ስዕልና ማሳያ ስፍራው

Views: 320

የስዕል ጥበብ ለኢትዮጵያውያን እንግዳ አይደለም። ዘመናዊ የአሳሳል ጥበብ የሚባለው ሳይተዋወቅ አስቀድሞ፣ ሰዓልያኑ ቀለምን ከቅጠላ ቅጠል አዘጋጅተው፣ በግድግዳዎችና በብራና ላይ ሲጠበቡ ኖረዋል። ስዕልን መተረኪያ፣ የጽሑፎቻቸው ማብራሪያና ማድመቂያም አድርገው ተገልግለውባቸዋል። ዛሬስ?

ዛሬ ላይ ዓለም በምትሄድበት ፍጥነት አይደለ፣ በእጅጉ እያዘገመም ቢሆን የኢትዮያ የስዕል ጥበብ ጊዜውን ሲከተል ይታያል። ለዚህም ማሳያው ዘመናዊ የአሳሳል ጥበብን ቀስመውና ኢትዮጵያዊ ብሩሻቸውን ያልለቀቁ ኢትጵያውያን ሰዓሊዎች መገኘታቸው ብቻ ሳይሆን፣ ስዕሎችን ማሳያ አርት ጋለሪ ወይም የስዕል ማሳያ ስፍራዎች አስፈላጊ መሆናቸው መታመኑም ላይ ነው። በአዲስ አበባ ከተማ ታድያ በጣት ተቆጥረው የማይሞሉ ጥቂት የስዕል ማሳያ ስፍራዎችን ነው የምናገኘው።

ተስፋዬ ገለታ ኡርጌሳ ሰዓሊ ነው። ትውልድና እድገቱ አዲስ አበባ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ የሥነ ጥበብ ማዕከል የስዕል ትምህርት ተከታትሏል። ኑሮውን በጀርመን ያደረገው ተስፋዬ፣ ከ10 ዓመት በኋላ የስዕል ሥራዎቹን ለእይታ ለማቅረብ ወደ አገሩ ተመልሷል። ‹‹ሁሌም እዚህ አገሬ ላይ የስዕል አውደ ርዕይ ማቅረብና ማሳየት እፈልግ ነበር።›› ይላል መለስ ብሎ ሲያስታውስ።

ፍላጎቱ ከልቡ ያልጠፋው ተስፋዬ፣ በጣልያን በተካሔደ አንድ የስዕል አውደ ርዕይ ላይ በተሳተፈበት ወቅት፣ አውደ ርዕዩን በማስተባበር ሲሠሩ ከነበሩት የአዲስ ፋይን አርት ጋለሪ መሥራች ባለቤቶችና ሥራ አስኪያጆች ጋር ተገናኘ። በዛም አዲስ አበባ ላይ ባለው የስዕል ማሳያ ስፍራ ስዕሉን እንዲያቀርብ በቀረበለት ግብዣ ስዕሎቹን ይዞ አዲስ አበባ ተገኘ።

ለስምንት ሳምንታት ይዘልቃል የተባለውና ‹‹ኖ ካንትሪ ፎር ንግ ሜን›› የተሰኘው አውደ ርዕይም፣ ታኅሳስ 18/2012 ቦሌ መድኃኒዓለም በኤድናሞል አለፍ ብሎ ወልድፍቅር ሕንጻ ላይ በሚገኘው አዲስ ፋይን አርት ጋለሪ ውስጥ በይፋ ተከፍቷል።

በወጣቶች እንዲሁም በስደት ላይ ትኩረት የሚያደርገውና ‹‹በስዕል ሥራዎቼ ዋናው ትኩረቴ ሰው ነው›› የሚለው ተስፋዬ፤ ቢቻል በየዓመቱ የስዕል አውደ ርዕይ ቢያዘጋጅ ደስተኛ ይሆን እንደነበር ይገልጻል። ‹‹የተወለድኩት ያደጉት እዚህ [ኢትዮጵያ] ነው፤ በዓመት በዓመት ባደርገው ደስ ይለኝ ነበር›› ሲል ይህን ፍላጎቱን ይገልጻል።
ታድያ በስዕል ሥራ ውስጥ ፈታኝ ያለውም እንደልቡ አውደ ርዕይ እንዳያቀርብ ያደረገውን የስፍራ አለመኖር ችግር ነው። ይህም እንደ ሰዓሊ ለመቆየት ፈተና ይሆናል ባይ ነው።

አዲስ ፋይን አርት ጋለሪ በአዲስ አበባ ከሚገኙ ለመጥቀስ ከሚያንሱ የግል የሆኑ የስዕል ማሳያ ስፍራዎች ተጠቃሽ ነው። መቀመጫውን በአዲስ አበባ እንዲሁም በኢንግሊዟ ለንደን ያደረገው ይህ የስዕል ማሳያ፣ ከአራት ዓመት በፊት የተመሠረተ ነው። በየሦስት ወሩም የኢትዮጵያውያን አርቲስቶችን ሥራ በቋሚነት በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ለእይታ ያቀርባል። ለምሳሌም ከለንደን በተጨማሪ በፓሪስ፣ ሌጎስ፣ ኬፕታውን፣ ጆሐንስበርግ፣ ኒውዮርክ እንዲሁም ዱባይ ከተሞች ላይ ኢትዮጵያውያን ሰዓሊዎች በገዛ ስዕሎቻቸው እንዲታዩ እድል መፍጠር ችሏል።

ይኸው የስዕል ማሳያ አንጋፋ ከሆኑ ሰዓልያን አንስቶ የአዳዲሶቹን በተጨማሪም የፎቶግራፍ ባለሙያዎችን ሥራዎችም ለእይታ እንዲቀርቡ ግድግዳዎቹን የሰጠ ነው። በዓለም ላይ ካሉ 27 ዓለም አቀፍ አዳዲስ/ወጣት የስዕል ማሳያዎች መካከልም እንደ አንዱ ሆኖ ተመርጧል። ለአንባቢ ትውስታ ይረዳ ዘንድም፣ ይህ የስዕል ማሳያ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ከሚገኙ ስዕላትና ፎቶግራፎች ውስጥ በርካታዎቹን ያቀረበ ነው።

የስዕል ማሳያው መሥራቾች መሳይ ኃይለልዑል እና ራኬብ ስለ ናቸው። ይህ ጋለሪ የመጀመሪያቸው እንደሆነ የሚናገሩት መሳይ፣ በዚህ የስዕል ማሳያ በጠቅላላ 15 አካባቢ ሰዓልያን እንዲያዘጋጁ እድል ተፈጥሯል። ‹‹የእኛ መነሻና ዓላማ ከማንም አናንስም የሚል ነው።›› የሚሉት መሳይ፣ ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች ሊደነቁ እንደሚገባ ነገር ግን ውጤታቸው ጎልቶ እንደማይታይ ጠቅሰዋል። ይህም የሆነበት ምክንያት በተለይም ስዕሎችን ሰብስቦ ማሳየትና ወደዛ ደረጃ የሚያደርሱ ባለሙያዎች ስለማይሳተፉ ነው ይላሉ።

‹‹በችሎታ ቢመዘን ኖሮ በጣም ሊታወቁ የሚገቡ አርቲስቶች ያፈራች አገር ናት። እንቅፋቱ ቢስተካከል ጥሩ ይሆናል።›› ብለዋል፤ መሳይ በሰጡት አስተያየት።

ራኬብም በበኩላቸው አርት ጋለሪ የመክፈት ሐሳብ መጀመሪያ የመጣው አስቀድሞ በነበሩበት የስዕል መሰብሰብ ሥራ ምክንያት እንደሆነ ጠቅሰዋል። ‹‹ያኔ የኢትዮጵያ አርቲስቶች ብዙ አይሳተፉም ነበር።›› ሲሉም ያስታውሳሉ። ይህ ከሰባት ዓመት በፊት ሲሆን፣ ከዛ በኋላ ራኬብና መሳይ ተገናኝተዋል። ለበርካታ ዓመታት በዘርፉ ሲንቀሳቀሱ ከቆዩት መሳይ ጋርም በመሆን ራኬብ በሚችሉት ሁሉ እየተንቀሳቀሱ፤ ‹‹የእኛ አርቲስቶችን በዓለም መድረክ እንዴት እናሳትፍ፤ መወዳደር እየቻሉና አቅም እያላቸው ለምን ያ አልሆነም›› ሲሉ በመጠየቅ አዲስ ፋይን አርት ጋለሪን ለመክፈት ተስማሙ፤ አደረጉትም።

