ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን መምራት ከጀመሩ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በርካታ ለውጦችን እንዳመጡ ይነገርላቸዋል። ከእሳቸው በፊት ለመሥራት ይታሰቡ ያልነበሩ ጉዳዮችን ከማንሳት ጀምሮ፣ በመንግሥትም የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ሳይቀር ይፋ በማድረግ ተቋሙ ተቀባይነቱ እንዲጨምር ማድረጋቸው ይነገራል። ባሳለፍነው ሳምንትም፣ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል እየተካሄደ ስላለው ጦርነት የመጀመሪያውን ዙር ሪፖርት ተቋማቸው ከተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ጽሕፈት ቤት ጋር በመሆን አውጥቷል። ስለሪፖርቱ አጠቃላይ ውጤት፣ እንዲሁም ስለተቀባይነቱ ከወቅታዊው ሁኔታ ጋር በማነፃፀር የአዲስ ማለዳው ቢንያም ዓሊ ከእሳቸው ጋር ቆይታ አድርጓል።
ባለፈው ሳምንት የወጣው ሪፖርት ተቀባይነቱ ምን ይመስላል?
ሪፖርቱ በአገር ውስጥም በዓለም አቀፍ ደረጃም ጥሩ ምላሽና ተቀባይነት አግኝቷል ብዬ አምናለሁ። በመጀመሪያ ደረጃ በኢትዮጵያ መንግሥት የተሰጠው ምላሽ የሚያበረታታ ነው። በአንዳንድ የተወሰኑ ጉዳዮች ላይ የተወሰኑ የሐሳብ መለያየቶች ቢኖሩም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት አጠቃላይ ሪፖርቱን፣ ዋና ዋና ግኝቶችና መደምደሚያዎቹን፣ እንዲሁም ምክረ ሐሳቦችን የሚቀበል መሆኑንና ሥራ ላይ ለማዋልም ከመንግሥት የተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ኢንተር ሚኒስትሪያል ኮሚቴ ማቋቋሙ በራሱ አንዱ አበረታች ምላሽ ነው። በሌላ በኩል፣ በጣም በርካታ የአውሮፓ አገራት ከአሜሪካም፣ ከእንግሊዝም ጥሩ ምላሽ ተገኝቷል። ሪፖርቱን ካጠኑትና በደንብ ካነበቡት በኋላ ከ16 በላይ የሚሆኑ አገሮች በጋራ ሆነው ያወጡት የጋራ መግለጫ አለ። ለሪፖርቱም፣ ለግኝቱም፣ ለሥራውም ምስጋናቸውንና አድናቆታቸውን በመግለጽ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ምክረ ሐሳቡን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥሪ ማስተላለፋቸው ይታወቃል። ይህም ጥሩ ምላሽ ነው።
በቅርቡ በተባበሩት መንግስታት ፀጥታው ምክር ቤት የቀረበው ውይይት ላይ የምክር ቤቱ አባሎችና የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ ኃላፊዎችም ጭምር ሪፖርቱን ተቀብለውና ድጋፍ ሰጥተው በተቀመጠው ምክረ ሐሳብ መሰረት ጥሪ ሲያቀርቡ ነበር። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው አብዛኛው ማኅበረሰብ ባገኘነው ግብረ መልስ መሠረት ቀና ምላሽ ተሰጥቷል። ይህም ተገቢ ነው ብለን እናምናለን። ነገር ግን ደግሞ፣ በማንኛውም ይህን በመሰለ ሥራ እንደሚጠበቀው ኹሉም ሰው በሪፖርቱ ይስማማል ማለት አይደለም። ኹሉም በግጭቱ ውስጥ የተሳተፉ ቡድኖች ይቀበሉታል ማለት አይቻልም። የተለየ ሐሳብ ያንፀባረቁ ወገኖችና ወንድሞች መኖራቸውን እገነዘባለሁ። እነሱም ቢሆን ግን ጊዜ ወስደው ሪፖርታችንን በጥሞና ቢያነቡትና ቢረዱት ከምክረ ሐሳቦቻችን ጋር ይስማማሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
የዘንድሮው ሪፖርት ከዚህ ቀደም ከወጡት በምን ይለያል?
