ሥራ አጥነት እና ስርዓት አልበኝነት በዛሬይቱ ኢትዮጵያ

Views: 367

ሳምሶን ኃይሉ በኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ የተንሰራፋው በተለይ የወጣት ዜጎች ሥራ አጥነት በጊዜ መፍትሔ ካልተሰጠው ወደ ለየለት ስርዓት አልበኝነት በማደግ የአገሪቱን ሕልውና ከፍተኛ አደጋ ላይ ይጥላል በማለት የተለያዩ አገራት ተመክሮን በማካተት መከራከሪያ ሐሳባቸውን አቅርበዋል። ለሥራ አጥነት በምክንያትነት ከጠቀሷቸው ነጥቦች በተጨማሪም መፍትሔ ይሆናሉ ያሏቸውን ምክረ ሐሳብም አቅርበዋል።

 

ከአራት ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ በፖለቲካ አለመረጋጋትና ኹከት እየታመሰች ትገኛለች። በቅርቡ የዓለም የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን በመጡበት ጊዜ መቀዛቀዝ ቢያሳይም ቀስ በቀስ ስርዓት አልበኝነት በኢትዮጵያ ዳግም እየተንሰራፋ ይገኛል። በዚህም ምክንያት በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲሞቱ አይተናል፣ ወደ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ ሕዝቦች የተፈናቀሉበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፤ በቢሊዮኖች የሚገመት ንብረትም ወድሟል። በቅርብ ጊዜ እንኳን ከአዲስ አበባ ወደ ተለያዩ ክፍሎች የሚወስዱ ዋና መንገዶች በተደራጁ ወጣቶች ሲዘጉ አስተውለናል። የፌደራሉ መንግሥት መቀመጫ የሆነችውን አዲስ አበባን ጨምሮ ሌሎች የአገሪቱ ከተሞች ሰላምና ፀጥታ በተለይም ካለፈው ሳምንት ወዲህ አጠያያቂ እየሆነ መጥቷል።

በርካታ ምክንያቶች ለዚህ ኹከት፣ ብጥብጥ እና ስርዓት አልበኝነት እንደ መንስዔ ሊጠቀሱ ይችላሉ። ከመሰረተ ልማት፣ የትምህርት እና የጤና ሽፋን እጦት በተጨማሪ በከፍተኛ ደረጃ የተንሰራፋው የሙስና ችግር እንደ መንስዔዎች ሊጠቀሱ ቢችሉም እያሻቀበ የመጣው የሥራ አጥነት ችግር በተለይም የወጣት ሥራ አጥ ቁጥር ያለቅጥ መጨመር እንደ ዋነኛ ሰበብ ተጠቃሽ ነው።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከ10 ሚሊዮን በላይ ሥራ አጦች እንደሚገኙ ጥናቶች ይጠቁማሉ። ከጠቅላላው ሥራ አጦች ውስጥም ደግሞ ወደ 70 በመቶ የሚሆኑት ከ24 ዓመት ዕድሜ በታች የሆኑ ወጣቶች ናቸው። በተጨማሪም ኹለት ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሥራ አጦች በየዓመቱ ይፈጠራሉ። ይህን እውነታ ከግንዛቤ ውስጥ ስናስገባ የሥራ አጥነት ችግር ሥር የሰደደ መሆኑን ማየት አያዳግትም።

የሥራ አጥ ቁጥር በአንድ አገር ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ሊያሻቅብ ይችላል። ለምሳሌ እንደ በኢትዮጵያ ባሉ ገጠራማ አካባቢዎች ወጣቶች መሬት አግኝተው በግብርና ሥራ የመሰማራት ዕድል በጣም የጠበበ ነው። ስለሆነም ወጣቶች ሥራ አጥ ሆነው በቀያቸው መቀመጥ አልያም ወደ ከተማ ለሥራ ፍለጋ መሰደድ ዕጣ ፋንታቸው ይሆናል። በከተሞች አካባቢ ደግሞ በየዓመቱ በኢንዱስትሪና አገልግሎት ዘርፎች የሚፈጠረው የሥራ ዕድል ካለውና ለሥራ ዝግጁ ከሆነው የሰው ኀይል ጋር አልተጣጣመም።

