ባለፉት አምስት ወራት ከጨርቃ ጨርቅ ገበያ 78.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኘ

0
728

ከ2013 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ12.8 ሚሊዮን ዶላር ዕድገት አሳይቷል

ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ጀምሮ እስከ ኅዳር 30/2014 ባሉት አምስት ወራት፣ የተለያዩ የጨርቃጨርቅ ምርቶችን ወደ ውጭ ገበያ በመላክ 78.5 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት መቻሉን የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
ይህም በባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 65.7 ሚሊዮን ዶላር ጋር ሲነጻጸር የ 12.8ሚሊዮን ዶላር ብልጫ እንዳለው ኢንስቲትዩቱ አመላክቷል። በዚህም በአምስት ወራት 79.5 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ዕቅድ ተይዞ፣ የዕቅዱን 98 በመቶ ማሳካት መቻሉም ተገልጿል።

ገቢው የተገኘው ድር እና ማግ፣ ጨርቃጨርቅ፣ አልባሳትና ባህላዊ አልባሳትን ወደ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ አሜሪካ እና የተለያዩ የአፍሪካና እስያ አገራት በመላክ መሆኑን የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ባንቲሁን ገሰሰ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ገቢው ከተሰበሰበባቸው አምስት ወራት ውስጥ በሦስቱ ማለትም በሐምሌ፣ መስከረም እና ጥቅምት የተሰበሰበው ገቢ ከታቀደው በታች መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም የመጣው በአምራች ፋብሪካዎች ግላዊ ችግር እንደሆነ ነው ዳይሬክተሩ የጠቆሙት።
በተያያዘም፣ በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት ከደረሰባቸው የጨርቃጨርቅ ማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ገቢ አለመሰብሰቡንና በተለይ በኮምቦልቻ በነበሩት ላይ የደረሰው የኪሳራ መጠን በታኅሣሥ ወር እንደሚታወቅ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ በመቀሌም በየወሩ ለውጭና ለአገር ውስጥ ገበያ ሠፊ ምርት የሚያቀርቡት ‹ቬሎሲቲ› እና ‹ዲቪኤል›ን የመሳሰሉ ስድስት ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች አሁን ላይ ሥራ አቁመው እንደሚገኙ አብራርተዋል።

በሌላ በኩል፣ አገሪቱ ለጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪው ግብዓት የሚውል ምቹና ሠፊ ቆላማ የጥጥ ማሳ ያላት በመሆኑ፣ በ2014 የምርት ዘመን 80 ሺሕ ሔክታር በጥጥ ለመሸፈን ታቅዶ ከ55-60 ሺሕ የሚደርሰውን በዘር በመሸፈን፣ ከ33 ሺሕ ቶን በላይ የተዳመጠ እና ጥራቱን የጠበቀ የጥጥ ምርት ይገኛል ተብሎ ይታሰባል ተብሏል።

ኢትዮጵያ በቂ የጥጥ ምርት እንዳላት የተገለጸ ሲሆን፣ አሁን ላይ ከጋምቤላ፣ አፋር፣ ደቡብ ኦሞ፣ እንዲሁም አማራ ክልል ማሳ ላይ የነበረው ጥጥ እየተሰበሰበ እንደሚገኝ ነው ዳይሬክተሩ ያመላከቱት። ሆኖም በሑመራ፣ መተማ፣ እና ሌሎች የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች በጦርነቱ ምክንያት ብዙ ጥጥ ማምረት እንዳልተቻለ ተገልጿል።

የጨርቃጨርቅ ዘርፉ ብዙ ችገሮች ቢኖሩበትም ብዙዎቹን ተቋቁሞ በማደግ ላይ ያለ በመሆኑን፣ አገሪቱ በቀጣይ ወደ ከባድ ኢንዱስትሪ ለምታደርገው ሽግግር የላቀ አስተዋጾ እንዳለው ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።
አሁን ላይ የፖለቲካና የጸጥታ ችግር ባለበት ኹኔታ ላይ ‹ኢንቨስተሮች› ተረጋግተው ሥራቸውን መሥራታቸው በዘርፉ ይፈጠራል ተብሎ ከታሰበው ቀውስ ያነሰ ችግር መፈጠሩን አንስተዋል።

ዳይሬክተሩ አያይዘውም፣ በሥራ ሒደት ወቀት የመብራት መቆራረጥ፣ የአመራር ብቃት ማነስ፣ የሠራተኛ አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆን፣ የግብዓት አቅርቦት ችግር፣ የረዥም ጊዜ የገበያ ልምድ አለመኖር፣ የመሳሰሉ ችግሮች እያጋጠሙ ቢሆንም፣ አንዳንዶቹ በጊዜ ሒደት ሊፈቱ የሚችሉ ናቸው ነው ያሉት።

የጨርቃ ጨርቅ ዘርፉ ከአገሪቱ የኢኮኖሚ ዘርፍ ያለው ድርሻ የላቀ ከመሆኑም በላይ፣ በዜጎች ላይ የሚፈጥረው የኢንዱስትሪ ባህል የጎላ ነው ሲሉ ዳይሬክተሩ አክለው ገልጸዋል።
በተያያዘም፣ በ2014 የምርት ዘመን 223 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከጨርቃጨርቅ ገበያ ለማግኘት ዕቅድ መያዙን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 165 ታኅሣሥ 23 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here