መነሻ ገጽሐተታ ዘ ማለዳየመስቀል አደባባይ ውዝግብ

የመስቀል አደባባይ ውዝግብ

መስቀል አደባባይ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከራስ ብሩ ወልደገብርኤል ከተቀበለች በኋላ ሕጋዊ ካርታ እና የባለቤትነት ማረጋገጫ የላትም ሲሉ የሕግ እና የታሪክ ምሁሩ አለማው ክፍሌ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በጉዳዩ ላይ ሰፊ መረጃ የሠጡን ቢኑ አሊ እንደሚሉት ግብር የከፈልንበትን ቦታ የአንድ ኃይማኖትን ብቻ መሰረት በማድረግ ስያሜ መስጠቱ ትክክል አይደለም ብለዋል። በ1983 ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ጋር ተነጋግረው መስቀል አደባባይ ወደሚለው ወደቀደመ ስሙ እንዲመለስ እና የመስቀል በዓላትን እስከ አሁን ድረስ እንዲከበርበት ተደርጓል።
የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንም በዚህ መሰረት በቦታው በዓላትን እያካሄደች ትገኛለች። ነገር ግን ቤተ-ክሕነቱም ሆነ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሕጋዊ ባለቤትነት አልተሰጣትም። ይህንን ሰሞነኛ ጉዳይ በተመለከተ ሰላማዊት መንገሻ ተከታዩን ዘገባ አዘጋጅታለች።

ኢትዮጵያ ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ በጋራ የገነቧት እና የሚኖሩባት አገር መሆኗ፣ እንደ አዲስ የሚነገር ዜና ወይም ታሪክ አይደለም። በዚህ ዘመን እያስቸገረ ያለው አንድ ነገር ከሚያግባቡ ጉዳዮች ይልቅ የሚለያዩ ጉዳዮች ላይ ማተኮር በስፋት መለመዱ ነው። መንግሥት በቀላሉ ሊፈታው የሚችለውን ችግር ራሱ እያወሳሰበ ለንትርክ በር ይከፍታል። ኃላፊነት ይሰማቸዋል ተብለው የሚታሰቡ ወገኖችም ችግሮችን ያለዝባሉ ሲባል፣ እነሱ ራሳቸው ብሶባቸው አቧራ ያስነሳሉ።

የጎዳና ላይ ዒፍጣር እና የዒድ አደባባይ ጥያቄ መሰረታቸው ምንድን ነው?
የጎዳና ላይ ዒፍጣር ሙስሊሞች በመላው ዓለም የሚያካሂዱት ሲሆን፣ አንድነትን የሚያመላክት ተግባር ነው፤ ሲሉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ቢኑ አሊ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም ረጅም የጎዳና ላይ ዒፍጣር የተካሄደው በ 1.6 ኪ.ሜ. ሲሆን፣ በግብጽ ደግሞ ሰባት ሺ ሰዎችን የያዘ የዒፍጣር ፕሮግራም ሪከርድ መስበር ችሎ ነበር።
በአገራችን ደግሞ ወልዲያ፣ ደሴ፣ አጣዬ፣ ከሚሴ፣፣ ኮምቦልቻ፣ ጅማ እና ባህርዳር የተካሄደ ሲሆን፣ በመዲናዋ አዲስ አበባ ደግሞ ሰፊ እና ንጹህ ቦታ ተመርጦ ፕሮግራሙ ተካሂዷል።
ከመካሄዱ በፊት ግን በርካታ ቅሬታዎች ሲቀርቡበት ቆይቷል። ቅሬታውንም ፖሊስ ከግምት ውስጥ አስገብቶ ከብዙ ክርክርና ውይይት በኋላ ሊፈቀድ ችሏል።
ግንቦት 1 ቀን 2013. በመስቀል አደባባይ ሊደረግ ታቅዶ ሲያበቃ በፈቃድ አሰጣጥ ላይ በተነሳ ውዝግብ ሳቢያ በአግባቡ ያልተከወነው የረመዳን ወር የዒፍጣር መርሐ ግብር፣ ወደ ማክሰኞ ግንቦት 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ተዘዋውሮ ቀድሞ በታቀደለት ሥፍራ በድምቀት ተከናውኗል ሲል ቢኑ ገልጸዋል።