ይህ ሪፖርት እስከዛሬ ይደረጉ ከነበሩት ሪፖርቶች የሚለየው አንደኛ፣ በኹለት ነጻ በሆኑና የተቋቋሙበት ዓላማ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ሥራ በሆኑ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ቦታው ላይ በመገኘት የተካሄደ የምርመራ ሥራ ሪፖርት መሆኑ ነው። እርግጥ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም ቢሆን ከዚህ በፊት ከትግራይ ግጭት ጋር በተያያዙ የተነሱ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን በተመለከተ ብዙ ዘገባዎችን ሲያወጣ እንደነበረ ይታወሳል። ይሄኛው ግን፣ ከዚህ በፊት ከነበሩት የሚለየው አገር ውስጥ ያለ ነጻ የሆነ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ብቻ ሳይሆን፣ ከተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ጽሕፈት ቤት ጋር ተጣምረው ይህን የመሰለ ጣምራ የምርመራ ሥራ መሆኑ ነው።
የጋራ ሪፖርቱ በኢትዮጵያ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በዓይነቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያ ነው። በዚህ መጠን በኹለቱ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ጥምረት የጋራ ምርመራ ተደርጎ የማያውቅ ስለሆነ፣ ይህ በዓይነቱ ለየት ያለ የመጀመሪያ ሥራ ነው። ምናልባት ከዚህ ከኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ምርመራ አልፎ ለሌሎችም አገሮች እንደጥሩ ምሳሌ ተደርጎ እንደልምድ ሊወሰድ የሚችል ጭምር ነው። ለምሳሌ፣ የአሜሪካ መንግሥት ባወጣው መግለጫ ላይ ሠነዱ ለሌላም ቦታ በምሳሌነት ሊያገለግል የሚችል አሠራርና ሪፖርት ነው ሲል አረጋግጦታል።
በትግራይ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የተፈፀመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በተመለከተ የተለያዩ ሐሳቦች ሲንሸራሸሩ የቆዩ ሲሆን፣ ይህኛው ሪፖርት ቦታው በመገኘት ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች በቀጥታ በማነጋገር፣ ከልዩ ልዩ ምንጮችም መረጃዎችን በማሰባሰብ የተሠራ ትክክለኛ፣ እውነተኛና ነጻ የሆነ ሪፖርት ስለሆነ በዚህ መልኩ ከተለያዩ ዘገባዎች በጣም የተለየ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።
ባካሄዳችሁት የማጣራት ሒደት ለፖለቲካ ትርፍ በፕሮፓጋንዳ መልክ ሲሠራጩ የነበሩና ውሸት ሆነው ያገኛችኋቸው ነበሩ?
መቼም ቢሆን በጦርነት ውስጥ ተፋላሚ የሆኑ ወገኖች የየበኩላቸው የራሳችን እውነት ብለው የሚሉት ነገር አለ። ኹለተኛ፣ ማንም መረዳት እንደሚችለው በጦርነት ውስጥ የሚፋለሙ ወገኖች ደግሞ የሚዲያ የፕሮፓጋንዳ ጦርነትም ላይ ይጠመዳሉ። ይህ ስለሆነም ተፋላማዎቹ በራሳቸውም ሆነ በደጋፊዎቻቸው አማካይነት የሚያሰራጩት የየበኩላቸው መረጃ ይኖራል። የበኩላቸው ትርጓሜ፣ የበኩላቸው ትርክት ይኖራቸዋል። የዚህ ዓይነቱ ገለልተኛ ምርመራ ሥራ የሚያስፈልገው ከእንዲህ ዓይነት የተፋላሚ ወገኖችና ደጋፊዎቻቸው ከሚነገረውና ከሚሰጠው መረጃ ባሻገር ትክክለኛውና እውነተኛው ነገር ምንድን ነው የሚለውን በመረጃና በማስረጃ በማስደገፍ በምርመራ ስልት ማጣራትና ማረጋገጥ ነው። እኔ እንደሚመስለኝ ከእንግዲህ ወዲያ በትግራይ ግጭት ውስጥ የተፈፀመ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምንድን ነው ብሎ ትክክለኛ መረጃ ለማየት የጣምራ ሪፖርቱ አንድ አሳማኝ የመረጃ ምንጭ ይሆናል።
በእርግጥ ይህ በጣምራ የተዘጋጀው ሪፖርትም ቢሆን ግን ኹሉንም ነገር በዝርዝር ዘግቦ ይጨርሳል ማለት አይደለም። ቢያንስ ጠቅላላ ባህሪው ምን የመሰለ እንደሆነ በትክክል በማስረጃ ላይ ያመላክታል። ቀሪው በዚህ ሪፖርት ያልተካተቱ ጉዳዮችም በቀጣይ በተከታታይ በሚወጡ የምርመራ ሥራዎች መረጋገጣቸው ይቀጥላል ማለት ነው። በቦታው ላይ በመገኘት እውነተኛ የሆነ ገለልተኛ የሰብዓዊ መብት ታሪኩ ወይም ሁኔታው ምንድን ነበረ ተብሎ ሲጠየቅ ሊታይ የሚገባ አሳማኝ ሠነድ ነው።
በሪፖርቱ ከተካተቱት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መካከል በሕፃናት ላይ ጭምር የሚፈጸም በርካታ የአስገድዶ መድፈር ድርጊት ተካቷል። ይህ አይነት ዘግናኝ ድርጊት የሚፈጸምበት ሁኔታ ምንን ያመለክታል?
