ስለኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንዳንድ ነጥቦች

0
1774

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የኢትዮጵያ ችግሮች ሁሉ ምንጭ አይደለም የሚሉት ተክለሚካኤል አበበ፥ ነገር ግን ሊሻሻሉ ወይም ሊብራሩ ይገባሉ ያሏቸውን አንቀጾች ለአብነት በማንሳት መከራከሪያቸውን አቅርበዋል። ከምንም በላይ የኢትዮጵያ ችግር ሕገ መንግሥታዊነት አለመዳበር እንዲሁም በሕገ መንግሥቱ ለክልሎች በግልጽ የተሰጡትን ሥልጣኖች ሳይጋፋ የፌደራል መንግሥቱ የኢትዮጵያዊያን ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን ሳይሸራረፉ፤ በሁሉም ክልሎች በእኩልነት እንዲፈጸሙ ከተጋና ሕገ መንግሥቱ ያቆየናል ይላሉ። ሁል ጊዜ አሮጌውን ንደን፣ ደምስሰን፣ አፍርሰን፣ አዲስ መገንባት ብቻ ሳይሆን ባለው ላይ መገንባት፤ ያለውን እያሻሻሉ መጓዝም መልመድ አለብን ሲሉም ይመክራሉ።

አሁን ላለው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት ጥብቅና አልቆምም። ግን ደግሞ ለኢትዮጵያ ችግር ሁሉ ምንጩ ሕገ መንግሥቱ ነው፤ ሕገ መንግሥት ከተለወጠ፥ የኢትዮጵያ ችግር ይቀረፋል ከሚሉት ወገንም አይደለሁም። በሰነድ ብቻ የመጣና በሰነድ ብቻ የሚሄድ ችግር የለም። በተደጋጋሚ በምሳሌ እንደገለጽኩት፤ ቅዱሳን መጻሕፍትን ለእምነት ተከታዮቻቸው እንደ ሕገ መንግሥት አድርገን ብንወስዳቸው፤ እነዚህ ቅዱሳን መጻሕፍት ከመጠፋፋት፣ ከጦርነት፣ ከተከለከሉ ሀጢያቶች አላዳኑንንም። እንደውም በእምነት/በሃይማኖት ሥም የሚፈጸሙ ግፎች አሁንም ድረስ ሞልተዋል። ስለዚህ የኢፌዴሪ’ን ሕገ መንግሥት የኢትዮጵያ ችግሮች ሁሉ ምንጭ፤ የዚህ ሕገ መንግሥት መለወጥም የችግራችን ሁሉ መፍትሄ አድርገን መመልከት ስህተት ነው። የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥት ደግሞ ደጋግሞ ማንበብ፣ መፈተሽ፣ መመርመር፣ መወያየት ያስፈልጋል።

በእኔ ንባብና እምነት ከሕገ መንግሥቱ ውስጥ ቢሻሻሉ ወይም ቢብራሩ፤ ቢቀነሱ ወይም ቢጨመሩ የሚባሉ አንቀጾች ይኖራሉ። ለምሳሌ፤ የመሬት የግል ባለቤትነት ቢረጋገጥ ደስ ይለኛል። የግለሰቦችና የቡድን መብቶችም ጎን ለጎን የሚቆሙ እንጂ፤ አንዱ ሌላውን የሚጨፈልቅ እንዳልሆኑ የሚደነግግ አንቀጽ ቢኖር ደስ ይለኛል። አንቀጽ 39 መኖሩ ይረብሽ ይሆናል እንጂ፤ ተፈጻሚነቱ አጠራጣሪ ነው። ይፈጸም ከተባለ፥ ለክልሎችም አደገኛ ነው። ምክንያቱም አንቀጽ 39 ይፈጸም ከተባለ፥ አማራ የሚባል፣ ኦሮሚያ የሚባል፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሚባሉ ክልሎች ሁሉ ሊናዱ ይችላሉና። ስለዚህ አንቀጽ 39 አያስቃዠኝም። አንቀጽ 39 የእልህ አንቀጽ ነው የምለው። በሙሉ አይፈጸምም። ለዚህም ነው ሕወሓት’ን ጨምሮ ኦነግም ሌሎችም የብሔር ድርጅቶች፤ በቅርብ ጊዜ ታሪካቸው ስለመገንጠል መብት አያወሩም። ሕወሓት፤ በቅርብ ጊዜ እንደዚያ እየተደበደበ ሁሉ፤ ስለመገንጠል ትንፍሽ አላለም። ይሁንና ሌሎች በተቃራኒው በቅርብ ጊዜ የተወለዱ የብሔር ድርጅቶች ግን ደፍረው ስለመገንጠል ያወራሉ።

የኢትዮጵያ ችግር ሕገ መንግሥቱ ሳይሆን ሕገ መንግሥቱ አለመተግበሩ ወይም የሕገ መንግሥታዊነት ባህል አለመኖር ወይም አለመዳበር ነው። በርግጥ ይሄ ችግር በተወሰነ መልኩ ከሕገ መንግሥቱ ይዘት ቢመነጭም፤ በአብዛኛው ግን የሚመነጨው፤ የመንግሥት አካላት፣ ፖለቲከኞና ሕዝቡም በተወሰነ መልኩ የሕገ መንግሥታዊነት መንፈስ ስላልገባው ነው። በከፊል ከሕገ መንግሥቱ ነው ስል፤ ለምሳሌ ፍርድ ቤቶች ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን ስላልተሰጣቸው፤ ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን ከማስፈጸም አንጻር ሽባ ናቸው። ሰዎች ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ሲጣስ፤ ወደ ፍርድ ቤት አቅንተው መፍትሄ መፈለግ አይችሉም። ከዚህ አንጻር፤ ሕገ መንግሥቱ ጎዶሎ ነው። የፍርድ ቤቶች ሽባነት ምንጭ ግን፤ ሕገ መንግሥታዊ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያችም ስላሉት እሱን በሌላ ጽሁፍ እንመለስበታለን።

ሉዓላዊ ማነው፤ ኢትዮጵያ ወይስ ክልሎች
አንዳንድ የሕገ መንግሥቱ አንቀጾችም አሻሚ ወይም ግራ አጋቢ ናቸው። ለምሳሌ፤ አንቀጽ 2 የኢትዮጵያ የግዛት ወሰን የፌደራሉን አባሎች ወሰን የሚያጠቃልል ሆኖ በዓለም ዐቀፍ ስምምነቶች መሰረት የተወሰነው ነው ይላል። አንዳንድ ሰዎች ይሄንን አንቀጽ ይዘው፤ ክልሎች/ብሔሮች ሉዓላዊ ናቸው፤ በሕገ መንግሥቱ የክልሎች እንጂ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የለም ሲሉ ይደመጣሉ። አንቀጹ ግፋ ቢል ግልጽነት ወይም ትርጉም ያስፈልገዋል። ይሁን እንጂ፤ ለክልሎች ወይም ለብሔሮች ሉዓላዊነትን አይሰጥም። አንደኛ ነገር፤ የኢትዮጵያ ፌደራል አባላት ክልሎች ናቸው ወይስ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ግልጽ አይደለም። ኹለተኛ፤ በዓለም ዐቀፍ ስምምነቶች መሰረት የተወሰነው ሲል ኢትዮጵያ ከ1983 በፊት የተመሰረተችና ድንበሯም ከዚያ በፊት የጸና እንደመሆኑ መጠን፤ በዓለም ዐቀፍ ሕግ መድረክ ወይም ዐይን፤ ሉዓላዊ ተደርጋ የምትታወቀው ኢትዮጵያ እንጂ፤ ክልሎች አይደሉም። ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ሉዓላዊ ክልሎችን ፈጠረ የሚለው ክርክር አያስኬድም።