ሃላል ፕሮሞሽን ‹‹ታላቅ የጎዳና ላይ ኢፍጣር በኢትዮጵያ›› በሚል ስያሜ የጎዳና ላይ ዝግጅት ለማድረግ ከመንግሥት ፈቃድ አግኝቶ የተንቀሳቀሰ ቢሆንም፣ መንግሥት የዝግጅት ቦታውን ቀይሩ የሚል ማሳሰቢያ ማስተላለፉ በድርጅቱ ተቀባይነት አለማግኘቱን በመጥቀስ በተለዋጭነት የቀረበው ቦታ ላይ ዝግጅቱን ለማከናወን እንደማይችል አስታውቆ ነበር። በዚህም ሳቢያ ዝግጅቱን ለመሰረዝ እንደተገደደ ሃላል ፕሮሞሽን ያስታወቀ ቢሆንም፣ ሕዝበ ሙስሊሙ በተባለው ሰዓት ወደ መስቀል አደባባይ በመትመም፣ የኢፍጣር ሥርዓቱ መታገዱን የሚቃወሙና አድሏዊ ሥርዓት መኖሩን በማንሳት የሚወቅሱ መፈክሮችን ሲያሰማ ቆይቶ ወደ ቤቱ ተመልሷል።

መርሃ ግብሩን ለማድረግ እንደማይቻል በደብዳቤ ለሃላል ፕሮሞሽን ያስታወቀው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ፣ 10,000 ተሳታፊዎች ይገኙበታል ተብሎ ለታሰበው መርሃ ግብር ጥበቃ ማድረግ እንደማይቻልና የከተማው ፖሊስና የጸጥታ ኃይል ተደራራቢ ፕሮግራም ያለበት መሆኑን በምክንያትነት አንስቷል። ነገር ግን ቁጥሩ ወደ 5,000 ቀንሶ እንዲካሄድ ሲል በድጋሚ ፈቃድ ሰጥቷል።

ይህንን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በበኩሏ የዒፍጣር መርሃ ግብሩ የሚካሄድበት አደባባይ የመስቀል ደመራ የሚከናወንበት በመሆኑ፣ ግጭት ይፈጥራል የሚል ሥጋት ያዘለ ደብዳቤ ለፀጥታ ቢሮ በማስገባት ተለዋጭ ስፍራ ለፕሮግራሙ እንዲሰጥ ጥያቄ አቅርባ ነበር። ይሁንና ይህ ጥያቄ በሕዝበ ሙስሊሙና በክርስቲያኑ ዘንድ ቅሬታ አስነስቷል። አደባባዩ ከሙዚቃ ድግስ እስከ ስፖርታዊ ዝግጅቶችና የፖለቲካ ቅስቀሳዎች የሚከናወኑበት፣ በዓመት ውስጥ ጥቂት መርሃ ግብሮችን ካስተናገደ በኋላ ክፍቱን የሚቆይ ሆኖ ሳለ፣ እንዲህ ያለው ክልከላ አግባብ የለውም በማለት በጋራ ተቃውመውታል። ለሌሎች ዝግጅቶች ሲሆን የሚፈቀድና ዒፍጣር የሚከለከልበትም አግባብ አግላይነት ያለበት ነው ሲሉም፣ በርካቶች በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ድምፃቸውን ሲያሰሙ ነበር።
ለአብነትም የእስልምና ንቁ አቀንቃኝና የመብት ተሟጋች አህመዲን ጄበል በፌስቡክ ገጻቸው እንዳሰፈሩት፣ ‹‹ጉዳዩ የኢፍጣር ሳይሆን በእኩል የመታየት ጉዳይ ነው›› ያሉ ሲሆን፣ እንደ ኹለተኛ ዜጋ መታየት ይብቃ ብለዋል።

እነዚህን ተቃውሞዎች ተከትሎ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተቃውሞውና ዝግጅቱ ሰላማዊ እንዲሆን ያደረጉትን በማመሥገን፣ ‹‹በከተማችን አዲስ አበባ ብዙ ቁጥር ያለውን የሙስሊም ማኅበረሰብና ሌሎችን ያሳተፈ የጎዳና ላይ ዒፍጣር ለማካሄድ የተዘጋጀው ዕቅድ፣ በአዘጋጁት አካላትና ግለሰቦች እንድናውቀው ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ ፕሮግራሙ በተሳካና የዓለም ሪከርድ በሚሰብር ሁኔታ እንዲፈጸም ከፍተኛ ጥረት ስናደርግ ቆይተናል። ከአዘጋጆቹ ጋር በተደጋጋሚ እየተገናኘን ለፕሮግራሙ ውጤታማነት በሙሉ ልባችን ስንሠራ ቆይተናል። ለስኬቱም እስከ መጨረሻዋ ድረስ በሙሉ አቅማችን ሠርተናል። ይህን ትልቅ ኃይማኖታዊ ሥርዓት ለአብሮነትና ለአገር አንድነት ለማዋል የተሠራው ሥራ የሐሳቡን አመንጪዎችና አዘጋጆቹን የሚያስመሠግን ታላቅ ተግባር መሆኑን እናምናለን። በእርግጥም ዛሬም በከተማዋ የተለያዩ ጎዳናዎች ላይ የዒፍጣር ፕሮግራሞች ተካሂደዋል፤›› በማለት ገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም አደባባዩ የእኛና የእናንተ መባል እንደማይኖርበትና በጋራ ጥቅም ላይ ሊውል የሚገባው እንደሆነ፣ የከተማ አስተዳደሩ በመግለጫው አትቷል።
እንደ ቢኑ ገለጻ ከሆነ የመስቀል አደባባይ ጥያቄ መነሳቱ ተገቢ ነው። ይህም ሲባል አገሪቷ ላይ ያለው መንገድ የጋራ ነው። ቢኑ እንደምሳሌ ካነሳቸው ጉዳዮች መካከል የአቢሲኒያ ባንክ ሊመሰረት ሲል የገንዘብ እጥረት መንግስት ገጥሞት ነበር። በዚህ ወቅት ባንኩን ለማቋቋም የሚያስፈልግ ገንዘብ የጠየቁት ከሼህ ሆጀሌ ነበር። ባንኩ ሙሉ የኢትዮጵያን ሕዝብ እየጠቀመ ነው እንጂ በሙስሊም ገንዘብ ሰለተቋቋመ የሙስሊሙን ማህበረሰብ ብቻ አላገለገለም። ይህ አንዱ የጋራ አገር እንዳለን የሚያሳይ ተግባር ነው ብለዋል።
በመሆኑም አደባባዩም ቢሆን ሁሉም የኃይማኖት ክፍል ግብር ይከፍልበታል። ስለዚህ በየዓመቱ ለማስፈጠር በአብዮት አደባባይ ዒፍጣር ማድረግ ሌላውን ኃይማኖት አይነካም ብለዋል።

በሁሉም ኃይማኖት ሙዚቃ የተከለከለ ነው። ሙዚቃ ሲካሄድበት ጥያቄ ሳይቀርብ ሙስሊሙ ጥያቄ ሲያቀርብ ይህን ያህል ውዝግብ መፈጠር አልነበረበትም ብለዋል። እንደውም ግብር የከፈልንበት ቦታ አንድን ኃይማኖት ብቻ መሰረት በማድረግ ስያሜ መስጠቱ ትክክል አይደለም ሲል ቢኑ አንስቷል።

በተጨማሪም በማኀበራዊ ድረ-ገጽ ሲሰራጭ የቆየው ኢድ አደባባይ ብሎ መፈክር የታየው የዛሬ አራት ዓመት የተነሳ ፎቶ ሲሆን አሁን ላይ ሽብር ለመፍጠር የሚቀባበሉት ጉዳይ መሆኑን ልንረዳ ይገባል ብለዋል።

