የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የተዘጋጀው አዋጅ ፀደቀ

Views: 209

የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ23 ተቃውሞና በኹለት ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ አፀደቀ።
ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት እንደተከራከረ የተገለፀ ሲሆን፣ በ23 ተቃውሞና በኹለት ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ መጽደቁን ከፓርላማ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

አዋጁ የሕገ መንግሥቱን አንቀፅ 29 ንዑስ አንቀፅ ስድስትን እና አገሪቱ ያፀደቀችው ዓለማቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብት /ICCPR/ አንቀፅ 19 ንዑስ አንቀፅ 3 ላይ የተደነገገውን መሰረት ያደረገ ሲሆን፣ በብሔር ብሔረሰብና በሕዝብ፣ በዘር፣ በፆታ፣ በሐይማኖት ወይም በአካል ጉዳተኝነት ላይ ተመስርተው የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮችንና የሐሰት መረጃዎችን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሲባል መሆኑ ተገልጿል።

በተጨማሪም ማንኛውም ሰው ሐሳቡን በነፃነት የመግለፅ መብቱን ሲጠቀም ግጭት ወይም ሁከት የሚቀሰቅስ፤ በግለሰብ ወይም ቡድን ላይ ጥላቻ የሚያስፋፋ ንግግሮችን ከማድረግ እንዲቆጠብ የሚያግዝ በመሆኑ የአገርን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳለው በሪፖርቱ ላይ ተቀምጧል።

በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተደረጉ ማሻሻያዎች አንቀፅ 2/2/ የጥላቻ ንግግር ማለት በአንድ ሰው ወይም በተወሰነ ቡድን ማንነት ላይ ያነጣጠረ ብሔር፣ ብሔረሰብንና ሕዝብን፣ ሐይማኖትን፣ ዘርን፣ ፆታን ወይም አካል ጉዳተኞችን መሰረት በማድረግ ሆን ተብሎ ጥላቻን፣ መድሎን ወይም ጥቃትን የሚያነሳሳ ንግግር ማለት ነው።

አንቀፅ 2/3/ ደግሞ ሐሰተኛ መረጃ ማለት መረጃው ሐሰት የሆነና የመረጃውን ሐሰተኝነት በሚያውቅ ወይም መረጃውን የሚያሰራጨው ሰው ካለበት አጠቃላይ ሁኔታ አንፃር የመረጃውን እውነተኝነት ለማጣራት በቂ ጥረት ሳይደረግ የሚሰራጭ ሁከትን ወይም ግጭትን የሚያነሳሳ ወይም ጥቃት እንዲደርስ የሚያደርግ የሐሰት መረጃ ነው በማለት በሪፖርቱ ላይ በሰፊው ተብራርቷል።

በተጨማሪም አዋጁ የተለያዩ የቅጣት መጠኖችን ያስቀመጠ ሲሆን፣ የጥላቻ ንግግር ወይም የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ወንጀሉ የተፈፀመው ከአምስት ሺሕ በላይ ተከታይ ባለው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ከሆነ ወይም በብሮድካስት አገልግሎት ወይም በየጊዜው በሚወጣ የሕትመት ውጤት ከሆነ ቅጣቱ እስከ ሦስት ዓመት የሚደርስ ቀላል እስራት እና ከብር 10‚0000 ያልበለጠ መቀጮንም ያስቀምጣል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የማኅበራዊ ሚዲያ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች በዚህ አንቀፅ የተቀመጠውን ግዴታቸውን በአግባቡ መወጣታቸውን እየተከታተለ፣ ለሕዝብ ይፋ የሚሆን ሪፖርት ማዘጋጀት እንዳለበት በሪፖርቱ በዝርዝር ተገልጿል።

ቅጽ 2 ቁጥር 67 የካቲት 7 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com