የተማሪ አመጽ ከየት ወደ የት? (ከአጼዎቹ እስከ አቢቹዎቹ)

Views: 337

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ላይ ተደጋግሞ የሚነሳ ሐረግ ነው፤ የተማሪዎች አመጽ። ይህም የንጉሠ ነገሥቱን ሥልጣን ከመነቅነቅ ጀምሮ ዛሬ ድረስ መንግሥትን እየፈተነ የዘለቀ እንቅስቃሴ ሆኖ ይታያል። አስቴር አስራት በበኩላቸው አሁን ላይ ያለው የተማሪ እንቅስቃሴ ‹የተማሪ እንቅስቃሴ› ከተባለ፣ አካሄዱ ሊስተካከል ይገባል የሚል ሐሳብ አላቸው። እንዲሁም ጨምረው፤ ለፖለቲካ ትርፍ ሌሎች በፈጠሩት መከፋፈል በተለይም በአማራ እና በኦሮሞ ተወላጆች መካከል እየሆኑ ያሉ ክስተቶች ‹የእኔም ደም ነው!› እያሉ አንዳቸው ለአንዳቸው የቆሙ ሕዝቦች መገለጫ ሊሆኑ አይገባም ይላሉ።

‹‹ታሪክ የሚያስተምረን ከታሪክ ምንም አለመማራችን ነው›› ፈላስፋው ፍሬድሬክ
እኔም እላለሁ “የአሁን ተማሪዎች፣ የቀደመው ተማሪዎች አመጽ በአገራችን ካስከተለው ጥቅምና ጉዳት የተማሩት ምንም ነገር የለም”
ዩኒቨርሲቲዎች እውነትና ትክክለኛ አስተሳሰብ የሚንጸባረቅባቸው ቦታዎች ናቸው። በኃይል ለመጠቀም መሞከር ከከፍተኛ ትምህርት ዓላማ በተቃራኒው መንገድ መሄድ ነው። በምንም አይነት መንገድ በዩኒቨርሲቲውም ሆነ እርስ በእርስ ኃይልን በመጠቀም የሚረብሹ ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች ናቸው ለማለት አያስደፍርም።

ይህ መሆኑ ቀርቶ ከኅዳር ወር 2012 ጀምሮ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎች አመጽ ማዕበል እንደመታው ውቅያኖስ ከወዲያ ወዲህ ሲላጋ ቆይቶ መዳረሻውን በአማራና በኦሮሚያ ክልል በሚገኙት ዩኒቨርሲቲዎች አድርጓል። በኹለቱም ክልሎች በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ሟችና ገዳይ፣ ደብዳቢና ተደብዳቢ፣ አጋችና ታጋች ሆነው የቀጠሉት የኹለቱ ብሔር ተወላጆች ናቸው። በቀጥታ አሁን ስላለው የተማሪዎች ነውጥ ምክንያትና ውጤት እንዲሁም ስለሚያስከትለው ቀጣይ ጉዳት ከማየታችን በፊት የተማሪዎች አመጽ በኢትዮጵያ ያለውን ታሪካዊ ዳራ በአጭሩ እንቃኝ።

ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቅ በኋላ የአገራቸው ኋላ ቀርነት ያስቆጫቸው (በጣሊያን መወረራቸውን ተከትሎ) የዘመኑ መሪ የነበሩት ንጉሥ ኃይለሥላሴ ከስደት እንደተመለሱ አገራቸውን ለማዘመን የተጠቀሙበት አንዱ መሣሪያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ማስፋፋት ነበር። ይህን ሕልማቸውን ለማሳካትም ቅንጡ የሆነውን መኖሪያ ቤታቸውን ለተማሪዎች ለቀው በመውጣት በጥቂት የዲፕሎማና የዲግሪ ተማሪዎችና ከካናዳ በመጡ መምህራን የከፍተኛ ትምህርትን በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አሀዱ ብለው አስጀመሩ።

