አንበሳ ጋራዥ በ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወደ ዴፖ ሊቀየር ነው

Views: 353

ከሃምሳ ዓመት በላይ የአንበሳ አውቶቡስ ማቆሚያ እና የጥገና ቦታ ሆኖ ያገለገለው ዋናው መሥሪያ ቤት፣ በአንድ ጊዜ ከ850 በላይ አውቶቡሶችን ማስተናገድ እንችልና የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲሰጥ ‹‹የካ ዴፖ›› በሚል ግንባታ ሊከናወንለት ነው።

በሦሰት ወራት ውስጥ የሚጀመረው ይህ ግንባታ፣ ኹለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ወጪ ይጠይቃል። በተለምዶ ገርጂ መብራት ኃይል ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ በሚገኘው የአንበሳ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት፣ በአስር ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ነው።

ዴፖው ሸጎሌ እና ቃሊቲ ዴፖዎች በጋራ ለአውቶቢሶች ከሚሰጡት አገልግሎት እጥፍ መስጠት እንደሚችል የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የፕሮጀክቶች ኃላፊ ኢንጅነር ናትናኤል ጫላ ገልፀዋል። ከዴፖዎቹ ጎን ለጎንም በሦስት ሺሕ 500 ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፍ ባለ ኹለት ክንፍና ባለ ዘጠኝ ወለል የአስተዳደር ሕንፃ ይኖረዋል። 120 የቤት መኪኖችን ማቆም የሚያስችሉ ከመሬት በታች የሚገነቡ ኹለት ወለሎች እንደሚኖሩትም ቢሮው አስታውቋል።

ናትናኤል አያይዘው ‹‹መዲናዋ ለተሽከርካሪዎች አገልግሎት የሚሰጡ ደረጃቸውን የጠበቁ መናኸሪያዎች እና የአውቶብስ ዴፖዎች የሏትም። ያሉትም ከ 40 እና 50 ዓመታት በፊት የተሠሩ ናቸው›› ብለዋል።

እነዚህ የአውቶቢስ ዴፖዎች በቂ ጥገና ለማድረግ የሚያስችል ስፍራ የሌላቸው፣ ማቆሚያዎቹ በዘመናዊ መንገድ ያልተደራጁ፣ መለዋወጫዎችን ለማስቀመጥ እና ጥገና ለማድርግ የማያመቹ እንዲሁም የአውቶቢሶችን ንፅሕን ለመጠበቅ የሚያስችል መንገድ ያልነበራቸው እንደነበሩ አንስተዋል።

እነዚህን ዴፖች በዘመናዊ መንገድ እንደገና ከመገንባት በተጨማሪ በሌሎች አካባቢዎች መሰል ዴፖዎችን ለመገንባት ቢሮው እቅድ እንዳለው ተናግረዋል። የየካ አውቶቢስ ዴፖ አሁን አገልግሎት በመስጠት ላይ ካሉት የሸጎሌ እና ቃሊቲ ዴፖዎች እጥፍ አገልግሎት መስጠት እንደሚችልም ኃላፊው ገልፀዋል።

የሸጎሌ እና ቃሊቲ ዴፖዎች እያንዳንዳቸው ከ250 እስከ 300 አውቶቡሶችን የመያዝ አቅም ያላቸው እና በአንድ ጊዜ ስድስት አውቶቡሶችን ማስተናገድ የሚችል የነዳጅ ማደያ ያላቸው ናቸው።

በአንፃሩ የየካው ዴፖ በአንድ ጊዜ 12 አውቶቡሶችን የማስተናገድ አቅም ሲኖረው፣ 850 አውቶቢሶቸን ማቆም እንደሚችል ተጠቁሟል። እንዲሁም ለአሽከርካሪዎች ሥልጠና ለመስጠት የሚያግዝ የምስል መለማመጃ (driving simulator) ያካተተ እና ለ50 አውቶቢሶች በተመሳሳይ ጊዜ ጥገና ለማከናውን የሚያስችል ነው።
ግንባታውን ለማስጀመር በተደረገ የመጀመሪያው ምዕራፍ ጨረታ ለውድድር ከቀረቡት 13 የአገር ውስጥ እና የውጭ ግንባታ ተቋራጮች ባላቸው አቅም መሰረት ስምንቱ ለቀጣይ ዙር ጨረታ አልፈዋል።

ከእነዚህ ስምንት ተቋራጮች መካካል የተቋራቾችን የገንዘብ አቅም እና ሌሎች ቴክኒካዊ ሰነዶች በመመዘን ላይ መሆኑን ቢሮው አስታውቋል። የጨረታ ሂደቱ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ተጠናቆ በኹለት ወራት ውስጥ ግንባታው እንደሚጀመርም ተገልጿል።

የዴፖው ዝርዝር የንድፍ ጥናት “ሲስትራ ሳ” በተሰኘ የፈረንሳይ ኩባንያ የተሠራ ሲሆን፣ በአካባቢ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ በተመለከተ ነጋሽ ታምሩ ዘውዴ እና “እንሲራድ” ሲቪል ኢንጂነሪንግ ሶልሽንስ የተሰኙ ድርጅቶች ጥናት እና የማማከር ሥራ እያከናወኑ መሆኑን ናትናኤል ጠቅሰዋል።

በቀጣይ ዓመታት በብዙኀን ትራንስፖርት አማራጭ ላይ በትኩረት ይሠራል። አዳዲሶቹ ዲፖዎችም በዘመናዊ መልክ የተደራጁ እና በርካታ አውቶቢሶችን ለማቆም የሚያስችሉ ናቸው ያሉ ሲሆን፣ መገናኛ አካባቢ የሚታየውን የተዘበራረቀ የትራንስፖርት ስርዓት ለማስተካከል የመገናኛ የብዙኀን ትርንስፖርት መናኸሪያ ከ 2 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለመገንባት ቢሮው በጨረታ በሂደት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የመገናኛ የከተማ የብዙኀን ትራንስፖርት ተርሚናል በ11 ሺሕ 790 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፍ ሲሆን፣ ስምንት ወለሎች እንደሚኖሩት ኢንጅነር ናትናኤል ገልጸዋል። በዚህም መሠረት አራቱ ወለሎች ለአውቶቡሶች እና ለታክሲዎች አገልግሎት መስጫ፣ አንድ የንግድ ማዕከል ወለል፣ አንድ የመኪና ማቆሚያ ወለል፣ የአስተዳደር ቢሮ እና የብዙኀን ትራንስፖርት ስምሪት ሥርዓትን ያካተተ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

ተርሚናሉ በአንድ ሰዓት ውስጥ ስድስት ሺሕ ለሚጠጉ የብዙኀን ትራንስፖርት ተጠቃሚዎች አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል የጠቆሙት ኢንጂነር ናትናኤል፣ በውስጡም የአውቶቡስ መጠበቂያ ቦታ፣ የትኬት ሽያጭ፣ የተሳፋሪ መጫኛና የማራገፊያ ቦታ ይኖረዋል ብለዋል።

ዘመናዊ ስምሪት አገልግሎት፣ የአውቶቡስ መርሃ-ግብር እና የአስተዳደር ቢሮዎች እንዲሁም ለአቅመ ደካሞች እና አካል ጉዳተኞች የሚሆኑ በጠቅላላው አምስት አሳንሰሮች ያካተተ መሆኑን ገልፀው፣ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

የጨረታ ሂደቱ መጨረሻ ላይ ከደረሰ በኋላ በኮሚቴ ውሰኔ መሰረት እንዲሰረዝ ተደርጓል የተባለ ሲሆን፣ አዲስ ጨረታ በማውጣት በተያዝነው በጀት ዓመት ግንባታውን ለማስጀመር ቢሮው እየሠራ ነው ብለዋል፤ የፕሮጀክት ኃላፊው።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙ መሥሪያ ቤቶች ላይ በመደረግ ላይ ያለው የአደረጃጀት ለውጥ እና የተቋማት የሥራ ድርሻ ሽግሽግ ከበጀት እጥረት ጋር ተዳምሮ፣ ለግንባታው በታሰበለት ጊዜ አለመጀመር በምክንያትነት ተነስተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 67 የካቲት 7 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com