የመስቀል አደባባይ ጉዳይ ከታሪክ አንጻር ያለው አንድምታ
የመስቀል አደባባይ ጉዳይ ከታሪክ እና ከሕግ አንጻር እንዴት እንደሆነ አዲስ ማለዳ የሕግ እና የታሪክ መምህር የሆኑትን አለማው ክፍሌ (ዶ/ር) አነጋግራለች። እንደ አለማው ገለጻ የኢድ አደባባይ ይኑረን ማለት እና ይህ አደባባይ የኢድ ይሁን ማለት የተለያየ ጥያቄ ነው ብለዋል።

የእስልምና ኃይማኖት እምነቱ ሊከበርለት ይገባል። አገር ውስጥ የሚኖረው በኃይማኖቱ ሲከበር ነው። ኢትዮጵያውያን ኃይማኖታችን ይለያይ እንጅ ወንድማማቾች ነን። ጥያቄዎች ሲቀርቡ በሰላም ነው የምንፈታው እንጅ በጦርነት መሆን የለበትም ይላሉ።
ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች እና የበርካታ ኃይማኖት ማንነቶች አገር መሆኗ ይታወቃል። እንደዚህ አይነት ከባድ የሆኑ ኃይማኖታዊ ጉዳዮች ሲነሱ ጥያቄዎችን በማደራጀት ለሚመለከተው አካል በማቅረብ ማስመለስ ይገባል እንጅ የሰው ቦታ ላይ ዘው ተብሎ አይገባም።

ጥያቄዎችን ለመጠየቅ የከተማዋን ማስተር ፕላን ሕግ እና ደንብ መሰረት በማድረግ ማንሳት ይቻላል። ኃይማኖትን መልክ በመያዝ ከውጪም ሆነ በውስጥ ላሉ አገር አፍራሽ ሀይሎች እድል መስጠት ተገቢ አይደለም። ከውጪ ድጋፍ የሚደረግላቸው አካላት ኃይማኖትን መሰረት አድርገው አገርን ማበጣበጥ አጀንዳቸው መሆኑን ማወቅ ይገባናል ብለዋል።

በአገራችን ቤተክርስቲያናት እና መስጂዶች ተቃጥለው ያውቃሉ። ሕብረተሰቡ የሚያመልክበት ስፍራ በሽብር ማቃጠል ተገቢነት የሌለው ተግባር መሆኑም ይታወቃል። ለምሳሌ ሞጣ መስጅድ መቃጠሉ አንድ የማምለኪያ ቦታ ማጣትን ያመላክታል። ነገር ግን ጉዳዩን ወደ ሽብር ተግባር ለመለወጥ ሲያጋንኑ የነበሩ አካላት ነበሩ። አሁን ደግሞ ኃይማኖታዊ እና በጣም ወሳኝ የሚባል ጉዳይ የኢድ-አደባባይ ጥያቄ ይዘው የሚያጋንኑ ፖለቲከኛ ጥቅመኞች መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል ብለዋል።
የታሪክ ምሁሩ አለማው ለአዲስ ማለዳ እንዳስረዱት ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የመስቀል በዓል ሲከበር የቆየው እስከ 1879 ድረስ እንጦጦ በሚገኘው በማርያም እና ራጉኤል ቤተክርስቲያናት ንጉሱ ምኒልክ እና ንግስቲቱ ባሉበት ነበር።

ከ1879 እስከ 1922 ድረስ ደግሞ አዲሱ ቤተመንግሥት አካባቢ ግቢ ገብርኤል እና ባታ ማርያም ቤተክርስቲያን ሲካሄድ ቆይቶ ነበር። ከዛ ደግሞ ከ1922 እስከ 1927 በጣሊያን ወረራ ዘመን የደመራ በዓል ተቋርጦ የነበረ ሲሆን፣ ንጉሠ ነገሥት አጼ ኃይለሥላሴ ከመጡ በኋላ ከ1933 እስከ 1966 ድረስ ከግዞት የተመለሰው የንጉሱ አስተዳደር ወደ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን እንዲዘዋወር አድርገው ያከብሩት ነበር።

ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ እስጢፋኖስ አካባቢ የመዘጋጃ ቤት በመኖሩ ምክንያት አሁን ወደሚከበርበት ቦታ ንጉሱ በካህናት ታጅበው እየተዘመረ ወደ መስቀል አደባባዩ በመሄድ መከበር መጀመሩ ይነገራል። ደርግ ከመጣ በኋላ ደግሞ በ1966 መስቀል የሚባል ነገር በመንግስት ደረጃ አይከበርም። ሶሻሊስት አስተሳሰብ ስለነበረው ምንም አይነት ሀይማኖታዊ ጉዳዮች ውስጥ አይገባም ነበር።

- ይከተሉን -Social Media

አሁን ያለንበት ደግሞ ከ1983 እስከ አሁን ድረስ ብጹዕ አቡነ ጳውሎስ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ጋር ተነጋግረው መስቀል አደባባይ ወደሚለው ወደቀደመ ስሙ እንዲመለስ እና የመስቀል በዓላትን እንዲከበርበት ተደርጓል። የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንም በዚህ መሰረት በዓላቶቿን እያካሄደች ትገኛለች። ነገር ግን ቦታው ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አልተሰጠም። ህጋዊ ካርታ እና የባለቤትነት ማረጋገጫ የላትም ሲሉ ባለሙያው ይገልጻሉ።

ይህ የሕዝብ አደባባይ ነው። ካርታ እና ማረጋገጫ በሌለበት ሁኔታ ሕጋዊነትን ማረጋገጥ አይቻልም። ነገር ግን ስሙ እውቅና ተሰጥቶት የመስቀል በአልን እንዲያከብሩ ተደርጓል ሲሉ አንስተዋል። መስቀል አደባባይ የራስ ብሩ ወልደገብርኤል ነው። ይህን ቦታ ደግሞ ለቤተክርስቲያን በስጦታ ሰጥተዋል። ነገር ግን ቤተክህነት ትልቅ ተቋም ሆኖ ሳለ ከግለሰብ የወሰደውን ይዞታ በሕጉ መሰረት አስፈጽሞ የግል ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ማውጣት ይጠበቅበታል። ይህ የይዞታ ማረጋገጫ ባላለቀበት እና የውርስ መብታቸውን ባላስከበሩበት ሁኔታ ለመከራከር እና የቤተክህነቱ ስለመሆኑ የሚያረጋግጡበት መንገድ አይኖርም ብለዋል።

ራስ ብሩ ከሞቱ ከ90 ዓመት በላይ ሆኗቸዋል። በዚህ ሁሉ ጊዜ ውስጥ የካርታ ፕላን በመውሰድ ባለቤትነታቸውን ማረጋገጥ ይገባቸው ነበር። ምናልባት ስጦታውን ሕጋዊ ማድረግ ያልተቻለው በውስጥ አሰራር የተፈጠረ ክፍተት ቢሆንም ቤተክርስቲያኗን የሚያጭበረብሩ አካላትን በማለፍ ባለቤትነትን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።

በአደባባዩ የድጋፍ ሰልፎች፣ የተቃውሞ ሰልፎች፣ የሙዚቃ ኮንሰርት፣ የስፖርት ፕሮግራሞች ተዘጋጅቶበት ያውቃል። ይህ ሁሉ ተግባር የሚከናወንበት አደባባይ የዒፍጣር ፕሮግራም እንዲያካሂዱ ጥበቃ እንዲደረግላቸው መጠየቃቸው አግባብ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በአገራችን በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ግጭቶች ታሳቢ በማድረግ ያልተፈቀደ ፕሮግራም የሚያካሂዱ ከሆነ ያልተጠበቀ ችግር ውስጥ እንደሚገባ ስለሚታወቅ የፖሊስ ጥበቃ እንዲደረግ ጠይቀው ነበር። በተጨማሪም የኮቪድ ወቅት እንደመሆኑ መጠን በጥንቃቄ ለመከወን የጠየቁት አግባብ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ይሁን እንጅ ኃይማኖትን መሰረት በማድረግ ወደ ፖለቲካ ለመቀየር እና አገር ለማፍረስ እና የውጭ ተልዕኮ ለማፈጸም የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ኢድ አደባባይ ይሁን በማለት የሰው ቦታ ለመውሰድ የሚጥሩ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።
እስከዛሬ ድረስ እነዚህ አገር አፍራሽ አካላት ብሔርን መሰረት በማድረግ ለብዙ ንጹሃን ዜጎች መጎዳት ተጠያቂ ሆነው የቆዩ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ኃይማኖትን መሰረት ያደረገ ጉዳይ በማንሳት እርስ በእርስ ለማጋጨት የታሰበ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል ብለዋል።
በአንድ ጀምበር ተነስተው ኢድ አደባባይ ሆኖ ይሰየምልኝ የሚሉት አገር ለማፍረስ የሚያሰቡ መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል።

