አባይና የነገይቱ ኢትዮጵያ

Views: 472

አባይ የህዳሴ ግድብ አርፎበት እንዲህ መነጋሪያ ከመሆኑ በፊት በአንድ ጎን በውበቱ የሚወደስ፣ በጉልበቱ የሚደነቅ፣ ማደሪያ የለውም እየተባለ የሚወቀስ የኪነጥበብ ማጣቀሻ ነበር። አሁን ህዳሴ ግድብ የሰፈረበት አባይ ታድያ ኢትዮጵያን እንደ ግብጽና ሱዳን ካሉ የጎረቤት አገራት ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ የዓለም አገራት ጋር ያገናኛት ጉዳይ ሆኗል። ይህንንም የሚያነሱት አግዮስ ምትኩ፣ የዛሬ ሙግት መጨረሻ ምንም ይሁን ምን ግብጽ ለኢትዮጵያ ሰላም ማጣት ልትንቀሳቀስ፣ በኢትዮጵያ ዙሪያ ያሉ አገራትንም ልታስነሳባት ትችላለች ሲሉ ስጋታቸውን ያካፍላሉ። ለዚህም የአገር ውስጥ አንድነትን ማጥበቅ ላይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ሲሉ ያሳስባሉ።

‹‹የማያረጅ ውበት የማያልቅ ቁንጅና፣
የማይደርቅ የማይነጥፍ በዘመን የጸና፤
ከጥንት ከጽንስ አዳም ገና ከፍጥረት፣
የፈሰሰ ውሃ ፈልቆ ከገነት፣
ግርማ ሞገስ፣
የአገር ፀጋ የአገር ልብስ
ግርማ ሞገስ
ዓባይ…
የበረሃው ሲሳይ
/እጅጋየሁ ሽባባው/
አባይ ሲሳይ ነው … ግን ደግሞ ሲሳይ ብቻ አይደለም። ዕዳም ነው፣ ለኢትዮጵያ።

አባይ ወይም ግዮን ለብዙዎች ሃይማኖት ነው። ከኤደን መናፈሻ ወንዞች አንዱ የሆነው ግዮን ከኤፍራጠስ፣ ጢግሪስና ኤፌስን ጋር ተደምሮ ትልቅ ሃያማኖታዊ ሥም ያለው ጠበል ነው። ፈውስን ሽተው የሚጠቀሙበት አያሌዎች ናቸው። አምነውበት፣ ዶሮና በግ፣ ፍየልና በሬ የሚሰውሉትም ብዙዎች ናቸው። አባይ አድባርና ቆሌያቸው ነውና።

ደግሞም አባይ ማለት ሃረግ ነው። ለተፋሰሱ አገራት መግባቢያ ቋንቋ ነው። አባይ 6 ሺሕ 700 ኪሎ ሜትር በላይ ይረዝማል። በዓለማችንም ላይ ረጅሙ ወንዝ ነው። ሳያጡ ያጡ ከ360 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የሚኖሩባቸውን አገራት ማለትም ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ታንዛንያ፣ ዮጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ የኮንጎ ዴምክራቲክ ረፐብሊክ፣ ኤርትራ፣ ግብፅና ሱዳንን የማያስተሳስር ጠንካራ…ወፍራም ሃረግ ነው። በአካባቢው የሚገኙ በተደጋጋሚ ድርቅ የሚጎበኛቸው የተፈሳሱ የላይኛው አገራትና ፍትሃዊ ባልሆነ መልኩ ወንዙን በሚጠቀሙት በግብፅና ሱዳን ጋር መነጋገሪያና ዕጣ ፈንታ መወሰኛ ስለሆነ አዎ አባይ ቋንቋ ነው።

በዚህም በአኅጉራዊና በዓለም አቀፋዊ የውሃ ጂኦ ፖለቲካ መገለጫነቱ ይጠቀሳል። አባይ ላይ ያለው ጉዳይ ከተፋሰስ አገራቱ አልፎ፣ አፍሪካን ተራምዶ እስከ መካከለኛው ምሥራቅ አውሮፓ እና አሜሪካ ይደርሳል። ከዚህም አልፎ በዓለም ዐቀፍ የገንዘብ የረድኤት ተቋማት- የውሃ- የሚትዮሮሎጂ – የአካባቢ- የመልከአ ምድርና የብዝኀ ሕይወት ምክር ቤቶች ቋንቋ ነው። ይህም የአባይ ጉዳይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አሳሳቢነቱ እየሰፋ መጥቷል። ለዚህም ተዋናዮቹ የመካከለኛው ምሥራቅ እና የሰሜን አፍሪካ አገራት ፍትሐዊ ያልሆነ ወንዙን የመጠቀም ፍላጎት ማሳየትና የላይኛው ተፋሰስ አገሮች ወንዙን ተጠቅመው ከድህነት ለመውጣት በሚያደርጉት ጥረት መካከል የሚፈታ እሰጣ ገባ ነው።

በኢትዮጵያና በመካከለኛው ምሥራቅ መካከል ያሉ ግንኙነቶችንም እያሻከሩ ከነበሩት ጉዳዮች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የአባይ ጉዳይ ነው። በጊዜ ሂደት ግብፅ የአረቡ አገር መሪ እየሆነች ስትመጣ የአባይ ጉዳይ ከኢትዮጵያና ከሌሎች የአረብ አገሮች ላይ ተፅእኖ እያሳረፈ መጥቷል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ከእስራኤል ጋር ያለን ግንኙነትም ከአባይ ጋር እየተገናኘ እየመጣ ነው። ኢትዮጵያም ከሌሎች አገራት ጋር ያላት ግንኙነት የአገራዊ ጥቅም – ማለትም ልማትዋና ህልውናዋ ላይ የተመሰረተ ሊሆን እንደሚገባ ይታወቃል።

