ብሔራዊ ባንክ እስከ 230 በመቶ የሚደርስ የደሞዝ ጭማሪ አደረገ

Views: 1149

ጭማሪው የሰራተኞችን የስራ ደረጃ መሰረት ባደረገ መልኩ የተደረገ ነው

ብሔራዊ ባንክ ከጥር 01/2012 ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ እስከ 230 በመቶ የሚደርስ የደሞዝ ጭማሪ ለሠራተኞቹ አደረገ።
ባንኩ ከ50 በመቶ እስከ 230 በመቶ የሚደርስ የደሞዝ ጭማሪ ተግባራዊ ማድረጉን ለሠራተኞቹ በላከው የውስጥ ደብዳቤ ላይ የገለፀ ሲሆን፣ ከደሞዝ ባሻገር በርካታ የጥቅማ ጥቅም ማሻሻያዎች እንደሚደረጉም ተጠቅሷል።

ጭማሪው የሠራተኞችን የሥራ እርከን መሰረት ባደረገ መልኩ መተግበሩንም የባንኩ ሠራተኞች ገልጸዋል። እንደ ጥበቃ፣ ፅዳት፣ ተላላኪ እና ጀማሪ ተቀጣሪዎችን በይበልጥ ተጠቃሚ ያደረገ ጭማሪ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዝቅተኛ የሥራ እና የደሞዝ እርከን ላይ የሚገኙ የባንኩን ሠራተኞች እስከ 230 በመቶ የሚደርስ ጭማሪ ያገኙ ሲሆን፣ በአስተዳዳር የሥራ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሠራተኞች ደግሞ ከ 50 በመቶ እስከ 70 በመቶ የሚደርስ ጭማሪ እንደተደረገላቸውም ሠራተኞቹ አስታውቀዋል።

ከዚህ ቀደም ባንኩ በተደጋጋሚ የደሞዝ ጭማሪ እና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎች ከሠራተኞቹ ሲቀርብለት ቢቆይም፣ ጭሪው ግን ለዓመታት ሳይደረግ መቆየቱን ለማወቅ ተችሏል።
በዚህ ምክንያትም በባንኩ ከፍተኛ የሠራተኞች የመልቀቅ ምጣኔ መኖሩን የገለጹት አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው አንድ የባንኩ ሠራተኛ፣ ከፍተኛ አቅም ያላቸው እና ባንኩንም ማገልገል የሚፈልጉ ሠራተኞች በደሞዙ ዝቅተኝነት ሥራ ለመልቀቅ መገደዳቸውን ጠቅሰዋል።

አክለውም ባንኩ ይህንን መሰረት በማድርግ ጥናት አድርጎ ነበር ያሉ ሲሆን፣ በዚህ ዓመትም የስድስት ወራት ሪፖርት በቀረበበት ወቅት ሠራተኞች ቅሬታቸውን ለባንኩ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።
ብሔራዊ ባንክ ያደረገው ጭማሪ ባንኩን ከሌሎች የግል እና የመንግሥት ባንኮች የተሻለ ክፍያ ያለው እንዲሆን ያደርገዋል ብለዋል።

‹‹የአመራር ለውጥ ከተካሄደ በኋላም የተሻለ የሠራተኞች አያያዝ እና በባንኩ አሰራር ላይም በርካታ ለውጦች መጥተዋል። አሁን በአንፃራዊነት የተሻለ የሠራተኛ አያያዝ ስላለ የሥራ ፍላጎታችንም ተሻሽሏል›› ሲሉም ሥማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ አንድ ሠራተኛ አስተያየት ሰጥተዋል። የተደረገው የደሞዝ ጭማሪም የሠራተኞችን ፍልሰት ይቀንሰዋል፣ ሠራተኞችም በተሻለ ተነሳሽነት እንዲሠሩ እንደሚያደርግ አያይዘው አንስተዋል።

ባንኩ በአዲስ አባበ እና በድሬዳዋ ቅርንጫፎችን በመክፈት አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ የተጠቀሰ ሲሆን፣ በሌሎች በርካታ ከተሞች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ወኪል በማድረግ አገልግሎት ይሰጣል። ባንኩ በጠቅላላው ከ1500 በላይ ሠራተኞችን በማስተዳደር ላይ ይገኛል። ከኹለት ዓመታት በፊት መጠነኛየደሞዝ ጭማሪ ቢያደርግም የሠራተኞችን ጥያቄ ግን የሚመልስ አልነበረም።
ብሔራዊ ባንኩ ለባንኮች እና ለሌሎች የገንዘብ ተቋማት ፈቃድ መስጠት እና መቆጣጣር፣ አገር ውስጥ ተቀማጭ ገንዘብ ማስተዳደር፣ የወለድ መጠንን መወሰን፣ የወርቅን ዕሴት እና የውጪ ምንዛሬ መጠንን መወሰንን የሚያካትቱ በርካታ ግዴታዎችና ኃላፊነቶች ተጥለውበታል።

ለበርካታ ዓመታት ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በመተንትን የሚጣወቁትአብዱልመናን መሀምድ የደሞዝ ጭማሪው የሰራተኞችን ፍልሰት ሊያስቀር ይችላል የሚለው በባንክ እና በፋይናንስ ዘርፉ የመክፍል አቅም የሚወሰን እንደሆነ ገልፀዋል

በብሔራዊ ባንኩ የተደረገው የደሞዝ ጭማሪ አግባብነት ያለው ነውም ብለዋል ተወዳዳሪ ክፍያ መክፈል ሰራተኞች በስራው ላይ እንቆዩ ለማድርግ እንደሚረዳም ጠቁመዋል፡፡
የዋጋ ግሽፈትን በተመለከተም የደሞዝ ጭማሪ የዋጋ ግሽፈትን ሊያመጣ የሚችለው ለጠቅላላው ማህበረሰብ ሲደረግ ነው በተወሰኑ ተቋማት የሚደረግ የደሞዝ ጭማሪ የዋጋ ግሽበት የሚያመጣበት ምክኒያት የለም ብለዋል፡፡

የተደረገው ጭማሪ የሰራተኞችን የስራ ተነሳሽነት መጨመሩን የገለፁት ባለሙያው ብሔራዊ ባንኩ አሁንም ቁልፍ ቦታዎች ላይ ያሉ ሰራተኞች የሚመዝንበትን መለኪያ እንዲሁም በእነዚህ ቁልፍ ቦታዎች ላይ በሚመደቡ ሰዎች አመራረጥ ላይ ለውጥ ሊያደርግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 66 ጥር 30 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com