እስልምና ኃይማኖትን ከሌሎች የአረብ አገራት ቀድማ እውቅና በመስጠት ኢትዮጵያ የመጀመሪያ መሆኗ ሊታወቅ ይገባል። ኢትዮጵያ ውስጥ እስልምናም ሆነ ክርስትና ኃይማኖቶች ቀደምት ታሪክ ያላቸው መሆኑ ግልጽ ነው።
ማንኛውም የአገሪቷ አንገብጋቢ ጉዳዮች ሲፈጠሩ ጥያቄ በተገቢው መንገድ መጠየቅ ይገባል። የሚመልሰው አካልም ቢሆን ሕግን እና መመሪያን በሚያከብር መንገድ ማስኬድ ይጠበቅበታል።

መፍትሄው ምንድነው?
ይህንን ጉዳይ የእስልምና ኃይማኖት ውስጥ ያሉ ትልልቅ አባቶች፣ የመጅሊሱ ምክርቤት እና የሚመለከታቸው አካላት ለተራ ፖለቲከኞች መተውና በር መክፈት የለባቸውም ብለዋል። ለእሬቻ በአል ተሰጥቶ ለኢድ ለማክበሪያ ለምን አይሰጥም የሚለውን ጥያቄ በሕጋዊ መንገድ ማስኬድ እንደሚገባቸው ተጠቁሟል። ሕጋዊ ሆኖ ሌሎች ቦታዎች መጠየቅ እንጅ ቦታውን ለመንጠቅ መሯሯጥ ተገቢ አይደለም ተብሏል። የፌደራል እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት፣ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያናት እና መዘጋጃቤት በጋራ በመሆን ጥያቄውን ከሕግ አንጻር መመለስ ይኖርባቸዋልም ተብሏል።

እንደመፍትሄ ከተነሱት ጉዳዮች መካከል ጉዳዩ በጣም ትልቅ ቦታ ሳንሰጠው አለሳልሰን ማለፍ ይገባናል ሲሉ የገለጹት መጋቢ ሀዲስ እሸቱ ናቸው። ይህ ጉዳይ ‹‹አይኗን እያወጧት ቅንድቤን አደራ›› እንደ ማለት ነው የሚሉት መጋቢ ሀዲስ፣ አገሪቷ ለራሷ በጣም ትልልቅ ጥያቄ ውስጥ ገብታ ሳለ አንድ ጉዳይ እየመዘዙ ነገሮችን ማጋነን ተገቢ አይደለም ብለዋል። እንደውም እንደነዚህ ያሉ ትንንሽ ጉዳዮችን አዳክሞ መተው አስፈላጊ ነው። ሁሉም ኃይማኖት በጋራ ተወያይቶ እንዴት እንገልገልበት፣ የአንዱ አገልግሎት ሳይቋረጥ ተግባብተን ማካሄድ እንጅ ከጀርባ ትርፍ ለሚፈልጉ አካላት በር መክፈት አይገባንም ሲሉ መጋቢ ሀዲስ ይገልጻሉ።


ቅጽ 3 ቁጥር 132 ግንቦት 7 2013

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች