ዳሰሳ ዘማለዳ ሐሙስ መስከረም 15/2012

Views: 538

 

1–በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ልዩ ቦታው ጎሮ ብርሃኑ ሆቴል አካባቢ አንድ ግለሰብ ነጋዴ መስሎ በመቅረብ አንድ ሙሉ ጊቢ ከእነ መኖሪያ ቤቱ በመከራየት በቤት ውስጥ 7 ባለ ሰደፍ ክላሽን ኮቭ ጠመንጃ ከ265 ጥይት ጋር ፣ 2 ማካሮቭ ሽጉጥ ከ22 ጥይትና፣ ሦስት የሽጉጥ ካርታዎችን ሸሽጎ መገኘቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።(አዲስ ማለዳ)

…………………………………

2- የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ምክትል ከንቲባ  ታከለ ኡማ በአዲስ መልክ ለኅብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሠጥ የተደራጀውን የራስ መኮንን ፓርክ  ዛሬ መስከረም 15/2012 መርቀው ስራ አስጀምረዋል።ከራስ መኮንን ፓርክ በተጨማሪ ጦር ኃይሎች አከባቢ የሚገኘው ሆላንድ ፓርክ(65 ሺ ካ.ሜ) እና የአቃቂ ፓርክ (62 ሺ ካ.ሜ) በተመሳሳይ መልኩ ለኅብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሠጡ ተመርቀው ወደ ስራ ገብተዋል።ዛሬ የተመረቁት ሦስት ፓርኮች በአጠቃላይ 13.9 ሔክታር በላይ ስፋት ያላቸው እንደሆነ ታዉቋል።(አዲስ ማለዳ)

…………………………………

3-የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ  ታከለ ኡማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለረዥም ጊዜያት ጥያቄ ስታቀርብባቸው ለነበሩ 15 ነባር የቤተ ክርስቲያኗ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታዎችን አዘጋጅቶ ዛሬ መስከረም 15/2012  ቅዱስ ፓትሪያርኩ በተገኙበት አስረክበዋል።(አዲስ ማለዳ)

…………………………………

4-የቡልቡላ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ በተያዘው ዓመት የሚጠናቀቅ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ኢንዱሰትሪዎች ልማት ኮርፖሬሸን አስታውቋል።ለግንባታው ከ6 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ለሚደረግበት የቡልቡላ ኢንዱስትሪ ፓርክ 180 ባለሃብቶችን ማስተናገድ የሚችል ሲሆን እስካሁን 23 ባለሀብቶች ጥያቄ አቅርበዋል። ፓርኩ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባ 400 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል።(ፋና ብሮድካስቲንግ)

…………………………………

5-በአገር አቀፍ ደረጃ “ህይወት ለህይወት… ደም ለግሰን ህይወት እናድን” በሚል መሪ ቃል ጥቅምት 15/2012 ዓ.ም በአንድ ቀን 10 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ መታቀዱን የጤና ሚኒስቴር አስታወቋል።በኢትዮጵያ አሁን ያለዉ ደም ለጋሽ ከ0.3 በመቶ በታች መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በ2011 በሀገር አቀፍ ደረጃ 222 ሺህ 434 ዩኒት ደም ከበጎ ፈቃደኞች መገኘቱን ገልፀዋል።(ኤዜአ)

…………………………………

6-ሱዳን ቢዝነስ ካውንስል ያዘጋጀው ከሱዳን እና ኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ዘርፍ የተወጣጡ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች እና የግል ባለሀብቶች የሚሳፉበት የንግድና የኢንቨስትመንት ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።የኹለቱ አገራት በቀጣይ በቱሪዝም፣ በግብርና ማቀነባበሪያ እና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ኢትዮጵያ ማመቻቸቷን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።የኢትዮጵያና ሱዳን ጥምር ኮሚቴ ተቋቁሞ በቋሚነት እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።(አብመድ)

……………………………….

7-ኢትዮጵያ ባዘጋጀችው የ10 ዓመት ቱሪዝም ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ጥናት ቀርቦ ውይይት ተካሄዷል።ጥናቱ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ቱሪስቶች እንዴት የቆይታ ጊዜያቸውን ማራዘም ይችላሉ? የሚለውን በሚመልስ መልኩ ጥናቱ መዘጋጀቱም ተገልጿል።ኢትዮጵያን በ2030 ከአፍሪካ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ቀዳሚ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ታዉቋል።(ዋልታ)

…………………………………

8-በኢትዮጵያና በኮሪያ ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ መካከል ለመዲናዋ ፈጣን የከተማ አውቶቡስ B6 ኮሪደር ፕሮጀክት የሚውል የ63 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የብድር ስምምነት ተፈርሟል።ብድሩ በ40 ዓመታት ውስጥ የሚከፈል ሲሆን፥15 ዓመት የእፎይታ የሚኖረው ሲሆን የወለድ መጠኑም 0 ነጥብ 01 በመቶ እንደሆነ ተገልጿል።(ፋና ብሮድካስቲንግ)

…………………………………………………………………………

9 – አራት ዓመታን ያስቆጠረው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በስራ ላይ በቆየባቸው ዓመታት ውስጥ  ከ3መቶ በላይ አደጋዎችን ማስተናገዱ ታወቀ። (ሸገር)

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com