ይሄም ተድበስብሶ አይቅር፤ የፀጥታ ኃይሎች ዛሬም ለሕግ/በሕግ ይገዙ!

Views: 380

ባሳለፍነው ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ 24 ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ የእምነት ክዋኔ በማከናወን ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ በፀጥታ ኃይሎች የተፈፀመው የአስለቃሽ ጭስ እና ጥይት ጥቃት የአዲስ አበባን ብሎም የኢትዮጵያን ሕዝብ ያሳዛነ ድርጊት ነበር።

ስለ ቤተክርስትያኑ የወጡ የተለያዩ መረጃዎች እንደሚሳዩት፣ የፀጥታ ኃይሎች ቤተክርስትያኑን ለማፍረስ ነበር ወደ ስፍራው ያቀኑት። ጥር 26/2012 ከለሌቱ ሰባት ሰዓት ላይ የተፈፀመው ይህ የጸጥታ ኃይሎች እንቅስቃሴ ወደ ጥቃት ተቀይሮ፣ ምንም ያልታጠቁ ኹለት የአካባቢው ነዋሪ ሰዎች ሕይወት እንዲያልፍ ምክንያት ሆኗል። ጥቂት የማይባሉ ዜጎችም ቀላልና ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ይህ ግድያ ለፖለቲከኞች ትርፍ ማግኛ ሲሆንና የፖለቲካ መልክ ሲይዝ ከመታየቱ በተጓዳኝ፣ አንድ ቤተሰብን ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ ወጣቶች ዘንድ ቁጣ የቀሰቀሰም ነበር።

ቤተክርስትያኒቱ በሕገ ወጥ ይዞታ ላይ ታንጻ ከሆነ እንኳን የፍትሐ ብሔር እና የወንጀል ሕጎች እያሉ በሲቪል ዜጎች ላይ፣ ያውም በእኩለ ሌሊት ጥይትና አስለቃሽ ጭስ መተኮስ በየትኛውም መለኪያ አግባብ አይደለም።

አገራችን ኢትዮጵያ ከዳር እስከ ዳር በተለያዩ ብጥብጦች ስትናጥ አንፃራዊ ሰላም የሰፈነባትን አዲስ አበባን መንግሥት አፈ ሙዝ እየመዘዘ ወዳልተፈለገ ቀውስ ለመክተት መሞከር በእሳት ጨዋታ ነው። የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑ ወጣቶች የሥራ አጥነት፣ የሥነ ልቦና እና ኢኮኖሚ ጫናዎችን ተቋቁመው ሰላማዊ ኑሮን ለመግፋት ቢጥሩም፣ መንግሥት በቸልታና በግዴለሽነት የሚለኩሳቸው እሳቶች ምን አልባት ካበድ ቀውስ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ማሰብ ያስፈልጋል።

ነገር ግን አሁንም ትልቁ ምስል የፀጥታ ኃይሎች ያለ አግባብ ኃይል መጠቀም መቀጠላቸው ነው። አዲስ ማለዳ በተለያዩ ጊዜያት በጸጥታ ኃይሎች ሕይወታቸው ስላላፉ እና ፍትህ ማግኘት ቀርቶ ስለ ግድያ ማብራሪያ እንኳን ያልተገኘባቸውን ጉዳዮች ታዝባለች፤ ዘግባለችም።

ለማስታውስም በሰኔ 17 እና 18 በተከታታይ ቀናት የኹለት ወጣቶች ሕይወት በጸጥታ ኃይሎች አልፏል። የጭነት አስተላላፊ የነበሩት የሙሉጌታ ደጀኔ እና የንግድ ባንክ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ኢሳያስ ታደሰ የአማራ ክልል እና የመከላከያ አመራሮች ላይ ግድያ በተፈፀመ ማግስት፣ ከተማዋ በፌደራል ኃይሎች ጥበቃ ስር ሳለች ነበር በጸጥታ ኃይሎች የኹለቱ ሰዎች ሕይወት ያለፈው።
የሟች ቤተሰቦችን በተደጋጋሚ ያነጋገረችው አዲስ ማለዳ፣ በግለሰቦቹ ግድያ በቁጥጥር ስር የዋለም ሆነ ምርመራ የተደረገበት የጸጥታ ኃይል ያለመኖሩን እና የዐይን እማኞችም ቃላቸውን የሚቀበላቸው ማጣታቸውን ይናገራሉ።

ለወራት ፍትሕን ፍለጋ የተጉላሉት ቤተሰቦች ተስፋ ወደ መቁረጥ መድረሳቸውንም ለአዲስ ማለዳ ገልፀው ነበር። ታዲያ በሕግ ያልተገደበ የጸጥታ ኃይሎች የኃይል አጠቃቀምን ለመገደብም አዲስ አዋጅ ይዘጋጃል ተብሏል። ነገር ግን አዋጁ እስከ አሁን ከአርቃቂው የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አልተሻገረም።

ለነገሩማ ችግሩ የሕግ ክፍተት ብቻ ሳይሆን የሲቪል ዜጎች ሕይወትን ዋጋ ሰጥቶ እና የነዋሪ ደኅንነት እንዲጠብቁ ብረት የያዙ ሰዎች፣ አፈ ሙዛቸውን ወደ ሕዝብ ሲያዞሩ ሃይ ባይ መጥፋቱ ነው። ይህም ዜጎች መንግሥት ይጠብቅናል ብለው በእለት ተእለት ሥራቸው ላይ እንዳያተኩሩ እና በየግላቸው ‹ራሴን መጠበቅ አለብኝ› በሚል እሳቤ ውስጥ እንዲቆዩ ያደርጋል። በዚህም ምክንያት የኃይል ሚዛን መዛባት መግጠሙ አይቀሬ ነው።

ታዲያ የጸጥታ ኃይሎች ልክ ያጣ የኃይል አጠቃቀም ወደ ሃይማኖት ቦታዎች መሄዱ ነገሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎታል። በአብዛኛው የዓለማችን የሃይማኖት ተቋማት ለእምነት መስዋእት መሆን ‹‹የጻድቅ ሞት›› ተብሎ የሃይማኖቶቹ መሠረት ለሆነው፣ ከሞት ወዲያ ላለው ሕይወት የሚያሸልም ድርጊት እንደሆነ ያስተምራሉ።

ለዛም ነው ሰዎች ከማንኛውም ኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ ወይም ፖለቲካዊ አጀንዳዎች ይልቅ የሃይማኖት አጀንዳዎች ብዙዎች ሊሞቱላቸው የሚዘጋጁላቸው ዓላማዎች ናቸው።
በአዲስ አበባ የተፈፀመውን ድርጊት የከተማው ምክትል ክንቲባ ለመፍታት ያደረጉት ጥረት የሚበረታታ እና የወጣቱን ቁጣ ለጊዜውም ቢሆን ያበረደ መሆኑ እሙን ነው። ነገር ግን እልፍ ችግሮችን የያዘችውን አዲስ አበባ የሚመሩት ምክትል ከንቲባው፣ እንዲህ ዓይነት ጥቃቶችን በየእለቱ ማብረድ አይችሉም። ስለዚህ የከተማው አስተዳደር የጸጥታ ኃይሎችን መሠረታዊ የሆነ የሕገ መንግሥት ሥልጠና በተደጋጋሚም ቢሆን በማሠልጠን የሰብአዊ መብቶችን ትርጉም ማስተማር ያስፈልጋል።

ከአንድ ሳምንት በፊት አንድ የመከላከያ አባል ቅዳሜ ጥር 23/2012 የቀድሞ ፍቅረኛውን በጠመንጃ ሕይወቷን አጥፍቶ የራሱንም ሕይወት ማጥፋቱን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል።
ታዲያ በጸጥታ ኃይሎች ሕይወታቸው ስለጠፋ ዜጎች አነሳን እንጂ ፖሊስ የመምታት፣ የመስደብ ወይም ያለ አግባብ የማሰር ሥልጣን ያለው የሚመስለው ኢትዮጵያዊ ቁጥሩ ቀላል አይደለም። አንድ ፖሊስ መታኝ ብሎ ክስ መመስረት እንደ ምዕራባዊ ቅንጦች እንጂ ሕዝብ በገዛ ገንዘቡ ያስታጠቀው ጠባቂውን የሚጠይቅበት ስርዓት ነው ብሎ የሚያስብ ብዙ አይገኝም።
ስለዚህም አሁንም የእነዚህ ወጣቶች ገዳዮች ጉዳይ ሳይድበሰበስ ተያዙ የተባሉት ሰባት ሰዎች ፍርድ ቤት ቀርበው በአገሪቱ ሕግ ይዳኙ ስትል አዲስ ማለዳ አጥብቃ ትጠይቃለች።

የጸጥታ ኃይሎች የሚከፈላቸው ዝቅተኛ ደሞዝ ሳይበግራቸው፣ ሕይወታቸውን አስይዘው የዜጎችን እና የአገርን ሰላም ሲጠብቁ የሚውሉ በመሆናቸው ሊከበሩና ሊመሰገኑ ይገባል። ነገር ግን የታጠቁት ትጥቅ ከወገናቸው በላይ የመሆን ሥልጣን የሚሰጣቸው አይደለም። አሁን ከሕግ ተጠያቂነት ቢያመልጡም ከሕሊና ፍርድ የማያመልጡበት ክስ ውስጥ መግባታቸው አይቀሬ ነው ሰከን ብለው ሊያስቡ ያስፈልጋል።

ይህም ጉዳይ እንደቀደሙት ሁሉ ተድበስብሰውና የቅርብ ቤተሰብ ብቻ እየተብከነከነባቸው ሊያልፉ አይገባም። ሕግን እየጣሱ ሕግ ማከበር የለምና፣ ጸጥታ አስከባሪዎች ጸጥታውን እነርሱ ራሳቸውም ሊያከብሩት እንደሚገባ መታወቅ አለበት።

አዲስ ማለዳም በተያዘው ሳምንት ያለ ፍርድ ሕይወታቸው ያለፈውን ወጣቶች ጨምሮ በጸጥታ ኃይሎች ያለ አግባብ ሕይወታቸው ላለፈ ዜጎች፣ ፍትህ ሳትዘገይ ትሰጣቸው፣ ይሄም ተድበስብሶ አይቅር ስትል ጥሪዋን ታቀርባለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 66 ጥር 30 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com