ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያልደመሩት የኢትዮጵያ ሴቶች የሰላም ጥያቄ

Views: 1906

ሴቶች እንደ አገር በሚከሰቱ አለመረጋጋቶች ብቻ ሳይሆን በመደበኛ እንቅስቃሴም ከቤት እስከ አደባባይ በሰላም ማጣት ውስጥ እንደሚኖሩ የሚጠቅሱት ሕሊና ብርሃኑ፤ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ከፍተኛ ጥቃቶችም በቸልታና በዝምታ እየታለፉ ስለመሆናቸው ይጠቅሳሉ። በሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ደረጃ ትኩረት የተነፈገ ከመሆኑ በላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኖቤል ሽልማትን ያገኙት አንድም ሴቶችን ወደ ሥልጣን በማምጣት ቢሆንም፤ በአንጻሩ ግን ማድረግ የሚገባቸውን ያህል አላደረጉም፤ እንደውም የሴቶች ጉዳይ እንደ ብሔር ጉዳይ ቢሆን ኖሮ በንግግሮቻቸው መካከል ጣል በሚያደርጉት ሐሳብ ግጭት በተፈጠረ ነበር ይላሉ።

ማኅበረሰባዊ ሰላም በአንፃራዊ መለኪያዎች ይገለጻል። ኢትዮጵያ ውስጥ የሰላም ማጣት ጥያቄ የጊዜና ስርዓት መቀያየር ሳይገድበው እስከ አሁን ድረስ በቋሚነት የሴቶች አንዱና መሠረታዊ ጥያቄ እንደሆነ ዘልቋል። የሴቶች ሰላም የብሔር ግጭትን ወይም ጠመንጃ መማዘዝን ሳይጠብቅ በየቀኑ በቤት ውስጥ፣ በሥራ ቦታ እንዲሁም በየመንገዱ መደፍረሱ የነበረና አሁንም የቀጠለ እውነታ ነው። ግጭቶች ሁሉ ብሔር ተኮር አይደሉምና።

ብሔርን መሠረት አድርገው በሚነሱ የእርስ በርስ ግጭቶች ላይም ቢሆን ሴቶች ላይ በተለየ መልኩ ያነጣጠሩ ፆታዊ ጥቃቶች የተለመዱ ናቸው። ይህም ዘመን ተሻጋሪ የማኅበረሰባዊ ባሕርይ ቅጥያ እንጂ ድንገቴና ከሰማይ የወረደ መዓት አይደለም። ማኅበራዊ እና ተቋም ወለድ የሆነው ሴትን ዝቅ የማድረግ አባዜ ለቤት ውስጥም ሆነ የአደባባይ የሴቶች ጥቃት ዋነኛው መንስዔ ነው። ስለዚህ ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት ድንገተኛ ማኅበራዊ ቀውስን ተከትሎ የሚወለድ ‘እኛን የማይመስል፣ ኢትዮጵያዊ ያልሆነ’ ችግር ሳይሆን፣ ሥር የሰደደ ከማኅበረሰባዊ ማንነታችን የሚፈልቅ እሳቤና ድርጊት ነው።

በነገራችን ላይ ቲፎዞ የማጣት ነገር ሆኖ እንጂ ባለፈው ዓመት እንኳን በመጀመሪያዎቹ ሰባት ወራት ዐሥራ ሦስት የሚሆኑ ሴቶች እዚሁ ከተማችን አዲስ አበባ ውስጥ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል። እነሱ ጃዋር የላቸውም፣ እስክንድር ጥያቄቸውን በአደራነት አልተረከባቸውም፣ ጉዳያቸውን ጉዳያችን ያሉት እንደሌላው ‘የፖለቲካ አክቲቪስቶች’ አድማጭ የላቸውም፣ ብቻ ምን አለፋችሁ ሰላምና ሕይወታቸውን ሲያጡ ልብ ያላቸው ወገን የለም።