‹‹እኛ ስንጀምር ሰዓሊ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ብሎ የሚያስብ ሰው ጥቂት ነበር። እኛ ከጀመርን በኋላ ግን ስናይ ከማንም አገር አያንሱም እንደውም ይልቃሉ። እኛ በትንሹ ባስተዋወቅናቸው ሰዓልያን ብዙ አግኝተናል። ማስተዋወቁ ላይ የሚሠራ ባለሙያ እጥረት እንደሁም የጋለሪ አለመኖር ነው ችግሩ። እኛ የጀመርነው ዓይነት ሥራ መስፋፋት ከቻለ በኢትዮጵያ፤ ችግሩ ተወግዶ፤ ኢትዮጵያ በስዕል አንደኛ መታወቅ የምትችል አገር ናት ብለን እናምናለን።›› ሲሉ ራኬብ አክለዋል።

ታድያ በኹለቱም ሰዎች እንደ እንቅፋት የተነሱት፤ የኢትዮጵያ ሰዓልያን እንዳይታወቁና ዘርፉም እንዳይሰፋ ያደረገው ስዕሎች የሚታዩበት አውድ ባለመፈጠሩ ነው። ከዚህም ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮችን ጠቅሰዋል። ‹‹እውነት ለመናገር እንቅፋቶቹ ብዙ ናቸው። አንደኛ ገንዘብ ያስፈልጋል። እሱ እንኳ ያለው ሰው ደፍሮ እንዳይገባ የሚያስቸግረው በመንግሥት የሚጠበቁ ነገሮች አሉ፤ በተለይ ታክስ። በጣም ታክስ የሚደረግ ዘርፍ ነው።›› መሳይ ሲናገሩ ያሉት ነው።

ቀጥውም፤ ‹‹እኛ የኢትዮጵያን ታሪክ ባህል ለውጪ የሚያስተዋውቁ ፈጠራ ሥራዎች ናቸው። እነዚህ እንዳያድጉ የሚያደርግ ሕግጋት መስተካከል አለበት። አርቲስቱም ላይ በዚህ በኩል ጫና አለ። በዚህ ምክንያት እኛም ዋጋችን ይንርል። ይህን ማስተካከል ከባድ ነው።›› ሲሉ አክለው ያብራራሉ።

ከውጪ አገር አንጻር በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ሲገልጹም፤ በውጪ አገራት መገናኛ ብዙኀንን ጨምሮ ለዘርፉ ትኩረት እንደሚሰጥ ጠቅሰዋል። የሚሠራውን መገናኛ ብዙኀን እንደሚከታተሉና እንደሚተቹ ጭምር። ከምንም በላይ ግን መሳይን የሚያሳስባቸው አርቲስቶች እንደ ነጋዴ ዋጋ ላይ መደራደራቸው ነው። ይልቁንም ሥራቸውን ነው ማሰብ ያለባቸው ሲሉ ይሞግታሉ። ‹‹ታክስን ማሰብ ለፈጠራ ሥራ ባለሞያ ከባድ ነው።›› ያሉት መሳይ፣ መቅደም ያለበት በታክስ ገቢ መሰብሰብ ሳይሆን ሰዓልያኑ እንዲያድጉ ቦታ ማመቻቸት ነው።