አስከትለውም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተለያዩ ሙያዎች የሚያሠለጥኑ ኮሌጆች እንዲከፈቱ አደረጉ። ከእነዚህም ውስጥ በሐረር አለማያ ግብርና ኮሌጅ (1954) በጎጃም ባህርዳር ፖሊ ቴክኒክ በ1963 እና ባህር ዳር መምህራን ኮሌጅ (1972)፣ በጎንደር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ (1954) እንዲሁም በጅማ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ (1954) ተጠቃሾች ናቸው።

የከፍተኛ ትምህርት በኢትዩጵያ ተጀምሮ ዐስር ዓመት እንኳን ሳይሞላው የተማሪዎች አመጽ ከፍተኛ ትምህርትን ‹‹ሀ›› ብለው በጀመሩበት በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ ተጀመረ። በ1960ቹ በነዋለልኝ መኮነን፣ ጥላሁን ግዛው እና ማርታ መብራቱ የተጀመረው ይህ ተቃውሞ፣ በመላው አገሪቱ ተቀጣጥሎ የወታደሩንና የጭቁኑን ሕዝብ ትኩረት ስቦ ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍም አግኝቶ ነበር።
በየሳምንቱ መሳፍንቱ እና መኳንንቱም ጭምር በሚታደሙበት የሥነጽሑፍ ዝግጅት የተጀመረው የአጼዎቹ ተማሪዎች ተቃውሞ፣ ቀስ በቀስ መኳንንቱንና ሹማምንቱን ያስከፋቸው ጀመር። በሚነበቡት ግጥሞች ያልተደሰቱት ንጉሡና የንጉሡ ባለሟሎች ተማሪዎችን ከዚህ ድርጊታቸዉ እንዲታቀቡ በተደጋጋሚ ቢነግሯቸውም፣ ድርጊቱ ግን ከቀን ወደ ቀን እየባሰ ስለሄደ ለማስጠንቀቅ ያክል የተወሰኑት እንዲታሰሩ ተደርገዋል።

ይህ በሥነጽሑፍ የተደረገው ዘመቻ እየተባባሰ ሲሄድ በ1963 ዩኒቨርሲቲው ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ የማረጋጋት ሥራ ለመሥራት ተሞክሯል። ነገር ግን መልኩን ቀይሮ በቀጥተኛ መፈክር መሬት ለአራሹ እያሉ በአደባባይ መፈክር ጀመሩ። የተማሪዎች ኅብረት አቋቁመው የዩኒቨርሲቲውን ጋዜጣ በመጠቀም ሙሉ በሙሉ ፖለቲካዊ ትግል ማካሄድ ጀመሩ። የኃይለሥላሴን መንግሥት የሚደግፈውን የአሜሪካን መንግሥት ተጽዕኖ መጥፎነት ለማሳየት ብለው ሴቶች አጫጭር ቀሚሶችን ለብሰው በአደባባይ መታየት ጀመሩ። በጣም በተደራጀ መልኩ አስር አስተዳደራዊ ጥያቄዎችን አንስተው በቃል፣ በበራሪ ወረቀት፣ በጋዜጣ በመሳሰሉት መንገዶች በማስተላለፍ ዘውዳዊ መንግሥትን እረፍት ነሱት።

ተቃውሞው ወደ ሌሎች ኮሌጆችና ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተስፋፍቶ ስለ ትምህርት ቤት ስርዓት፣ ስለ መሬት፣ ስለ ተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም በአጠቃላይ ስለ መንግሥት አገዛዝ አንስተው አገራዊ ተቃውሞ እንዲካሄድ አደረጉ። በአጠቃላይ መሬት ለአራሹ፣ ዳቦ ለተራበ፣ ድህነት ወንጀል አይደለም፣ ዴሞክራሲ፣ እኩልነትና ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም የሚሉ ሐሳቦች በመስዋእትነት ቢታጀቡም በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተጀምሮ መላ አገሪቱን ያዳረሰዉ እንዲሁም በስተመጨረሻ የንጉሡ ወታደሮችም ጭምር የተቀላቀሉበት ተቃዉሞ የንጉሣዊውን ስርአተ-መንግሥት በማዳከም አሽቀንጥሮ ጣለው።

ምንም እንኳን መነሻ ሐሳባቸው በብዙ መስዋዕትነት ዘውዳዊውን አገዛዝ ከኢትዮጵያ ምድር መገርሰስ ቢችልም፣ ሕዝባዊ መንግሥት ሳይመሰረት በወታደራዊ መንግሥት ተጠለፈ። በመሆኑም መሬት ለአራሹ የምትለዋን ጥያቄ ብቻ ለመመለስ ጥረት ያደረገ፣ በአንጻሩ ምሁራንን፣ ተማሪዎችን እና የተማሪዎችን ጥያቄ ገሸሽ ያደረገ ፍፁም አምባገነናዊ ወታደራዊው መንግሥት (ደርግ) ሥልጣን ተቆጣጠረ። እንደተቆጣጠረም አፈሙዙን ወደ ምሁራን፣ ተማሪዎች እና ሻል ያለ አስተሳሰብ ወዳላቸዉ በማዞር ዘግናኝ ጭፍጨፋ ፈፀመ።

በዩኒቨርሲቲ ጥያቄ አንግበዉ የተነሱት ተማሪዎች አብዛኞቹ ተገድለዋል፣ ተሰደዋል፣ ቀሪዎቹም ደርግን ለመፋለም በረሃ ገብተዋል። ይህ ራሱን ለአገርና ለወገን መስዋዕት ያደረገ ዘውዳዊ አገዛዝን ከኢትዮጵያ ምድር ተደምስሶ አብዮት እንዲቀጣጠል ያደረገው ትውልድ፣ ለኢትዮጵያ እድገት ቁልቁል መንደርደር አስተዋጽኦው ቀላል የሚባል አልነበረም። ከድጥ ወደ ማጥ እንደሚባለው፣ በአዋቂ መሀይማን ስር የወደቀችው ኢትዮጵያ የሕዝብ እልቂትን፣ ርሀብን፣ ድህነትን ከማስተናገድ አላዳናትም። እንደውም አብዮት ልጆቿን እስከ መብላት አድርሷታል።

አገርን በሀይማኖት፣ በብሔር በቋንቋ ሳይከፋፈል በሶሻሊዝም መመሪያ ሕዝብን ለማገልገል የመጣው ወታደራዊ መንግሥት፣ ከሰው ይልቅ ለመመሪያ ሲጨነቅ ‹ኢትዮጵያ ትቅደም!› እያለ አገር ማለት ሰው መሆኑን ስላልገባው ከተማሪ አመጽ አላመለጠም። ‹‹ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም›› በሚሉ ትንታግ በሚተፉ ወጣቶች እረፍት ያጣው ወታደራዊ መንግሥት፣ ኹለት አስርት ዓመታትን እንኳን መቆየት ሳይችል ቀርቶ በወያኔ ጦር ሊወገድ ችሏል።

ለዚህም የተማሪዎች ሚና እጅግ ከፍተኛ ነበር። እጅግ ምስጢራዊ በሆነ መንገድ የሚያደርጉት የስለላ ሥራ፣ የተደራጀ ቡድን በመፍጠር ሕይወታቸውን መስዋዕት አድርገው ኢሕአፓ በሚል ጥላ ስር ተጠልለው የደርግን መንግሥት ውድቀት አፋጥነዋል። የዚያን ዘመን ወጣቶች ትምህርታቸውን በአግባቡ መማር ስላልቻሉ ለስደት ተዳርገዋል። ሸፍተው ተዋግተዋል። የሚያሳዝነው ግን ልክ እንደ አሁኑ ዘመን ተማሪዎች ሰውን መግደል እንደ ቀላል ነገር የሚታይበት ጊዜ መሆኑ ነው። የተማሪዎች ፓርቲም (ኢሕአፓ) ቢሆን እንቅፋት ናቸው ያላቸውን አመራሮች ለመግደል አያመነታም ነበር። ምላሹ እጥፍ ሆኖ ቢጠብቀውም።

የደርግ መንግሥት አምባገነናዊ አገዛዝ የመረረው በነሱ አገላለጽ ‹ምሬት የወለደው› የወያኔ ጦር በአሁኑ አጠራር ኢሕአዴግ መሣሪያ ጨብጦ እንደገባ፣ በ1983 በኤርትራ ሪፈረንደም ምክንያት የስድስት ኪሎ ተማሪዎች ተቃውሞ አሰምተው፤ የተወሰኑ ተማሪዎች ሞተዋል። ከ1985 በኋላ በነበረው የተሻለ የሚመስል መመሪያ በማምጣት ለተወሰኑ ዓመታት ከተማሪ አመጽ ሙሉ በሙሉ ባይባልም በተወሰነ መልኩ ማረፍ ችሎ ነበር።

ከዚያ በኋላ በአደባባይ ለተቃውሞ የሚወጡ ተማሪዎችን ማየት የተጀመረው በ1993 ነው። ‹የፌዴራል ፖሊስ ከዩኒቨርሲቲው ይውጣ፣ ስርዓተ ትምህርቱ ይሻሻል፣ የዩኒቨርሲቲው ጋዜጣ መታተም ይጀምር› የመሳሰሉ ጥያቄዎች ተነስተው ከሰብዓዊ መብት የመጡ ሰዎች ጭምር ጣልቃ የገቡበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጥያቄ እየበረታ መጥቶ አመጽ ሊነሳ ችሏል። አመጹ ከመጠንከሩ የተነሳ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስድስት ኪሎ ግቢ ተኩስ እስከመሰማት ደርሶ፣ በርካታ ተማሪዎች ታስረው እንደነበር በጊዜው የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪ የነበሩ ሰዎች ያወሳሉ። ችግሩ በመጉላቱ የተነሳ በኃይለሥላሴ ዘመን እንደተደረገው ሁሉ ስድስት ኪሎ ግቢ ለአንድ ዓመት ያክል ትምህርት እስከመቋረጥ ደርሷል።

ለነገሮች ምላሽ የሰጠ በመምሰል ዴሞክራሲን ለማስፈን ጥረት ያደረገው የኢሕአዲግ መንግሥት፣ በአንፃራዊ መልኩ በቅድመ ምርጫ እንቅስቃሴዎች ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በ1997 እንዲካሄድ ጥረት ቢያደርግም ባልጠበቀው መልኩ የቅንጅት ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ ፓርቲ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተማሪዎች ከፍተኛ ድጋፍ ማግኘቱ ድንጋጤ ዉስጥ ከተተው። በምርጫዉ በከፍተኛ ልዩነት የተሸነፈዉ ኢሕአዴግ በድኅረ ምርጫ በወሰዳቸው የማጭበርበር እርምጃዎች (ኮረጆ መስረቅ፣ ዉጤት ማስቀየር እና ዳግም ምርጫ ማካሄድ) በሥልጣን ለመቆየት ያደረገው ጥረት፣ ማእበል የሆነ የተማሪዎች ተቃዉሞን አስከተለ።

ይህ የተማሪ አመጽ ያስደነገጠው የኢሕአዲግ መንግሥት በብሔር የማናከሱን ሥራ አጠንክሮ በመያዝ ለአንድ ወገን ብቻ በማድላት በተለይም በሕዝብ ብዛትና በመሪነት ሚና ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ኹለቱን ብሔሮች ማጋጨት ጀመረ። በክረምት ወቅትም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በአቅራቢያቸው ካለው ዩኒቨርሲቲ በማስገባት ከ14 እሰከ 30 ቀን በማቆየት ስብከት በሚመስል (በወቅቱ የነበሩት ተማሪዎች የፖለቲካ ጥምቀት ይሉት ነበር) መንገድ ብዙ ተማሪዎችን ‹የነፍጠኛው ገዥ በኦሮሞው ላይ ያደረሰው ተጽዕኖ› ምን ያክል ከባድ እንደነበር ማሳየትና ቁርሾ ማስያዝ ጀመረ።
በጊዜው የትምህርት ሚኒስትር የነበረው ስንታየሁ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ተፈራ ዋልዋ፣ አዲሱ ለገሰ አማራነታቸው ሳይገድባቸው የ‹ነፍጠኛውን ገዥ› ጭካኔ በማሳየት በመካከል የነበረውን መቃቃር ወደ ከፋ ጥላቻ እንዲያድግ አድርገዋል።

ከኹለቱ ብሔር የመጡ ተማሪዎች ከበስተጀርባ ምን አለ? ለምን እንደባደባለን? የሚለውን ጥያቄ ከማንሳት ይልቅ በሕወሐት መረብ ውስጥ ገብተው ይናከሳሉ። ይህም በአገሪቱ ደረጃ ከኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድርስ ያሉትን ተማሪዎች የጥላቻ መንፈሳቸው እንዲጎለብት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

የኹለቱ ብሔር ተማሪዎች የኢሕዴግ መንግሥት ፌዴራሊዝም በሚል መዋቅር ልክ እንደምትታለብ ላም ብሔርና ብሔረሰቡን ጨው እያላሰ ለአንድ ብሔር የቆመ መንግሥት እንደነበር የገባቸው ዘግይቶ ነው።

ይህ መረዳትም ለዘመነ ዐቢይ መምጣት አበርክቶው ከፍተኛ ነበር። በተለይ በኦሮሚያ ክልል በርካታ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው የተማሪዎች ጥያቄ በእድሜ ሳይገደብ ከአንደኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ድረስ ብዙ አገራዊ ኪሳራዎችን አምጥቶ ለድል በቅቷል።

በዘመነ ኢሕአዴግ የከፋፍለህ ግዛ መርህ የተንገሸገሸው ወጣት፣ ‹ማነህ እንደ እኔ የተበደልክ?› በሚል መንፈስ እርስ በእርስ ተቀናጅቶ ‹የኦሮሞ ደም የኔም ደም ነው፤ የአማራው ደም የኔም ደም ነው› በሚል ልብ የሚነካ መፈክር ስንትና ስንት ልጆቹን ሕይወት መስዋዕት አድርጎ አገሪቱን የተቆጣጠረውን የወያኔ መንግሥት ቀንጥሶ ጣለው።

ዛሬ ያ ወጣት አማራው ከኦሮሞ ጋር ኦሮሞው ከአማራ ጋር አልማርም ሲል መሰማቱ ለታሪክ አሳፋሪ ክስተት ነው። ትናንት ስንትና ስንት ኪሎሜትር አቋርጦ የአንቦጭን አረም ለማጥፋት የሄደው ወጣት በውስጡ የተዘራበትን የዘረኝት አንቦጭ አብቦ ስር ሰዶበት አብሮ ለመማር ተስኖት አገሩን እንደ ባቢሎን ግንብ ለማፍረስ ደፋ ቀና ሲል እየታየ ነው።

ለበርካታ ዓመታት ሲዘራ የነበረው የዘረኝነት መንፈስ ከግለሰብ አልፎ አካባቢን፣ ሰፈርን፣ አገርን ወርሮ ነገ አገር ይረከባሉ ተብለው ስንትና ስንት በጀት ፈሰስ እየተደረገላቸው የሚማሩ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ተጠናውቷቸዋል። ትናንት መንግሥትን የሚያክል የንጉሠ ነገሥታቱን ሥልጣን የቀማ የተማሪ ኃይል፣ ዛሬ እርስ በርስ እንደ እፉኝት ልጅ እየተጋደለ እንዲያልቅ እያደረገ ነው።

ይህች አገር ለበርካታ ጊዜ መሪ አጥታ ስትሰቃይ ቆይታለች። ታሪክ እንደሚነግረን ሕዝቦቿ በመሪ እጥረት በጎሳ፣ በብሔር፣ በሀብት፣ በስራና በተለያየ መንገድ ተከፋፍለው ሲበደሉባት፤ በፍትህ ጥማት ሲሰቃዩ ቆይተውባታል። አሁን ደግሞ መሪ ብቻ ሳይሆን ሕዝብም አጥታለች። የሀይማኖት አባቶች፣ ወላጆች፣ አዛውንቶች ሁሉም ወጣቱን በተለይም ዩኒቨርሲቲውን ወጣት የጥያቄውን አቅጣጫ እንዲቀይርና በትክክል ፍትህና ዴሞክራሲ ፈላጊ ከሆነ፣ ጓደኛውን በመግደል ወንድሙን ማዳን እንደማይችል በመንገር ሊይዙት ይገባል። ያ ካልሆነ የኢትዮጵያ እጣፈንታ አሳሳቢ ነው። ብዙዎቹ እንደሚሉት ‹‹እውነት ግን ይህች አገር ወዴት እየሄደች ነው?›› ያስብላል።

የአሁኑ ዘመን የተማሪ አመጽ ይበልጥ እንዲከፋ ያደረገው የፌዴራል መንግሥቱ ችላ ማለት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎረቤት አገራት ጉዳዮች ተጠምደዋል፤ ትምህርት ሚኒስትሯ በተበላሸው የትምህርት ዶሴ በመጠመዳቸው ፖሊሲ በማስተካከል ላይ ናቸው። የወጣቶች ሚኒስቴርም በተመሳሳይ በሌሎች ሥራዎች ላይ ተጠምደዋል። ዩኒቨርሲቲዎች ጊዜያዊ ሰላም ለማምጣት ከተማሪዎች ጋር ሌባና ፖሊስ በመጫወት ላይ ናቸው።

ስለዚህ ተማሪው አደብ ገዝቶ ተገቢውን ጥያቄ በተገቢ መንገድ ማቅረብ ይጠበቅበታል። በአማራ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ የኦሮምያ ክልል ተማሪዎች እንዲሁም በኦሮምያ ክልል የሚገኙ የአማራ ክልል ተማሪዎች በየቤተሰባቸው ተበትነው ማየት እንደ አገር ያሳቅቃል። እንደ መፍትሔ ዩኒቨርሲቲዎች የሚወስዱት እርምጃም ቢሆን ዘላቂነቱ አሳሳቢ ነው። የምርጫ ጊዜ ከፊታችን ተጋርጧልና። ተቃውሞ በግድያ መግለጽ ደም መመለስ እንደ ግዴታ በሚቆጠርበት ሰገር አስፈሪነቱን ያጎላዋል።

የተማሪዎች ጥያቄም በፍጥነት መልስ ሊያገኝ ይገባል። እነዚህ የአገሪቱ ተስፋዎች በቋንቋና በሰፈር ለሚቀርባቸው ሰው አድልተው ሌላውን እያሳቀቁና እያባረሩ እንዲኖሩ መፍቀድ ስህተት ነው። በእርግጥ ከተወለዱበት ጊዜ ጀምረው የተዘራባቸውን የዘረኝነት መንፈስ በአንድ ጀንበር ማጽዳት ባይቻልም፣ እነሱን ጥፋተኛ ከማድረግ ይልቅ በትዕግስት አገራዊ መፍትሔ ማምጣት ከመንግሥት ይጠበቃል።

አስቴር አስራት (ዶ/ር)
asgone16@gmail.com

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com