ዳሰሳ ዘ ማለዳ (የካቲት 03/2012)

Views: 569

የመሬት ወረራ ለከተማ አስተዳደሩ ፈተና ሆኗል ተባለ

የመሬት ወረራ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፈተና እየሆነ መምጣቱ ተገለፀ። ሙስናና ብልሹ አሰራር፣ የመረጃ አያያዝ ማነስ፣ የግልጽነትና ተጠያቂነት ችግሮች ከህግ ስርአቶች አለመከበር  ለመሬት ወረራው መስፋፋት በምክንያት ተጠቅሷል። በከተማዋ ህገወጥ የመሬት ወረራ እና ተያያዥ ችግሮችን አስቀድሞ ለመከላከል እና አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ የመሬት መረጃ አያያዝ ስርዓቱን የማዘመን ስራ እየተሰራ መሆኑን የከተማ መሬት ልማት ቢሮ  ገልጿል ።(ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

አዲስ ዘመን ጋዜጣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ላለፉት ስምንት ወራት በደብዳቤ፣ በስልክና በአካል በመገኘት መረጃ ቢጠይቀም ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆኑ የዕንባ ጠባቂ ተቋም መረጃውን እንዲያሰጠው ይግባኝ ጠየቀ። አዲሰ ዘመን ጋዜጣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባለፉት ስምንት ወራት በቃል፣ በደብዳቤና በአካል ጭምር በመሄድ ስለተቋሙ እንቅስቃሴ፣ በተቋሙ አለ ስለሚባለው የግልጽነትና የአሠራር ችግር፣ የብድር አሰጣጥና አመላለስ፣ የብድር ብልሽትና መንስዔ፣ በተቋሙ ስለተከሰቱ የብድር ብልሽቶችና ተጠያቂነት፣ የቀጣይ ማሻሻያና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች ለባንኩ ፕሬዚዳንት ጨምሮ በየደረጃው ላሉ ኃላፊዎች ማብራሪያ እንዲሰጡትና ተቋሙ ላይ ያሉ አሠራሮችና የባንኩ አካሄድ ለባንኩ ባለቤት ለኢትዮጵያ ህዝብ ግልጽ እንዲያደርግ በተደጋጋሚ ቢጠየቅም የተለያዩ ሰበቦችን በመደርደር መረጃውን ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆኑ ይግባኝ መጻፉን አመላቷል።(የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

በአስቸኳይ ፓስፖርት ለማውጣት ክፍያ የሚፈፅሙ ተገልጋዮችን መልስ የለኝም አትጠይቁኝ የምትለዋ የኢሚግሬሽን፣ የዜግነት እና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ሰራተኛ ከሥራ መታገዷ ተገለጸ፡፡ ከተግልጋዮች ቅሬታ የቀረበባት ባለሙያዋ ጉዳይዋ በዲሲፕሊን እንደሚታይም ተነግሯል፡፡ (ሸገር ኤፍ ኤም)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

በአሁኑ ሰዓት በለይቶ ማቆያ ማእከል ውስጥ የኮሮና ቫይረስ በሽታ ምልክት ታይቶበት የገባ ሰው አለመኖሩ ተገለጸ፡፡ የቫይረሱን ስርጭት በተመለከተ 39 ጥቆማዎች ለኢንስቲትዩቱ የድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል የደረሰው ሲሆን በሁሉም ጥቆማዎች ላይ ማጣራት እንደተደረገ አስታውቋል፡፡(የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

ከጥራት ደረጃ በታች የሆነ 19 ሺህ ሰባት መቶ በላይ ጀሪካን ፓልም የምግብ ዘይት ወደ ሀገር ውስጥ ሊገባ ሲል መታገዱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባለፉት 6 ወራት 875,691.42 ሜትሪክ ቶን የገቢ ምርቶች ላይ የጥራት ቁጥጥር ለማድረግ አቅዶ በ1,465,177.44 ሜትሪክ ቶን ምርቶችን ቁጥጥር አድርጎል፡፡የቁጥጥር ስራው የተካሄደው አስገዳጅ የኢትዮጵያ የጥራት ደረጃ የወጣላቸው የገቢ ምርቶች ላይ ሲሆን ፓልም የምግብ ዘይት፣የቤት ክዳን ቆርቆሮ፣የአርማታ ብረት፣ ሳሙና፣ሚስማር እና የታሸጉ ምግቦች ይገኙበታል፡፡(አዲሰ ማለዳ)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

የዘንድሮው የመከላከያ ሠራዊት ቀን “የሀገራችንን ሉዓላዊነትና የሕዝባችንን ሠላም በፅናት እንጠብቃለን” በሚል መሪ ሃሳብ የፊታችን ቅዳሜ የካቲት 7/ 2012  እንደሚከበር ታውቋል። በዓሉ ከሕብረተሰቡ ጋር በሚደረጉ ውይይቶች፣ በበጎ አድራጎት ስራዎች፣ በስፖርታዊ ውድድሮች፣ የሠራዊቱን ዝግጁነት በሚያሳዩ ወታደራዊ ሰልፎችና ትርዒቶች ታስቦ ይውላል። ቀኑ እስካሁን ሠራዊቱ የሔደባቸው ጉዞዎች የሚቃኙበት፣ ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን በማረጋገጥም እንዳለፉት ጊዜያት ሁሉ ተልዕኮውን በጽናት ለመወጣት ያለውን ዝግጁነት የሚያሳይበት ነው ብሏል ።(ኢዜአ)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

አስገዳጅ የኢትዮጵያ ደረጃ መስፈረት ያላሟሉ ምርቶችን ሲያመርቱ የተገኙ ዘጠኝ ፋብሪካዎቸ ላይ እርምጃ መውሰዱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ቁጥጥር ከተደረገባቸው 185 ፋብሪካዎች ውስጥ ከ47 ፋብሪካዎች ላይ ወካይ ናሙናዎችን በመውሰድ የፊዚካል እና የላብራቶሪ ምርመራ የተደረገባቸው ሲሆን በላብራቶሪ ምርመራ ውጤት መሰረት የዘጠኝ ፋብሪካዎች ምርት ከደረጃ በታች በመሆናቸው ከማስጠንቀቂያ እስከ እሸጋ የሚደርስ እርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡እርምጃ የተወሰደባቸው የሳሙና፣ የሲሚንቶ፣የውሃ እና የወይን ፋብሪካዎች ሲሆኑ የ14 ፋብሪካዎች ናሙና የላብራቶሪ ውጤት እስከሚደርስ እየተጠበቀ መሆኑም ተገልጿል፡፡

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

በደምቢዶሎ ዩንቨርሲቲ ተማሪዎች የተፈጸመው ብቻ ሳይሆን ቀጣዩ ጊዜ እንደሚያሳስባቸው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጥምረት እና የኢትዮጵያ ሴቶች ህግ ባለሙያ ማህበር አስታወቁ፡፡ በሴቶች ላይ የሚፈፀመው ጥቃት መልካቸውን እየቀየሩ እና እየጨመሩ ለመምጣታቸው በደምቢዶሎ የታገቱት ሴት ተማሪዎች አንድ ማሳያ ነው ሲል የኢትዮጵያ ሴቶች ህግ ባለሙያ ማህበር ገልጿል ።በመሆኑም በሴቶቹ ላይ አስካሁን የተፈፀመው ብቻ ሳይሆን ወደ ፊት የሚፈፀመውም ያሳስበናል ብሏል።(ኢትዮ ኤፍ ኤም)

 

 

 

 

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com