ገቢዎች ሚኒስቴር በታኅሳስ ወር 18.1 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን አስታወቀ

Views: 703

የገቢዎች ሚኒስቴር በታኅሳስ ወር ከ18.1 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን አስታወቀ። በታኅሳስ ወር መሥሪያ ቤቱ 18 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰሰብ አቅዶ
የነበረ ሲሆን፣ ከእቅዱ በላይ ማሳካት መቻሉ ተገልጿል።

በተመሳሳይ ወርም ከአገር ዉስጥ ገቢ 8.59 ቢሊዮን ብር የተሰበሰበ ሲሆን፣ ከቀረጥና ታክስ 9.5 ቢሊዮን ብር ሰብስቧል። በአጠቃላይ የወሩን እቅድ 102 በመቶ ማሳካት መቻሉም ተጠቅሷል። የገቢ መጠኑም  ካለፈዉ ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ2.6 ቢሊዮን ብር ብልጫ ሲኖረው፣ የ23 በመቶ ጭማሪ  አሳይቷል።

ባለፉት ስድስት ወራትም ሊሰወር የነበረ 7.8 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡ የተገለፀ ሲሆን፣ ገንዘቡንም  ለመሰብሰብ 2 ሺሕ 225 ግብር ከፋዮችን ኦዲት በማድረግ ላይ መሆኑ ተገልጿል። በግማሽ ዓመቱም ወለድና ቅጣትን ጨምሮ 17.3 ቢሊዮን ብር ገቢ በኦዲት መሰብሰቡ ተገልጿል።

የግብር ከፋዮች የሕግ ተገዢነት ደረጃ ዝቅተኛ መሆን፣ ግብር ከፋዮች ሰነድ እንዲያቀርቡ ሲጠየቁ ፍቃደኛ አለመሆን፣ የአካውንቲንግ ሶፍት ዌር መለያየት ለኦዲተሮቹ ፈተና መሆን፣ የገበያ ዋጋ መረጃ አለመኖርና በየዘርፉ የትርፍ ህዳግ ማነጻጸርያ የሕግ ማዕቀፍ ችግርና ከቅሬታ ሰሚ ተቀባይነት ማጣት ችግሮች መስተዋላቸው ታውቋል።

ኦዲት የሚደረጉ ድርጅቶች በአድራሻቸው አለማግኘትና ለረጅም ጊዜ ሂሳባቸውን ያላሳወቁ ድርጅቶች  መኖራቸው እንዲሁም  የ3ኛ ወገን መረጃዎችና  ከፌደራል እና ክልል ተቋማት ለኦዲት ሥራዎች በወቅቱ ከማግኘት አኳያ አስቸጋሪ መሆናቸው ባለፉት ስድስት ወራት የኦዲት ሥራዎችን ለማከናወን ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እንደነበሩም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል። በኅዳር ወር 18.3 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 19.2 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ ችሎ የነበረ ሲሆን፣ የእቅዱን 104 በመቶ ማሳካት እንደቻለ መግለፁ ይታወሳል።

ቅጽ 2 ቁጥር 63 ጥር 9 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com