መነሻ ገጽአንደበት‹‹ባንኮች ካፒታላቸውን ማሳደጋቸው ክርክር የማያስፈልገው ጉዳይ ነው›› የዘመን ባንክ ፕሬዝዳንት ደረጀ ዘነበ

‹‹ባንኮች ካፒታላቸውን ማሳደጋቸው ክርክር የማያስፈልገው ጉዳይ ነው›› የዘመን ባንክ ፕሬዝዳንት ደረጀ ዘነበ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንክ ማቋቋሚያ ካፒታል መጠኑን ከ500 ሚሊዮን ብር ወደ 5 ቢሊዮን ብር ማሳደጉ ከገንዘብ ግሽበትና አቅም ጋር እንዲሁም ከኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጋር የተገናዘበ ካፒታል ባንኮች ሊኖራቸው እንደሚገባ በመታመኑ እንደሆነ ይታወቃል። በአብዛኛው መመርያው አግባብና የሚጠበቅ ነው የሚል አስተያየት የተሰጠበት ቢሆንም፣ የአገሪቱን የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ለማሳደግና የበለጠ እንዲራመድ ለማድረግ ከተፈለገ ግን የማቋቋሚያ ካፒታሉ መጠን አሁንም እጅግ ዝቅተኛ ነው ሲሉ የሚናገሩት የዘመን ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ ደረጀ ዘነበ ከአዲስ ማለዳ ጋዜጠኛ ሰለማዊት መንገሻ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አዲስ ማለዳ፡ የዘመን ባንክ አመሰራረቱን እና አዳዲስ ያስተዋወቃቸውን ቴክኖሎጂዎች ቢገልፁልን?
ደረጀ፡ እ.አ.አ በ2008 ዓ.ም በአንድ ቅርንጫፍ አገልግሎት የመስጠት ፍልስፍና ሥራውን የጀመረው ዘመን ባንክ ቅርንጫፎች ለማስፋት ሳይሆን በቴክሎጂ ተደራሽ ለመሆን ሲሰራ ቆይቷል።
ባንኩ ቀደም ሲል የኢንተርኔትና የሞባይል ስልክ ባንኪንግ አገልግሎቶችን በወቅቱ የነበሩ ቴክኖሎጂዎችንም በመጠቀም ለደንበኞቹ በማስተዋወቅና በመተግበር ቀደምት ሲሆን አሁን ደግሞ ከጊዜውና ከቴክኖሎጂው ጋር በመራመድ ይበልጥ ዘመናዊና ለደንበኞች ተደራሽ ለማድረግ የኢንተርኔትና የሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያውን በአዲስ መልክ ማቅረቡንም አቶ ደረጀ ገልጸዋል።

ዘመን ባንክ ያሰባቸው የቴክሎጂ ተደራሽነት አገሪቷ ያላት የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት እና ባንኮች እርስ በርስ ያላቸው የቴክሎጂ ሽግግር እንቅፋት ስለሆነበት ቅርንጫቹን ወደ 60 በማሳደግ የቴክኖሎጂ ስራውን አቆይተውት እንደነበር ደረጀ አንስተዋል። ደረጀ አክለውም አሁን ላይ ባንኩ ለተቀማጭ የሚጠይቀው የ25 ሺሕ ብር መጠን ወደ 5 ሺሕ ብር ዝቅ ማድረጉን እና በክልሎች ደግሞ ደንበኞች ባላቸው አቅም እንዲያስገቡ የተሻሻለ መሆኑን አንስተዋል።
በተጨማሪም ባንኩ የሞባይል ባንኪንግ እና ኢንተርኔት ባንኪንግ በማሻሻል ከንክኪ ነጻ ቪዛና ማስተር ካርዶች ለሕብረተሰቡ ይፋ ማድረጉን ገልጸዋል።