‹‹እውነት ለመናገር አሁን በመንግሥት በኩል ያለው የሚመስለው እንጠቀም ብቻ ነው።›› ሲሉም እይታቸውን ጠቅሰዋል።

ለምሳሌ የፎቶግራፍን ጉዳይ ያነሱት መሳይ፤ ‹‹የሚያሳዝነው እኛ ኢትዮጵያ ውስጥ ፎቶግራፍ አትመን አንሸጥም። ምክንያቱም ወረቀቱ ለብዙ ዓመት ይኖራል ተብሎ ስለሚታመን እዚህ አገር ያን ማሟላት አንችልም። ብዙ ዓመት እድሜ ያለው ወረቀት ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ለአታሚ ድርጅቶች ያለው ጣጣ ከባድ ስለሆነ›› ብለዋል።
ለዚህም ነው፤ ጠቅላይ ሚኒስተሩ ቢሮ የገቡት ፎትግራፎች ከለንደን ተገዝተው፣ ዱባይ ፍሬማቸው ተሠርቶ ኢትዮጵያ የደረሱት። ወረቀቱ ብቻ አይደለም፤ ቀለሙ ደግሞ ሌላ ችግር ነው ይላሉ። ‹‹እኛ በራሳችን ማሽን እናስገባና እናትም ብንል ታክሱ ስንት እንደሆነ ማሰብም አንፈልግም።››

ራኬብም በተመሳሳይ ያለውን የቦታ ችግር ጠቅሰዋል። ከኖሩበትና በስዕሉ ዘርፍ ለዓመታት በሠሩበት ለንደን ከተማ ያላቸውን ተሞክሮ በመጥቀስ ሲያስረዱ የሚከተለውን አሉ፤ ‹‹በለንደን ያሉ አርቲስቶች ብዙ ድጋፍ አላቸው። ትምህርት ቤት አለ፤ ይከፈልላቸዋል፤ ቁሳቁስ ታክስ አይደረግም በርካሽ ይገኛል። ትርፋማ ካልሆኑ ገንዘብ በብድር ሊወስዱ ይችላሉ።›› ብለዋል።

በአንጻሩ በኢትዮጵያ ባለው ድህነት ምክንያት የሚጠበቁ ችግሮች እንዳሉ ሆነው፤ ሰዓልያን እንደ ነጋዴ መታየታቸውንና ከፍተኛ ታክስ መጫኑን እንደ ትልቅ ችግር ይጠቅሱታል። ጥበቡ እንደ ቅንጦት ስለሚታይም ለሰዓልያኑ ተጨማሪ እንቅፋት ሆኗል ይላሉ። ‹‹አርቲስት ሲባል እንደ አገር ሀብት መታየት አለበት። አሁን የፈጠራ ሥራ የሚሠራ ባለሞያ የአሁኑን ዘመን ለነገው የሚናገርና የሚያብራራ ሥራ ነው የሚሠራው። የውጪ አገር ሰዎች እኛን መጥተው ለማየት የሚችሉበት አንዱ መንገድ ተደርጎ ነው መወሰድ ያለበት።›› የራኬብ አስተያየት ነው።

ስምረት መስፍን ሰዓሊትና መምህርት ናት። በአዲስ አበባ የተለያዩ የስዕል ማሳያ ስፍራዎች ስእሎቿን በተለያየ ጊዜ አሳይታለች። የስዕል ማሳያ ስፍራዎች እጅግ ፈታኝ መሆናቸውን ትገልጻለች። በመንግሥት በኩል ብሔራዊ ሙዝየም ሰልፍ ተይዞና ተራ ተጠብቆ ከሚቀርበው ባሻገር፣ አዲስ አበባ ሙዝየም እንዲሁም ብሔራዊ ቴአትር ትንሹ የስዕል ማሳያ ከግል ይዞታ ውጪ ከሆኑት ተጠቃሽ ናቸው። አሁን ላይ የብሔራዊ ቴአትር እድሳት ላይ በመሆኑ አንድ የስዕል አውደ ርእይ ማዘጋጃ ስፍራ እንደቀነሰም ለአዲስ ማለዳ ጠቅሳለች።

በግል የሚገኙት ታድያ የየራሳቸው አሰራር እንዳላቸው የምትጠቁመው ስምረት፣ ከስዕል ሽያጭ የሚወስዱት ከፍተኛ ድርሻ (እስከ 70 በመቶ)፣ በጊዜ ገደብ የሚያስፈርሙት ውል (ለተወሰኑ ዓመታት ሌላ ቦታ የስዕል አውደርዕይ ላለማቅረብ)፣ ከአንዱ ጋር የሠራ ሌላ ጋር ለማቅረብ የሚኖረው ትግል ወዘተ ፈታኝ መሆናቸውን ትጠቅሳለች።