በዚህ በግጭት ውስጥ ባደረግነው የምርመራ ሥራ፣ ባጣራነውና ባረጋገጥነው መሠረት ልዩልዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ጾታን መሠረት ተደርጎ የሚፈጸመው ጥቃት ነው። በሕፃናት ሴቶች በወንዶችም ላይ ጭምር የተፈጸመ ወሲባዊ ጥቃት አንዱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ መገለጫ ነው። በጣም አሳዛኝና በጣም ጭካኔ በተሞላበት መንገድ የተፈተመም ነው። በሪፖርቱ ያረጋገጥነው አነስተኛውን መጠን እንጂ ሙሉ የጥሰቱን መጠን አልደረስንበትም። ምክንያቱም፣ የዚህ አይነት ጥቃት በጠባዩ ምስጢራዊ ሆኖ የሚቀር ነው። አብዛኞቹ የደረሰባቸውን በአደባባይ ስለማይናገሩ ሙሉ መጠኑንም ልናውቀው አንችልም። ነገር ግን ቢያንስ ምን አይነት ጾታ ተኮር ጥቃት እንደነበር፣ እንዲሁም እነዚህ ጥቃቶች በግጭት በተሳተፉት ኹሉም ወገኖች የተፈጸሙ መሆኑን አረጋግጠናል። ይህ ስለሆነም አንደኛ የአጥፊዎችን ተጠያቂነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ኹለተኛ፣ የተጎዱትንና የተጠቁትን ሰዎች ሕይወታቸውን መልሶ ማቋቋም እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው።
የተፈናቃዮችን ሁኔታና የዕርዳታ ስርጭቱን በተመለከተስ ምን ተመልክታችኋል?
ጦርነት ሌላው መገለጫው ደግሞ ለበርካታ ሰዎች መፈናቀል ምክንያት መሆኑ ነው። አንደኛ ቀጥታ በጦርነቱ ምክንያት ከአካባቢያቸው የሚፈናቀሉ ሰዎች አሉ። ኹለተኛ ደግሞ፣ በግዳጅ ከአካባቢያቸው እንዲፈናቀሉ የሚደረጉ ሰዎች አሉ። ይህ ሁኔታ ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ ቀውስ ፈጥሯል። ሰዎች መፈናቀላቸው ብቻ ሳይሆን፣ ንብረቶቻቸው የተዘረፉባቸው፣ የወደሙባቸው በርካታ ሰዎች አሉ። ስለዚህ፣ በጣም አሳሳቢ የሆነ መጠነ ሠፊ የሰብዓዊ ቀውስ ፈጥሯል። እነዚህ በጦርነቱ የተጎዱ ሰዎች መልሶ ማቋቋምና ሕይወታቸው ወደነበረበት እንዲመለስ ማድረግ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው።
የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦትን በሚመለከት ልዩልዩ እንቅፋት አጋጥሞ እንደነበር ተመልክተናል። በግጭት ውስጥ የሚቀርብ አቅርቦት ስለነበረ የፀጥታ ሁኔታውና ሠላም አለመኖሩ ዋነኛውና የመጀመሪያው እንቅፋት ሁኖ አግኝተነዋል። በመቀጠል በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ ኹሉም ወገኖች የሚያደርጓቸው አንዳንድ መንገድ የመዝጋት ሁኔታዎች ለሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦቱ እንቅፋት ፈጥሮ የነበረ መሆኑን ተመልክተናል። ነገር ግን፣ ከዚህ ባለፈ መጠን በልዩ ልዩ ወገኖች ይዘገብ እንደነበረው መጠን የኢትዮጵያ መንግሥት ሆነ ብሎ አስቦ አቅዶ የዕርዳታ እህልን በመከልከል ረሃብን እንደጦር መሣሪያ ለመጠቀም ሠርቷል የተባለው አባባል ግን በማስረጃ የተደገፈ ሆኖ አላገኘነውም።
የጦር ምርኮኛን በተመለከተ የተመለከታችሁት የአያያዝ ሁኔታ አለ?
የፌደራሉ መንግሥት የተናጥል ተኩስ አቁም አድርጎ ከትግራይ ክልል ከወጣ በኋላ ትግራይ ክልል ልንደርስ የምንችልበት ሁኔታ ባለመፈጠሩ በሚፈለገው መጠን የሚፈለጉ ቦታዎች ላይ በመድረስ የፈለግናቸውን ኹሉ በማነጋገር ምርመራ ለማካሄድ እንዳንችል ውስንነት ፈጥሮብናል። በሌላ በኩል፣ በተቻለ መጠን ምርኮኛ የነበሩና ከሲቪል ማኅበረሰብም ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች፣ ቤተሰቦቻቸውን፣ የአካባቢው ማኅበረሰብን፣ የሕክምና ባለሙያዎችንና ተቋማትን፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን፣ ዕርዳታ ሰጪዎችንና የመንግሥት ተቋማትን የመሳሰሉትን ኹሉ በማነጋገር ነው ይህንን ሪፖርት ያዘጋጀነው። በዚህ መንገድ ብዙ ዓይነት የመብት ጥሰቶችን ነው የተመለከትነው። ሲቪሎችን ከማጥቃት አንስቶ ሕገ-ወጥ ግድያዎች፣ ማፈናቀሎች፣ የማሰቃየት ዕርምጃ፣ ወሲባዊ ጥቃት እና የጦር ምርኮኞች ላይ የተፈጸመ ተገቢ ያልሆነ አያያዝን የመሳሰሉ ተመልክተናል። እነዚህ ኹሉ ድርጊቶች በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግም ሆነ በእስረኛ አያያዝ ሕግ የተከለከሉ ጥሰቶች ስለሆኑ ሪፖርቱ በዝርዝር የሚያሳይ ነው።
የሚፈጸሙ ጥፋቶችን በተመለከተ ተጠያቂነትን ለማምጣት ምን መደረግ ይገባል ይላሉ?
የኢትዮጵያ መንግሥት ለሪፖርቱ በሰጠው ምላሽ እንደገለጸው፣ ከዚህ ቀደምም ገልፆ በነበረው መሠረት እንደሚታወቀው በተወሰነ አይነት ወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎችን በተለይ ጾታን መሠረት ካደረገ ጥቃት ጋር በተገናኘ ጥፋት ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ ወታደሮች ላይ ዕርምጃ መውሰዱን መግለጹ ይታወሳል። ነገር ግን፣ በጉዳዩ ላይ የተሟላ መረጃ ስላልተሰጠ ለወደፊት የተሟላ መረጃ እንሰጣለን ያሉትን መጠበቁ ይሻላል።
በዚህ ሪፖርት መሠረት የተጠያቂነት ዕርምጃ ይወሰዳል ብለን እንጠብቃለን እንጂ፣ ከዚህ ቀደም የተወሰደ የተጠያቂነት ዕርምጃ የለም ። ለወደፊት ግን ሪፖርቱ መነሻ ይሆናል ብለን እንጠብቃለን። ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የወንጀል ምርመራ ማካሄድን ይጠይቃል። በምርመራው መሠረት ክስ መስርቶ አጥፊዎችን በፍርድ ሒደት ማስቀጣት ይጠይቃል።
በቅርቡ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ የፍትሕ ስርዓቱን በማፋጠን ላይ የሚያመጣው ለውጥ ይኖራል?
የአስቸኳይ ጊዜው ዐዋጅ አገር ውስጥ የተፈጠረው ሁኔታ ከፈጠረው ስጋት አኳያ በፓርላማ የታወጀ ነው። ከሰብዓዊ መብት አንጻር ስንመለከተው ኹል ጊዜ እንዲህ አይነት ዐዋጅ የሰብዓዊ መብቶችን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል። ይህን ስለምናምን ስጋት ይፈጥርብናል። ለምን እንደታወጀ ግንዛቤ ቢኖረንም፣ በአንዳንድ መሠረታዊ መብቶች ላይ ገደብ ስለሚጥልና ለመንግሥት የሕግ አስከባሪ አካላት ሰፋ ያለ ሥልጣን ስለሚሰጥ የሰብዓዊ መብትን አደጋ ላይ እንዳይጥል አሳሳቢ ስለሚሆን ክትትል ማድረግ ጀምረናል። እስካሁንም ቢሆን የተወሰዱ ዕርምጃዎችና እስሮች ምንም በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም፣ እየተከታተልን ነው። ዐዋጁ መብትንና ጥበቃዎችን ሙሉ ለሙሉ ያስቀራል ማለት አይደለም። መሠረታዊ መብቶችን በማይጥስ መልክ ተግባራዊ መሆኑን ለማረጋገጥ ክትትልና ጥረት እያደረግን እንገኛለን።
ከተኩስ አቁሙ ወዲህ ተፈጸመ ስለሚባለው ጥሰት የማጣራት ሒደቱን እያካሄዳችሁ ነው?
ይሄኛው ሪፖርት የሚመለከተው እስከ ሰኔ መጨረሻ ድረስ ያለውን ነው። ከዛ ጊዜ በኋላ ግጭቱ ወደአጎራባች ክልሎች የተስፋፋ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በዙ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አቤቱታ እየተደመጠ መሆኑ ይታወቃል። ኹለታችንም ተቋሞች በየበኩላችን ከዛ በኋላ ያለውን ኹኔታ በሚመለከት ክትትልና ምርመራ እያደረግን ነው። ይህ ስለሆነም ምናልባት በአንድነት ወይም በየተራ በተናጥል የምናወጣቸው ሪፖርቶች ይኖሩናል።
በኦሮሚያ ወለጋ፣ በቤኒሻንጉልና የመሳሰሉትን አካባቢዎች በምርመራችሁ ውስጥ የማካተት ዕቅድ አላችሁ?
አዎን! ከሁኔታው አንጻር በትግራይ ክልል ተነስቶ ወደ አጎራባች ክልል የተስፋፋው ግጭት አብዛኛውን ትኩረት መሳቡ ቢታወቅም፣ ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ከግጭት ጋር የተያያዘ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያለው እዛ አካባቢ ብቻ አይደለም። ሌሎች አካባቢዎችም ከዛ ያላነሰ አሳሳቢ የሰብዓዊ መብት ሁኔታ በመኖሩ እሱንም አቅማችን በፈቀደ መጠን ለመከፋፈልና ምላሽ ለመስጠት ጥረት እያደረግን ነው።
ግን ተቋማዊ አቅማችን በጣም ውሱንነት አለው። በጣም በውሱን አቅም ነው እነዚህን ሁሉ ሥራዎች ለማከናወንና መፍትሔ ለመፈለግ ጥረት የምናደርገው። ሆኖም በቻልነው መጠን ጥረት እያደረግን ነው።
ሒደቱ እየቀጠለ፣ ቅሬታ እየቀረበ እናንተም ሪፖርት እያዘጋጃችሁ ነው ማለት ነው?
አዎን! የሚቀጥል ሥራ ነው፣ የሚያቋርጥ ሥራ ሳይሆን ኹሉም ቦታ ላይ በየጊዜው በዋና መሥራያ ቤታችንም፣ በቅርንጫፎቻችንም አማካይነት በርካታ ክሶች ይቀርቡልናል። እና እነዚህን መሠረት እያደረግን የምናካሂደው የምርመራ ሥራ አለ። ነገር ግን፣ አንባቢዎች አንዱ ሊረዱት ከሚያስፈልገው ነገር ውስጥ፣ ምርመራ የምናደርግባቸው ጉዳዮች በሙሉ ኹሉም የግድ የአደባባይ ሪፖርት ይቀርብባቸዋል ወይም ይወጣባቸዋል ማለት አይደለም። ይልቁንም በጣም በርካታ ጉዳዩች፣ ጉዳዩ የሚመለከተው የክልልና የፌዴራል መንግሥት ጽሕፈት ቤቶችና ኃላፊዎችን በማነጋገር ዕልባት ለማግኘት ጥረት የምናደርግበት ብዙ ሥራ አለ።
ስለዚህ ሁሉም ነገር ላይ የግድ ሪፖርት ይወጣል ማለት አይደለም። ነገር ግን አንከታተለውም ማለት አይደለም። ብዙ ያላግባብ የታሠሩ ሰዎች ጉዳይ፣ ለምሳሌ ክትትል እያደረግን ያለአግበብ የታሠሩ ሰዎች ከእስር እንዲለቀቁ ወይም የዋስትና መብት እንዲከበር ጥረት የምናደርግባቸውና ውጤት የምናገኝባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ። ግን ያንን ሁሉ ሪፖርት እናደርጋለን ማለት አይደለም። በመደበኛነት ከምናከናውነው ሥራ ውስጥ አንዱ እንዲህ ያለ የሰብዓዊ መብት ክትትል በየቀኑ ማካሄድ ነው።
ከመንግሥት የሚጠበቀው ምንድን ነው?
መንግሥትን ወይም ከመንግሥት ውጪ ያሉ ሌሎች ማናቸውም ወገኖች ቢሆኑ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በሚያደርገው የሰብዓዊ መብት ምርመራ ሥራ ትብብር ማድረግ አለባቸው። ራሳቸውን እንዲገኙ ከማድረግ አንስቶ በሮቻቸውን ክፍት ማድረግ፣ ለምርመራ ሥራው ተገቢ መረጃ መስጠት፣ የሚያውቁትን መረጃ ማጋራት፣ ትክክለኛና እውነተኛ መረጃ መስጠት የመሳሰሉትን ጨምሮ ተግባራዊ ዕገዛ ማድረግ ይጠበቃል።
እንዲሁም፣ ለሥራችን ድጋፍ መስጠታቸው በጣም ጠቃሚ ነው። ምክንያም ይህ ተቋም የሚሠራው ለሌላ ማንኛውም ዓላማ ሳይሆን ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ብቻ ነው። እና የሰብዓዊ መብቶች ደግሞ በማንኛውም ወገን ተጥሶ ሲገኝ ሪፖርት ያደርጋል፤ በመንግሥት ጸጥታ ኃይሎችም ይሁን ወይም ከመንግሥት ውጪ ባሉ ኃይሎች የተፈጸሙ ጥሰቶችን በሙሉ እንመረምራለን፣ እናጣራለን፣ ሪፖርት እናደርጋለን፣ የመፍትሔ ሐሳብ እናቀርባለን፣ አፈጻጸሙን እንከታተላለን።
ስለዚህ በምርመራ ሥራ ብቻ ሳይሆን ከሰብዓዊ መብት ጥሰት በኋላ ሊወሰዱ በሚገባቸው ዕርምጃዎችም ላይ የኹሉንም ወገኖች ተባባሪነትና ዕገዛ ስለሚጠይቅ ኹሉም ወገኖች በዚህ መሠረት እንዲተባበሩ አደራ እንላለን።
ዓለም አቀፍ ግንኙነት ጋር በተያያዘ አንዳንዶች ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር እንዲህ ያሉ ሪፖርቶን ይጠቀማሉ ይላሉ። በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
የኢትዮጵያን ጉዳይ በሚመለከት ባለፈው አንድ ዓመት ያህል ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ሲሰጥ የነበረው ትንታኔ፣ ሲገመት የነበረው ዘገባ በተወሰነ መጠን ሲያወዛግብ የነበረ መሆኑ ይታወቃል። ይህም በተወሰነ መልኩ የሚመነጨው በጉዳዩ ላይ ነጻ፣ ገለልተኛ የሆነ የምርመራ ሪፖርት ባለመኖሩ ነበር።
እንዲህ ዓይነት ነጻ ገለልተኛ ሪፖርት ባለመኖሩ የተነሳ አንደኛ በግጭት ውስጥ የሚሳተፉ ወገኖች፣ ኹለተኛ ደጋፊዎቻቸው በየበኩላቸው የራሳችን እውነት ነው ብለው የሚሉትን ነገር ስለሚያራምዱና በተወሰነ መጠን ደግሞ አንባቢዎች መረዳት እንደሚችሉት በግጭት ውስጥ የሚሳተፉ ወገኖች ደግሞ የፕሮፓጋንዳ ሥራ ስለሚሠሩ፣ ከተለያዩ ወገኖች የሚደመጠው ዘገባ ትክክለኛው ነገር ምን እንደሆነ ለማወቅ አስቸጋሪ አድርጎት ስለነበር፣ ራሱን የቻለ ውዝግብም ፈጥሮ ነበር።
ስለሆነም፣ አሁን እኛ ያካሄድነው ዓይነት ምርመራና ሪፖርት መኖሩ ስለሰብዓዊ መብት ኹኔታውና ስለተፈጠረው ነገር፣ በግጭት ውስጥም ስለሆነውና ስላልሆነው ነገር፣ ትክክለኛውን ግንዛቤ ለመያዝ የሚረዳ እንዲሆን ነው። ያ ትክክለኛው ነገር መታወቁ ደግሞ አንደኛ እውነት በትክክል መታወቅ ስላለበት፣ ኹለተኛ የተባለውን ነገር ለይቶ በማረጋገጥ ደግሞ ተገቢውን ዕርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ስለሆነ፣ ሪፖርቱ ከዚህ አንጻር ጠቀሜታ ነው ያለው፤ ለኹሉም ወገኖች ማለት ነው።
በመጀመሪያ ደረጃ ለኢትዮያውያን፣ ከዛ በመቀጠል ደግሞ ለኢትዮጵያ ወዳጆችና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በትክክል የሆነውንና ያልሆነውን ነገር በመለየት ተገቢውን ምላሽ ለመስጠትና ኢትዮጵያን ከዚህ ቀውስ ውስጥ እንድትወጣ ለማገዝ ተጨባጭ የሆነ መረጃና ምክረ ሐሳብ ይኖራቸዋል ማለት ነው። አሁንም ማየት የጀመርነው ይህንን ነው።
የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆኑ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ አባላት ይህን ሪፖርት መሠረት በማድረግ ሊወሰዱ የሚገቡ ዕርምጃዎችን፣ ምክረ ሐሳብ በመስጠት ላይና የሪፖርቱ ምክረ ሐሳቦችም ተግባራዊ እንዲሆኑ ጥሪ ማድረግ ጀምረዋልና፤ ይህ መልካም ነው ብዬ አስባለሁ።
ከገለልተኝነት ጋር በተገናኘ ኮሚሽኑ ተጠሪነቱ ለማን ነው? የገንዘብ ድጋፍስ የሚያገኘው ከማን ነው?
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የተቋቋመውና ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። ይህንን ዓይነት ኮሚሽን ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ በኹሉም አገራት ውስጥ አለ። ሥማቸው በኢንግሊዘኛ <National Human right Institution> በመባል ይታወቃል። በዓለም ላይ ያሉ ኹሉም አገራት ማለት ይቻላል፤ ልክ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዓይነት ተቋም አላቸው። በብዙ አገራት ውስጥ የተለመደውና የሚፈለገው አሠራርና በተባበሩት መንግሥታት ምክረ ሐሳብ የሚሰጥበት የተቋማቱን ነጻነት ለማረጋገጥ፣ ከሥራ አስፈጻሚ ተጽዕኖ ነጻ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚቋቋሙት እና ተጠሪነታቸው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። የኢትዮጵያም በዚህ መሠረት ነው የተቋቋመው።
ግን ኹሉም አገራት ለሰብዓዊ መብት ጥበቃ፣ መስፋፋት፣ መከበር እገዛ እንዲያደርጉ ነጻ የሆኑ እንዲህ ያሉ ተቋማትን እንዲያቋቁሙ ይበረታታሉ። ስለዚህ ይህ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በኹሉም አገር ያለ ተቋም ነው።
ነገር ግን፣ በየአገሩ የተቋማቱ ነጻነት መኖር አለመኖሩ እንደ የአገራቱ የፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታ የሚወሰን ነው። ኢትዮጵያ ውስጥም ከዚህ በፊት በነበረ የፖለቲካ አስተዳደር የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽኑ ብቻ ሳይሆን ብዙ መንግሥታዊ ተቋማት ብዙም ነጻነት ሳይኖራቸው፣ ብዙም ውጤታማ ሳይሆኑ፣ ብዙም አቅም ሳይኖራቸው የኖሩ መሆኑ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህን ተቋም እውነተኛ፣ ነጻ፣ ጠንካራና ውጤታማ ተቋም ለማድረግ ብዙ ጥረት ተደርጓልና በዚህ መሠረት በአገር ውስጥም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም ነጻ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ተቋም መሆኑ ተቀባይነት እጅግ እያገኘ መጥቷል። ለዚህ ማረጋገጫው ከተባበሩት መንግሥታት ጋር ያከናወነው የሪፖርት ሥራ አንዱ ነው። ግን ከዛ ቀደም ብሎም ሆነ ከዛ በኋላም የኮሚሽኑ በአገር ውሰጥም በዓለም አቀፍ ደረጃም ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱ ከሥራውም የሚታይ ይመስለኛል።
የገንዘብ ምንጩ እንደማኛውም መንግሥታዊ ተቋም መንግሥት ለሰብዓዊ መብት ሥራ ሀብት መመደብ ስላለበት አንዱ የበጀት ምንጩ ከመንግሥት የሚመደብለት በጀት ነው። ይህ በጀት በፓርላማ አማካይነት በቀጥታ የሚመደብ ነው። መንግሥት ደግሞ ለሰብዓዊ መብት ሥራ ሀብት የመመደብ ኃላፊነትና ግዴታ ስላለበት፣ አንዱ የገቢ ምንጫችን በፓርላማ አማካይነት ከመንግሥት የሚመደበው በጀት ነው።
ነገር ግን፣ እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አቅማችን ዝቅተኛ የሆነ አገር ስለሆንን፣ እንኳን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አንድ ተቋም ይቅርና፣ ጠቅላላ አገራችንም እንደ ሌሎች በርካታ የአፍሪካ አገራት ከለጋሽ አገራት የሚገኝ ዕርዳታንም የሚጠቀም መሆኑ ይታወቃል። ስለሆነም እኛም ከዓላማችን ጋር የሚስማማ፣ ነጻነታችን ላይ ተጽዕኖ የማያደርግ፣ ከዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች በራሳችን መሥፈርት የቴክኒክም የገንዘብ ዕገዛም እንቀበላለን። ስለዚህ ከመንግሥት በሚገኝና ከዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች በሚገኝ ዕርዳታ ሥራችንን እናካሂዳለን ማለት ነው።
ከሰሞኑ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣው ሪፖርት አለ። እንዲህ ያሉ ሪፖርቶችን እንዴት ነው የምትገመግሟቸው?
አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሒውማን ራይትስ ወችን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በብዙ አገራት ላይ የሰብዓዊ መብት ሁኔታዎችን እየተከታተሉ ሪፖርት የሚያወጡ መሆኑ ይታወቃል። ስለዚህ እነዚህ ሪፖርቶች ጠቃሚና አስፈላጊ ናቸው። እርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚወጡ ሪፖርቶች ላይ አንዳንድ ምክንያታዊ የሆኑ ጥያቄዎች መነሳት መጀመራቸው ይታወቃል። ያ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እነዚህ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚያወጧቸው የሰብዓዊ መብት ሪፖርቶች በትኩረት መታየትና መወሰድ አለባቸው ብዬ አምናሁ።
እንደተረዳሁት ከሰኔ በኋላ የተከፈተውን ሁኔታ የሚመለከት ሪፖርት መሆኑን ተገንዝቤአለሁ። አስቀድሞ እንደገለጽኩት፣ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በኩልም ከሰኔ በኋላ በተለይ የሕወሓት ጥቃት ወደ አማራ ክልል እና ወደ አፋር ክልል ከተስፋፋ በኋላ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በሚመለከት፣ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በኩልም የተከናወነ ሪፖርት ስላለ በቅርብ ቀናት ውስጥ ይፋ ይደረጋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 158 ሕዳር 4 2014