“ሥጋ የሚታለምባት” ሀብታም የቀንድ ከብት አገር

Views: 753

ሸማቾች የቀንድ ከብት፣ የበግና የፍየል ዋጋ ጣሪያ በመንካቱ መግዛት አልቻልንም ሲሉ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። አዲስ ማለዳ፣ የአዲስ ዓመት ዋዜማን ተከትሎ “የሥጋ ዋጋ እንደምን ሰነበት?” ስትል ሸማቾችንና ነጋዴዎችን አናግራ ነበር። ሁሉም ለማለት በሚቻል መልኩ፣ በአገሪቱ የሚታየው የሥጋ ዋጋ መናር በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩትም አግባብ ነው ብለው አያምኑም። የቀንድ ከብት አገር እየኖርን ሥጋን የምናልም ሕዝቦች ሆነናል ሲሉም በርካቶች ቅሬታቸውን አቅርበዋል። አንዳንዶች ባለፉት ሦስት ዓመታት በአገሪቱ የነበረውና አሁንም ያለው አለመረጋጋት ለዋጋው መናር ምክንያት ነው ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ የመንግሥትን ትኩረት አለመስጠት በምክንያትነት ያቀርባሉ።

የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም በ2018 (እ.ኤ.አ.) ባወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብት ከአፍሪካ ቀዳሚውን ስፍራ ከያዙት አገሮች አንዷ ብትሆንም፣ ለሕዝቡ ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ማቅረብ አለመቻሏ ሲያስተቻት ይደመጣል። ከዘርፉ የምታገኘው ጥቅም በተለይ ወደ ውጪ በመላክ የምታገኘው የውጭ ምንዛሬ፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው ከእቅዷም ሆነ ካላት አቅም ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ነው። የቁም እንስሳት ኮንትሮባንድ ንግድ፣ እንስሳቱ ወደ ውጪ ከመላካቸው በፊት የሕክምናና የመሳሳሉት ክትትል የሚደረግባቸው ኳራንቲኖች አለመኖር እና የመሳሰሉት ለአፈጻጸሙ እና ገቢው ዝቅተኛነት በምክንያትነት ይጠቀሳሉ። ከፍተኛ መጠን ያለው የቁም ከብት ተልኮ እየተገኘ ያለው አነስተኛ የውጭ ምንዛሬ ገቢም ሌላው ተግዳሮት ተደርጎ ይወሰዳል። አገሪቱ ካላት አቅም አንጻር ወይ ሕዝቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት አልቻለ፣ ወይ የውጭ ምንዛሬውን ችግር ለመቅረፍ አላገዘ ሲሉ ብዙዎቹ ይተቹታል።

አዲስ ማለዳም የሸማቹን ቅሬታ እውነትነት ለማረጋገጥ ባካሔደችው የዘፈቀ የገበያ ትዝብት፣ ተመሳሳይ የቤት ኪራይ የሚከፍሉ ሥጋ ቤቶች በከፍተኛ የዋጋ ልዩነት ሥጋ ሲቸበችቡ ለማየት ችላለች።

በደረሰን ጥቆማ መሰረት ሰሚት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ፣ በተለምዶ ፊጋ በሚባል ሰፈር በርካታ ሰዎች የተሰለፉበት ሥጋ ቤት አስተዋልን። ከሥጋ ቤቱ በየአራትና አምስት ሜትር ርቀት አራት ሥጋ ቤቶች ቢኖሩም የሚገበያይ ሰው የላቸውም፤ ሁኔታው ግራ ስላጋባን ወረፋ ከያዙት ሰዎች መካከል በ50ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙትን አሰገደች ተስፋሁንን ጠየቅናቸው፣ እሳቸውም “የተሰለፍነው ሥጋ በተሻለ ዋጋ ስላለ ነው” አሉን። አክለውም “እዚህ አንድ ኪሎ ሥጋ 180 ብር ነው፤ በምትመለከታቸው ሥጋ ቤቶች ደግሞ 300 ብር ገደማ ነው” ሲሉ አከሉልን። ሁሉም የሚሸጡት የከብት ሥጋ ቢሆንም፣ በአንድ ኪሎ ሥጋ ላይ የ120 ብር ልዩነት አላቸው። የሰልፉ ምክንያት እሱ ነው ሲሉ ገለጹልን።

ብዙ ደንበኛ በማስተናገድ ላይ የሚገኘውን ደንድር ዘበርጋን በጉዳዩ ዙሪያ አነጋገርነው፣ በሥራ ውጥረት ላይ ቢሆንም ጎረቤቱ ሥጋ ነጋዴዎች አስተያየቱን መስማት እንደሌለባቸው አስጠንቅቆን ምላሽ ሰጠን። እንደ ደንድር ገለጻ፣ በአካባቢው ያሉ ሥጋ ቤቶች ሥጋ የሚመጣላቸው በአንድ መኪና ከቄራ ነው። የቤት ኪራያቸውም ዋጋው ተመሳሳይ ነው። ነገር ግን እነርሱ በአንድ ጊዜ ብዙ ለማትረፍ ስለሚፈልጉ ዋጋውን ከፍ ያደርጉታል። እርሱ ደግሞ ብዙ ሸጦ ደንበኞቹን አስደስቶ ማትረፍ ይፈልጋል።

ሥጋ ሲሸጥላቸው የነበሩ እናት በደንድር ሐሳብ አልተስማሙም። እነዚህ ሰዎች ዋጋ ጨምረው የሚሸጡት ራስ ወዳድና ለወገናቸው የማያስቡ በመሆናቸው ነው። እነሱ በልተው ስለሚያድሩ ስለሌላው ችግር ማሰብ አይፈልጉም ሲሉ ነጋዴዎቹን አጥብቀው ይኮንናሉ።

በአንድ ኪሎ ሥጋ ላይ የ120 ብር ጭማሬ አድርጎ መሸጥ ጤናማ ነው? ስንል የጠየቅነው ሥጋ ነጋዴ መልሱ አጭር ነበር፣ “ነጻ ገበያ ነው፤ በፈለኩት ዋጋ መሸጥ እችላለሁ፤ የሥጋ ዋጋ ሲጨምር እኔም እጨምራለሁ፤ ሲቀንስ እቀንሳለሁ፤ የአገር ዋጋ ነው” ሲል መለሰልን። ሌላ ምላሽ ሊሰጠን ፈቃደኛ ባለመሆኑ መቀጠል አልቻልንም።

ሕገ ወጥ የቁም እንስሳት ንግድ
በአዲስ አበባ እየተባባሰ በመጣው ሕገ ወጥ የቁም እንስሳት ንግድ ሳቢያ መንግሥትና ሕጋዊ ነጋዴዎች እየተጎዱ፣ ሕገ ወጦች ደግሞ አለአግባብ እየበለጸጉ ነው ሲሉ፣ የኢትዮጵያ ቁም እንስሳት ንግድ ማኅበር፣ ነጋዴዎች፣ ሕግ አስከባሪዎች፣ ገቢ ሰብሳቢና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተመሳሳይ ድምጽ ያሰማሉ።

በዚህም የዘርፉ ሕጋዊ ነጋዴዎች ለኪሳራ እየተዳረጉና መንግሥትም ማግኘት የሚገባውን ከፍተኛ ገቢ እያጣ ሲሆን፣ በአንጻሩ ሕገ ወጥ ነጋዴዎችና ተባባሪዎቻቸው ደላሎች ባልተገባ መንገድ እየበለፀጉ መሆኑን ሰኔ 27/2011 በጋራ ባዘጋጁት መድረክ ላይ መናገራቸው ይታወሳል።

