ ማእድናት መኖራቸው ቢረጋገጥም፣ እስካሁን ስላልተሰራበት የአካባቢው ህዝብ በድህነት ሲቆራመድ ኖሯል ሲሉ ገልጸዋል። አሁን ግን የክልሉ መንግስት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት መሆኑን አውስተው ርእሰ መስተዳድሩ ከባለሃብቶች ጋር መምከራቸውንም አስታውቀዋል።

ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ ነሐሴ 26/2011 የክልሉን ተወላጅ ባለሃብቶች በአቫንቲ ብሉ ናይል ሆቴል በክልሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ዙሪያ ባወያዩበት ወቅት፣ ህግን መሠረት አድርጎ ለመጣ ማንኛውም ጥያቄ የክልሉ መንግስት አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሰጥ መናገራቸው ይታወሳል። በክልሉ ለባለሀብቶች ፈጣን ምላሽ አለመስጠት እና በሥራ ኃላፊዎች እና በባለሀብቶች መካከል ተከታታይነት ያለው ውይይት አለመኖር ለክልሉ ምጣኔ ሀብታዊ ችግሮች መነሻዎች እንደሆኑ ተናግረው ነበር፡፡ ባለሃብቶቹም የኢንቨስትመንት ቦታ የወሰዱ ባለሀብቶች አፈፃፀም በየስድስት ወራት ቢገመገም፣ የዳያስፖራውን ማኅበረሰብ ቀርቦ ማወያየት ቢቻል፣ ተመሳሳይ ውይይቶች በአዲስ አበባ ከተማ ቢካሄዱ፣ በምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ ዙሪያ የተሻለ አስተሳሰብ ያላቸውን ሰዎች መጠቀም ቢቻል፣ ልማት አማካሪ ካውንስልም ቢቋቋም የሚሉ ምክረ ሃሳቦችን አቅርበዋል፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 44 ጳጉሜ 2 2011

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com