ባንኩ አሁን ያለንበትን አስቸጋሪ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ግምት ውስጥ በማስገባት ደንበኞች ከንክኪ ነጻ የሆነ ግብይት እንዲፈጽሙ የሚያስችሉ “Contactless” ቪዛና ማስተር ካርዶችን ያዘጋጀ ሲሆን ደንበኞች እነዚህን ካርዶች ወደ ኤቲኤም ወይም ፖስ ማሽን በማስጠጋት ብቻ ማንነታቸውን እንዲለይ በማድረግና የምስጢር ቁጥር (Pincode) በመጠቀም በፍጥነት አገልግሎት ማግኘት የሚያስችል ቴክኖሎጂ መፈጠሩን ደረጀ ገልጸዋል።

ባንኩ ይፋ ያደረገው ቴክኖሎጂ “ዘመን ፕላቲኒየም” የጉዞ ቅድመ ክፍያ ማስተር ካርድ አገልግሎት ሲሆን፣ ይህም አገልግሎት እስካሁን ከአገራችን ወደ ውጪ ለሚደረጉ ጉዞዎች የሚያስፈልጉ የውጪ አገር ገንዘቦችን ደንበኞች በጥሬ ገንዘብ አማካይነት ሲስተናገዱ መቆየታቸውን የገለጹት አቶ ደረጀ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይህን አገልግሎት በፕላስቲክ ካርድ መስጠት እንዲችል ያወጣውን መመሪያ ተከትሎ ዘመን ባንክ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን በባንኩ የተዘጋጀ “ዘመን ፕላቲኒየም” የጉዞ ቅድመ ክፍያ ማስተር ካርድ በማዘጋጀት ወደ ውጪ የሚጓዙ ደንበኞቹ እንዲጠቀሙበት ማድረግ ተችሏል።

ይህ የጉዞ ቅድመ ክፍያ ማስተር ካርድ አገልግሎት ደንበኞች ለጉዟቸው የሚያውሉትን ወጪ አስቀድመው መገመት እንዲችሉና በካርዱም ላይ የሚገኘውን የውጪ ምንዛሬ ገንዘብ ይዘው በመጓዝ ክፍያዎችንና አገልግሎቶችን ለማግኘት የሚያስችል መሆኑንም ደረጀ ገልጸዋል።

በዚህ አገልግሎት ደንበኞች የእጅ ስልካቸውን በመጠቀም ብቻ የተለያዩ ክፍያዎችን ማለትም የዲኤስ ቲቪ፣ የስልክና የመሳሰሉትን ክፍያዎች በቀላሉ መፈጸም የሚያስችላቸው ሲሆን፣ በተመሳሳይ ሌሎች ክፍያዎችን ለምሳሌ የአውሮፕላን ጉዞ ትኬት፣ ውሃ፣ መብራት፣ ሆስፒታል፣ ት/ቤት፣ የዩኒቨርሲቲዎች፣ የኮሌጆችንና ሌሎች ተዛማጅ ክፍያዎችን መከወን እንዲቻል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት እንደሚገኝና በቅርቡም ስራው ተጠናቅቆ አገልግሎትል ይጀምራ ተብሎ እንደሚጠበቅ ኃላፊው ጠቁመዋል።

ባንኩ በተለይ ከንክኪ ነፃ ቪዛና ማስተር ካርዶችን እንዲሁም ዘመን ፕላቲኒየም የጉዞ ቅድመ ክፍያ ካርዶችን አገልግሎት ላይ ለማዋል ከማስተር ካርድና “CR2 Limited” ከተባለ የአየር ላንድ ኩባንያ ጋር ከ10 ዓመት በላይ በጋራ በመጣመር ሲሰራ ቆይቷል።
ባንኩ በቴክኖሎጂው ዘርፍ አበይት ስራዎችን ከመስራት ባለፈ መንግሥት “የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” በማለት ላዘጋጀው አገራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ መተግበር የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

አዲስ ማለዳ፡ ብሔራዊ ባንክ ያወጣቸው ባንኮች ወደ ዲጂታል ባንኪንግ እንዲሸጋገሩ የሚያደርጉ መመሪያዎች ለዘመን ባንክ እና ለአገሪቱ ባንኮች ምን ማለት ናቸው?
ደረጀ፡ ዲጂታል ባንኪንግ ቴክኖሎጂን ለሕብረተሰቡ ማዳረስ ነው። ባንኮች ተደራሽ በሆኑ ቁጥር ሕብረተሰቡ ወደ ባንክ ቅርብ መሆን ይችላል። ስለዚህ የባንክ መሰረታዊ ስራ የገንዘብ አቅርቦት በመሆኑ ተደራሽነታቸውን ቅርንጫፍ በመክፈት ብቻ ሳይሆን በቴክሎጂ እና በጋራ በመስራት ሊሆን ይገባል።

ባንኮች በቴክሎጂ መደገፋቸው እጅ በእጅ የሚደረጉ የጥሬ ገንዘብ ልውውጦችን መቀነስ ያስቻላል። ሰዎች ከባንክ በተደጋጋሚ ጥሬ ገንዘብ በማውጣት እና በማስገባት የሚጠቀሙ ከሆነ ባንኮች የገንዘብ እጥረት ችግር ይገጥማቸዋል። ስለዚህ የጥሬ ገንዘብ ዝውውር ሲቀንስ የባንኮች ውስጥ የሚኖር ገንዘብ ይጨምራል። ሰዎችም ራሳቸውን በራሳቸው በማስተናድ በአቅራቢያቸው ባሉ ሁኔታዎች መጠቀም እንዲችሉ ያደርጋልል።

ይህ ራስን በራስ ማገልገል በተስፋፋ ቁጥር ባንኩ ለሰው ሀይል የሚያወጣውን ወጪ ይቀንሳል፤ ይህ ደግሞ ባንኮች የሚያቀርቡትን አገልግሎት እንዲጨምሩ ያስችላል።
እንደ ደረጀ ገለጻ ከሆነ በፊት ባንኮች ላይ በርካታ ወረቀቶች እና የሰው ሀይል ይታያል፤ በአንጻራዊነት ከበፈቱ በተሻለ ሁኔታ ወደ ቴክኖሎጂ ብንቀርብም ብዙ ይቀረናል ብለው ያስባሉ።
አዲስ ማለዳ፡ ገንዘቦችን የማስተላፍ እና ይዞ የመንቀሳቀስ በተመለከተ የሚወጡ ገደቦች ቴክሎጂዎችን ከመጠቀም ጋር እንዴት ማስኬድ ይቻላል?
ደረጀ፡ ገደብ ዝምብሎ የሚቀመጥ አይደለም። አንድ ሰው በሳምንት ከ5 በላይ ዝውውሮችን ማካሄድ አይቻልም ሲባል ቢዝነስ ውስጥ ያልተሳተፉትን እንጂ በንግዱ ላይ ያሉ ሰዎችን አይደለም። ለምሳሌ ከአንድ ሺሕ በላይ ሰራተኛ ያለው ተቋም ፔሮል ሲሰራ ከ5 በላይ ዝውውር አታደርግም አይባልም።

በተቀመጠው ፍሬም ወርክ ውስጥ በልዩ ሁኔታ የሚፈቀዱ አሉ። ማስረጃ አቅርበው የገንዘብ ዝውውሮችን እንዲያካሂዱ የሚደርግበት እንጂ ሁሉንም የመከልከል ሁኔታ የለም።
ከዚህ ጋር ተያይዞ መረጃውን ግልጽ በማድረግ ባንኮች እና ብሔራዊ ባንክ መስራት ይኖርባቸዋል። በአማካይ አንድ ግለሰብ ከ5 በላይ ዝውውሮች ሲያካሂድ አልታየም። በተጨማሪም አንድ ግለሰብ ይዞ መንቀሳቀስ የሚችለው ከ200ሺሕ ብር በላይ ሆኖ አያውቅም። መመሪያው እንደየስራ ባህሪያቸው ብዙ እንቅስቃሴ ላላቸው ግለሰቦ አስገዳጅ አይደለም።