ሸማቾች ግን በሁለቱም አሳብ አይስማሙም፣ “በየመንደሩ ሕገ ወጥ እርድ እየፈጸሙ በውድ ዋጋ የሚሸጡልን ሕጋዊ ንግድ ፈቃድ ያላቸው ሥጋ ቤቶች ናቸው’ኮ” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁት መገናኛ ሾላ ገበያ አካባቢ በሚገኝ ሥጋ ቤት ሥጋ ሲገዙ ያገኘናቸው እናት፣ “በኅብረት ሥራ ማኅበራት 160 ብር የምንገዛውን ሥጋ ሕጋዊ ነጋዴ የሚባሉት 300 ብር እየሸጡልን ነው፤ በኅብረት ሥራ ማኅበራት 200 ብር የሚሸጠው የክትፎ ሥጋ ደግሞ 400 ብር በመሸጥ ላይ ናቸው። እነዚህ ነጋዴዎች ለመንግሥት ግብር ስለሚከፍሉ ብቻ መንግሥት ሕጋዊ አላቸው እንጂ ለኅብረተሰቡ ሕገ ወጦች ናቸው” ሲሉ ይከሷቸዋል።

ጉርድ ሾላ ከሸማቾች ሥጋ ሲገዙ ያገኘናቸው አይነኩሉ ይፍሩ በበኩላቸው፣ “መንግሥት ሕጋዊ የሚላቸው የሚገባውን ስለቆረሱለት ነው። ሸምቶ አዳሪውን ጦም ማሳደራቸውን ግምት ውስጥ መክተት አይፈልግም። እንደኔ ከሆነ ሕዝብን የሚበድል ነጋዴም ሆነ ማንኛውም አካል ሕጋዊ ፈቃድ ቢኖረውም ሕጋዊ ሊባል አይችልም” ብለዋል።

ማኅበራቱ፣ የዘርፉ ሕጋዊ ነጋዴዎች ለኪሳራ እየተዳረጉ ነው ሲሉ የሚያቀርቡትን አቤቱታ አይነኩሉ አይስማሙበትም፣ አብዛኛውን ሥጋ ነጋዴ ሥጋውን የሚያቀርበው እራሱ በህገ ወጥ መንገድ እየተገበያየ መሆኑን መንግሥትም ያውቀዋል። ከቄራ ኹለት በሬ ከወሰደ እራሱ አንዱን ያከናውናል ሲሉ ሕገ ወጥ ንግዱ በሕጋዊ ሥጋ ነጋዴዎች እንደሚብስ ያስረዳሉ።

የኢትዮጵያ የቁም እንስሳት ንግድ ማኅበር የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ኀላፊ አንተነህ ዓለሜ እንደተናገሩት፣ አገሪቱ ሰፊ የቁም እንስሳት ሀብት ቢኖራትም የአረባብ ስልቱ በዘመናዊ መንገድ ያልተደገፈና ኋላ ቀር በመሆኑ ተጠቃሚ መሆን አልቻለችም።የመዲናዋ የገበያ ማዕከላት አስፈላጊ መሰረተ ልማት ያልተሟላላቸው በመሆናቸው ለግብይትም ሆነ ለቁጥጥር ምቹ አለመሆናቸውን አስታውቀዋል።

የተመቸ የከብቶች ማጓጓዣና የእንስሳት ማድለቢያ ስፍራዎች እጥረትም ተጠቃሽ የዘርፉ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል። በእንስሳት ንግድ ላይ የተንሰራፋው ሕገ ወጥ አሠራርም ዘርፉ እንዳያድግ ሸብቦ የያዘ ሌላው ማነቆ መሆኑን አንተነህ አክለዋል።

ኢትዮጵያ 57 ሚሊዮን የቀንድ ከብት ያላት ሲሆን፣ ከዘርፉ የምታገኘው ገቢ ግን አነስተኛ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። የታየው የፀጥታ ችግር በሥጋ አቅርቦት ንግድ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳረፉን የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ደበሌ ለማ ይጠቅሳሉ። በተለይ ፍየሎች በብዛት ከቆላማው የኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልሎች እንደሚገኙ ተናግረው፣ በእነዚህ አካባቢዎች ለሦስት ዓመት በታየው አለመረጋጋት ሳቢያ የአቅርቦት እጥረት ማጋጠሙን ይጠቅሳሉ።

