የእለት ዜና

ዩኒቨርስቲ ስትገቢ…

Views: 469

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ሰሞኑን በርካታ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት /ዩኒቨርስቲዎች/ አዳዲስ እና ነባር ተማሪዎቻቸውን እየጠሩ ነው። ማንኛውም የሕይወት ምዕራፍ ጅማሬ በአዲስ መልክ ሲገለጥ እንግዳና አዲስ መሆን የተለመደ ነው። በዩኒቨርስቲም ከኹለተኛ ዓመትና ከዛ በላይ የሆኑ ተማሪዎች አዳዲሶቹን ‹‹ፍሬሽ›› እያሉ የሚጠሩት ራሳቸውም ያለፉበትን ጎዳና ስለሚያወቁ ነው። በሌላ አነጋገር እናቶቻችን ‹‹አልችልም!›› የሚል ሰው ሲገጥማቸው ‹‹ማንም ከእናቱ ሆድ አልተማረም›› እንደሚሉት ነው፤ ሁሉም በሒደት ይለመዳል።

ታድያ ምንም እንኳን የምናውቀውና በይፋ የተነገረ ጥናት ባይኖርም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ስናተኩር፣ የሴቶች ቁጥር ይቀንሳል። በተለይም ከአንደኛ እና ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ካለው የሴቶች ብዛት አንጻር በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ ሴቶች ጥቂት ሊባሉ የሚችሉ ናቸው። ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ዩኒቨርስቲ መግባት አብሮ የሚያመጣውን ፈተና የሚነግራቸው ስለመኖሩ ግን እጠራጠራለሁ።

እርግጥ ነው ማንም ሰው በእናቱ ሆድ የተማረ አይደለም፤ በሕይወት ሒደት ነው ያወቀው የተማረው። ነገር ግን ደግሞ ሁሉም ሰው ማስተማሪያ ፊደል መሆን የለበትም፤ በአንዱ አካሔድ ሌላው ሊማር ይገባል።

ልክ እንደዚሁ ሁሉ እህቶቻችን ወደ ዩኒቨርስቲ እንግዳ ሆነው ሲገቡ ያለውንና ሊገጥማቸው የሚችለው ከመሳዮቻቸው ሊነገራቸው ይገባል። ወጣትነትና የነጻነት እድሜ በመሆኑ ነገሮችን የሚያዩባቸው መንገዶች፣ ቅድሚያ መስጠት ስላሉባቸው ጉዳዮች፣ ማህበራዊ ግንኙነታቸው ምን መምሰል እንዳለበት፣ ከመምህራን የሚመጡ ጾታዊ ትንኮሳና ፈተናዎችን እንዴት መጋፈጥ እንደሚችሉ መንገዱን ማሳየት ይጠበቃል።

ቤተሰብ ከሁሉም ጠብቆና ከልሎ፤ እንዲሁም ከልክሎ ያሳደጋቸው ልጆች፤ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች፤ ዓለም በግላጭ የምታገኛቸው አንድም በእነዚህ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ነው። የሚገጥማቸው ፈተና በተባራሪ የሰሙት ሊሆን ይችላል እንጂ ቀርቦ የነገራቸው ከሌለ መዓት የወረደባቸው ያህል እንዲጨነቁ፣ እጅ እንዲሰጡና እንዲሸነፉ፣ እንዲሸሹም ያደርጋቸዋል።

ለምሳሌ በአሁኑ የትምህርት ስርዓትም መቀጠሉን ባላውቅም፤ የመጀመሪያ ዓመት ለተማሪዎች ከባዱ ጊዜ ነው። ታድያ ተማሪዎች ውጤታቸው ቀንሶ ‹ከተጫሩ› ወይም ደግሞው እንደማሩ ከተነገራቸው፣ ያንን እንዴት ማለፍ እንደሚቻልና በቀጣይ ዓመት ተዘጋጅቶ መቅረብ ስለሚቻልበት መንገድ የሚነግራቸው የለም። ይህም ባሉበት ከተማ ከቤተሰብ ተሸሽገው፣ አጉል ህይወት ውስጥ ገብተው ትምህርታቸውን ብቻ ሳይሆን ራሳቸውን እንዲያጡ ያደርጋል።

ብዙ ጊዜም በትምህርት ቤት ቆይታ ተማሪ መሆን ስላለበት ነው እንጂ ሊያጋጥመው ስለሚችለው ችግር አይነገረውም። ‹‹ፈተናውን እንደምንም እለፍ አለበለዚያ ሕይወትህ ይበላሻል፤ ለአገር ሸክም ለቤተሰብህም ማፈሪያ ትሆናለህ›› ነው እንጂ፤ ፈተናውን ባታልፍ፣ በመካከል ችግር ቢያጋጥምህ በዚህ መንገድ ልትወጣውና ልታሳልፈው ትችላለህ ተብሎ አይነገረውም። ቢያንስ እኔና እኩዮቼ በተማርንበት ጊዜ ይህ አይነገርም ነበር፤ ወይም እኔ አልሰማሁም።

ከዚህ ባለፈ ደግሞ አንድ ዓመት ያለፈ የዩኒቨርስቲ ቆይታ ያላቸው ተማሪዎች ለአዳዲሶቹ እነዚህን ነገሮች መንገር ይኖርባቸዋል። በራሳቸው ባይደርስ እንኳን ከጓደኞቻቸው ገጠመኝ በመነሳት ነው፤ አዳዲሶቹም እንደው ቢያንስ ከሰሙት ተነስተው በራሳቸው የሚበጀውን መንገድ ለመምረጥ ይችላሉ።

ይህ ደግሞ ሴቶች ላይ ይበረታል። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ ሴቶች ትምህርቱ ካለው ከሚጠበቅ ጫና ባሻገር በዙሪያቸውም የሚከቧቸው ፈተናዎች ይኖራል። ተማሪዎችም ብልጥና ብልህ መሆን ይጠበቅባቸዋል። እህቶቻችንም ዩኒቨርስቲ መግባታቸውን አረጋግጠው፣ አስፈላጊውን ቁሳቁስ ሸክፈው ወደየሚማሩበት ሲያቀኑ፣ አብረው ጥንካሬን እና ብልሃትን መያዝ መርሳት አይገባም። ብቻ በጠቅላላው ለሌላ መማሪያ ከመሆን በፊት ከሌሎች ተምሮ የተሻለ መንገድ የሚያወጣ ትውልድ ለማፍራት መነጋገር፣ መመካከር ይበጃል ለማለት ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 50 ጥቅምት 8 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com