ትምህርት ወደ ቀደመ ክብሩ ይመለስ!

Views: 160

ዓለማችን አሁን ለደረሰችበት ደረጃ ትልቁን ሚና የተጫወተው ትምህርት ነው። በነገሥታቱ ዓይን የተወደዱና ሞገስ ያገኙ ሰዎች ባሕር ማዶ አቅንተው እንዲማሩ የትምህርት ዕድል ያገኙ እንደነበር መዛግብት ያስረዱናል። እነዚሁ ሰዎች ትምህርታቸውን አጠናቅቀው አገራቸውንና መንግሥትን ለማገልገል ቀናዒ መሆናቸውንም እንታዘባለን።

ባሕር ተሻግረው ትምህርት እንዲማሩ ዕድል ያገኙ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው የነበራቸው ስሜትና መቆርቆር ጥልቅ ነበር። ትምህርታቸውን ቀስመው ወደ አገር በመመለስ የሚጠበቅባቸውን ለማበርከት ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ ለማድረግ ያላቸው ቁርጠኝነት እንዲህ በቀላል የሚታይም አይደለም።

ከብዙዎቹ ጥቂቶቹን እንጥቀስ እንኳን ብንል ከአፄ ዮሐንስ ጀምሮ እስከ ጣልያን ወረራ ድረስ በአስተርጓሚነት፣ በመንግሥት ልዑክነት፣ በከንቲባነት፣ በሴኔተርነትና በአርበኝነት አገራቸውን ያገለገሉት ከንቲባ ገብሩ ደስታ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ኦሮምኛ ቋንቋ የተረጎመው ኦኔሲሞስ ነሲብ፣ በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት አስተዳዳሪነት፣ ጣና ሐይቅ ላይ ግድብ ለመሥራት ከአሜሪካ ኩባንያ ጋር በተደራዳሪነት እና በሌሎችም ተግባራት ያገለገሉት ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ መጥቀስ ይቻላል። በአንድ ወገን የእነዚህ በውጪ ተምረው የመጡ ሰዎች የአገር ተቆርቋሪነት በተጓዳኝ በጊዜው የነበሩ ነገሥታት ለትምህርትና ለተማረ ክብር ያላቸው መሆን በወቅቱ የተፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ረድቷል።

ከዚህ በኋላም በጊዜ ሒደት ማኅበረሰቡ የዘመናዊ ትምህርት ጥቅምን ሲረዳና ባዕድ እንዳልሆነ ሲያውቅ ልጆቹን ለማስተማር አልዘገየም። ይህ ነገር ምንም እንኳን በስፋት ይታይ የነበረው በከተማ ላይ ብቻ ቢሆንም መማር እንደሚያስከብር የሚያምነው የኅብረተሰብ ክፍል ግን ቀላል አልነበረም።

ውሃ በነጻና በብዛት የሚገኝ በመሆኑ ሲሸጡት ዋጋው ቢቀንስም በሚሰጠው ጥቅሙ ግን ዋጋው በእጅጉ ትልቅ እንደሆነ ሁሉ፤ ለትምህርት ግን ይህ ሳይሆንለት ቀረ። የተማረ ቁጥር እየጨመረ፣ የተመራቂ ቁጥር ከፍ እያለ፣ ሦስተኛ ዲግሪ የያዙ ሲበራከቱና መማሪያ ተቋማት እየተስፋፉ ሲሔዱ ለትምህርት ያለው ግምት በአንጻሩ እየቀነሰ መጣ።

ይህ ግን ተገቢ እንዳልሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች። ትምህርት ሰውን በእውቀትና ክህሎት ያንፃል፤ በሙያ ያጎለብታል። የሰው ልጅ ከእንስሳ የተሻለ የሚያደርገውን ምክንያታዊነት ከሚሰጡት መካከል ወሳኝ የሆነው ትምህርት እንደ ቀደመው ጊዜ በክብርና በአግባቡ ሊያዝ ይገባል።

ቋሚ ነገር እንጂ ጊዜያዊ የሆነውን ሁሉ ብልጭልጭና ከንቱ እያለ ይኮንን የነበረ ማኅበረሰብ ‘ከሦስት ዲግሪ አንድ ግሮሰሪ’ የሚል ፈሊጥ ማዘውተሩ፣ “ልጄ ምን ተማረ?”ን ጥሎ ተመረቀልኝ ላይ ማተኮሩ፣ መማር ሳይሆን መመረቅ መለካኪያ መሆኑና ትምህርትን ከሀብትና ንብረት ማፍሪያነት ጋር ማጣመዱ በማኅበረሰቡ የታየ ጥፋት ነው። መንግሥትም በበኩሉ ለዚህ መንስዔ የሆነው ‘የማስፋፋትና ማሰራጨት’ አባዜና ትምህርትን ሸቀጥ አድርገው ውጤትና ነጥብን በችርቻሮ የሚሸጡ የትምህርት ተቋማትን ቸል በማለቱ ዛሬ ላይ አድርሶናል።