በጠራራ ፀሐይ ጃንሜዳ ላይ ብልታቸው ሲሰፋ፣ በመሥሪያ ቦታቸው አንጀታቸው እስኪወጣ ሲተለተሉ አልያም የሰውነት ክፍላቸው ተቆራርጦ በሻንጣ ይዞ የተሰወረ “ፍቅረኛ” ጠፍቶ ለወራት ሲፈለግ ብዙ ኢትዮጵያውያን ጆሮም አልነበራቸው። የፈረደብን ጥቂቶች ገንዘብ ስናዋጣ፣ ደም ስንለግስ፣ ፖሊስ “ጠፉብኝ” ያላቸውን ተጠርጣሪዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ስናፈላልግ ስንት ወራት አሳለፍን? ስንት ለውጥ የሚጠነሰስበት፣ የፆታ እኩልነት መቃናት የሚነደፍበት ስንት ጊዜስ ባከነ?

ይህ ሁሉ ሲሆን ታዲያ በማኅበራዊ ሚዲያ፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ጭምር የመንግሥት አካላት ጆሮ እንዲደርስ ቢደረግም አንዳችም ውጤት ሳይገኝበት፣ በአልሰማንም ታልፏል። ይባስ ብሎ ለመክሰስ የሄዱ ሴቶች ሲደበደቡ፣ ሲደፈሩ፣ የዜግነት ክብራቸው ሲገፈፍ ‘ያው ያጋጥማል፤ አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታም ማስተዋል ግድ ይላል’ ’እነ እንትና (አንዱ ወንድ “አክቲቪስት”) እኮ ስለዚህ ጉዳይ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እንዲጽፉ ቢደረግ ምናልባት ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሊሰሟችሁ ይችላሉ’ በሚሉ ኀላፊዎችና ሚኒስትሮች ተሸንግለው ወደ ቤት ይላኩ ይሆን እንጂ ጠብ የሚል ፍትሕ አላገኙም።

ሚኒስቴር ያልተመደበላት ሰላም
የሴቶች ሚኒስቴር (በአሁኑ አጠራር የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር፤ ምን አለፋችሁ! የሁላችንም ሚኒስቴር)ም ቢሆን “ሴቶች ዘረኝነትን በመጠየፍ ለሰላማችን ግንባር ቀደም ሚናችንን እንወጣ” ከሚሉ ስብሰባዎችና ፎቶዎች ውጪ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ብዙም ሊደፍረው የማይፈልገው አጀንዳ ሆኖበታል። የሹመት መጀመሪያ ላይ ቃል የተገቡ የሴቶች የሕግና ፍትሕ ጥያቄዎች ሳይመለሱ መሞሸርና ድግስን መርጧል። ነጭ በነጭ አድርጎ “ጀግኒት ዘረኝነትን ትጠየፋለች” እያሉ ለፎቶ መደርደርና የተግዳሮቶቹን ግዝፈት አቅልሎ ማየት የስንት ጀግና ኢትዮጵያውያን ሴቶች ችግርና እንባን ማራከስ ይሆናል።

ለኢትዮጵያ ሴቶች የሰላም ጥያቄ ዳር ድንበር ማስከበር፣ የብሔር ግጭትን መፍታት አልያም ዘረኝነትን ማጥፋት ብቻ መልስ አይደለም። የኢትዮጵያ ሴቶች ከቤት እስከ አደባባይ የሰላም ጥያቄ አላቸው። በቤት ወይም በሚኖሩበት አካባቢ ከሚያውቁት፣ ቤተሰብ ከሚሉት ወንድ እስከ እንግዳ ጥቃት ይደርስባቸዋል። በብሔር ማንነትም ውስጥ ቢሆን የሌላ ብሔር ወንድ ሳይሆን በእራሳቸው ብሔር ወንድ ከፍተኛና ተደጋጋሚ ጥቃት እንደሚደርስባቸው የኢትዮጵያ ሥነ ሕዝብና ጤና ዳሰሳን ጨምሮ ብዙ ጥናቶች ይሳያሉ።

“የኔ ወገን የሆነች ሴት ተጠቃች ኡ…ኡ” የሚል ወንድ የምትሰሙት የሌላ ብሔር ወንድ ጥቃት ያደረሰ ጊዜ ነው። ልክ ‹የእኔን ብሔር ሴት፣ እኔ እንጂ ሌላ ወንድ አይግደልብኝ› ዓይነት ነገር። እናም ጀግኒት ዘረኝነትን አልያም ድንበር ዘለል ጠብን ብቻ ሳይሆን ቤትና አካባቢዋ ያለ የሰላም መነፈግንም ትጠየፋለች።

የሰላም ሚኒስቴርም ቢሆን ‘የዜጎች ሰላም’ በሚል ጥቅል የሰላም ጥሪ ተጥዶ ፆታዊ ጉዳዮችን አላይም አልሰማም ብሏል። የሰላም ሚኒስቴር በአገራችን ሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆኑትን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን እና ብሔራዊ መረጃና ደኅንነትን ማዘዝ የሚችል ባለ ብዙ ሥልጣን መሥሪያ ቤት ቢሆንም፥ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀር ‘በሴት የሚመራ’ እየተባለ ቢሞካሽም፣ ለሴቶች ሰላም አንዲትም ጠጠር እስከ አሁን አልተወረወረም።

ሰላም እና ደኅንነት ጥናት የተማሩት ጠቅላዩም ቢሆኑ ሰላምን የመረዳት አቅማቸው ከዚሁ ብዙም አልዘለለም። “ሴቶችን አብቅቻለሁ፣ አሉ የተባሉ ሴቶችን ሁሉ ወደ ሥልጣን አምጥቻለሁ፣ እጅ በደረት” ማለታቸው አሳሳቢ ሆኖ ሳለ፣ የብሔራዊ ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን 41 አባላት ውስጥ 5 ሴቶች ብቻ መካተታቸው እርቅ እና ሰላም ላይ ስላላቸው ግንዛቤ ይናገራል። ግጭቶችን ለመፍታት እንዲሁም ሰላምን ለማስከበር የተቀመጡ የዓለም ዐቀፍ ሕጎች እና የዲሞክራሲያዊ መሠረት የሆነው የውክልና ሐሳብ ይህን ዓይነት ጎዶሎ ውክልናን አይቀበልም።
ሴቶች ቻሉ/አልቻሉም ብለን ብናስብም፣ ፍለጋው ቢከብደን/ቢቀለንም ኅብረተሰቡ ውስጥ ያላቸውን ቁጥር የሚመጥን ውክልና ሊሰጣቸው ይገባል።

ይህ ሐሳብ ጉዳዩን አቅላይና ተገቢ ያልሆነ ሊመስል ይችላል ነገር ግን የሴቶች ውክልና፣ በሴቶችና በወንዶች መካካል እኩልነትን ለማስፈን የሚረዳ ቁልፍ የሰብዓዊ መብት መርኅ መሆኑ መታወቅ አለበት። የሚወከሉት ሴቶች ተቆርቋሪነታቸው ለሴቶች ቢሆንም ባይሆንም፣ የሴቶች ጥያቄን ፈቀቅ የሚያደርግ አቅምና ፍላጎት ኖራቸውም አልኖራቸውም፣ በአንፃሩ የስርዓተ ፆታ እኩልነት ላይ ከአንዳንድ ሴቶች የበለጠ ተቆርቋሪ የሆኑ ወንዶች ኖሩም አልኖሩም፤ ተመጣጣኝ ውክልና የመብት ጉዳይ ነው!

በዚያ ላይ የወንዶችን ከበቂ በላይ መወከል (over-representation) የተለመደ ሆኖ ችግሩን ለማየት ስለማንፈቅድ እንጂ ይሄኔ ሴቶች 36 ወንዶች 5 ሆነው ቢሆን ኑሮ እኩይ ፆተኝነት አያስተኛንም ነበር። ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከሚሰነዘሩ ትችቶች፣ ፆተኛ ቀልዶች ጀምሮ በየቤቱ ከሚሰጡ አስተያየቶች ‘ውይ ሴቶቹ እርቁን ተቆጣጥረውት የለ እንዴ’፣ ‘አሁንማ ጊዜው የእናንተ ነው፤ ግን እንደው አልበዛም ይሄ ሁሉ ሴት፣ አሁን ሰላም ሊያመጣ ነው?’፣ ‘ሴት ሲበዛ… አይደለምን ነገሩ!’ የሚሉ አስተያየቶችና አሽሟጣጭ የወንዶች ማኅበራዊ አመፅን እንሰማ ነበር።

