ሰሎሜ ሾው ከፋና ቴሌቪዥን ጋር ያለውን ውል አቋረጠ

Views: 622

በፋና ቴሌቪዥን ለአንድ ዓመት ተኩል በሳምንት አንድ ጊዜ እየተዘጋጀ ሲተላለፍ የነበረው ሰሎሜ ሾው ከመጪው ሳምንት ጀምሮ ከፋና ቴሌቪዥን ጋር ያለውን ውል በይፋ እንዳቋረጠ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ለአዲስ ማለዳ አረጋገጠ።

ሰሎሜ ሾው በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሥነልቦናዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር የተለያዩ ባለሙያዎችን በመጋበዝ ትንታኔ እንዲሰጡ እና በጉዳዮች ላይ እይታቸውን በማጋራት የሚቀርብ ፕሮግራም ነበር። ከአንድ ዓመት በላይም በፋና ቴሌቪዥን ዘወትር ረቡዕ ምሽት 2 ሰዓት ከ30 ጀምሮ ሲተላለፍ ሲታይ ቆይቷል።

የሶሎሜ ሾው በተለይም ሰፊ የሆነ የዝግጅት ክፍል መዋቅር እንደነበረው እና በጥናት ላይ የተመሠረቱ ዝግጅቶችን ሲያዘጋጅ መቆየቱን ለዝግጅት ክፍሉ ቅርበት ያላቸው የአዲስ ማለዳ ምንጮች ይናገራሉ። ምን አልባትም የዝግጅቱ መቋረጥ ከማስታወቂያ እጥረት ጋር የተያያዘ ሳይሆን እንደማይቀር እና ይህም ሆነ ተብሎ በብሮድካስተሩ ጫና የመጣ ሳይሆን እንደማይቀርም ይናገራሉ።

‹‹ተባባሪ አዘጋጆች በተለያየ ምክንያት ከእኛ ጋር ይሠራሉ፤ በተለያየ ምክንያት ከእኛ ጋር ያላቸውን ውል ደግሞ ሊያቋርጡ ይችላሉ። የሰሎሜ ሾው መቋረጥ ከዚህ የተለየ ምንም ምክንያት የለውም›› ሲሉ የፋና ቴሌቪዝን የመዝናኛ ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ ዘካርያ ብርሃኑ ለአዲሰ ማለዳ ተናግረዋል። ‹‹የሰሎሜ ሾው ከዚህ ሳምንት በኋላ አይተላለፍም›› ሲሉም ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ዋና አዘጋጁ በፋና ብሮድካስቲንግ በኩል ‹‹ፕሮግራሙ እንዲቋረጥ አልተደረገም›› ያሉ ሲሆን፣ ‹‹ሰሎሜ ሾው ከእኛ ጋር የነበረው ቆይታ ተጠናቋል፤ በሰላማዊ መንገድም ተለያይተናል››ሲሉም አክለዋል። በቀጣይ የሚተካኩ ፕሮግራሞች ይኖራሉ፤ ይህም አዲሰ ነገር አይደለም፤ ሲሉዘካርያስ ለአዲሰ ማለዳ አስረድተዋል። የሰሎሜ ሾው እና ፋና በሠላማዊ መንገድ እንደተለያዩ ዘካርያስ ይናገሩ እንጂ፣ በሰሎሜ ሾው አዘጋጆች እና በጣቢያው መካከል ግን ችግሮች መኖራቸውን ሳይጠቁሙ አላለፉም። በመገናኛ ብዙኀን በተለይም ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ከተባባሪ አዘጋጆች ጋር ራሳቸው በሚያወጧቸው ሊያስማማቸው በሚችል ውል መሰረት ሥራዎችን በጋራ እንደሚሠሩ ይታወቃል። በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የመገናኛ ብዙኀን ፈቃድ እና ምዝገባ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ፋንታሁን አስረስ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ተባባሪ አዘጋጆች ከቴሌቪዥን ጣቢያዎች እና ከሬዲዮ ጣቢያዎች ጋር ስለሚኖራቸው ስምምነት በባለሥልጣኑ በኩል የተቀመጠ መስፈርት አለመኖሩን ጠቁመዋል።

በኹለቱ በኩል አለመስማማት ቢኖር እንኳን ችግራቸውን የሚፈቱት ኹለቱ ባደረጉት ስምምነት መሆኑንም ይገልፃሉ። ‹‹እኛ ለጣቢያዎች የምናሳስባቸው ነገር ቢኖር፣ ከተባባሪዎች ጋር ሲሠሩ የንግድ ፈቃድ እንዳላቸው እና ሕጋዊነታቸውን ማረጋገጣቸውን ነው።›› ብለዋል።

በተባባሪ አዘጋጆች እና በጣቢያዎች ስለሚኖረው ስምምነት የብሮድካስት ባለሥልጣን መስፈርት የለውም ያሉት ፋንታሁን፣ ይሁን እንጂ መገናኛ ብዙኀን የዜና ዘገባዎችን፣ የትምህርት፣የሕጻናት፣ የሴቶች ጉዳይ እና ሌሎችንም በተባባሪ አዘጋጆች አልያም በመገናኛ ብዘኀን ባለቤቶች መሥራት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን እንደሚያስገድድ ይናገራሉ።

በኢትዮጵያ ዐስር የመንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያዎች (ቅርንጫፎችን ሳያካትት) ሲኖሩ፣ ኻያ ሦስት የንግድ ቴሌቪዥኖች በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ተመዝግበው ፈቃድ አግኝተዋል።

ሰሎሜ ታደሰ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ቦታዎች በኃላፊነት ያገለገሉ ሲሆን፣ ለአብነት ያህልም በፖለቲካው ዘርፍ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት መንግሥት ቃል አቀባይና በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ፣ በኢትዮጵያ ሬዲዮ እና ቴሎቪዥን የመጀመሪያዋ ሴት ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆን፣ በ‹የኛ› የሬዲዮ ፕሮግራም በዋና ዳይሬክተርነት የመሩ ናቸው። በሴቶች መብት ላይ ባላቸው የረጅም ዓመት አቋምም ይታወቃሉ።

ሰሎሜ ዳግም ወደ ፖለቲካው ለመመለስ በምርጫ በ1997 ለአገር አቀፍ ምርጫ ለመወዳደር ቢሞክሩም፣ የእጩ ተወዳዳሪዎች ዝርዝር በመሙላቱ በእጣ ተለይተው ሳይወዳደሩ መቅረታቸው ይታወሳል። አዲስ ማለዳ ሰሎሜ ታደሰን በስልክ ብታገኛቸውም አስተያየት ለመስጠት የሚችሉበት ሁኔታ ውስጥ እንዳልሆኑ በመግለጻቸው፣ የዝግጅታቸውን የወደፊት እጣ ፈንታም ሆነ የውሉን መቋረጥ ምክንያት ለማወቅ ሳይቻል ቀርቷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 63 ጥር 9 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com