ኤጄቶ የሲዳማ ክልል ርክክብ እስከ የካቲት 15 እንዲካሄድ ጠየቀ

Views: 590

እስከ የካቲት 15 ድረስ የሥልጣን ርክክብ ተካሂዶ የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምስረታ የማይከናወን ከሆነ የሲዳማ የወጣቶች ቡድን የሆነው ኤጄቶ ተቃውሞ እንደሚያስነሳ አስጠነቀቀ።

ሲዳማ ዞን ከደቡብ ክልል ወጥቶ ራሱን የቻለ ክልል መሆኑን በድምጹ ካረጋገጠ ሦስት ወራት ቢቆጠሩም ገዢው ፓርቲ የሲዳማን ክልል ለመመስረት እያቅማማ መቆየቱን የገለጹት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ራሱን ኤጄቶ ብሎ የሚጠራው የወጣቶች ስብስብ አመራር ናቸው።

መንግሥት ከሕዝቡ የሚተላለፉትን ጥሪዎች በቸልታ የሚያልፍበት መንገድ የሚመጡትን ችግሮች ከማባባስ በቀር ወደ መፍትሄ የሚያቀርብ አማራጭ ሊሆን እንደማይችል የጠቀሱት የኤጀቶ አባል መንግሥት በአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል የተወሰነውን ውሳኔ ላለማስፈፀም ምርጫ እየፈለገ እንደሆነ እንዲያምኑ እንዳደረጋቸው ተናረዋል።

ላለፉት ኹለት ሳምንታት በአዳማ ከተማ ሲደረግ በነበረው የብልጽግና ፓርቲ ስብሰባ ላይ የሲዳማ አመራሮች ከተሳተፉ በኋላ አዲስ አበባ በመሄድ ከጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ ውይይት አድረገዋል። የደቡብ ክልል አመራሮችም ጭምር የተሳተፉበት ይህ ስብሰባ ለሦስት ቀናት የቆየ ሲሆን የዚህ ስብሰባ ውጤት የክልልነት የሥልጣን ርክክቡን የሚያራዝም በመሆኑ ምክኒያት ኤጀቶ በድጋሚ ወደ ጥያቄ መግባቱን አስውቋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የደቡብ ክልል አመራሮች የሥልጣን ርክክቡን ለማዘግየት እየጣሩ እንደሆነ እና ለሲዳማ አመራሮች ሕዝቡን እንዲያሳምኑ አጀንዳ ተሰጥቷቸዋል ሲሉ እኚሁ የኤጀቶ መሪ ተባግረዋል።

ከዚህ ቀደም በ11/11/2011 በመንግሥት ቸልታ ምክንያት ተፈጠረ ያሉትን ደም መፋስ በማስታወስ አሁንም ለሚመጣው ነገር ዋነኛ ተጠያቂ መንግሥት ነው ብለዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የሲዳማ ዞን አስተዳዳሪ የሆኑት ደስታ ዳሞ ድምፀ ውሳኔውን ተከትሎ “በሁለት ወር ውስጥ የሲዳማ ክልላዊ መንግሥትን እንመሰርታለን ብለን ግብ ጥለን እየሠራን እንገኛለን›› ብለው ነበር። አክለውም ‹‹ክልል የመሆን ሂደቱ አላለቀም፤ገና ነባሩ ክልል እውቅና አልሰጠውም፤ ይህን ለማድረግ የራሱ ሂደት አለው ነው እንጂ ተከልክሎ አይደለም›› ሲሉም ተናግረዋል።

በተያያዘም የሲዳማ ዞን የሕዝብ ግንኙነት ዋና ኃላፊ የሆኑት ገነነ አበራ ሥራዎች መሄድ ባለባቸው መንገድ እየሄዱ መሆኑን እና በጉዳዩ ላይ ሰኞ የሲዳማ ዞን አስተዳዳሪ ደስታ ዳሞ መግለጫ እንደሚሰጡበት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በ11/11/11 የሲዳማን ክልልነት እናውጃለን የሚሉ እንቅስቃሴዎች በዞኑ መበራከታቸውን ተከትሎ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ያጠፋ እና የንብረት ውድመት ያስከተለ እልቂት እንደነበር የሚታወስ ነው። አሰቃቂውን ሁኔታም ተከትሎ በሐምሌ 15 2011 የሲዳማን ዞን ጨምሮ መላው የደቡብ ክልል እስከ አሁን ድረስ በኮማንድ ፖስት ስር ይገኛል።

የሲዳማ ዞንን ጨምሮ የደቡብ ክልል አሁንም የፀጥታ መዋቅሩ በፌደራል መንግስት ስር ወይም በኮማንድ ፖስት ቁጥጥር ውስጥ ይገኛል።

ቅጽ 2 ቁጥር 67 የካቲት 7 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com