እንደሚታወቀው ግን ግብፅ – “አል ሰላም” ወይም “የሰላም ቦይ” ፕሮጀክት የአባይን ወንዝ በሲውዝ ቦይ በኩል ወደ ሲናይ በረሃ በማሳለፍ ወደ እስራኤል የማሻገር ሩጫዋን ከጀመረች ከ10 ዓመታት በላይ ሆኖታል። ስለዚህ የአባይን ውሃ ከእስራኤል ጋር የማጣበቅና ለኢትዮጵያ ሌላ አዲስ ጠላት የመፍጠር ሴራ እየተፈፀመ ይገኛል።

በዚህም ጉዳይ ላይ ያለው ስጋት የግብፅና የእስራኤል ትብብር ዘላቂነት በኢትዮጵያ ደኅንነት ላይ ምን ውጤት እንደሚኖረው መገመት አያስቸግርም። ይህንንም ግልፅ የሆነ የዓለም አቀፍ ሕግ መጣስ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት አሳውቋል።

የናይል ሸለቆ አሥር የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የሚጋሩት ወንዝ ነው። ይህ ወንዝ ግብፅ ላይ ደርሶ አስዋን ግድብ ከመግባቱ በፊት ሲለካ 84 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ነው። ከዚህ ውስጥ 72 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ኢትዮጵያ የምታበረክተው ነው። ግን ግብፅ ኢትዮጵያንም ሆነ ሌሎች የተፋሰሱ አገራትን ሳታማክር “የሰላም ቦይ” እና ‹ቶሽካ› ፕሮጀክቶች እስኪጠናቀቁ ድረስ በዲፕሎማሲ እያዘናጋችም- በጦር ኃይል እያስፈራራችም የአባይን ውሃ በለመደችው የአንበሳነት ድርሻ ለመጠቀም እንቅስቃሴዋን ለአፍታ እንኳ አልገታችም። በተለይም “የአባይ ውሃ ጥራቱን በጠበቀና እጅግ ምቹ በሆነ ሁኔታ መጠቀም” የሚል እስከ ደም ጠብታ የሚዘልቅ የሚመስል አቋም ይዛለች።

ምን እንኳን በአባይ ላይ የሚተኮስ ጥይት የከፋ ቢሆንም ጥይቱ ቢተኮስም ባይተኮስም ከውሃ ፍትሃዊነት ጥያቄ አንፃር ኢትዮጵያ አሁን እየገነባች ያለው የህዳሴ ግድብ ፍትሃዊነቱ አያጠያይቅም። ነገር ግን ብዙ ሰዎች የሚያነጋግረው ግድቡን ግብፅ ባታስቆመውም ወደፊት ከግድቡ ውሃና ከመጠቀም ጋር ተያይዞ የሚባሉ ችግሮች ብዙ ናቸው።

ከእነዚህም መካከል አንደኛው ከዓመታዊ ገቢዋ አንፃር ከፍተኛ በጀት በመመደብ ከዓለማችን ቀዳሚ አገሮች ጎራ የምትሰለፈዋ ግብፅ፣ በጦር ኃይል ፍትሐዊ የሆነውን የኢትዮጵያ ውሃ የመጠቀም መብት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጫና ልታሳድራለች የሚል ነው። ይህንንም ለማድረግ በአገሪቱ የተለያየ አቅጣጫ ባሉ ድንበሮችና ጠረፎች የተለያዩ ቡድኖችን የጦር ኃይል በማስታጠቅና የእርስ በእርስ ግጭት በመፍጠር አገሪቱን ወደ ቀድሞ ድህነቷ እንድትመለስ ልትገፋት ትችላለች የሚለው ነው።

ኹለተኛው ደግሞ ግብፅ ብቻዋን ወይም ከተባባሪዎቿ ጋር ቀጥታ ኢትዮጵያን አጥቅታና አሸንፋ ከአባይ ውሃ ላይ ምንም አይነት ፕሮጀክት የማያስብ፣ አሻንጉሊት መንግሥት የማስቀመጥና እርሱን የመጠበቅ ጉዳይ ልትፈፅም ትችላለች የሚለው ነው።

ስለዚህ ግብፅና ሱዳን አባይን እንዳሻቸው ሲጠቀሙ ኢትዮጵያና ቀሪ የራስጌ የተፋሰሱ አገራት በተለይም ኢትዮጵያ ሊቃጡባት የሚችሉትን ዘርፈ ብዙ ጥቃቶችና ችግሮች ቀድመው በማጤንና በመገንዘብ መዘጋጀት ያሻታል።

ከዚህም ውስጥ በዋናነት የሕዝቦችን አንድነትና አገር ወዳድነት ማጠናከር ወሳኝ ሂደት ነው። ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ አሰራሮችን በማስፈን አገሩን የሚጠላና በጠላት ኃይል ተደራጅቶ አገሩን ከሚጎዳ የራስ አገር ዜጋ እንዳይፈጠር መጣር ለኢትዮጵያ ያለውና ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። የማይተኙልን ጠላቶች በዙሪያችን አሉና።

አግዩስ ምትኩ በemail አድራሻቸው
agyos19@gmail.com ላይ ይገኛሉ።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com