ይህን ደግሞ ለመቅረፍ ብርን በመያዝ ከባንክ ባንክ ከመዘዋወር ይልቅ ቴክኖሎጂዎች ሀገር ውስጥ እየገቡ ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን ለረጀም ጊዜ ጥሬ ገንዘብ በእጃችን መያዝ ስለለመድን ብር ሳንይዝ በቴክኖሎጂ ግብይት መፈጸም ልምዱ የለንም።
በአደጉት አገራት የ2 ብር ቡና ጠጥተው በካርድ ከፍለው ነው የሚሄዱት። እኛ ጋር ትልልቅ የገንዘብ ዝውውሮች በቴክኖሎጂ የሚደገፍ ከሆነ ሰዎች ብር የማውጣት እድላቸው ይቀንሳል፤ ይህ ደግሞ በአገሪቱ መታተም ያለበተን ገንዘብ መጠን ይቀንሳል፤ የሚታተመው ገንዘብ መጠን በቀነሰ ቁጥር የአገሪቱን ወጪ ይቀንሳል። በአገሪቷ አስፈላጊ ለሚባሉ ወጪዎች ብቻ ብር ይታተማል፤ ይህም የባንኮችን የተቀማጭ ገንዘብ ይጨምራል።

አዲስ ማለዳ፡ የብሔራዊ ባንክ አዲሱ ካፒታል የማሳደግ መመሪያው እንዴት ይገመግሙታል? ካፒታልን ለማሳደግ የሚጠቀሙት መንገዶች ከባለአክሲዮኖች የሚሰበሰቡ ትርፎችን መልሶ ገቢ ማድረግ አንዱ አማራጭ ነው፤ ይህ ቅሬታን አያስነሳም ወይ?
ደረጀ፡ ብሔራዊ ባንክ የባንክ ማቋቋሚያ ካፒታል መጠን ወደ 5 ቢሊዮን ብር ከፍ ለማድረግ የሄደበት አቅጣጫ ጥሩ መሆኑን የገለፁት ደረጀ የካፒታል ማሳደግ ጥያቄ መምጣት የነበረበት ከባንኮቹ ነበር፤ ምክንያቱም ባንኮቹ ኢኮኖሚውን መቋቋም እንዲችሉ ያደርጋቸዋል። በርግጥ አንዳንድ ባንኮች ቀድሞው አውጥተዋል።ዘመን ባንክም ቢሆን ታህሳስ ወር ላይ ባደረገው ጉባኤ አምስት ቢሊየን ለማድረስ እቅድ ይዟል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንክ ማቋቋሚያ ካፒታል መጠኑን ከ500 ሚሊዮን ብር ወደ 5 ቢሊዮን ብር ማሳደጉም ከገንዘብ ግሽበትና አቅም ጋር እንዲሁም ከኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጋር የተገናዘበ ካፒታል ባንኮች ሊኖራቸው ይገባል ከሚል ነው።
በአብዛኛው መመርያው አግባብና የሚጠበቅም ነው የሚል አስተያየት የተሰጠበት ቢሆንም፣ የአገሪቱን የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ለማሳደግና የበለጠ እንዲራመድ ከተፈለገ ግን የማቋቋሚያ ካፒታሉ መጠን አሁን እጅግ ዝቅተኛ ነው ብለዋል።
ባንኮች በተሰጣቸው እጅግ ሰፊ ጊዜ ካፒታላቸውን ማሳደጋቸው ኢኮኖሚው ሲንገጫገጭ መቋቋም እንዲችሉ፣ ቴክኖሎጂን እንዲያሳድጉ፣ በጋራ በመዋሃደ አንድ ትልቅ ባንክ እንዲመሰርቱ ያስችላቸዋል።

ባንኮች ካፒታላቸውን ያሳድጉ በሚለው አዲሱ መመርያ ላይ ሌላው የሚነሳው ጉዳይ የባንክ ማቋቋሚያ ካፒታል 5 ቢሊዮን ብር ይሁን ሲባል ባንኮች ወደ ውህደት ሊሄዱ ይችላሉ የሚል ግምት ማሳደሩ ነው። እንደ ደረጀ ገለፃ ለአገራችን ከ5-10 ባንክ በቂ ነው። ባንኮችም ጠንካራ ካፒታል እንዲኖራቸው ይዋሃዱ ሲባል ፍርሀት ሊኖር አይገባም።

