መነሻ ገጽማረፊያሰሞነኛ‹‹የዝናብ አዝንበናል›› እሰጣገባ

‹‹የዝናብ አዝንበናል›› እሰጣገባ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 14 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሳላቸው ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። ከጥያቄዎቹ መካከል ስለ ኑሮ ውድነት፣ ስለሕዳሴው ግድብ፣ ስለወቅታዊ አሳሳቢው የሰላምና መረጋጋት ጉዳይ፣ በትግራይ ስለተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ እና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች ተዳሰዋል። ብዙዎች በተለይ በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ላይ ከጠቅላዩ ምላሽ እየመዘዙ ድጋፍ እና ተቃውሞ፣ ምስጋና እና ነቀፌታ፣ ምርቃት እና እርግማን አዝንበዋል።

ትኩረት ከሳቡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሾች መካከል ‹‹ባለፉት ሳምንታት በሰሜን ሸዋ፣ በጎጃም ያያችሁት ዝናብ የተፈጥሮ ሳይሆን እኛ ያዘነብነው ነው›› በማለት ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ዝናብ ማዝነብ መቻሏን መናገራቸው ከምክር ቤት አባላት የአድናቆት ጭብጨባ ሲቸራቸው፤ በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ለአንዳንዶች መሳለቂያ ለሌሎች ደግሞ የመከራከሪያ ርዕስ ሆኖ ሰንብቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማብራሪያቸው ኢትዮጵያ በኹለት ዓመታት ውስጥ ኹለት ሳተላይት ማምጠቋን በተለይ በኅዋ ሳይንስ ሥሟ ከሚጠቀሱት ጥቂት የአፍሪካ አገራት መካከል እንድትመደብ አስችሏታል ሲሉ ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ በጣም ትልቅ አገር ናት መቅደም ነበረባት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ የኅዋ ሳይንስ እውቀቱ አለን፣ መልከዓ ምድሩ አመቺ ነው እንዲሁም በመስኩ የሰለጠኑ ባለሙያዎችም አሉን ብለዋል። ‹‹መቅደም ነበረብን›› ሲሉም ቁጭት አዘል አስተያታቸውንም ሰንዝረዋል።

ከብዙዎቹ ስላቆች መካከል አንዱ ‹‹የሰሞኑ ጸሐይ ሲቀቅለን ታዲያ ጠቅላዩ እንዴት አስቻላቸው? ዝናቡን በማዝነብ ቀዝቀዝ ሊያደርጉን ይገባል ነበር›› ሲል ሲወርፋቸው፤ ሌላኛው ደግሞ ‹‹ቆይታችሁ ሰው ፈጠርን እንዳትሉ ብቻ!›› ብሏል፤ ይህንን ተከትሎ በአስተያየት መስጫው ላይ ‹‹እውቀት አልቦ ስላቅ!›› ስትል አንዷም አጣጥላዋለች።

ሌሎች ደግሞ የገረመን የጠቅላዩ የተሰደቡበት የዝናብ ማዝነብ ጉዳይ ቀላል እና ሊያሰድባቸው አይገባም ያሉ ሲሆን በተመሳሳይ ሌሎችም እንዲሁ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ያቃለሉ እየመሰላቸው ራሳቸውን ትዝብት ላይ ጥለዋል ሲሉም ትችቱን ተችተዋል። ባይሆን ጠቅላዩ ሊወቀሱ የሚገባው ‹‹ለቴክኖሎጂ የሚሰጡትን ግምት እና ትኩረት ምናለ ዜጎች ደኅንነት ቢጨነቁ›› ብለዋል፤ የቴክኖሎጂ ፍቅራቸው፥ በየቀኑ የተለማመድነውን የዜጎች ግድያ አስረስቷቸዋል ሲሉ ትችታቸውን በዚሁ ማኅበራዊ ትስስር መድረክ ገጻቸው ላይ ያሰፈሩም ነበሩ።

አንዳንድ መደበኛ መገናኛ ብዙኀን ለጉዳይ ትኩረት በመስጠት፥ ዝናብ የማዝነብ ቴክኖሎጂን ከአገራት ተመክሮ ጋር በማያያዝ ሰፊ ሽፋን መስጠታቸው ጭምር በትችትም በምስጋናም መነጋገሪያ ሆነዋል።
ታዋቂ ከሆኑት ሰዎች መካከል የቀድሞው የኢሳት ቴሌቪዥን ሥራ አስኪያጅ እና የማኅበራዊ አንቂ አበበ ገላው በፌስቡክ ገጹ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ዝናብ ማዝነብ ይሄ ምንም አያስገርምም ሲል አስተያየቱን ማስረጃዬ ብሎ ካቀረበው መረጃ ጋር አንድ ላይ አጋርቷል።

‹‹እርቀን ሳንሄድ ጎረቤታችን ኬኒያ ‹አርቴፊሻል ዝናብ› መጠቀም ከጀመረች ዐሥርት ዓመታት አስቆጥራለች። ኢትዮጵያ ገና ሙከራ ላይም ሆና ግርምትና ትንግርት ማስከተሉ ግን ራሱ ያስገርማል። ነገሩ ቀላል ነው። እኛ ካልቻልን ያው እንደተለመደው አንድ የእስራኤል ወይንም የቻይና ካምፓኒ በተመጣጣኝ ወጪ ሊሠራው ይችላል። ‘Cloud Seeding’ የቆየ ቴክኖሎጂ ነው። ምንም ትንግርት የለውም።››

ኢትዮጵያ ዘመናዊ ድሮኖችን ከገዛች ዓመታትን አስቆጥራለች የሚለው አበበ፥ ድሮኖች ጥቅም ላይ የሚውሉት ቦንብ ለመጣል ብቻ አይደለም፤ ኬሚካል ረጭተው ዝናብ ያመጣሉ። ‹‹ድሮኖቹ ቦንብ ሲያዘንቡ አጨብጭበን ዝናብ ሲያዘንቡ ግራ ከገባን ችግር አለ ማለት ነው›› ሲል አስተያቱን ቋጭቷል።

በመደበኛ መገናኛ ብዙኀን እና በማኅበራዊ ትስስት መድረኮች በተለይ በፌስቡክ በቀትታ በተላለፉው የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የተወካዮች ምክር ምላሽና ማብራሪያ፥ ኢትዮጵያ ባጠረ ጊዜ ውስጥ ውጤት ከሚያስመዘግቡ አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ እንድትሆን ከሚያስችሏት መካከል ወሳኙ ቴክኖሎጂ መጠቀም ነው፤ ቱሪዝሙም፣ ኢንዱስትሪም ሆነ ግብርናው ቴክኖሎጂ ይፈልጋሉ ብለዋል። ‹‹ኢትዮጵያ ቢዘህ ረገድ ውጤት እያስመዘገበች ሲሆን ውጤቱን ማጠናከር ከቻልን ብዝኀ ዘርፍ ባልናቸው ሴክተሮች በጣም ትልቅ የሆነ ለውጥ በዐሥር ዓመታት ውስጥ ይመጣል›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የመንግሥታቸው የትኩረት አቅጣጫው መሆኑን ከመጠቆም ባሻገር ጠንካራ ተስፈኝነታቸውን አልሸሸጉም።


ቅጽ 3 ቁጥር 125 መጋቢት 18 2013

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች