ፓርቲዎች ከጥምረት ባሻገር ሥራቸው መሬት ላይ ሊወርድ ይገባል!

Views: 188

ከአራት ዐሥርት ዓመታት ብዙም የማይዘለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕድሜው እምብዛም በጥምረት፣ ኅብረት፣ ቅንጅት ወይም ግንባር በሚል በጋራ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ አብሮ የመሥራት ባሕል አላዳበሩም። ቀደምቶቹ ፓርቲዎች ለምሳሌ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) እና የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) ምንም እንኳን የሚከተሉት ርዕዮተ ዓለም ሶሻሊዝም ቢሆን መጠነኛ የአካሔድ ለውጥ ነበራቸው። በጋራ የሚያስተሳስራቸውን እና የተሻለ ውጤታማ የሚያደርጋቸውን ጥምረት ወይም በጋራ ጉዳዮች ዙሪያ አብሮ የመሥራት ባሕል አልነበራቸውም።

ይባስ ብሎ ከመወያየት፣ ከመደራደር ወይም ሰጥቶ ከመቀበል የፖለቲካ አካሔድ ይልቅ “ከሃዲ” እና “አድርባይ” በሚል ይፈራረጃሉ። ከመፈራረጅም ባሻገር የአንዱ መኖር ለሌላው ሥጋት የሆነበት ብሎም የመጠፋፋት መጥፎ አሻራ ጥሎ ያለፈ ግንኙነት እንደነበራቸው ይታወቃል። በዕድሜ መግፋት ወይም ተተኪ በማጣት በሚመስል መልኩ አሁን ባለው ወቅታዊው የኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ የጎላ ሚና መጫወት ባይችሉም የቀረቻቸውን እስትንፋስ ይዘው የእርቅ እና አብሮ የመሥራት መንፈስ እንደሌላቸው ይታወቃል። የየፓርቲዎቹን ሽንፈቶች አንዱን በሌላው ላይ በማላከክ እንዲሁም በተጠያቂነት መክሰስ የተለመዱ ናቸው። በዘመን ሒደት ውስጥ አብሮ ለመሥራት እንኳን ባይሆን ለመተራረም ዝግጁ አለመሆናቸው ይታወቃል።

የደርግ መንግሥትን የተካው ኢሕአዴግ ከመጣ በኋላ የብዝኀ ወይም መድብለ ፓርቲ ስርዓት በሕገ መንግሥት ደረጃ እውቅና ተሰጥቶት ተግባራዊ ተደርጓል፤ ምንም እንኳን በተፈለገው ደረጃ ውጤታማ ባይሆንም ቅሉ።

የመድብለ ፓርቲ ስርዓት በሕግ እውቅና ማግኘት በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ አገራት ለበርካታ ብሔራዊ እና ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲዎች መፈልፈል ምክንያት ሆኗል። አገሪቱ ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት አዲስ በመሆኗ የፓርቲዎች መብዛት እንደ ችግር የሚታይ ሳይሆን ተፈጥሯዊ ወይም የሚጠበቅ እንጂ እንግዳ ደራሽ እንዳልሆነ ይታመናል። ይሁንና እነዚህ በኹለት ዓይነት መስመር የተመሰረቱ ፓርቲዎች በአመዛኙ ተመሳሳይ ርዕዮተ ዓለም ማለትም ሶሻሊዝም፣ ሊብራል ዴሞክራሲ አልያም ሶሻል ዴሞክራሲን የሚከተሉ ሲሆን ፕሮግራማቸውም ሆነ ዓላማቸው ተቀራራቢ የሚባል ዓይነት እንደሆነ ይታወቃል።

በመሆኑም በብዙ ጥምረቶች፣ ቅንጅቶች፣ ኅብረቶች እና ግንባሮች ለመፍጠር ሙከራ ተደርጓል። ይሁንና ሁሉም በሚያስብል ሁኔታ ውጤታማ ሆነው አያውቁም፤ ጠንክረው ወጥተው ጥሩ ተገዳዳሪ መሆን የቻሉ ግን ጥቂት አብነቶች አሉ።

በተለይ በተቃዋሚዎች ጎራ ጠንክረው መውጣት የቻሉት ከአንድ እጅ ጣት ቁጥር አይበልጡም፤ እነሱም ቢሆን ወይ አጭር ጊዜ ነው የሠሩት አለበለዚያም ያን ያክል የሚባል ተጽዕኖ ሳይኖራቸው ዕድሜ የሚቆጠርላቸው ናቸው። ከዚሁ ጎራ ሊጠቀሱ የሚችሉ ፍንጭ ያሳዩ ነበሩ፤ ምንም እንኳን ስኬታቸው በአጭሩ የተቀጨ ቢሆንም።

በ1997 ሦስተኛው አገራዊ ምርጫ ከመካሔዱ ጥቂት ወራት በፊት የተቋቋመው ቅንጅት ለአንድነትና ዴሞክራሲ (ቅንጅት) ተቀናጅቶ በመሥራት ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል ያሳየ ስብስብ ነበር። በሕዝቡ ዘንድ ያለው ተሰሚነት ከመጨመር ባሻገር በምርጫ ወቅት በአብዛኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ እና በአንዳንድ ገጠር አካባቢዎች ሊያሸንፍ ችሎ ነበር። ይሁንና ውስጠ ፓርቲ ጥንካሬው እና በመርህ ያለመገዛት አካሔዱ ቆይታው በአጭሩ እንዲቀጭ አድርጎታል፤ የመራጭ ሕዝቡን ድምጽ እንዲባክን አድርጓል።

ሌላው ከተቃዎሚ ጎራ በጠንካራነት የሚመደበው ሶሻል ዴሞክራሲን በሚያቀንቅኑ የተለያዩ የብሔር እና ኅብረ ብሔራዊ የፓርቲ ስብስቦች የሆነው መድረክ ተጠቃሽ ነው። መድረክ ምንም እንኳን በ1997 በተካሔደው ምርጫ ላይ እንደ ቅንጅት ንቁ ተሳታፊ ቢሆንም የዕድሜ ርዝመቱን ያክል ተጽዕኖ ማምጣት ያልቻለ ድርጅት መሆኑ ይታወቃል። በአሁኑ ወቅትም እስትንፋስ ኖሮት በሕይወት ቢኖርም ይሔ ነው የሚባል ተገዳዳሪም ተጽዕኖ ፈጣሪም ነው ብሎ አፍ ሞልቶ መናገር አይቻልም።
በቅርቡ ደግሞ ተጠቃሽ የሚሆነው የተቃዋሚ ፓርቲዎች ውሕደት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ነው። ፓርቲዎችን በማክሰምና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች በማካተት ጠንካራ ፓርቲ ሆኖ ለመውጣት ትልቅ ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛል። ከኢዜማ በዘለለ መሬት ላይ ጠብ ያለ እና ጎላ ያለ ሥራ እየሠራ የሚገኝ ፓርቲ ወይም ፓርቲዎች ከተቃዋሚው ጎራ ማግኘት አይቻልም። ፓርቲዎቹ ግን ቁጥራቸው አሻቅቦ አሁንም በመቶዎች ይቆጠራል።

ከላይ ከተጠቀሱት በተቃራኒ ስኬታማ ጉዞ ያደረገ፤ ተጽዕኖው ከፍተኛ የሆነ ገዢው ግንባር ነው፤ አሕአዴግ። በስምምነት ለመቀጠል የሚችለውና ረጅም ዓመታት አብሮ መዝለቅ የቻለው በአራት ብሔራዊ ፓርቲዎች ግንባር መፍጠር የተቋቋመው እንዲሁም ያለፉትን ሦስት ዐሥርት ዓመታት መንበረ መንግሥቱን በመያዝ እያስተዳደረ ያለው ኢሕአዴግ ነው።

ይሁንና ከመስከረም 2012 ጀምሮ አብሮ የመሥራት ስምምነት ውሎች በክልል ገዢ ፓርቲ እና በዛው ክልል ውስጥ ተቃዋሚ በሆኑ ብሔራዊ ፓርቲዎች መካከል በመፈራረም በጎ ሁኔታ ታይቷል።

የመጀመሪያውን አብሮ የመሥራት ውል የፈረመው የኦሮሚያን ክልል የሚያስተዳድረው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሲሆን ከሌሎች አራት በክልሉ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ጋር ውል አስሯል። ይሁንና አብሮ መሥራት በሚል ሾላ በድፍኑ የሆነ ምስጢራዊነት ባልተለየው አብሮ ለመሥራት ስምምነት አደረጉ ከሚል ውጪ በስምምነቱ ውስጥ የተካተቱ ዝርዝር አጀንዳዎች ምንነት በይፋ አልተገለጸም።

አዲስ ማለዳ ባደረገችው ማጣራት ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው አጀንዳዎች በቁጥር 15 መሆናቸውን አውቃለች። ከስምምነቶቹ መካከልም ቋንቋ፣ ራስ በራስ ማስተዳደር፣ ቀጣዩ ምርጫ እንዲሁም ሰላምና መረጋጋትን የተመለከቱ ጉዳዮች ዋነኛዎቹ እንደሆኑም ታውቋል። የአጀንዳዎቹ በይፋ አለመነገር ከሕዝብ ጀርባ ተደብቆ የፖለቲካ ቁማር ለመጫወት ነው የሚል ትችት ያስነሳልና ቀሪዎቹ አጀንዳዎች ለሕዝብ ይፋ ይደረጉ ብላ አዲስ ማለዳ በአጽንዖት ታሳስባለች።

በተለይ ፓርቲዎቹ በስምምነታቸው መሰረት በቅርቡ በተለያዩ የኦሮሚያ ክፍሎች የተነሱትን ግጭቶችና ስርዓት አልበኝነት ማስቆም ባይችሉ እንኳን ጉዳቱ እንዲቀንስ ማድረግ ነበረባቸው። በርግጥ ጥምረቱ እየተጠናከረ ሲሔድ በሰላምና መረጋጋት እንዲሁም በዘላቂ ሁኔታ ችግሮችን ለመፍታትና አገራዊ ሰላም ለማስፈን እርቀ ሰላም ለማውረድ ሚናቸው ከፍተኛ ይሆናል ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

በተመሳሳይ የገዢው ግንባር አባል የሆነው እና የአማራ ብሔራዊ ክልልን እያስተዳደረ የሚገኘው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ሦስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ታዋቂ ግለሰቦች እና ምሁራን በተገኙበት የምክክር ጉባኤ አካሒዷል። በጉባኤው ማጠቃለያ ላይም ፓርቲዎቹ በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረስ መቻላቸው ተዘግቧል።

በተጨማሪም የገዢው ግንባር አጋር የሆኑት የሶማሌ እና የአፋር ብሔራዊ ክልሎችን የሚያስተዳድሩት ድርጅቶች በየክልላቸው ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ድርድር መጀመራቸው ይበል የሚያሰኝ ነው።

በርግጥም እንደዚህ ዓይነት ስምምነቶች ፋይዳቸው ዘርፈ ብዙ እንደሚሆን አዲስ ማለዳ እውቅና ትሰጣለች። የፓርቲዎቹ ጥምረት ፋይዳ በዋናነት አብሮ ከመሥራት ባሻገር የጋራ ርዕይና ዓላማ ላላቸው ፓርቲዎች ውሕደት የራሱን አዎንታዊ ሚና ይጫወታል። ይህም ፓርቲዎቹ ጠንካራ ተገዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። በተጨማሪም ለአገር ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም አገራዊ እርቅ ለማስፈን ሚና እንዲጫወቱ ጥምረቱ የጎላ ሚና ይጫወታል ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 53 ጥቅምት 29 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com