ዳሰሳ ዘ ማለዳ ጥቅምት 21/2012

Views: 927

1-በአዲስ አበባ ከተማ በዘጠኝ ክፍለ ከተሞች በ69 ነጥብ 2 ሄክታር መሬት ከ20 ሺሕ 504 በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ጥቅምት 22/2012 እንደሚጀመር ተገለጸ።ለቤቶቹ ግንባታ ከ55 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት የተመደበ ሲሆን ወጪው በከተማ አስተዳደሩ እና በባንክ ብድር ይሸፈናል።በ20/80 እና በ40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም የሚገነቡ ሲሆኑ የቤቶቹን ግንባታ በኹለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ርብርብ እንደሚያደርግም ተገልጿል።(ዋልታ)
……………………………………………………………..
2-በአዳማ በተከሰተው ግጭት ምክንያት የተጠረጠሩ 98 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸዉን የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አምሳሉ አብዲሳ አስታወቁ።16 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፣ 157 ሰዎች ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ አንድ ቤት ሙሉ ለሙሉ ተቃጥሎ ወድሟል፣ አስር ቤቶች ፈራርሰዋል፣ 15 የፋብሪካ መኪናዎች ተቃጥለዋል፣ ኹለት ኮንቴነሮችም በተመሳሳይ ተቃጥለዋል፣ 34 የግል ቢሮዎችና ንብረቶቻቸው ተጎድተዋል፣ አንድ የብረሃን ባንክ ቅርንጫፍ መስኮቶች መሰባበራቸዉን ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)
……………………………………………………………..
3-ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፎች በጋራ ሊሰሩ እንደሆነ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር) አስታወቁ።ኢትዮጵያ በሆስፒታሎች እየዘረጋች ያለችው ዘመናዊ የሕክምና አስተዳደር ስርዓት በኤርትራ ሆስፒታሎችም ለመተግበር በሚቻልበት ሁኔታ፣በኢትዮጵያ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚሰሩ ኩባንያዎች በኤርትራም ለመስራት በሚችሉበት እንዲሁም በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችም ስልጠና እና የልምድ ልውጥ ማድረግ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ምክክር አድርገዋል።(አዲስ ማለዳ)
……………………………………………………………..
4-የኢትዮጵያ ምርት ገበያ 7 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው 131 ሺሕ ቶን ምርቶችን በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ማገበያየቱን አስታወቀ።አፈጻጸሙ የዕቅዱን በመጠን በ140 በመቶ እንዲሁም በዋጋ ደግሞ በ145 በመቶ ያሳካ ሲሆን ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በመጠን የ86 እንዲሁም በዋጋ የ70 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ገልጿል።(ፋና ብሮድካስቲንግ)
……………………………………………………………..
5-ኢንጂነር ማስተዋል ስዩም የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሆነዉ ተሾሙ።ምክር ቤቱ በተጨማሪም ተሾመ አግማስን በምክትል ከንቲባነት እንዲሁም ኹለት የካቢኔ አባላትን ደግሞ የገቢዎችና ሴቶች ሕጻናትና ወጣቶች መምሪያ ኃላፊዎች በማድረግ ሹመታቸውን አጽድቋል።ምክር ቤቱ ሹመቱን ያጸደቀው 4ኛ ዙር 7ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት ነው።(አብመድ)
……………………………………………………………..
6-የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በረከት ስምዖንና ታደሰ ካሳን የመከላከያ ማስረጃ ለመስማት ለህዳር 24/2012 ቀጠሮ ሰጠ።ፍርድ ቤቱ መስከረም 30/2012 በዋለው ችሎት ዐቃቤ ሕግ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት አላቸው ብሎ ያሰባቸውን ባለ 141 ገፅ ተጨማሪ የሰነድ ማስረጃዎች መርምሮ ብይን ለመስጠት ለዛሬ ጥቅምት 21/2012 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ይታወሳል።በዚህም ፍርድ ቤቱ በዛሬው ዕለት በዋለው ችሎት ተጨማሪ 141 ገፅ እና ከዚህ በፊት የተመለከተውን 666 ገፅ የሰነድ ማስረጃ መርምሮ ብይን ሰጥቷል።(ፋና ብሮድካስቲንግ)
……………………………………………………………..
7-በየመን ሰንዓ ‹ጂዋዛት› በሚባል የኢሜግሬሽን ማቆያ ጣቢያ ከ650 በላይ ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙ ታዉቋል። ስደተኞቹ ከአንድ እስከ ሦስት ዓመት በየመን በተለያዩ አካባቢዎች በእስር ቤት የቆዩ ሲሆን ነገር ግን ተከታትሎ የሚያስፈታቸውም ሆነ የሚጠይቃቸው አካል እንዳልነበር ገልጸዋል።ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ በሕገ ወጥ መንገድ ሲጓዙ የመን ላይ በሁቲ አማጽያን በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ያስታወሱት ኢትዮጵያውያኑ ‹ሳዓዳ› የሚባል ቦታ በእስር አቆይተዋቸው እንደነበርና ‹‹ወደ ሀገራችሁ ትመለሳለችሁ›› በሚል ወደ ሰንዓ መወሰዳቸውን ተናግረዋል።(አብመድ)
……………………………………………………………..
8-አገር አቀፍ የወንጀል መከላከል ስትራቴጂ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩን የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሕግ ጥናት ማርቀቅና ማስረፅ ዳይሬክተር የሆኑት በላይሁን ይርጋ አስታወቁ።ሁሉንም የወንጀል አይነቶች ለመቀነስ ያስችላል ተብሎ የተዘጋጀዉ የስትራቴጂው ዝርዝር አላማዎችም ለወንጀል ድርጊቶች መፈጸም ምቹ የሆኑ ሁኔታዎችን በማስወገድ እና የወንጀል መከላከል ስራን ሊያግዙ የሚችሉ አሰራሮችን በመዘርጋት የወንጀል መከላከል ስራ ማከናወን፤ ለኅብረተሰቡ ዋና ስጋት የሆኑ፣ ልዩ ትኩረት የሚሹና ተጽዕኖ የሚፈጥሩ የወንጀል ድርጊቶችን አይነትና መንስኤዎቻቸውን በመለየት ድርጊቶቹን ለመከላከል የሚያስችል እንደሆነ ገልጸዋል።(ኢቢሲ)

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com