በመሆኑም የተንሰራፋ የሥራ አጥነት ችግር የተለያዩ መዘዞችን ሊያስከትል ይችላል። የመጀመሪያው የሥራ አጥነት ችግር መዘዝ የአገርን የምጣኔ ሀብት ዕድገት መግታት ወይም መቀነስ ነው። በተጨማሪም የሥራ አጥነት ችግር ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ ዜጎች ቁጥር ከማናሩም በላይ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ከፍተኛ የሆነ የገቢ አለመጣጠን (Income Inequality) እንዲፈጠር ያደርጋል።

የሥራ አጥነት አሉታዊ ተጽዕኖ በዚህ ብቻ አያበቃም። ከላይ ከተጠቀሱት እክሎች በተጨማሪ የሥራ አጥነት ችግር የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ኹከትና ብጥብጥ ሊያስከትል ይችላል። የተለያዩ አገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየውም ያለ ሥራ የተቀመጡ ወጣቶች በቀላሉ ኹከትና አለመረጋጋት በሚናፍቁ ግለሰቦች፣ ፖለቲከኞች፣ ተቋማትና የፖለቲካ ፓሪቲዎች ሊሸነገሉ ይችላሉ። ለዚህ ነው “The Youth Bulge” ንድፈ ሐሳብ ያስተዋወቁት የፖለቲካ ሳይንስ ሊቆቹ ግሬ ፉለር እና ጃክ ጎልድስቶን በሥራ አጥነት ችግር እና በስርዓት አልበኝነት መካከል ጥብቅ የሆነ ትስስር አለ የሚሉት።

እንደ የፖለቲካ ሳይንስ ሊቆቹ አባባል በተለይም ወጣትና ወንድ የሆኑ ሥራ አጦች በበዙ ቁጥር በተደራጀ መልኩ የሚከናወንና በዋነኛነት በወጣት ሥራ አጦች የሚመራ ኹከት ይበዛል። ከሳህራ በታች ያሉ እንደ ናይጂሪያ፣ ዝምቧብዊ እና ደቡብ አፍሪካ አገራት ለዚህ እንደማሳያ ሊቀርቡ ይችላሉ። በተለይም የምርጫ ጊዜ በቀረበ ቁጥር በእነዚህ አገሮች ሥራ አጥ ወጣቶች ኹከትና ብጥብጥ ሲቀሰቅሱ በሰፊው ይስተዋላል።

በኢትዮጵያ ያለውም ተመሳሳይ ሁኔታ ነው። ባለፉት አራት ዓመታት ኢትዮጵያን እያናጋት ባለው ኹከትና ብጥብጥ ዋነኛ ተዋናዮች የሆኑት ወጣት ሥራ አጦች ናቸው። የሚቀጥለው አገር ዐቀፍ ምርጫ እየቀረበ መምቱን ከግምት ውስጥ ስናስገባም ለችግሩ መፍትሔ መሻት ለነገ የሚተው እንዳልሆነ መረዳት አያዳግትም።

መንግሥት የሥራ አጥነትን ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። በዋናነትም ራሱ በሚያስገነባቸው የመሰረተ ልማትና ኢንዱስትሪ ተኮር የሥራ ዕቅዶች አማካኝነት የሥራ ዕድል ለዜጎቹ በተለይም ለወጣቶች ለመፍጠር ሞክሯል። በአገር ውስጥ እየተገነቡትና በሒደት ላይ ያሉት መንገዶች፣ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪያል ፓርኮች የዚህ ውጥን አካል ናቸው። በተጨማሪም ወጣቶች የራሳቸውን የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በማደራጀትና የብድርና የሥራ ቦታ በማመቻቸት ችግሩን ለመቀነስ ተጥሯል። ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ውጥኖች በጣም ትንሽ ለውጥ ብቻ ነው ያመጡት።

ለዚህም ዋነኛ ምክንያት ውጤታማ ፖሊሲ አዘጋጅቶ ሥራ ላይ ማዋል ባለመቻሉ ነው። ውጤታማ ፖሊሲ ለማዘጋጀትና ሥራ ላይ ለማዋል ሥራ አጥነትን በመተንተን ሥራ አጦች እነማን እንደሆኑ፣ ምን ዓይነት ክህሎት እንዳላቸውና እንደሚያስፈልጋቸው በተጨማሪም የት ቦታ እንዳሉ በጥልቀት ማወቅ ይጠይቃል።
ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ ሥራ አጥነት የሚፈጠረው በጉልበት ገበያው (labor market) ያለው የሰው ኀይል መጠን ካለው የሥራ ዕድል በላይ ሲሆን ነው። ይህ በኢትዮጵያ ከሚታየው ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል። የሕዝብ ብዛት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ቢመጣም አገር ውስጥ የሚፈጠረው የሥራ ዕድል ግን በጣም አነስተኛ ነው። መፍትሔውም የግል ባለሀብቱን ሥራ የመፍጠር አቅም የተለያዩ ማበረታቻዎችን በመስጠት ማሳደግ ነው።