ሕገ መንግሥቱ ሉዓላዊነትን ለብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሰጥቷል፤ ዜጋው ቦታ የለውም ወይም ዜጎችን አያውቅም የሚለው አንዱ ክስ በተደጋጋሚ ይሰማል። ከአንቀጽ 2 እና 39 ሌላ፤ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 8’ን ነው እንደማስረጃ የሚጠቅሱት። አንቀጽ 8 የሚገኘው የሕገ መንግሥቱ መሰረታዊ መርሆዎች በሚገኙበት ምዕራፍ 2 ውስጥ ነው። በዚሁ ምዕራፍ ውስጥ ብዙ ሌሎች ሕገ መንግሥታዊ መሰረታዊ መርሆዎች ተጠቅሰዋል። ለምሳሌ፤ አንቀጽ 9 ማናቸውም ሕጎች፣ አሠራሮች፣ ልማዶች ከሕገ መንግሥቱ ጋር መቃረን እንደሌለበቸው፤ አንቀጽ 10 ደግሞ የዜጎችና ሕዝቦች ሰብኣዊ መብቶች መከበር እንዳለባቸው ይደነግጋል። ስለዚህ አንቀጽ 8’ን ከሌሎች አንቀጾች ለይተን መመልከት የለብንም። ወይንም ሕገ መንግሥቱ እንደ አንድ ወጥ ሰነድ ይተረጎማል እንጂ፤ የተወሰኑ አንቀጾችን መዘን ለእኛ እንዲመቸን ብቻ አድርገን ጠምዝዘን መተርጎም የለብንም። ሕገ መንግሥቱ እንደ አንድ ወጥ ሰነድ ሲተረጎም፤ ሉዓላዊነት፥ በቀጥታ እንደ ዜጋም ይሁን በተዘዋዋሪ እንደ አንድ ብሔር/ብሔረሰብ/ሕዝብ አባል፤ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ሥልጣን ነው።

ከብሔር እና ከዜጋ የቱ ይበልጣል?
የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች ሁሉ እኩል ናቸው፤ አንዱ ከሌላው አይበልጥም። በግድ ጠምዝዘን አንቀጽ 8 ከአንቀጽ 9 ወይም 10 ይበልጣል ካላልን በስተቀር፤ ሕገ መንግሥቱ የዜጎችን መብት ከብሔሮች ወይም ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት አስበልጦ አላስቀመጠም። ኹለቱም መብቶች ጎን ለጎን የተቀመጡ ናቸው። በዚህ ረገድ፤ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በመምረጥ መመረጥ መብት ዙሪያ ለቀረበ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በመጋቢት 1995 የሰጠው ውሳኔ ዐይን ገላጭ ነው። በዜጎችም ሆነ በብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች መካከል ልዩነትና አድለዎ ማድረግ እንደማይቻል፤ እንዲሁም የግለሰቦችና፤ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መሰረታዊ መብቶችና ነጻነቶች የተሳሰሩ፣ የማይነጣጠሉና እኩል እንደሆኑ፤ አንዱ ከሌላ የማይበልጥ፤ የማያንስ እንደሆነ እንዲሁም አንዱ ለሌላው ሲባል መብቱና ነጻነቱ እንደማይሸራረፍና ገደብ እንደማይጣልበት ነው። (“የሕገ መንግሥታዊ ውሳኔዎች” መጽሔትን፤ ቅጽ 1፤ ገጽ 25/26 ይመልከቱ።)

እነዚህ መብቶች ሳይጋጩ እንዴት አጣጥመን እንደምንተረጉማቸው ዘዴዎችና ብልኀቶች፤ የሕገ መንግሥት አተረጓጎም ስልቶች ስላልፈጠርንና ስላላዳበርን፤ ወይም ሕገ መንግሥቱ በነጻነት፣ በትርጉም፣ በምርምርና በማሻሻል እንዲዳብር እድል ስላልተሰጠው ነው፤ ሕገ መንግሥቱ የችግሮች ሁሉ ምንጭ የመሰለው እንጂ፤ ሕገ መንግሥቱ እንዳለ ሥራ ላይ ቢውል፤ ችግሮቻችንን ሊፈታ፤ ባይፈታ እንኳን፤ በሰላም እንድንፈታ እድልና መንገድ ይሰጠናል። እንዳለመታደል ሆኖ ግን ሕገ መንግሥቱን ታግለው ያመጡትና ሥራ ላይ እያዋሉት ያሉት ኀይሎችም፤ ለሕገ-መንግሥቱ ታማኞች አይደሉም። ወይንም በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሰነቀሯቸው መብቶች ምድራዊ ትርጉም አልገባቸውም። ስለዚህ በየዕለቱ ላለፉት 26 ዓመታት፤ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡት መብቶች ሲጣሱና ሲቀለበሱ እንመለከታለን።

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ውስጥ የዜጎችን መብት የሚጠብቁት አንቀጾች በቁጥር የብሔሮችን መብት ከሚጠብቁት አንቀጾች ይበልጣሉ። ከአንቀጽ 14 እስከ 38 የሚደነግጉት፤ ስለግለሰብ ወይም ዜጋ ወይም ኢትዮጵያዊያን መብት ነው። ሕገ መንግሥታዊነት ሰርጾብን ቢሆን ኖሮ አንቀጽ 38 ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በዘር፣ በቋንቋ፣ በብሔር፤ በብሔረሰብ … ልዩነት ሳይደረግበት፤ በአገሪቱ የፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ የመሳተፍ፣ የመምረጥ የመመረጥ መብት እንዳለው ይደነግጋል። እንደሕገ መንግሥቱ ቢሆን ኖሮ እኔን፣ ቋንቋዬም ይሁን ብሔሬ፤ ጨፌ ኦሮሚያ ገብቼ ከመፈንጨት አያግደኝም ነበር። ሀብት የማፍራት፣ የመኖር፣ በነጻነት የመንቀሳቀስ መብትማ ምንም ጥያቄ ሁሉ የለውም። ስለዚህ በየጊዜው በየሰበብ አስባቡ የምንሰማቸው የዜጎች መፈናቀልና መገደል ከፍተኛ የሰብኣዊና ሕገ መንግሥታዊ መብት ጥሰት ናቸው።

አንቀጽ 25 ይሄንኑ የእኩልነት መብት ይደነግጋል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ፣ ማንኛውም ሰው ከሕግ በታች እኩል ነው። በብሔሩ፣ በዘሩ፣ በቋንቋው፣ በሃይማኖቱ፣ በጾታው … መድልዎ አይደረግበትም። በኦሮሚያ ውስጥ ሽመለስ አብዲሳ፤ ከተክለሚካኤል አበበ የበለጠ መብት የለውም። ማንኛውም ኢትዮያያዊ፤ አንዳንዴ ደግሞ ማንኛውም ሰው፤ ኢትዮጵያዊ መሆን ሁሉ አይጠበቅበትም፤ በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉ መብቶች አሉት። አንቀጽ 39 ከአንቀጽ 25 አይበልጠም። ለምሳሌ፤ ኹለቱም የሚሻሻሉበትን አንቀጽ ብንመለከት ተመሳሳይ ናቸው። ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያውን፤ የሁሉም ክልሎች ምክር ቤቶች፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ በ2/3ኛ ድምጽ ማጽደቅ አለባቸው። የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 104 እና 105’ን ይመለከቷል።

ሕገ መንግሥታዊነት አልሰረጸም፤ ሕገ መንግሥታዊነት ይለምልም!
ኢትዮጵያ ውስጥ ችግሩ ሕገ መንግሥቱ ሳይሆን፤ ሕገ መንግሥታዊነት አለመዳበር ነው። የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ሕገ መንግሥቱን አልተረዱትም ወይም ሆን ብለው አጣመው ተርጉመውታል ወይም ኢሕአዴግ በፈለገው መንገድ ብቻ እየተተረጎመ ስለመጣና፤ ሕገ መንግሥቱ ማለት ኢሕአዴግ/ብልጽግና የሚለው ስለሆነ ሕገ መንግሥቱ በነጻነት እንዲዳብርና እንዲያድግ እድል ስላልተሰጠው እንጂ ሕገ መንግሥቱ ያለምንም ማሻሻያ የኢትዮጵያዊያንን መብት የሚጠብቅበት ኀይልና ሥልጣን አለው። ሕገ መንግሥታዊነት ምን ያህል እንዳልዳበረ ደግሞ ጥሩ ምሳሌ የራሱ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤው የምርጫን መራዘም የተመለከከተው የቅርብ ጊዜ ውሳኔ ነው።

የሕገ መንግሥታዊ አጣሪ ጉባኤው ውስጥ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንትን ጨምሮ ሌሎች 6 ታዋቂ ሕግ ባለሙያዎች ቢኖሩም፤ የወሰኑት ውሳኔ፤ ኢሕአዴግ ከቀናት፤ ሳምንታት ስብሰባ፤ ግምገማ በኋላ ከሚያወጣቸው መግለጫዎች ያልተለየ ውሳኔ ነው። እንኳንስ የኢሕአዴግ/ብልጽግና ባለሥልጣናት ጋር የተማሩ የተመራመሩ የሕግ ባለሙያዎችን፤ የተሰጣቸውን ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን፤ በቅጡና የሕዝብን መብት በሚያስጠብቅ መልኩ አልተረዱትም። ውሳኔያቸው ምንም ይሁን ምንም ቢያንስ የግራ ቀኙን ሐሳብ ማስፈር ሲገባው፤ የመንግሥትን ፍላጎት ብቻ ባማከለ መልኩ፤ እንዲያውም መንግሥት ከጠየቀው በላይ መብት በሚሰጥ መልኩ ምርጫው ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘምና፤ እስከዚያውም ገዢው ፓርቲ ሥልጣን ላይ እንዲቆይ ወስነዋል።

ስለዚህ የችግራችን ሁሉ ምንጭ ሕገ መንግሥቱ ነው፤ ሕገ መንግሥቱ ይሰረዝ፣ ይሻር፣ ይቀደድ የሚሉ ኀይሎች አንድም ሕገ መንግሥቱን በቅጡ አልተረዱትም፤ በሌላም በኩል፤ አውቀውም ይሁን ሳያውቁት፤ አገሪቱ ላይ ሌላ ችግር የሚጋብዙ ናቸው። ምክንያቱም ይሄ ሕገ መንግሥት የሚቀደደው፤ በእኛ መቃብር ላይ ነው የሚሉ ኀይሎች በሌላ አንጻር ተሰልፈዋልና፤ ሁላችንም ካከረርን፤ ትርፉ መጫረስ ነው። እነ ስዩም መስፍን በተወሰነ መልኩም ቢሆን ሕገ መንግሥታችንን እናስጠብቃለን ብለው ነው በስተርጅና ጫካ ገብተው፤ ፍጻሜያቸው በሚያሳዝን መልኩ የሆነው። ለ27 ዓመታት አሸነፉን። ለኹለት ዓመት ተኩል ታገሉ። ለጊዜው ተሸነፉ። ፓርቲያቸው እንጂ ሐሳባቸው ግን ተሸንፏል ማለት አንችልም። ሕገ መንግሥቱ ተቀዶ እንዲጣል የምንፈልገውን ያህል ሕገ መንግሥቱ ከተነካም ለመሞት የተዘጋጁ እንዳሉ እያየን ነው። በሁሉም ወገን ማክረር እንቀንስ። ችግራችን ሕገ መንግሥቱ አይደለም። ከሆነም፤ በከፊል ነው።

መቀየር ያለበት ምንድን ነው?
ኢትዮጵያ ውስጥ መቀየር ያለበት፤ ሕገ መንግሥቱ ሳይሆን፤ የሕገ መንግሥቱ መንፈስና የገዢው ፓርቲዎች አስተምህሮ፣ የካድሬዎቻቸው ርኩስ መንፈስ ወይንም ድንቁርና ነው። በኢትዮጵያ እስካሁን በአብዛኛው እየተፈጸመ ያለው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ሳይሆን ቀደም ሲል ኢሕአዴግ፤ አሁን ደግሞ የተረከበው ብልጽግና የፖለቲካ ርዕዮትና መረዳት ነው። ሕገ መንግሥቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ጭቆና ነበር፤ ብሔር ብሔረሰቦች ባህላችንን እንዳናሳድግ፣ በማንነታችን እንዳንኮራ ማዕቀብ ተጥሎብን ኖረናል ባሉና፤ እንደቡድን ካልቆምን አውሬ ይበላናል ባሉ ቡድኖች አሸናፊነት የተሰናዳ ሰነድ ነው። ስለዚህ የሕገ መንግሥቱ መንፈስ በዚህ የተቃኘና፤ እንደብሔር ሥልጣን የያዙ ኀይሎች የቡድን መብታቸውን ለማስከበር የት ድረስ መሄድ እንደለባቸው ድንበር ጠፋባቸው። ስለዚህ የግለሰቦች መብት ላይ ተረማመዱበት። ማስታረቅ ያለብን እነዚህን ኹለቱን ሐሳቦች ነው። የቡድንና የግለሰብ መብቶች፤ በሕገ መንግሥቱ እንደተረጋገጠው እንዴት ጎን ለጎን መሄድ ይችላል።
ሕገ መንግሥቱን በሙሉ ማስፈጸም ከጀመርን፤ መብታችንን ማስከበር፣ የማንፈልጋቸውንም አንቀጾች በትዕግስትና በሒደት በድርድር ማስለወጥ እንችላለን።

የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥት መተግበር ማለት ደግሞ የትም ክልል ኑሩ፤ የኢትዮጵያዊያን መብት ሳይሸራረፍ መፈጸም/መከበር ማለት ነው። ለምሳሌ፤ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ክልሎችን ፈጠረ፤ እንጂ ክልሎችን ለዚህ ወይም ለእነዚያ ብሔሮች በባለቤትነት አልሰጠም፤ ቢያንስ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ በግልጽ የተቀመጠ እንደዚያ ዓይነት አንቀጽ የለም። የፌደራል ሕገ መንግሥቱ ይሄንን ሥልጣን፤ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ፤ ለክልሎች አልሰጠም። ሥልጣን እንደሀብት ስለሚጣፍጥ፤ አንዳንድ ቡድኖች፣ ክልሎች፤ በኢሕአዴግ ፖለቲካዊ ትርጓሜ በመታገዝና፤ ሃይ ባይ ስላጡ ያንን ሥልጣን ነጥቀው ለራሳቸው ወሰዱ እንጂ፤ የፌደራል ሕገ መንግሥቱ እንዲህ ያለውን ሥልጣን ለክልሎችም ይሁን ለብሔሮች/ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አልሰጠም። የብሔር ብሔረሰቦችን መብቶች የሚደነግጉት አንቀጾች፤ አንቀጽ 2፣ 8፣ 39 እና 47 ለየትኛውም ብሔር፥ የትኛውንም ክልል በብቸኛ ባለቤትነት አይሰጡም። ይሄ አንድን ክልል ለአንድ ወይም ካንድ ለበለጠ ብሔሮች ብቻ በባለቤትነት መስጠት ሕገ መንግሥታዊ አይደለም። ይሄንን በብዙ መልኩ መመልከት ይቻላል።

የክልሎች ብቸኛ ባለቤት ብሔር/ብሔረሰብ የለም
አንደኛ፤ እነዚህ ከክልሎችን ለዚህ ወይም ለእነዚያ ብሔሮች በባለቤትነት የሚሰጡ ክልላዊ ሕገ መንግሥታት ከፌደራል ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9 ጋር ስለሚጣረሱ፤ ሕገ መንግሥታዊ አይደሉም።

ኹለተኛ፤ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40(3) ማናቸውም የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ነው ይላል። ሲቀጥልም፤ መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ሀብት ነው። በሰለጠነው ዓለም ቢሆን ብዙ የሚያከራክርና ለትርጉም የተጋለጠ አንቀጽ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ግን መሬት የሕዝብና የመንግሥት ነው። ክልልን ክልል የሚያሰኘው ደግሞ በከፊል ፖለቲካዊ ሐሳብ/ርዕዮተ ዓለም በከፊል ደግሞ መሬት ነው።

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 46(2)፤ ክልሎች የሚዋቀሩት፤ በሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነት እና ፈቃድ ላይ በመመስረት ነው ይላል። የኢትዮጵያ ክልሎች የተዋቀሩት እነዚህን መሰረት አደርጎ ነው ወይ የሚለው ክርክር እንደተጠበቀ ሆኖ፤ አሁን ባለው ሕገ መንግሥት የኢትዮጵያ ክልሎች የተመሰቱበት መሬት የክልሎቹ ሳይሆን የኢትዮጵየ ሕዝቦችና መንግሥት ነወ። ስለዚህ ክልሎች የተቋቋሙት በሕዝብ የጋራ ሀብት፣ መሬት ላይ ነው። አንዱ ክልል ብድግ ብሎ ይሄ ምድር የእከሌ ብሔር ነው ወይም የነእከሌ ብሔር ነው ማለት አይችልም። ይሄንን የሚሉ ክልላዊ ሕጎች አገሪቱን የመሰረታትን ሕገ መንግሥት ስለሚጥሱ፤ ተፈጻሚ መሆን የለባቸውም ወይም በሕገ መንግሥት ተርጓሚው አካል ፊት ቀርበው መፈተሸ አለባቸው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕገ መንግሥቱን የሚተረጉመው አካል፤ ፍርድ ቤቶች ወይም ሕገ መንግሥታዊ ፍ/ቤት ሳይሆን ፖለቲካዊ ተቋም ማለትም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስለሆነ የብሔሮችን ወይም ክልሎችን መብት በሚሸራርፍ መልኩ የመተርጎም እድሉ ጠባብ ነው የሚል ክርክር ይነሳል። በሰለጠነውም ዓለም ቢሆን ለምሳሌ ካናዳ፤ አብላጫ ወንበር ያለው ፓርቲ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያዎችን በቀላሉ ሊያደርግ ይችላል። ዴሞክራሲያዊ ፉክክርና ባህል በሌለበት ዓለም ግን ፖለቲካኞች የነገ ምርጫቸውን ስለሚያስቡ ሕዝብ የማይቀበለው አተረጓጎም ከወሰኑ፤ ምርጫ ላይ ተአማኒነትና ድምጽ ያጣሉ። ስለዚህ ድምጻቸውን አደጋ ላይ ጥለው፤ ተገቢ ያልሆነ አተረጓጎም ያሰፍናሉ ተብሎ አይታመንም። ዞሮ ዞሮ ሕዝብ በዴሞክራሲዊ መንገድ የሚደግፈው አተረጓጎም ከሆነም ግን በሒደት ሕዝቡን በማስተማር መለወጥ እንጂ፤ እኛ የማንፈልገው አተረጓጎም ስላሸነፈ የግድ ስህተት ነው ማለት አይደለም።

ሦስተኛ፤ የፌደራል መንግሥቱን ሥልጣን የሚደነግገው አንቀጽ 51(5) የመሬት፣ የተፈጥሮ ሀብትና ቅርሶች አጠባበቅና አጠቃቀም በተመለከተ ሕግ ያወጣል ይላል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥልጣንን የሚደነግገው አንቀጽ 55(2) (ሀ) የመሬት፣ የተፈጥሮ ሀብት እንዲሁም ድንበር ተሸጋሪ ወንዞችንና በኹለትና ከዚያ በላይ ክልሎች ውስጥ ያሉ ሀይቆችን አጠቃቀም በተመለከተ ሕግ ያወጣል ይላል። ክልሎች እንኳንስ ክልሉን በባለቤትን ለተወሰነ ብሔር መስጠት ይቅርና፥ በመሬቶች ላይ ሕግ ማወጣትም አይችሉም። ይሄ ሥልጣን የሌለው ክልል፤ ይሄ ክልል የዚህ ወይም የእነዚያ ብሔሮች ነው ሊል አይችልም።

ስለዚህ ኢሕአዴግ/ብልጽግና በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ሲያስፈጽመውና ሲተረጉመው በመጣው አካሄድ ምክንያት ዝም ቢባሉም፤ አንዳንድ ብሔሮች፣ አንዳንድ ክልሎችን በብቸኝነት የእኛ ነው የሚሉት ነገር ሕገ መንግሥታዊ አይደለም።

ችግሩ ሕገ መንግሥቱ ሳይሆን ክልሎችና ባለሥልጣናት እንዲሁም ፖለቲከኞች ሕገ መንግሥቱን የተረዱበት ቅኝት አንድም በድንቁርና፤ አለያም በየዋህነት ወይም በራስ ወዳድነት የተቃኘ መሆኑ ነው። በተጨማሪም የፌደራል መንግሥቱ የሰብኣዊ መብቶችን ለማስፈጸም ወኔና ፍላጎት ስላነሰውና፤ በክልሎች ጉዳይ ጣልቃ ገባህ እንዳይባል ስለሰጋ የተፈጠሩ ችግሮች ናቸው። በርግጥ ሕገ መንግሥቱ በግልጽ ፍርድ ቤቶችን ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮችን መተርጎም ባይችሉም መተግበር ወይም የማስፈጸም ሥልጣን ቢሰጣቸው መልካም ይሆናል። ከዚህ አንጻር ችግሩ መዋቅራዊ ነው።

ፌደራል መንግሥት ሆይ ወደ የት ነህ?
በሕገ መንግሥቱ ለክልሎች በግልጽ የተሰጡትን ሥልጣኖች ሳይጋፋ፤ የፌደራል መንግሥቱ የኢትዮጵያዊያን ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን ሳይሸራረፉ፤ በሁሉም ክልሎች በእኩልነት እንዲፈጸሙ ከተጋና ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ከማስፈጸም አንጻር የሚያፈነግጡ ክልሎችን በማስተማር ወይም በማስገደድ ሕገ መንግሥትን እንዲያስፈጽሙ ማድረግ ከቻለ፤ ሕገ መንግሥቱ ያቆየናል።

በርግጥ የፌደራል መንግሥቱ በክልሎች ጉዳይ ጣልቃ የሚገባበት ሕገ መንግሥታዊ አግባብ ልቅ አይደለም፤ ጥብቅ ነው። አንቀጽ 51(14) የፌደራል መንግሥቱ በክልል ጣልቃ የሚገባው በክልል ሲጋበዝ ወይም ሲጠየቅ ነው ይላል። አንቀጽ 55(16) መሰረት ሰብኣዊ መብት ሲጣስ፤ በኹለቱ ምክር ቤቶች ፈቃድ ጣልቃ ሊገባ የሚችልበት አግባብ አለ። ከክልሉ አቅም በላይ ነው የሚለውን መወሰን ግን ቀላል አይደለም። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅም ጣልቃ ሊገባ የሚችልበት አግባብ አለ።
አሁን የአገሪቱ በሙሉ ገዢ ፓርቲ አንድ በሆነበት ጊዜ ይሄንን ማድረግ ካልተቻለ፤ በዴሞክረሲያዊ ውድድር የተለያዩ ፓርቲዎች ሲገዙ፤ የፌደራል መንግሥቱ በክልሎች ሥልጠን ጣልቃ ለመግባት ምን ያህል ፈታኝ ሊሆንበት እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ከዚህ አንጻር ሕገ መንግሥቱ መዋቅራዊ ችግል አለበት ማለት እንችላለን። ከዚህ አንጻር፤ ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻልና ክልሎች የዜጎችን መብት በሚጥሱበት ጊዜ የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ ስለሚገባበት አግባብ እንዲሁም ሕገ መንግሥታዊ የአቤቱታና የይግባኝ መንገዶችን በማሻሻያ መልኩ ማስገባት፤ ወይም ፍርድ ቤቶችን በተወሰነ መልኩ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮችን/ክርክሮችን እንዲዳኙ ሥልጣን መስጠት ያስፈልጋል። ይሁን እንጂ፤ ኀላፊነት የሚሰማው ኀይል፤ ሕገ መንግሥቱን ለመሰረዝ ለመደለዝ መቸኮል የለበትም።

ማጠቃለያ
ሕገ መንግሥት የሚዳብረው በስክነት ነው። የኢሕአዴግ/ብልጽግና’ን ፖለቲካ ስለጠላን ብቻ ሕገ መንግሥቱን በጥቅሉ አቅልለንና አሽቀንጥረን መጣል ተገቢ አይደለም። በሕገ መንግሥት ውስጥ ሁሉም ባይሆኑም አብዛኞቹ አንቀጾች ጠቃሚ በመሆናቸው ራሱን ሕገ መንግሥቱን ተጠቅመን ሕገ መንግሥታዊነት እንዲሰፍን ብንታገል ጠቃሚ ይሆናል። ምናልባትም የሚያነታርኩ የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ምንም እንኳን ቁልፍልፍና ከባድ ቢሆኑም የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ሊሻሻል የሚችልበት አግባብና አንቀጾች አሉ።

ዴሞክራሲ የድርድርና የሰላማዊ ፉክክር ዓውድ/ሒደት እንደመሆኑ መጠን በድርድር፣ በፉክክር እና በምክክር ሕገ መንግሥቱን በሰላማዊ መንገድ ታግሎ ማሻሻል እንጂ ተቀዶ ካልተጣለ ሰላም አይመጣም የሚለው ሐሳብ ዴሞክራሲያዊም ሥልጡንም አይደለም። ሁልጊዜ አሮጌውን ንደን፣ ደምስሰን፣ አፍርሰን፣ አዲስ መገንባት ብቻ ሳይሆን ባለው ላይ መገንባት፤ ያለውን እያሻሻሉ መጓዝም መልመድ አለብን። ስለዚህ በሕገ መንግሥቱ ላይ የሚደረገው ውይይትና ንግግር በዚህ መልኩ እንዲቃኝ እንመከክራለን። በሚቀጥለው ደግሞ ስለአንቀጽ 39 የእኔን አረዳድ እጽፋለሁ።

ተክለሚካኤል አበበ ከካናዳ፣ ቶሮንቶ በሕግ ማማከር እና ጥብቅና ቢሮ ከፍተው የሚሠሩ ባለሙያ ሲሆኑ በኢሜል አድራሻቸው lijtekle@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 116 ጥር 15 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here