የብሮድካስት ባለስልጣን በወራት ውስጥ እንደ አዲስ ሊደራጅ ነው

Views: 291

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ከሁለት ወር ባነሰ ግዜ ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን በሚል ስያሜ እንደ አዲስ የሚያደረጀው አዋጅ ረቂቅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበ ሲሆን ይህን ተከትሎ ባለስልጣኑ አዲስ ከሚቀበለው ተልዕኮና ሃላፊነት አንጻር አዲስ አደረጃጀት የመዘርጋት ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጻል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የራዲዮ እና ቴሌቪዥን ማሰራጫ ተቋማትን ይዘት ከመቆጣጠር ባለፈ የዲጂታል መገናኛ ብዙሃንን እንዲቆጣጠር የሚዲያ ህጎችን የሰበሰበው ረቂቅ አዋጅ እንደ አዲስ የሚያዋቅረው ሲሆን አዋጁ በቅርብ ግዜ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ ይጠበቃል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የደረሰው ይህ ህግ መንግስት ቅድሚያ ከሚሰጣቸው እና በመሻሻል ላይ ካሉ አዋጆች መካከል መሆኑ ተገልጿል። በአዋጁ ላይ መጨመርና መቀነስ ያለበትን ጉዳይ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እንዲሁም ሃላፊዎች ሃሳብ የሰጡበት ሲሆን ጠቅላይ አቃቤ ህግ ያቋቋመው የህግ አማካሪ ጉባኤ እና የህግ ማርቀቅ ስራ ክፍል ከብሮድካስት ባለስልጣን በጋራ ህጉ የተሻለ የመገናኛ ብዙሃን ከባቢ እንዲኖር እንዲያስችል ተደርጎ መሰራቱን ባለስልጣኑ ተናግሯል።

ለዚህም በቴክኖሎጂ ተቋሙን ለማደራጀት ጥረቶች እየተደረጉ ሲሆነ በሰው ሃይል ረገድ ተጨማሪ ባለሙያዎችን ለመቅጠር እየሰራ እንደሚገኝ የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ወንዶሰን አንዱአለም ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል። የብሮድካስት ባለስልጣን የሚፈልጋቸውን ባለሙያዎች ከመገናኛ ብዙሃኑ ገበያ እየተሸማ የሚቀጥር ተቋም በመሆኑ የተሻለ ጥቅማ ጥቅም እንዲኖሩት ከቦርድ ጋር በጋራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም የነበረውን አይነት የመቆጣጠር ስልት ይዞ የመቀጠል ፍላጎት እንደሌለው የገለጸው ባለስልጣኑ ከሚዲያዎች ጋር የአባራሪና የተባራሪ ሩጫ ውስጥ መግባባት አይፈልግም ብለዋል ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ። ነገር ግን ባለስልጣኑ መገናኛ ብዙሃኑን ከደገፈ በኋላ አጥፍተው ከተገኙ ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል።

መገናኛ ብዙሃን በነጻነት የሚሰሩበትን መንገድ ማመቻቸት፤ በቴክኖሎጂ የተደገፈ መቆጣጠር አቅምን በቋሚነት መዘርጋት ማሰቡን እና ይህንንም ለመገናኛ ብዙሃን በማሳወቅ በህግ አካሄድ በመከተል አጋጭ የሆኑ ሃሳቦች በሚያሰራጩ መገናኛ ብዙሃን አሰራሮችን ለመዋጋት ብሮድካስት ባለስልጣን ፍላጎቱም አቅሙም እንዳለው አስረድተዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ የፖለቲካ ትኩሳት በመገናኛ ብዙሃኑ ላይ ነጸብራቅ የሚታይ ነው ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ ፣ ከዲሞክራሲ፤ ፖለቲካ ልምምድ ጋር አብሮ ብለው እንደሚያስቡ ለአዲስ ማለዳ ነግረዋል።

በህጉ ረቂቅ ላይ የተሳተፉት እና የሚዲያ የህግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ሰለሞን ጎሹ በበኩላቸው ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት አዋጁ በዚህ መልኩ መዋቀሩ የተቋማትን ነጻነት የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈ ሙያን የሚያበረታታ ፤ ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ የሚያደርግ እንዲሁም የብሮካስት ባለስልጣንን ውሳኔዎች በህግ ፊት ይግባኝ እንዲባልባቸው የፈቀደ ረቂቅ መሆኑን ጠቅሰው ምክርቤቱም ያፀድቀዋል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

ይሁንና ባለስልጣኑ በቀጣይም የህትመት ሚዲያውን ይዘት የሚቆጣጠርበት ስልጣን እንደማይኖረው አዋጁ መደንገጉን ተናግረው በቀጣይ ሶስት አመታት የህትመት መገናኛ ብዙሃኑን ራሳቸውን የሚቆጣጠሩበት መንገድ አዳብረው ራሳቸውን የሚቆጣጠሩበት አሰራር እንደሚዘረጋም ተናግረዋል፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 52 ጥቅምት 22 2012

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com