ውጤታማ ፖሊሲ ለማዘጋጀትና ሥራ ላይ ለማዋል ሥራ አጥነትን ከዚህ በበለጠ በጥልቀት መመርመር ያስፈልጋል። ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት ሥራ አጥነትን እንደሚከተለው ሊከፈል ይችላል። የመጀመሪያው የመቅጠር ፍላጎትና አቅም (Demand-Deficient Unemployment) ሲቀንስ የሚከሰት ነው። ይህም በዋናኝነት የአገርን የምጣኔ ሀብት ዕድገት ሲገታ ወይም ሲቀንስ የሚከሰት ነው። ይህንን ዓይነት ችግር ለመቅረፍ መንግሥት ምጣኔ ሀብቱን እንዲያንሰራራ በማድረግ የቀጣሪዎችን የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም ማሳደግ ይጠበቅበታል።

ኹለተኛው ደግሞ መዋቅራዊ የሆነ ሥራ አጥነትን (Structural Unemployment) የሚባለው ሲሆን ብቁ የሆነ የሠራተኛ እጥረት፣ በቀጣሪና ሠራተኛ መካከል በሚኖር የቦታ ልዩነት እንዲሁም በቴክኖሎጂ ለውጥ ምክንያት ይከሰታል። በኢትዮጵያ ይኼኛው ዓይነት ሥራ አጥነት ችግር በስፋት ይስተዋላል። ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከ100 ሺሕ በላይ ተማሪዎች በየዓመቱ ቢያስመርቁም አሰሪዎች ብቁ ሠራተኛ ለማግኘት ሲቸገሩ ይስተዋላል። ለዚህም ነው ብዙ የተመረቁ ሥራ አጥ ወጣቶች በከተሞች ላይ የሚታዩት።

ይህንን ችግር ለመቅረፍ መፍትሔው በጥናት ላይ የተመሰረተና ጥራት ያለው የትምህርት መዋቅር መዘርጋት ነው። ከቦታ ልዩነት ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን ሥራ አጥነት ችግርን ደግሞ ጠንካራና ዘመናዊ የሆነ የጉልበት ገበያ (efficient labor market) በመዘርጋት መቀነስ ይቻላል። ከአዳዲስ ቴክኖሎጂ ውጤቶች ጋር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ማስተዋወቅም መዋቅራዊ የሆነ ሥራ አጥነትን ለመቀነስ ይረዳል።

በገጠር አካባቢ የሚታየውን ሥራ አጥነትና በስፋት የሚስተዋለውን ወደ ከተማ ስደት ለመቅረፍ ለወጣቶች የእርሻ መሬትን በአዲስ መልክ ማከፋፈልና ከሚኖሩበት ቦታ ያልራቁ የጎጆ ኢንዱስትሪዎችን ብሎም የግብርና ውጤቶች ማቀነባበሪያዎችን በግል ባለሀብቱ እንዲከፈቱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው። ሌሎች የሥራ አጥነት ዓይነቶችንም በጥልቀት በማጥናት ለረጅም ጊዜ ሲንከባለል የመጣውንና የኢትዮጵያን ህልውና እየተፈታተነ ያለውን የሥራ አጥነትን ችግር በቶሎ መፍታት ያሻል ።
አለበለዚያ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች እየተስተዋሉ ያሉት በዋናነት ሥራ አጥ ወጣቶች የሚሳተፉባቸው ኹከቶች ከፍ ወዳሉ ብጥብጦች ብሎም ወደለየለት ስርዓት አልበኝነት በማደግ የአገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ እንደይጥል ያሰጋል።
ሳምሶን ኃይሉ የአዲስ ማለዳ ጋዜጣ እህት መጽሔት ‘ኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው’ ምክትል መራሔ አሰናጅ ሲሆኑ በኢሜል አድራሻቸው ebr.magazine1@gmail.com ማግኘት ይቻላል።

ቅጽ 1 ቁጥር 51 ጥቅምት 15 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com