ከባድ ሴት?

Views: 495

ዛሬም በአንድ ገጠመኝ ልነሳ። ለሥራ ጉዳይ ከከተማ መውጣት ኖሮብኝ ማለዳ የተሳፈርኩት አሽከርካሪ ሾፌር ጋር በጨዋታ መካከል ስለሚሠራበት ተቋም ባለቤት አለቃው ተነሳ። ሴት ናት። በብዙ ተቃውሞዎችና በብዙ ድጋፎች መካከል ሳይሞቃት ሳይበርዳት ሥራዋን የምትሠራ። ‹‹ሥራ እንዴት እየሆነላት ነው?›› ስል ጠየቅሁ።

‹‹ኧረ እሷ ጎበዝ ናት! ከባድ ሴት ናት›› አለኝ። በዚህ አሽከርካሪ አውድ ውስጥ ሆኜ ባስበው፤ ‹‹ደፋር ናት›› ቢል እስማማ ነበር፤ ግን ከባድ ናት ግራ ገባኝ። ‹‹እንዴት ማለት? ጠንካራ ናት?›› አፌ አላረፈም ጠየቅሁ። ‹‹ኧረ በቃ ከባድ ናት! የድሮ ሴት ጭምት ነበረች፤ ለዛ ነው አገር ሰላም የነበረው። እንደውም እናንተ ወደ ሥልጣን መምጣት ስትጀምሩ ነው አገር እየተረበሸ ያለው…›› ቀጠለ። አልተናደድኩም፤ በፍጹም ትርጉም ከመስጠት የማይጠጋና የማይደረስ ነገር ለሚናገሩ ሰዎች መናደድ ሞኝነት ነው፤ አለማወቅ ስለሆነ ማስተማር ስለሚሻል።

ባይሆን ይህ ሰው ከተናገረው መካከል አንዱ ሐሳቤን ሰረቀው። ‹‹እስከ አሁን አላገባችም…ለትዳር የምትሆን አይደለችም።›› ቀጠለ፤ ትዳር ያልመሰረተችው ወይም በእርሱ አስተሳሰብ የማትመሠርተው ከባድ ሴት ስለሆነች ነው። ‹‹ግን ለወንድ እንደዛ ተብሎ ያውቃል?›› ብዬ ከመጠየቅ አልቦዘንኩም።

‹‹ቢሆንም…ሴት በአስተሳሰብ ወይም በገንዘብ ወንዱን ስትበልጠው ጥሩ አይደለም›› ሲል አያይዞ ብዙ ተናገረ። የእይታውን ጥግ እስከ ጥግ ማየት ስለፈለግሁ ሊያናግረው የሚችለውን ሁሉ ጥያቄ ቀጠልኩ። የባሰው ደግሞ ‹‹አንቺም ኃይለኛ ሴት ነሽ መሰለኝ…ለትዳር አስቸጋሪ የምትሆኚ ትመስያለሽ›› ብሎኝ አረፈው!
በእርግጥ ብዙ ሊያበሳጭ የሚችል ነገር ተናግሯል። ግን ምን ብዬ እደግመዋለሁ! እንዳልኩት የማያውቅን ማስተማር ነው፤ ማሳየት። ወሬውንና አስተያየቱን ሁሉ የሃሜተኛ እንዲሆንበት ማድረግ፣ ሰውን ከሰው በታች ወይም ሰውን ከሰው ባላይ አድርጎ ማሰብን ከተራ አስተያየት እንዲመደብ አድርጎ ማሳየት ነው።

አሁን ይህ ሰው አለቃው ላይ ምን ቢናገር፤ እርሷ ሩጫዋ አይቆምም። እንደ ግመሎቹ እዛም አዚም የሚጮኹትን ትታ ጉዞዋን ትቀጥላለች፤ ቀጥላለች።

ከባድ ሴት መሆን ምን ዓይነት እንደሆነ አላውቅም። ላለማወቅ ፈልጌ አይደለም፤ ግን ግራ ስለሚገባኝ ነው። ቁጡ፣ የተሰማትን የምትናገር፣ ለመብቷ የምትሟገት፣ በሥራና ቁምነገር የማታሾፍ፣ ለጊዜ የምትሳሳ ሴት ናት ከባድ ሴት? ስኬታማና ውጤታማ፣ ሁሉን በማባበል የማትፈጽምና የመርህ ሰው ስትሆን ነው ከባድ የምትባለው? ምነው ለወንዱ ጊዜ ሲሆን ይህ የማይሠራ?

እርግጥ ነው ሰው መሆንና የኑሮ ሁኔታ ለሴቶች ብቻ ሳይሆን ለወንዶችም ጭምር፤ ለሁሉም የሰው ልጅ የሚያላብሰው ጸባይ ይኖራል። ይህ ደግሞ ሰው የመሆን ውጤት ነው። ጎበዝና ብርቱ፣ በራስ ጥረት አንድ ደረጃ ላይ መድረስ መቻልና ቆፍጣና መሆን ግን ከባድ ከማሰኘት አልፎ ‹‹ትዳር ያሳጣል›› ብሎ ማሰብ ትክክል ነው ብዬ አላምንም።

አንድ ሰው ለሌላ ሰው ያለው ግምት ምንም ትርፍ ላይኖረው ይችላል፤ ፖለቲከኛ ካልሆነ በቀር። ነገር ግን አመለካከቱ በማወቅ ይሁን ባለማወቅ የተቀረጸበት መንገድ በአቅራቢያው ባሉ ሰዎች፣ በሚመሠርተው ቤተሰብ እንዲሁም በልጆቹ ላይ ማረፉ አይቀርም። ይህ ነው ጉዳት ሊያመጣ የሚችለው። ሴት ልጅ ያለችው አባት ‹‹ከባድ ሴት ትዳር አታገኝም›› ብሎ ክብደትን በራስ መቆምና ብርቱ መሆን ጋር አያይዞ ካስረዳት፣ ‹‹ሴት ስለሆንሽ ለስላሳ እና አባባይ ሁኚ ቆፍጠን አትበይ›› ካላት፤ ስህተቱ በዚህ ይታያል ማለት ነው። እንግዲህ ለወንድሞቻችን ከባድ ሴት ልጅ ይስጣቸዋ! ለአገርም ከባድ ሴቶች እንዲበዙላት።
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 60 ታኅሣሥ 18 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com