ከተጠቀሱት አካባቢዎች ባለፉት ሦስት ዓመታት በነበረው አለመረጋጋት ሳቢያ በቂ የፍየል አቅርቦት እንዳልነበር ተናግረው፣ በዚህ የተነሳም ነጋዴዎቹም ባለቄራዎቹም መቸገራቸውን ይገልጻሉ። እንደ ደበሌ ገለጻ፤ በጸጥታ ችግር ሳቢያ አርሶ አደሩም እንስሳቱን ወደ ገበያ ለማውጣት ይቸገራል።

“ኹለተኛው በቁም እንስሳት ብዛት እንደ አገር ቀዳሚነቱ ቢኖረንም፣ ግብይቱ ሕግን ተከትሎ ከመፈፀም አኳያ ውስንነቶች አሉ” ሲሉም ይገልጻሉ። ሕጋዊ በሆነ መልኩ ግብይቶችን ከማድረግ ይልቅ ሕገ ወጥ ግብይት የሚፈጸምባቸው ገበያዎች እየተስፋፉ እንደሚገኙም ይጠቁማሉ።

ኢትዮጵያ ባላት የእንስሳት ሀብት ከዓለም በዐሥረኛ ከአፍሪካ በአንደኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፤ ነገር ግን በዚህም ተጠቃሚ መሆን አልቻለችም። የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም በ2018 (እ.ኤ.አ.) ያወጣው ሪፖርት እንዳሚያሳየው፣ ኢትዮጵያ 56.7 ሚሊዮን ከብቶች አሏት። ካሉት ከብቶች መካከል 12.65 ሚሊዮኑ ደግሞ የሚታለቡ ላሞች መሆናቸው በምግብ ራስን ለመቻል ሌላው መልካም አጋጣሚ ነበር። ከከብቶቹ የሚገኘው ወተት፣ ሥጋ፣ ቅቤና ከዶሮ እንቁላል የመሳሰሉት ተዋጽዖዎችም የአንድን አገር ዜጎች የምግብ ጥያቄ ከመመለስ ባለፈ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ መሆን የሚችሉ ናቸው። ነገር ግን እንደ እርሻ ግብርናው ሁሉ የከብት ሀብቷም የዜጎችን የምግብ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ አይደለም። የኹለቱ ዘርፎች ድምርም የዜጎችን የምግብ ፍላጎት የሚያረካ ስላለመሆኑ የንግድ ሚኒስቴር ማስረጃዎችን ጠቅሶ መናገር ይቻላል።

ሸማቾች መንግሥት የተጠቀሱትን ችግሮች በማስወገድ ለተጠቃሚው ፍትሐዊ በሆነ ዋጋ የሚቀርብበትን መንገድ መፈለግ አለበት ሲሉ ይጠይቃሉ። “በአሁኑ ወቅት አገሪቱ በዘርፉ ያላትን ግዙፍ ሀብት ተጠቅማለች ማለት አያስደፍርም” የሚሉት ደበሌ በበኩላቸው፣ ከዘረፉ ተገቢ የሆነ ጥቅም ይገኝ ዘንድ አስፈላጊው እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ጠቁመው፤ በዚህ ላይ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት በጥምረት መሥራት አለባቸው ብለዋል። በተለይ በቆላማ የአገሪቱ አካባቢዎች ተወስኖ የቆየውን የቁም እንስሳት ገበያ ከማስፋት ባሻገር የባለሀብቱንና የአቅራቢውን የገበያ ትስስር ማጠናከር ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

ቅጽ 1 ቁጥር 45 መስከረም 3 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com