- ይከተሉን -Social Media

መዋሀድ ከሆነ ለምንድነው የፈራነው? 80 ብሔር ብሔረሰብ ስላለ 80 ባንክ ያስፈልጋል ማለት አይደለም። ባንክ ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ትልቁን ድርሻ እንደመውሰዱ መጠን ባንኮች ተዋህደው የገበያ አድማሳቸውን ያሰፋሉ፤ የሰው ሀይል እና ቴክኖሊጂ ይዘው መወዳደር እንዲችሉ ያደርጋቸዋል ሲሉ ደረጀ ገልጸዋል።

ኬኒያ ውስጥ ያሉ 50 ባንኮች እኮ አብዛኞቹ አመታዊ ትርፋቸው ከአንድ ባለሃብት ራሱ አይበልጥም። ስለዚህ ባንኮች መብዛታቸው ሳይሆን ኢኮኖሚውን ማሳደጋቸው ላይ ትኩረት መሰጠት ይገባዋል።
ካፒታል ለማሳደግ አንደኛው አማራጭ በየአመቱ ከሚያገኙት ትርፍ ካፒታል ማሳደጊያ የሚያውሉ ሲሆን፣ ሁለተኛው ባለአክሲዮኖቹ ለሌሎች ግለሰቦች አክሲዮን የመሸጥ ሁኔታ አለ፤ ይህ በባለአክሲዮኖች ፍላጎት የተመሰረተ ነው። ስለዚህ ምንም ቅሬታ አይፈጥርም።

አዲስ ማለዳ፡ ለመጨረሻ ጊዜ የተመሰረቱት ባንኮች 2013 ላይ ሲሆን አሁን ቀድሞ ከተፈጠሩት ጋር አብረው መጓዝ ይችላሉ ወይ? ባንኮች በአንድ ተግባር ላይ ተወስነው/ስፔሻላይዝ ያደረጉ ሆነው/ ማቋቋም በተመለከተ ምን ሀሳብ አለዎት?
ደረጀ፡ ባንኮች ካፒታላቸውን ማሳደግ የሚገደዱት ብሔራዊ ባንክ ባንኮቹን ለመታደግ ያደረገው ትልቅ ስራ ነው። ወደፊት የሚመጣውን ኢኮኖሚ ቀውስ ለመቋቋም ያስችላቸዋል።
አዳዲስ የሚመጡ ባንኮች ከነባሮቹ ጋር መዋሃድ ለምን አይፈልጉም። መዋሃድ እንደ ትልቅ አማራጭ ነው ማየት ያለባቸው።

አሁን ያሉበት የካፒታል መጠን አቅም እንደሌለው እየታወቀ፣ ብሔራዊ ባንክ አቅማቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው እያወቀ ዝም ካለ ተወቃሽ ነው የሚሆነው።
እንደ እኔ ካፒታል ማሳደግ መመሪያ እንደውም ያነሰ ነው ባይ ነኝ። ከውጪ ባንኮች ሲመጡ እኮ በገንዘብም በካፒታልም ካለነው ባንኮች በእጥፍ ይዘው ነው የሚመጡት። ስለዚህ ለአዲሶቹም ሆነ ለነባሮች የተሰጠው የጊዜ ገደብ ከበቂ በላይ መሆኑ መታወቅ ይገባዋል።
የባንክ ገቢ አንድ ሱቅ ከሚያኘው ገቢ በእጥፍ የተሻለ መሆን ይገባዋል። ከህዝብ የተሰበሰበውን ገንዘብ በአደራ አስቀምጦ ለተጠቃሚው በሚፈልገው በላይ ማበደር መቻል አለበት።

በአሁኑ ወቅት ካሉት 16 ባንኮች በተጨማሪ በርካታ ባንኮች ወደ ኢንዱስትሪው ይገባሉ፤ እነዚህ ባንኮች ወደ ሥራ ሲገቡም የአገሪቱ ባንኮች ቁጥር ወደ 30 እና ከዚያም በላይ እንደሚያድግ በማስታወስ፣ ለአገሪቱ ግን 30 እና 40 ባንክ አያስፈልጋትም ብለዋል።
አሁን ባለው የኢትዮጵያ ሁኔታ 5 እና 10 ባንኮች በቂ መሆናቸውን በመጥቀስም ጠንካራ ባንኮች ከተፈለጉ ጠንካራ ካፒታል የሚያሻ በመሆኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያም ይህንን ታሳቢ ያደረገ ነው ሲሉ አክለዋል።
ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አንድ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው የተከፈለ ካፒታል አሥር ሚሊዮን ብር ነው የሚል መመርያ አወጣ። የመጀመርያዎቹ የግል ባንኮችም በዚሁ ሁኔታ ተመሥርተው ወደ ሥራ ሊገቡ ችለዋል።

የባንክ ማቋቋሚያ ካፒታል መጠኑ 500 ሚሊዮን ብር እንዲሆን ከተወሰነ በኋላ፣ እስካሁን ድረስ አንድም አዲስ ባንክ ወደ ሥራ ያልገባ ሲሆን፣ በዚህን ያህል ካፒታል ባንክ ለማቋቋም መንቀሳቀስ የተጀመረው በቅርቡ ነው።፡ 100 ሚሊዮን ብር በሚጠየቅበት ወቅት ባንክ ለማቋቋም ላይ የነበሩ ባንኮች፣ የመመሥረቻ ካፒታል መጠኑ 500 ሚሊዮን ብር ሲሆንባቸው፣ 500 ሚሊዮን ብር መሙላት አንችልም ብለው የአክሲዮን ሽያጫቸውን አቋርጠው እንደነበር ይታወሳል።

በ500 ሚሊዮን ብር ካፒታል ባንክ ለመመሥረት እንደ አዲስ እንቅስቃሴ የተጀመረው ከሦስት ዓመት ወዲህ ነው ማለት ይቻላል። ይህም ከአሥር ዓመት በፊት 500 ሚሊዮን ብር ካፒታል አክሲዮን ሸጦ ማሟላት አንችልም ብለው ያቆሙና ሌሎችን ጨምሮ 500 ሚሊዮን ብር ማሟላት ይቻላል ያሉ ወደ ሃያ ባንኮች አክሲዮን ሸጠው ኢንዱስትሪውን ለመቀላቀል እየተንቀሳቀሱ ቢሆንም፣ አዲሱ የብሔራዊ ባንክ የባንክ ማቋቋሚያ ካፒታል ካሰቡት በላይ እንዲዘጋጁ ግድ ብሏቸዋል።

ኬንያ ካሉ ባንኮች እንወዳደር ቢባል ምን ያህል እንጓዛለን? የእኛ በጣም ትንንሾች ናቸው:: የሚሉት ደረጀ ለውጪው ውድድር መዘጋጀት አለብን ብለዋል። ይህ ብቻ አይደለም አገራችን ውስጥ ሁልጊዜ በውጪ ኢንቨስትመንት ተደግፈን መኖር እንደማይቻል በመረዳት፣ የራሳችን ጠንካራ ኢንቨስተሮች፣ ትልልቅ ገንዘብ የሚያበድሩ ተቋማት መፍጠር አለብን ብለዋል። በኢትዮጵያ አንድ የእርሻ ባንክ ያስፈልጋታል የሚሉት ደረጀ አንድ ኢንቨስትመንት ባንክም ሊኖራት ይገባልና እንዲህ ያሉ የባንክ ዓይነቶች ላይም ትኩረት ይሰጥ ብለዋል። ይህ ሁሉ የሚሆነው ግን ባንኮች ጠንካራ ካፒታል ሲኖራቸው ነው።