ይህ ጉዳይ ለስዕል ማሳያ ስፍራ ባለቤቶች የተነሳ እንደሆነ፣ የታክሱን ነገር ማንሳታቸው አይቀርም። መሳይ እንዳሉትም ታክሱ በሚፈጥረው ጫና ምክንያት አስተባባሪና አሰናጆች ሰዓልያኑ ላይ የበለጠውን ጫና ያሳድራሉ። ይህም ነው አንድም ተስፋዬ እንዳለው በትምህርት የሠለጠኑም ቢሆኑ፣ የሙያው ፍቅር አብዝቶ ያናወዛቸውና እረፍት የነሳቸው ካልሆኑ በቀር በሙያው እንዳይቆዩ የሚያደርገው።

መሳይ ይህ ሁሉ ችግር ቢፈታ፣ ለዘርፉ መንግሥት ትኩረት ቢሰጥ፣ ቅንጦት ሳይሆን ‹ነገረ – ሰው› እንደሆነ መረዳት ቢመጣ፤ እንደ አዲስ ፋይን አርት ጋለሪ ዓይነት ብዙ አውዶች በየከተማው ቢኖር እመኛለሁ ብለዋል። ይህም ጠቀሜታው ብዙ መሆኑን ሲጠቅሱ፣ዘርፉ በሌላው ዓለም ኢንደስትሪ መሆኑን ያነሳሉ። በተለይ በአፍሪካ የስዕል ጥበብ የዓለምን ትኩረት እያገኘ መሆኑንና አቅምና ፍላጎት ያለው ገዢ አዲስ ነገር ፍለጋ በመንቀሳቀስ ላይ ስለሆነ፣ ዛሬ የገዙትን ነገ በእጥፍ ዋጋ ለመተመንም ጉጉት ላይ ያሉ ብዙዎች በመሆናቸው፣ ‹‹ሁሌም አዳዲስ ሥራዎችና ቦታዎች ነው የሚፈልጉት።›› የመሳይ አስተያየት ነው።

እናም እነዚህ የስዕል ማሳያዎች መኖራቸው አንድም ገበያውን ለመሳብ ይጠቅማሉ። ዘርፉ ላይ በቂ ትኩረት ከተደረገም በዚህ መንገድ ገቢውና ገንዘቡ በራሱ ጊዜ እንደሚመጣም መሳይ ጠቅሰዋል።

ራኬብም በበኩላቸው የስዕል ጥበብ ከእይታ ባሻገር የገቢ ጥቅም እንዳለው ያነሳሉ። ለዚህም በየከተማው ከአንድ ሺሕ በላይ ማሳያዎች ያሉባትን ለንድን ከተማን በምሳሌነት ማስቀመጥ ይቻላል ብለዋል። ‹‹መጀመሪያ አርቲስቱን ይረዳሉ። ጋለሪም እንደ ባህል መለዋወጫ እንጂ እንደ ሱቅ አይታይም። ከዛም አልፎ ተቋማት አሉ፤ ባህልን የሚንከባከቡ።›› ብለዋል። በዚህ አካሄድ በኢትዮጵያም ስዕልን ኢንደስትሪ ማድረግ ይቻላል ሲሉ ጠቅሰዋል።
‹‹ግን ትኩረት ያስፈልጋል። እነሱን [አርቲስቶችን] በመርዳት ነው የሚጀመረውና ሁሉም ይህን መረዳት አለበት።›› ብለዋል።

ይህ ሲሆን የስዕል ጥበባቸውን ይዘው በሰው አገር የሚገኙ እንደ ተስፋዬ ያሉ ሰዓልያን፣ እንደ ስምረትም በአገራቸው እየለፉና በውጣ ውረድ መካከል የሙያ እርካታቸውን ለመሙላት ከትርፍ ጎድለው እየደከሙ ላሉ ለውጥ ይመጣል። አገርም የገቢ ምንጯን ለማስፋት አዲስ በር ይከፍትላታል።

ቅጽ 2 ቁጥር 62 ጥር 2 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com