የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ዋጋ እስከ 20 ብር ሊቀንስ ይችላል ተባለ

Views: 1397

ከቀረጥ ነጻ እንዲሆን ተጠይቋል

የወር አበባ የንጽህና መጠበቂያ ለረጅም አመታት ቀረጥ ሲጣልበት ከነበረው የቅንጦት እቃዎች ዝርዝር በመውጣት በመድኃኒት ጤና አገልግሎት ዘርፍ እንዲካተት የጤና ሚኒስቴር በወሰነው መሰረት የህግ ማእቀፍ ተዘጋጅቶ ወደተግባር ሲገባ በአንድ እሽግ ምርት ላይ እስከግማሽ ድረስ የዋጋ ቅናሽ ሊያሳይ እንደሚችል ተገለጸ።
የጤና ሚኒስቴር የልጃገረዶችን ጤና ለማሻሻል የሴቶች የወር አበባ ንጽኅና መጠበቂያ ግብዓቶችን ማግኘት ለማይችሉ ለማድረስ በተያዘ ዕቅድ፣ የንጽህና መጠበቂያ ለጤና አገልግሎት የሚውል ምርት ተደርጎ እንዲወሰድ ውሳኔ ተላልፏል ብሏል ።

ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመሆን አቅም ለሌላቸው ልጃገረዶች የወር አበባ የንጽህና መበቂያ ቁሳቁስ በትምህርት ቤት፣ ክሊኒኮች፤ በጤና ተቋማት በተለይም ከወሊድ በኋላና ከጽንስ ማቋረጥ ጋር ተከትሎ የጤና አገልግሎት በሚሰጥባቸው ተቋማት ለማዳረስ እየታሰበበት እንደሆነ በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህጻናት ጤና ዳይሬክተር ዶ/ር መሰረት ዘላለም ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የመድኀኒት አቅርቦት ኤጀንሲ በበኩሉ፣ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶቹ ለጤና አገልግሎት በሚታዩ መልኩ በቀጣይነት የጥራት ቁጥጥር እየተደረገባቸው እንደሚቀርቡ ነው የገለጸው።

በኢትዮጵያ የንጽህና መጠበቂያ በቅንጦት ዕቃ አይነት የሚመደብ ከ 67 እስከ 123 በመቶ ቀረጥ የተጣለበት ሆኖ ቆይቷል። በዚህም በአማካይ የአንድ እሽግ የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ ዋጋ 40 ብር ገደማ እንዲሆን አድርጎታል። የተሸለ ጥራት ያለው የንፅህና መጠበቂያ ዋጋ ደግሞ እስከ 65 ብር የሚሻገር እንደሆነ የአዲስ ማለዳ የገበያ መረጃ ያመላክታል።

የንጽህና መጠበቂያ ከቅንጦት ዕቃ ዝር ዝር በመውጣት የተወሰነው የፖሊሲ ውሳኔ ለጉምሩክ ኮሚሸን እስካሁን ቤፋ እንዳልደረሰ የኮሚሽነሩ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወንድወሰን ደገፋ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የፖሊሲ ለውጦች ሲኖሩ ህግ የማውታት ስልታን ላለው የገንዘብ ሚኒስቴር ከተላኩ በኋላ በሚጣው ህግ አማካኝነት ለኮሚሽኑ መደበኛ ህግ እንደሚላክ ገልጸው እስካሁን ግን ውሳኔውን በሚዲ ከመስማት ባለፈ በኮሚሽኑ የሚታወቅ መረጃ እንደሌለ ተናግረዋል።
‹‹የንጽህና መጠበቂው ከሚሰራበት ቁስ በመነሳት፣ ከወረቀት መሰል ምርት ይሰራል በልን ብንወስድ እንኳን የ20 በመቶ ታሪፍ ለውጥ ይኖረዋል፣ ይህም በዋጋው ላይ ከ 40 እስከ 50 በመቶ ቅናሽ ሊያመጣ ይችላል›› ሲሉ አስረድተዋል። ‹‹የጤና መገልገያ መሣሪያ አልያም መድኀኒት በሚል ተመዝግቦ ከመጣ ግን ቅናሹ ከዛም አልፎ ከፍተኛ ቅናሽ ያመጣል።››
ነግር ግን የገንዘብ ሚኒስቴር የሚልከው ህግ ታይቶ የመጨረሻ ቅናሹ የሚታይ ይሆናል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ሠላሳ አምስት ሚሊዮን ሴቶች የወር አበባን የሚያዩ ቢሆንም 70 በመቶ የሚሆኑት የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ተደራሽ አይደሉም። የተሻለ ግንዛቤ ያላቸው ሴቶችም ቢሆኑ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ዋጋው ውድ ስለሆነ በቀላሉ ገዝተው መጠቀም አይችሉም።

በሴቶች ላይ የሚሠራ፣ ሴቶች ወደፊት እንዳይሔዱና ትልቅ ደረጃ እንዳይደርሱ የሚያጋጥማቸውን እንቅፋቶች ነጥሎ ማውጣት ዓላማው ያደረገውን የሴቶች የጀግኒት ንቅናቄ፣ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ከቀረጥ ነጻ ሆኖ ሊገባ እንደሚገባ ይገልጻሉ። ይህንንም የንቅናቄው አምባሳደር ድምጻዊት ፀደኒያ ገብረ ማርቆስ ለአደስ ማለዳ ገልጻለች።

ይሁንና ከቀረጥ ነጻ መሆን ብቻ ሳይሆን በመመሪያ በማስደገፍ ሴቶች አቅማቸው በፈቀደ መለኩ እንዲቀርብላቸው በከፍተኛ መጠን ዋጋ ከአምስት እስከ ሰባት ብር ድረስ መውረድ እንዳለበት ፀደንያ ታነሳለች።

ኢትዮጵያ ውስጥ 10 ሚሊዮን ያህሉ እድሜያቸው ከ 10 እስከ 19 ዓመት የሆናቸው አፍላ ወጣቶች፣ 83 በመቶ የሚሆኑት በገጠር አካባቢዎች የሚኖሩ ስለመሆናቸው መረጃዎች ያሳያሉ። ይህም በከተማ ብቻ የታጠረውን የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ተደራሽ እንዳይሆንላቸው አድርጓል።

በ2012 በኢትዮጵያ በተሠራ መለስተኛ ሥነ ሕዝብ ጤና ዳሰሳ እንዳመላከተው፣ ሴቶች በተማሩ ቁጥር በሥነ ተዋልዶ ጤና አጠቃላይ በቤተሰብ ጤና ላይ መሻሻል እንዲኖረው የላቀ ድርሻ አላቸው። የንጽህና መጠበቂያ በሌለባቸው ትምህርት ቤቶች የሚቀሩ የሴት ተማሪዎች ቁጥርም በርካታ ስለመሆኑ በዳሰሳው ተገልጿል። የትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ፣ በአንድ ቋት ፕሮግራም በትምህርት ቤቶች የንጽህና መጠበቂያዎችን ለማቅረብ እየተቻለ ስለመሆኑ ይገልጻል።
የ2018 የተባበሩት መንግሥታት ጥናት እንደሚያሳየው፣ ከ10 ልጃገረዶች አንዷ ከወር አበባ ጋር በተገናኘ ትምህርቷን ታቋርጣለች፤ 20 በመቶ ያህሉ ደግሞ በትምህርት ገበታቸው ላይ አይገኙም።

ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በተገኘ መረጃ ከ2010 እስከ 2012 ድረስ አጠቃላይ ንጽህና መጠበቂያ አምራች በሚል ፈቃድ የወሰዱ 766 አምራቶች፤ 761 አስመጪዎች እንዲሁም 33 ላኪዎች መኖራቸው ተገልጿል።

ቅጽ 2 ቁጥር 55 ኅዳር 13 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com