ባህር ዳር ከተማ አንድ ሊትር ቤንዚን በጥቁር ገበያ እስከ 70 ብር እየተሸጠ ነው

Views: 349

በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች የነዳጅ እጥረት የተከሰተ ሲሆን በባህር ዳር ከተማ ተባብሶ አንድ ሊትር ቤንዚን በጥቁር ገበያ እስከ 70 ብር ድረስ እየተሸጠ ነው። የከተማ ውስጥ የትራንስፖርት አገልግሎቶችም በከፊል ሥራ አቁመዋል።
በባህርዳር ከተማ በተከሰተው እጥረት ሳቢያ በሕገወጥ መልኩ በጥቁር ገበያ በተለይም በከተማው ቀበሌ 07 እና 14 ቤንዚን እየተሸጠ ሲሆን፣ ባጃጆችም በዚህ ዋጋ ገዝተን አያወጣንም በሚል የታሪፍ ጭማሪ ማድረጋቸውን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ነዋሪ ይናገራሉ።
ከኹለት ሳምንት በላይ ያስቆጠረው እጥረት፣ መሠረታዊ ምክንያቱ ባለመታወቁ የተለያዩ መላምቶች ከእጥረቱ ባሻገር የተለያዩ ውዥንብሮን መፍጠሩንም ነዋሪዎች ተናግረዋል። በከተማዋ የፍላጎት መጨመር እና የነዳጅ አቅርቦት ማነስን ተከትሎ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ አልፎ አልፎ የነዳጅ እጥረት ከዚህ በፊት ቢኖርም፣ አሁን የተከሰተው አይነት እጥረት ግን ያልተለመደ መሆኑን ብሎም የእለት ተእለት እንቅስቃሴያቸውን እንዳወከባቸው ነዋሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ከኹለት ሳምንት በፊት ከሱዳን ጋር የሚያገናኘው የመተማ መንገድ ላይ በተደጋጋሚ የሚያጋጥሙ እገታዎችን ተከትሎ፣ መንግሥት በወሰደው እርምጃ መስተጓጎል ተፈጥሯል በሚል የቀረበው አስተያየት ትክክል አይደለም የሚሉት የክልሉ ንግድ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አብዲሳ ገበያው ይናገራሉ። ከጅቡቲም ሆነ ከሱዳን የሚገባው ነዳጅ ላይ ምንም አይነት መስተጓጎል የለም የሚሉት ኃላፊው፣ ይልቁንም ሆነ ተብሎ የተፈጠረ የነዳጅ ማከማቸት ችግሩን አባብሶ እዚህ አድርሶታል ብለዋል።
እንደ ዋነኛ የችግሩ ምንጮች ወደቦች ላይ ያለውን የወረፋ መብዛት፣ የነዳጅ አከፋፋይ ድርጅቶች የተሽከርካሪዎች ማርጀት እንዲሁም ማደያዎች የመጠባበቂያ መጠን አልፎ እስከሚያልቅ ድረስ ያለማሳወቅ መሠረታዊ ችግር ናቸው ብለዋል።
በተጨማሪም የመንገድ ሥራ ድርጅቶች ከሚያስፈልጋቸው በላይ የመያዝ እና መደበቅ አንዱ ምክንያት ሲሆን፣ የሚመለከተው አካል የቁጥጥር ሥራ ከመሥራት አንጻር አቅም ማነስ አለ ብለዋል። ኃላፊው ስለ ጥቁር ገበያ የማውቀው ነገር የለም ያሉ ሲሆን፣ እንዲህ ዓይነት እጥረቶች ላይ ተመሳሳይ ነገሮችን እንደሚሰሙ፤ ነገር ግን ተጨባጭ ነው ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል።
አክለውም ሳምንቱን ሙሉ ተጨማሪ ቤንዚን ሲገባ እንደነበር እና እስከ ሰኞ ድረስ ተጨማሪ እንደሚገባ፤ ይሀም እጥረቱን ያረጋጋዋል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።
‹‹በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደ መፍትሔ አይተን የምንንቀሳቀሰውም ነዳጅን የሚደብቁ አካላት ላይ የቁጥጥር እና የክትትል ሥራ መሥራት ላይ ሲሆን፣ በተጨማሪም ነዳጅ በአግባቡ ለተፈለገው አገልግሎት ብቻ እንዲውል የማድረግ እና የሚመለከተው አካል የማጣራት ሥራ እንዲሠራ ይደረጋል›› ብለዋል።
ወደ ክልሉ የተላከውን እና የገባውን የነደጅ መጠን ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመተባበር የማጣራት እና የመከታተል ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ዋና ኃላፊ ዓለማየሁ ፀጋዬ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፤ እንደ አገር ከአቅርቦት ጋር በተያያዘ ምንም አዲስ ነገር እንዳልተፈጠረ እና እንቅስቃሴው እንደተለመደው መሆኑን ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 62 ጥር 2 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com