ትምህርትን ወደ ቀደመ ክብሩ መመለስ መቻል አገርን ለጥበበኞች አሳልፎ እንደመስጠት ይቆጠራል። ትምህርት ገንዘብ ከማከማቸት ጋር አይወዳደርም፤ አይነጻጸርምም። መማር እውቀትን መሸመት፣ ክህሎትና እሴትን አዳብሮ መቀጠል ማለት ነው። መነገድ ደግሞ አትርፎ መሸጥ፣ ሸጦ ማትረፍ። ባሕር ማዶ በሀብት ቀዳሚ ደረጃ ላይ ከተመዘገቡ ሰዎች መካከል እውቀትን በብልሃት መጠቀም የቻሉት ይጠቀሳሉ። እነዚህም የፈጠራ ሥራን ለዓለም ያበረከቱ ናቸው።

ትምህርት ለዚህ ቁልፉ ነው። በገንዘብ የሚናቅ ሳይሆን በተቻለ መጠን ገንዘብን የሚፈጥር ሊሆን ይገባል። ሁሉም ነገር በገንዘብ ሊገዛ እንደሚችል የሚያምን ትውልድ ያለውን ነገር ሁሉ አውጥቶ ከመሸጥ አይመለስምና፣ ትምህርት ላይ ጥንቃቄና ትኩረት ማድረግ በእጅጉ አስፈላጊ ነው።

በቅርቡ ይፋ የተደረገውና ተግባራዊነቱ የሚጠበቀው አዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ መነሻው የቀደመው ስርዓተ ትምህርት ውድቀት ነው። ምንም እንኳን የቀደመውን ስርዓት ሙሉ ለሙሉ ያልተሳካለት ማለት እንደማይቻል የዘርፉ ምሁራን የሚናገሩ ቢሆንም ትምህርትን መንግሥት ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋሉ፣ ከተደራሽነት ባሻገር ጥራትን ማዕከል ያደረገ የትምህርት ስርዓት አለመዘርጋቱ፣ ለመምህራን የሚሰጥ ተከታታይ ሥልጠናም ሆነ ማበረታቻ ሙያውን በሚመጥን መልኩ አለመሆኑ፤ ካለም በሚፈለገውን ልክ ውጤታማ አለመሆኑ ለቀደመው የትምህርትና ሥልጣና ስርዓት ለውድቀቱ ተጠቃሽ ምክንያት ናቸው።

የተማሩ የተባሉ ሰዎች ሥራ ሳያገኙ መቅረታቸው የመማራቸውን ዓላማ እንዲጠራጠሩ ያደረገው ሥራ ጠባቂ እንጂ ፈጣሪ እንዲሆኑ የሚያስችል የትምህርት ስርዓት ባለመተግበሩ መሆኑ ግልጽ ነው። በከተሞቻችን ባሉ የግንባታ ሥራዎች ኢትዮጵያዊ በአገሩ ድንጋይና አሸዋ ሲሸከም ከባሕር ማዶ የመጡት አለቃ ሆነው እንዲያዙ የቆሙት የተሻለና የተለየ እውቀት ኖሯቸው ሳይሆን በኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓቱ በተግባር የተፈተነና ወደዛ የሚያመራ ባለመሆኑ ነው። ይህንንም አዲስ ማለዳ አብዝታ ትቃወማለች።

አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታም በባለሙያ እንጂ በፖለቲካ ነገረ ፈጆች እጅ ሳይገባ እንዲተገበር ይገባል። ችግር ፈቺ ሊሆን የሚገባው ፍኖተ ካርታው ችግር ፈጣሪ እንዳይሆን እንዲሁም ተጨማሪ የአገር ሥጋት እንዳይሆን ጥንቃቄ ያስፈልጋል። በተለያየ አቅጣጫ በተለያዩ ወገኖች በአዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ዙሪያ የተነሱትን ጥያቄዎች የሚመለከተው የመንግሥት አካል በአንክሮና ተመልክቶና አጥንቶ ተገቢ የሆነ ሙያዊ ብሎም ሁሉንም ወገን አሸናፊ የሚያደርግ ምላሽ መስጠት ይጠበቅበታል ስትል አዲስ ማለዳ አጽንዖት ትሰጣለች።

በመጨረሻም ትምህርት ለብቻው ግብ ባለመሆኑ ኢትዮጵያን ለማሳደግም ሆነ ለማበልጸግ የሚጠበቅበትን ድርሻ እንዲያበረክት በመጀመሪያ በሰፊው ኅብረተሰብ ውስጥ ሰርፆ ያለውን በጎ ያልሆነ አመለካከት መለወጥ ቀዳሚ ሥራ መሆን ይገባዋል፤ ትምህርት ወደ ቀደመ ክብሩ እንዲመለስ።

ቅጽ 1 ቁጥር 45 መስከረም 3 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com