ዳሰሳ ዘ ማለዳ (የካቲት 5/2012)

Views: 238

 በሞጣ ከተማ ለደረሰው ጉዳት መልሶ ማቋቋም የሚውል 209 ሚሊዮን ብር ተሰበሰበ

ለተቃጠሉት የሞጣ መስጊዶች መልሶ ግንባታ እና ንብረት ለወደመባቸው ዜጎች ማቋቋሚያ የሚውል ከ209 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ዛሬ የካቲት 05/2012 በሠጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ  አስታወቀ። ከጥር 22/2012 ጀምሮ በተካሄደው የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ከተጠቀሰው ጥሬ ገንዘብ በተጨማሪ ከ700 ሺህ ብር በላይ በዓይነት መሰብሰቡንም ምክር ቤቱ የገለጸ ሲሆን ከህዝበ ሙስሊሙ ባለፈ ህዝበ ክርስቲያኑም በድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ላይ መሳተፉን ምክር ቤቱ ገልጿል።

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር ) ወደ ተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ያቀኑ ሲሆን በቆይታቸው በሀገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን መብት እና ጥቅም የሚያስከብሩ ውይይቶችን እንደሚያደርጉ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን  በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል። በቆይታቸውም ከ15 ሺህ ኢትዮጵያውያን ጋር  ይወያያሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡(ጠቅላይ ሚኒስትር ጽኅፈት ቤት)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

 

በመድረክ ትወና ከ40 ዓመታት በላይ ያገለገሉት አንጋፋው አርቲስት ጀምበሬ በላይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።አርቲስቱ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ1949 እስከ 1953  በቀድሞዉ የሀገር ፍቅር ማህበር በአሁኑ የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት በመድረክ ትወና ያገለገሉ ሲሆን ከ1953 እስከ 1988 በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በመድረክ ትወና ሲያገለግሉ ቆይተዋል። በተያያዘ ዜና የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ተጫዋች የነበረው ሞገስ ታደሰ ባጋጠመው የጤና እክል ሕክምና ላይ ቆይቶ በዛሬው ዕለት የካቲት 05/2012  ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ሞገስ ታደሰ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ከ’C’ ቡድን ጀምሮ እስከ ዋናው ቡድን፣ ለሲዳማ ቡና፣ ለአዳማ ከተማ፣ ለኤሌክትሪክ እና ለወልድያ ክለቦች ተጫውቷል።(ፋና ብሮድካስቲን ኮርፖሬት)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

በያዝነው 2012 ግማሽ ዓመት ወደ 18 ሺህ ቶን የሚጠጋ ደረቅ ቆሻሻን  ሰብስቦ መልሶ ወደ ሀብትነት በመቀየር የ52 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡ መንግስት ካደራጃቸው 74 የህብረት ሽርክና የፅዳት ማህበራት በተጨማሪ በራሳቸው ተነሳሽነት ደረቅ ቆሻሻን የሚሰበስቡ ከ40 በላይ የግል የፅዳት ድርጅቶች በከተማዋ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡(ኢቢሲ)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

የጅማ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ዛሬ የካቲት 05/2012  በጅማ ከተማ ስታዲየም የድጋፍ ሰልፍ ያካሄዱ ሲሆን ሰልፉ  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን (ዶ/ር)፣ መላውን የለውጥ አመራር እና ብልጽግና ፓርቲን ለማበረታታት ያለመ እንደሆነ ተጠቅሷል። በሰልፉ ላይም  የተሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎች ሰዎች ባላቸው ፖለቲካዊ አመለካከትና አስተሳሰብ ሊሰደቡ አይገባም ብለዋል።(ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

በአዲስ አበባና በተወሰኑ ክፍሎች በቴክኖሎጂ የተደገፈ የትራፊክ አስተዳደር ስርእት ዝርጋታ እንደሚጀምር የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂ ጌታሁን መኩሪያ ለአዲሱ ሚኒስትር ዶ/ር አብርሀም በላይ በተቋሙ ሲከናወኑ የነበሩ አበይት ተግባራትን በተመለከተ የመዉጫ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ተናግረዋል፡፡ (የሳይንስ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር)

 

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ሲያደርግ የነበረውን ድጋፍ ማድረግ ባለመቻሉ በአግባቡ መማር እንዳልቻሉ ገለፁ። ዩኒቨርሲቲው በዓመት እስከ 8000 ብር ድጋፍ ያደርግ እንደነበር ተማሪዎቹ ተናግረዋል። የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጽኀፈት ቤት ኃላፊ አራጋው ልጃለም ጉዳዩን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር ለመፍታት እንሞክራለን ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።(ዶይቼ ቬለ)

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ በ25 ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ባደረገው ድንገተኛ ጉብኝት ህግ ተላልፈው ተገኙ ባላቸው 6 የግል ከፍተኛ ተቋማት ላይ እንዲዘጉ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ፡፡ እርምጃ ከተወሰደባቸው መካከል ፓራዳይዝ ቫሊ ኮሌጅ አዳማ ካምፓስ፣ ኢትዮ ስማርት ኮሌጅ አድዋ ካምፓስ እና በጋምቤላ ከተማ 4 ተቋማት  ላትጆር ኮሌጅ፣ዌስተርን መካኢየሱስ ኮሌጅ፣ ሾውቤል ኮሌጅ እና ሉተራን ካቶሊክ ኮሌጅ ይገኙበታል ብሏል፡፡ (ኢትዮኤፍኤም)

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com