የኢትዮጽያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሙሉ የመዋቅር ለዉጥ ሊያደርግ ነዉ

Views: 144

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከተደራጀበት አላማ አንፃር መሰረቱን የሳተ መዋቅር በመያዙ የሰብዓዊ መብት ተልዕኮን ለማስፈፀም በሚረዳ መልኩ የመዋቅር ለውጥ አድርጎ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ገለፀ። የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) እንደገለፁት የተቋሙን አቅም እና ተግዳሮቶች የሚለይ ፈጣን የዳስሳ ጥናት፣ የሕግ ማእቀፍ ክፍተቶችን መሙላት፣ በሽግግር ወቅት የዕለት ተዕለት ሥራዎችን ስለማስቀጠል እና አዲስ የሰብዓዊ መብት ስትራቴጂ መንደፍ የኮሚሽኑ የስድስት ወር ዋና ዋና ተግባራት ነበሩ፡፡

በተባበሩት መንግሥታት በፀደቀዉ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት ብቃት እና ገለልተኛ መመዘኛ መስፈርት መሰረት የተሰጠዉ ደረጃ ‹‹መስፈርቱን የማያሟላ›› መሆኑን ዳንኤል ገልፀው ኮሚሽኑ የመቋቋሚያ ማእቀፉን፣ የአሰራር ነፃነቱንና ብቃቱን በማሻሻል በዓለም አቀፉ መድረክ ያለውን ደረጃ ለመቀየር የሕግ ማዕቀፍ ክፍተቶች ጥናቱ የሚያግዝ እንደሚሆን ገልፀዋል።

ኮሚሽነሩ በ2012 በጀት ዓመት በስድስት ወራት 704 አቤቱታዎችን ማስተናገዱን፣ 191 አቤቱታዎች በኮሚሽኑ ሥልጣን ተቀባይነት እንዳገኙ፣ ለ22ቱ መፍትሄ ሰጥቶ 102 ጉዳዮች በምርመራ ሂደት እንዳሉ እንዲሁም 49 ጉዳዮች በማስማማት ሂደት ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ኮሚሽኑ መጭውን አገራዊ ምርጫ በተመለከተ ስልታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ለማድረግ ምክክር እና ዝግጅት መጀመሩንና ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር እና ዝግጅት መጀመሩን ዋና ኮሚሽነሩ ተናግረዋል። በሌላ በኩል ኮሚሽነሩ አዲስ በሚውጡ አዋጆች ላይ ከሰብዓዊ መብቶች አንፃር አስተያየት እና ምክረ ሀሳብ በመስጠት እገዛ እያደረገ እንደሆነና ወደፊትም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።

ኮሚሽኑ የ2012 በጀት ዓመት የስድስት ወር ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቀት ከምክር ቤቱ አባላት ትችቶችን አስተናግዷል። በስድስት ወር ውስጥ ኮሚሽኑ ያከናወናቸው ተግባራት በቁጥር ያለመገለፃቸው እና ችግሮች በጥልቀት ተመርምረው ለምክር ቤቱ አለማቅረባቸው በዋናነት የኮሚሽኑን ሪፖርት ያስተቹ ነጥቦች ናቸዉ። ኮሚሽኑ የማረሚያ ቤቶችን መደበኛ የክትትል ሥራ በተመለከተ እና የምርጫ ወቅት የሰብዓዊ መብቶች ክትትል በሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ላይ በተደረገው ሕዝበ ውሳኔ ላይ ያደረገውን ክትትልና ውጤት ‹‹በመጠናቀር ላይ ይገኛል›› በሚል መግለፁ ከምክር ቤቱ አባላት ጠንካራ ትችቶችን አንዲያስተናግድ ምክንያት ሆነዋል።

በተጨማሪም በኮሚሽኑ የተሠራዉ ሥራ በቂ እንዳልሆነ እና በአገሪቱ ያለውን ወቅታዊ የሰብዓዊ መብት አያያዝ በዝርዝር አቅርቦ ለመንግሥት ማሳወቅ እንደነበረበት ከምክር ቤቱ አባላት ትችት ቀርቦበታል። የምክር ቤቱ አባል የሆኑት ሽሻይ ሀ/ስላሴ በተመረመሩት ውጤቶች ላይ ዝርዝር መግለጫ ያልተሰጠበት ገና በሂደት ላይ ያለ እና ያለተሟላ ሪፖርት ነው ሲሉ ተችተዋል። የፍትህና ዴሞክራሲ ቋሚ ኮሚቴ በሪፖርቱ ላይ የታዩ ጉድለቶችን እና በቀጣይ ሊስተካከሉ ይገባቸዋል ያላቸውን ነጥቦች አስቀምጧል።

ከተቀመጡት ጉድለቶችም ለመንግሥት በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የማማከር ሥራ መሥራት እንዳለበት እና በቀጣይ የተሻለ ሪፖርት መቅረብ እንዳለበት ኮሚቴው አስቀምጧል። እንዲሁም ለቀጣዩ አገራዊ ምርጫ እቅድ አቅዶ ወደ ሥራ መግባት እንዳለበት ቋሚ ኮሚቴው በሪፖርቱ ላይ በሰጠዉ ማጠቃለያ ገልጿል።

ቅጽ 2 ቁጥር 64 ጥር 16 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com