የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች ሥልጠና በመንግሥት ወጪ መደረጉ ቅሬታ አስነሳ

Views: 799

የመንግሥት ተንቀሳቃሽ ሂሳቦች ዝግ ሆነው ቆይተዋል

ብልፅግና ፓርቲ ከመስተዳድር ጀምሮ እስከ ዞን ላሉ የቢሮ ኃላፊዎች እና ምክትል ቢሮ ኃላፊዎች በአዳማ ከተማ እየሰጠ ላለው ሥልጠና የውሎ አበልን ጨምሮ ሌሎች ወጪዎችን ከመንግሥት ካዝና እንዲሸፈን መደረጉ ቅሬታ አስነሳ።

ለፓርቲው አባላት እና ከክልላዊ መስተዳደር ጀምሮ እስከ ዞን ባሉ መዋቅሮች ለሚገኙ የቢሮ ኃላፊዎች እና ምክትል ኃላፊዎች በአዳማ ከተማ ላለፉት 15 ቀናት ሥልጠና ሲሰጥ ቆይቷል። ለሥልጠና የተላኩ ኃላፊዎች ወጪም ከመንግሥት ካዝና መሸፈኑን ጨምሮ ሥልጠናው በሥራ ቀናት ላይ በመደረጉ በሥራዎች ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን በማንሳት በርካታ ቅሬታዎች በመቅረብ ላይ ይገኛሉ።
ሥማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንደተናገሩት፣ በደቡብ ክልል የቢሮ ኃላፊዎች እና ምክትል ኃላፊዎች ለሥልጠናው አዳማ ሲላኩ የግለሰቦች ወጪ እና ውሎ አበል ከመንግሥት ካዝና ወጪ የተደረገ ነው። ‹‹አንድ የቢሮ ኃላፊ በቀን 755 ብር የውሎ አበል፣ ሌሎች ወጪዎችን ሳይጨምር ይከፈለዋል›› ብለዋል።

‹‹ይሄ ማለት አንድ የቢሮ ኃላፊ በእነዚህ ቀናት ከ 20 ሺሕ ብር በላይ ያስፈልገዋል›› ብለው ባለፉት ቀናትም ለሥልጠናው ገንዘብ ማነሱን በመግለፅ ተጨማሪ ገንዘብ ወጪ ሲደረግ መመልከታቸውን ተናግረዋል።

አክለውም የቢሮ ኃላፊዎች መኪኖች እና ሹፌሮች እዛው አዳማ መሆናቸውን ገልፀው፣ በክልል ርእሰ መስተዳደር ጽሕፈት ቤት ላይ ውሳኔ የሚሰጥ ሰው ያለመኖሩን እና ውሳኔ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች እየተጓተቱ ተገልጋዮች እየተስተጓጎሉ ይገኛሉ ሲሉ ገልፀዋል። የድርጅት ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት በርዕሰ መስተዳደር ቢሮ ስር የአማካሪነት ሥልጣን ተሰጥቷቸው ከመንግሥት ካዝና ደሞዝ እየተከፈላቸው ይገኛል ሲሉም አክለው ጠቅሰዋል።

የቢሮ ኃላፊዎች ባለመኖራቸውም ሰዎች ጉዳይ ለማስፈፀም ችግር እንደገጥማቸው የተገለፀ ሲሆን፣ መሰል የድርጅት ሥልጠናዎች እና ስብሰባዎች ሲኖሩ ውሳኔ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ አፋጣኝ ውሳኔ የሚሰጥ ኃላፊ ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱም ተነስቷል።

በአንዳንድ ክልሎች የመንግሥት ተንቀሳቃሽ ሂሳቦች ተዘግተው እንዲቆዩ የተደረገ ሲሆን፣ የክልል መስተዳድር ቢሮዎች ውስጥ መደበኛ የመንግሥት ስራዎችን ለማከናወን መቸገራቸውን በሱማሌ ክልል የሚገኙ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በሶማሌ ክልል የቢሮ ኃላፊዎች አለመኖራቸውን ተከትሎ፣ ከበጎ አድራጎት እና መሰል ሥራዎች ውጪ ያሉ የባንክ ሂሳቦች ታግደው እንዲቆዩ እንደተደረገ አዲስ ማለዳ ከታማኝ ምንጮች ማረጋገጥ ችላለች። ይህንንም ተከትሎ እንደ ጨረታ ማስከበሪያ ያሉ ክፍያዎች ለመክፈል እና ሌሎች መደበኛ ሥራዎችን ለማከናወን ችግር እንዳጋጠመ ከስፍራው ማረጋገጥ ተችሏል።

ይህንን ጨምሮ ለበርካታ ጊዜያት በክልሉ የድርጅት ሥልጠናዎች ሲኖሩ ወጪው በድርጅቱ ቢሸፈንም እንኳን ከመንግሥት ካዝና አበል ይከፈላል የተባለ ሲሆን፣ በሥልጠናዎች ቢሮዎች ዝግ ሆነው እንዲቆዩ ይደረጋል ተብሏል። ውሳኔ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች እንዲዘገዩ ምክንያት መሆኑን በሶማሌ ክልል ያሉ ምንጮች ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ቢሮ ኃላፊ ታዪ ደንደአ በኦሮሚያ ክልል ሥራዎች እንዳይስተጓጎሉ ለማድረግ ውክልና ተሰጥቷል፣ በተወሰነ መልኩ መስተጓጎሎች መኖራቸው ግን የማይቀር ነው ያሉ ሲሆን፣ የሥልጠና ወጪዎች ግን በብልፅግና ፓርቲ ማእከላዊ ጽሕፈት ቤት የተሸፈኑ ነበሩ ሲሉ ጉዳዩን አስተባብለዋል።

የህዝብን ሀብት ለአንድ ፖለቲካ ፓርቲ ጉዳይ ማዋል ከስነ ምግባር ያፈነገጠ ነው የዓለማቀፍ የሕገ መንግሥት የምርምር ኢንስቲቱት (አይዲኢኤ) አርታኢ የሆኑት አደም ካሴ (ዶ/ር) ድርጊቱ በህጋዊነቱም ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

አክለውም ስለ ምርጫ ሜደው መንግስት ቃል በገባው ልክ እየሄደ ስላለመሆኑ የሚያመላክት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የተዘጋጁ የህግ ማዕቀፎችም ቢሆኑ የህዝብን ሀብት ከአገር ጥቅም ከሆነ ጉዳይ ይልቅ በስልጣን ላይ ላለው ፓርቲ ጥቅም ማዋልን ለመቆጣተር የሚያስችሉ እና በቂ እንዳልሆኑ ገልፀዋል ፡፡

የኢትዮጵያ የምርጫ፣የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ ምዕራፍ ሶስት ቁጥር ሰባት ላይ የመንግስት ሰራተኛ እና ኃላፊ ሆኖ በራሱ ሳይሆን በመንግስት የስራ ሰዓት እና ኃላፊነት ተቋሙን በመጠቀም እጩዎችን ያስተዋወቀ ወይም ሌሎች ዕጩዎች በህጋዊ መንገድ እንዳያስተዋውቁ ያደናቀፈ የስነ ምግባር ጥሰት እንደፈፀመ እንደሚቆጠር ይገልፃል፡፡ እንዲሁም የመንግስትን ንብረት ለምርጫ ቅስቀሳ መጠቀም እንደማይቻል ያትታል ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ አንቀፅ የምርጫ ቅስቀሳን ብቻ የሚመለከት ነው እንጂ ከዛ ውጪ ያሉ ሉሎች ዝርዝር ጉዳዮችን የሚዳስስ አይደለም የሚሉ ሀሳቦች ይነሳሉ፡፡

አዲስ ማለዳ በሚኒስትር ማዕረግ የብልፅግና ፓርቲ የውጪ እና የአገር ውስጥ ግንኙነት አስተባባሪ አወሎ አብዲን በስልክ ለማነጋገር ከፍተኛ ጥረት ብታደርግም፣ ስብሰባ ላይ መሆናቸውን በመግለፅ ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋ፣ አዲስ ማለዳ ምርጫ ቦርድን ለማነጋገር ያደረገችው ጥረትም ሳይሳካ ቀርቷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 66 ጥር 30 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com