ሴቶች ብሔር ቢሆኑ…
ጠቅላይ ሚኒስትሩም ቢሆኑ ‘ያገኘሁት ዐሥር ሴት ነው፣ ዐሥሩንም አስገብቻለሁ’ ከሚል የግብር ይውጣ አስተያየት በተጨማሪ እስከ አሁን በነበራቸው ውይይቶች በአገር ዐቀፍ ደረጃ ያለውን የሴቶች ፆታዊ ጥቃት ችግሮችና ጉዳዩን የሚከታተሉ የሴቶች መብት ላይ የሚሠሩ ተቋማት ተወካዮች ጋር ለመወያየት አለመፍቀዳቸው ብዙ ይናገራል። በነገራችን ላይ በየንግግራቸው መሐል እያዳለጣቸው ጣል የሚያደርጉት ግድ የለሽ፣ ፆተኛ አስተያየቶች ይሄኔ ብሔር ላይ ተብለው ቢሆን ኖሮ አገሪቱ ሰላም አታድርም ነበር።

አሰባችሁት? “አገሪቱ ውስጥ ያሉት ዐሥር የእንትን ብሔር ሰዎች ናቸው፤ ያሉትን በሙሉ አምጥተናል፣ እናንተው ጨምሩ” ቢሉ እና ቀጠል አድርገውም “ለነገሩ የዚህ ብሔር ሰዎች ከጀርባ መምከር ነው የሚወዱት፣ ለእሱ ደግሞ በቂ አለን፤ ደግሞም እንደዚህ ፐብሊክሊ እየወጡ መቆጣት ምናምንም አይወዱም። በነገራችን ላይ እንትናን መርጠነዋል፤ እንትና ማለት እኮ ኻያ የእንትን ብሔር ሰው ማለት ነው” ብለው ቢሆን? ይህን በፍፁም ማን አለበኝነት ብለዋል! ያው ከየትኛውም የብሔርም ሆነ የሃይማኖት (እምነት) ተከታዮች በላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው 51%ቱ የኢትዮጵያ ሴቶች ላይ ሆኖ ሰሚና ገሳጭ ጠፋ እንጂ!

የሴቶች መብት ሰላምና ልማትን ካረጋገጥን በኋላ የምንመለስበት ትርፍ አጀንዳ ሳይሆን ልክ በፖለቲካ ለውጡ እንደመጣው የፖለቲካ ምኅዳር መስፋት እኩል ቦታ ተሰጥቶት ሊታይ የሚገባ ጉዳይ መሆን አለበት። የኖቤል የሰላም ሽልማትን ሊያሸንፉ የቻሉት ጠቅላዩም ሲያሸንፉ የተሞገሱበት፣ በሌሎች አገራት መሪዎች የተሞካሹበት፣ ሥልጡን ሆነው የቀረቡበት አንደኛው ምክንያት ሴቶችን ወደ ተለያየ የኀላፊነት እርከን እንዲመጡ ማድረጋቸው እንደሆነ ይገለጣል። ሆኖም ብዙ እንደሚቀራቸው ሲተቹ ባለመስማቴ ቅር ብሎኛል። ለነገሩ ኖቤሉ ለእርሳቸው እንጂ ብዙ የሰላም ጥያቄ ላላቸው፣ የቀን ተቀን እስትንፋሳቸው በወንዶች ፈቃድ ለወደቀ ብዙኃን ኢትዮጵያውያን ሴቶች ኦስካርም ጭምር ነው፣ በአድርጌያለሁ ሥም ብዙ የተተወነበት። ሰላም።
ሕሊና ብርሃኑ የሥርዓተ-ፆታና የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ በዚህ አድራሻ ይገኛሉ bhilina.degefa@gmail.com

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com