ቦጋለች ገብሬ (ዶክተር) ስናስታውስ

Views: 458

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

አንድ ሰው ብቻውን ምን ያህል ለውጥ ማምጣት እንደሚችል በተለያዩ የሕይወት አጋጣዎች እንዲሁም የአገር ጉዳዮች አይተናል። አንድ ሆነው ሳለ የሚቻል የማይመስል ሥራን ሠርተው ያሳዩ ሰዎችም ‹‹ብቻዬን ምን አቅም አለኝ!›› ለምንል ሰነፍ ሰዎች ጥሩ የህሊና አርጩሜ አቀብለው ነግረውናል። ከእነዚህ ሰዎች መካከል የብዙዎች እናት የሆኑት ቦጋለች ገብሬ አንዷ ናቸው።

በተወለዱበት ከንባታ ውስጥ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ተጽእኖዎችን ተመልክተው ዝም ያላሉ ሴት ናቸው። በተለይም በተቋማቸው ኬ ኤም ጂ በኩል የሴት ልጅ ግርዛትን በመከላከል የሠሩት ሥራ የበርካታ ሴቶችን ሕይወት ከህመም የታደገ ነው። ለዛም ነው በከንባታ ያሉ ሴቶች አመስግነዋቸው የማይጠግቡት።

ቦጋለች በከንባታ የሴት ልጅ ግርዛትን ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ማስቀረት ችለዋል። ለሴቶች ጠበቃና ተቆርቋሪ ናቸው፤ አይሰለቹም። ለተፈጥሮ ስሱ ናቸው፤ በከንባታ የሚገኘው ማረፊያ ቤታቸውን ልምላሜና ማማር ያየ ይህን ይመሰክራል።

በየዓመቱ ታድያ ‹‹እናቴ›› ብለው ከሚጠሯቸው የከንባታ ወጣት ሴቶችና እናቶች ጋር ቀጠሮ አላቸው፤ ዓመታዊ መገናኛ መድረክ ያዘጋጃሉ። ይህ አንድም ሴቶቹ የእጅ ጥበብና ሙያቸውን ለእይታ የሚያቀርቡበት፣ ሙያቸውን ወደ ሥራ እንዲቀይሩ ለማድረግ ማበረታቻ መድረክ ነው። በተረፈ ሴቶች ሰብሰብ ብለው የራሳቸው ችግር ላይ ተወያይተው መፍትሔ መውለድ እንደሚችሉ ያዩበታል፤ በመድረኩ።

የሚገርመው ቦጋለች ገብሬ ‹‹የተነሳሁለት የሴት ልጅ ግርዛትን የመከልከል ሥራ ስለተሳካ ይበቃኛል›› አላሉም፤ የሴት ልጅ ጥቃትን ደግሞ አነሱ። ለሴቶች የሕክምና አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ የሚችሉትን ሁሉ አደረጉ። በኹለት ዓመት በፊት ገደማ በከንባታ በተደረገ ዓመታዊው መድረክም የቤት ውስጥ ጥቃት እንዲወገዝና ሴቶች ለዚህ እንዲተባበሩ ሲሉ ጠሩ። ወንዶቹን ከሴቶች ላይ እጃችሁን አንሱ አሉ፤ ቃል አስገቧቸው።

የአካባቢው አስተዳደር ወይም የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ አቅሙና ሥልጣኑ እያላቸው የቦጋለችን ሩብ እንኳ እንዳልሠሩ ግልጽ ነው። እኚህ በጎ አድራጊ፣ የሰብአዊ መብ ተሟጋች ብርቱ ሴት፤ ልብ ላለ እጅግ በጣም አረዓያ የሚሆን ተግባርን ፈጽመዋል።

መነሻና መድረሻዋ በውል የማይታወቀው የምድር ሕይወት ዶክተር ቦጋለች ገብሬን መዝገብ ዘግታለች። ለብዙ ሴቶች እናትና ጠባቂ የነበሩት ቦጋለች እስከ ወዲያኛው አሸልበዋል። የሠሯቸው ሥራዎች፣ በጎ ምግባራቸውና አረዓያነታቸው ግን ፈቅዶ ጆሮውን ለሰጠና ዓይኑን ለከፈተ ሕያው ምስክር ሆነው ይቆያሉ። የከንባታ እናቶችም ለልጅ ልጆቻቸው ሁሉ ሥማቸውን ሲነግሩ ሥራቸውን ሲያወሱ ይኖራሉ፤ ውለታቸው ቀላል አይደለምና።

የእኚህ ሴት ሕይወት ለሴቶች መብት ትግል፣ የእኩልነትን የፍትኅ ጥያቄ ለቆሙ ለሌሎች በርካታ እህቶች መጽሐፍ ነው። ከላይ እንዳልኩት አንድ ሰው ብቻውን ማምጣት የማይችል የሚመስለንን ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ ናቸው። የማፈልገውንና እኩይ የሆነውን ነገር ሁሉ ማስቆም እንደማይሳነን ሕይወታቸው ይነግረናል።

ያም ብቻ አይደለም፤ ሕይወታቸው ‹‹እኔ ደኅና መሆኔ ብቻ በቂ ነው›› የሚለውን ውድቅ አድርጎ ያሳየናል። እኔ የተሻለ ስፍራ ላይ መቀመጤ፣ እኔ መማሬ፣ እኔ ማወቄ፣ እኔ ለራሴ መብት መቆም መቻሌ… ወዘተ ብቻ በቂ ነው? አይደለም። ለእህት መቆምን፣ ለሌሎች ሴቶችና እናቶች መብትም መሟገትን፣ ብርሃን ከታየን ሌላዋም ሴት እንዲታያት ማድረግን፣ ህመምን መጋራትን በዶክተር ቦጋለች ገብሬ ሕይወት እናያለን። አንዳንዱ ሰው ሲታደል እየኖረም፣ አልፎም ያስተምራል።

የተፈጥሮን ሕግ መቀበል አማራጭ የሌለው በመሆኑ የቦጋለችን ኅልፈት ስንቀበል፤ ሠርተው ያቆዩት ሁሉ አፍርቶ እንዲቀጥል እንጂ እንዳይከስምና ወደኋላ መመለስ እንዳይኖር የአካባቢውን አስተዳደር አስተውሉ እያልን፤ ዓላማቸውን ይዘው ጉዟቸውን ለሚቀጥሉ ተረካቢዎችም አደራ እየላክን ነው። የዶክተር ቦጋለች ገብሬ የነፍስ እረፍት፤ ለዘንነው መጽናናት ያድለን።
ሊድያ ተስፋዬ

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com