- ይከተሉን -Social Media

አሁን የሚወጡ መመርያዎችም ነገን ተሻግረው መመልከት ሲችሉ ነውና ብሔራዊ ባንክ የባንክ ማቋቋሚያ ካፒታል መጠን ማሻሻል አለበት። ይህንን ለማድረግ ራሱ ነባራዊ ሁኔታው ይገፋዋል። የገንዘብ የመግዛት አቅም እየቀነሰ ሲሄድ፣ ባንክም መመርያውን ሊያሻሽል ይችላል። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ባንክ ለማቋቋም አምስት ቢሊዮን ብር ያውም አምስትና ሰባት ዓመት ሰጥቶ አይሆንም። አምስት ቢሊዮን ብር ኢምንት ነው፤ መጨመር አለበት። ይህም ለባንኮችና ለአገር ጠቃሚ ነው። በተለይ እንደ አገር ጠንካራ ተወዳዳሪ ለመሆን የባንኮች ካፒታል መጠን ማደግ መሠረታዊ ነው።

አዲስ ማለዳ፡ የስቶክ ማርኬት መምጣት ባለአክሲዮኖች የማሸሽ ነገር እንዲፈጠር አያደርግም ወይ?
ደረጀ፡ በመጀመሪያ ደረጃ ኣዳዲስ ባንኮች ስቶክ ማርኬት ላይ ሊገቡ አይችሉም፤ መረጃውም የላቸውም። ስለዚህ ባለአክሲዮኖች ኢንቨሰት ለማድረግ መሄድ ይኖራል። ነገር ግን ኢንቨስት የሚደርጉት ንግዶች ላይ በመሆኑ መልሶ ኢኮኖሚውን ነው የሚጠቅመው ይላሉ ደረጀ።

አዲስ ማለዳ፡ ብሔራዊ ባንክ ብዙ ገንዘቦችን አትሜያለሁ ብሏል። የአገሪቱ ገንዘብ የመግዛት አቅም ያወረደው ይህ ይሆን?
ደረጀ፡ ብሔራዊ ባንክ ብዙ ገንዘብ አትሜያለሁ ሲል ኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ስርጭት ለማዳረስ የሚስችል አትሜያለሁ ነው ያለው እንጂ ከኢኮኖሚው በላይ አይደለም።
ገንዘቡ በሚቀየርበት ጊዜ ገንዘብ አድጓል፤ ስለዚህ የማበደር አቅም አድጓል። በፊት እጥረት የነበረበትን ቀርፏል። ገንዘብ ደግሞ በአገራችን በጥሬ መገበያየት ሰለተለመደ ብዙ ገንዘብ አለ። ለዚህም ነው የድጂታል ባንኪንግ አስፈላጊነቱ። መርካቶን የሚያክል ትልቅ የንግድ ገበያ እንኳን እስከአሁን በጥሬ ገንዘብ እየተገበበያዩ ነው። ይህ የተፈጠረው በተቋማት መካከል ግልጽ የሆነ አሰራር ባለመኖሩ ነው።

ነጋዴዎችን በተለያዩ ማበረታቻዎች ቴክሎጂዎችን እንዲጠቀሙ የማድረግ ኃላፊነት ያለባቸው የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በጋራ በመሆን ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ባንክን እና ባንክን የሚያስተሳስር ቴክኖሎጂዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። እነዚህ ሁሉንም ባንኮች የሚያስተሳስር ቴክኖሎጂዎች በነጋዴዎች በኩል ተደረሽ እንድንሆን ያስችላል።
የብር የመግዛት አቅም ዝቅ የሚለው ፍላጎት እና አቅርቦት አለመመጣጠን ነው። ስለዚህ አቅርቦት ካነሰ ገንዘብ የመግዛት አቅም አይኖረውም። የዶላር መጨመርም ቢሆን የኢኮኖሚው ነፀብራቅ ነው። ለዶላር ያለው ፍላጎት ከጨመረ አቅርቦት ደግሞ ከሌለ ዋጋ ይጨምራል።
የዘመን ባንክ 32 ፎቆች ያሉት አዲሱ ህንጻ በቻይና ዊ ተገንብቶ በጁድዋ አማካሪ ድርጅት ዲዛይኑ የተሰራ ሲሆን ከሶስት ወራት በኋላ ስራ እንደሚጀምር አዲስ ማለዳ ሰምታለች።


ቅጽ 3 ቁጥር 130 ሚያዚያ 23 2013

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች