ዳሰሳ ዘ ማለዳ ኅዳር 2/2012

Views: 308

1- አማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) በአዲሱ ሕብረ-ብሔራዊ ፓርቲ ተዋህዶ ለመሥራት የወሰነ ሲሆን “ኢትዮጵያዊነትን ከማንነት ጋር አስተሳስሮ የሚያስኬድና የእውነተኛ ፌዴራሊዝም መተግበሪያ መሆኑን በመገንዘብ የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ በአዲሱ አገራዊ ሕብረ ብሔራዊ ፓርቲ ተዋህዶ ለመታገል ወስኗል” ሲሉ በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የአማራ ክልል ኢንደስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ መላኩ አለበል ገልጸዋል። (አዲስ ማለዳ)
……………………………………………………………..
2- የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያስተላለፈውን መመሪያ ባልተቀበለው የአትሌት ሌሊሳ ዴሲሳ እና የአትሌት ሩቲ አጋ ወኪል ሁሴን ማኪ ላይ የውል ማቋረጥ እርምጃ መውሰዱን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታወቀ። የአትሌቶቹ ወኪል ሁሴን ማኪ በስራቸው ያሉ አትሌቶች ከውድድር በኋላ ማገገም እያለባቸው አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንዲወዳደሩ በማድረጋቸው ቅጣት መተላለፉን የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን የኮምዩኒኬሽን ሥራ ሒደት ተወካይ አቶ ስለሺ ብስራት ተናግረዋል። (ኢቢሲ)
……………………………………………………………..
3- በአደገኛነቱ የሚታወቀዉ የሊማሊሞ መንገድ ቅርስ እንዲሆን በማሰብ በምትኩ በሌላ አቅጣጫ ተለዋጭ የሊማሊሞ መንገድ ግንባታ ሥራ መጀመሩን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን አስታወቀ። የሊማሊሞ አደገኛ መንገድ በአዲሱ ዲዛይን መሰረት ከደባርቅ እስከ ዛሪማ 68 ነጥብ 62 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለዉ ሲሆን፣ ዲዛይን እና ግንባታን በጋራ ባካተተ መልኩ በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ ይገነባል። ግንባታዉ ከ2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚገነባ ሲሆን ሥራዉ የሚከናወነው ቤይጂንግ ኧርባን ኮንስትራክሽን ግሩፕ በተባለ የቻይናው ዓለም አቀፍ ተቋራጭ ድርጅት መሆኑም ታዉቋል። (የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)
……………………………………………………………..
4- በአዲስ አበባ ከተማ ኅዳር 1/2012 በተከሰተ እሳት አደጋ ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን የከተማዋ እሳት አደጋ ቢሮ አስታወቋል። ከአደጋዎቹ አንዱ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ሜክሲኮ ኬኬር ህንጻ ኹለተኛ ፎቅ ላይ በኤሌክትሪክ መስመር ምክንያት የተፈጠረ የእሳት አደጋ ሲሆን እሳቱ ወደ ሌሎቹ የህንጻው ክፍሎች ሳይዛመት መቆጣጠር መቻሉን ተገልጿል። ሌሎቹ ኹለት አደጋዎች የደረሱት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 እና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 በኹለት መኖሪያ ቤቶች የተከሰቱ ናቸው። በእነዚህም ቤት ውስጥ የተለኮሰ ሻማ እና ከምግብ ማብሰያ ኩሽና የተነሳ እሳት የአደጋው መንስኤዎች መሆናቸዉ ታዉቋል። (ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8)
……………………………………………………………..
5- በድሬዳዋ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ እንደ አዲስ ባገረሸው ግጭት በአራት ሰዎች ላይ የመሣርያ ጥቃት ሲደርስ ከአስር የሚበልጡ በመጠኑ መጎዳታቸውን የድሬደዋ ድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታል አስታወቀ። ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ባይረጋገጥም፣ በትላንቱ ግጭት ቦምብ መፈንዳቱን የሚያመለክቱ መረጃዎች አሉ። የድሬዳዋ ድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር የሺዋስ መኳንንት በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ በከተማው ቀፊራ እና ገንደጋ እንዲሁም አዲስ ከተማ አካባቢዎች እንደ አዲስ አገርሽቶ የተጀመረውን ግጭት ተከትሎ በርካታ የተጎዱ ሰዎች ወደ ሆስፒታሉ መጥተዋል። (ዶቼቬሌ)
……………………………………………………………..
6- ኢትዮጵያ የቪዛ አገልግሎት አሰጣጥን በማቅለል ከመጀመሪያዎቹ የአፍሪካ አገራት አንዷ መሆኗን “አፍሪካ ቪዛ ኦፕንነስ ኢንዴክስ” ባወጣው አዲስ ሪፖርት አስታወቀ። በሪፖርቱ መሰረት ኢትዮጵያ ከሌሎች አፍሪካ አገራት አንጻር 32 ደረጃዎችን በአንድ ጊዜ በማሻሻልም የመጀመሪያዋ አገር ለመሆን በቅታለች። በአሁን ወቅት በአማካኝ በ27 የአፍሪካ አገሮች ያለ ቪዛ ጉዞ ማድረግ እንደሚቻል የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽንና የአፍሪካ ልማት ባንክ ሪፖርት ያመለክታል። ከአፍሪካ አገራት 47ቱ ደግሞ በፈረንጆቹ 2019 የቪዛ አሰጣጥ አገልግሎታቸውን እንዳሻሻሉ ተገልጿል። (ኢቢሲ)
……………………………………………………………..
7-በመስከረምና በጥቅምት ወራት 239 ሰነድ አልባ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን በኩዌት የኢፌዴሪ ኤምባሲ አስታወቀ። ኤምባሲው በመስከረምና በጥቅምት ወራት የኩዌትን የመኖሪያ ፈቃድ ሕግ ተላልፈዋል በሚል በአገሪቱ የተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች እና በመንግሥት መጠለያ የነበሩ 239 ዜጎች ከሚመለከታቸው የአገሪቱ የሕግ አካላት ጋር በመነጋገርና አስፈላጊውን የጉዞ ሰነድ በማዘጋጀት ወደ አገራቸው በሰላም እንዲመለሱ አድርጓል። (ዋልታ)

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com