በማኅበራት ቤት ለሚገነቡ የኮንዶሚኒየም ተመዝጋቢዎች የቅድሚያ ቁጠባ ዋጋ ሊቀነስላቸው ነው

0
1372

• 960 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ከሪል ኢስቴት አልሚዎች ተነጥቆ ለኅብረት ሥራ ቤት ግንባታ ሊተላለፍ ተወስኗል

የአዲስ አበባ አስተዳደር የቤት ልማት ትኩረት ከኮንዶሚኒየም ወደ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ቤት ግንባታ መዛወሩን ተከትሎ በጋራ መኖሪያ ቤት ተመዝግበው የነበሩ ነዋሪዎች ዝቅተኛውን ቁጠባ ብቻ አቅርበው ቤት እንዲገነቡ ሊደረግ ነው።

አዲስ ማለዳ ባለፈው የካቲት 2 ዕትሟ አስተዳደሩ ከዚህ በኋላ ከ960 ሺሕ ለሚልቁት የ20/80 እና 40/60 ኮንዶሚኒየም ተመዝጋቢዎች ቤት ገንብቶ የማስተላለፍ አቅም ስለሌለው ትኩረቱን ወደ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ቤት ማዛወሩንና ለዚህም የነበረውንው የኅብረት ሥራ ማኅበራት የቤት ማደራጃ መመሪያ መከለሱን ከምንጮቿ ስለማረጋጋጧ መዘገቧ ይታወሳል። ይሁንና መመሪያው ከሚያስቀምጣቸው መስፈርች መካከል አንዱ በማኅበራት ተደራጅቶ ቤት መገንባት የሚፈልግ ሰው ቅድሚያ የቤቱን አጠቃላይ ዋጋ ግምት 50 በመቶ መቆጠብ እንዳለበት የሚስገድድ መሆኑንም አብራ ዘግባለች። ይህም ማለት አንድ ሚሊዮን ብር ዋጋ ላለው ቤት፣ ገንቢው ቀድሞ 500 ሺሕ ብር መቆጠብ አለበት ማለት ሲሆን፣ ይህም ለአብዛኛው የአዲስ አበባ ቤት ፈላጊ ነዋሪ አቅም የማይደፈር ስለመሆኑ በቀዳሚው ዘገባችን አስነብበናል።

በሌላ በኩል ለአስተዳደሩ ካቢኔ ውሳኔ ሊቀርብ በመጠናቀቅ ላይ ያለው የቤት ፍላጎትና የፋይናንስ አማራጮች ላይ ባተኮረው ጥናት መሰረት ከኮንዶሚኒየም ምዝገባ ወጥተው በማኅበራት በመደራጀት የራሳቸውን ቤት ለመገንባት ፍላጎቱ ያላቸው ተመዝጋቢዎች ቁጥር ከ300 ሺሕ መብለጡን ምንጮቻችን አስታወቀዋል።
ሆኖም በኮንዶሚኒየም ተመዝግቦ እስካሁን ቤት ሲጠብቅ የኖረን ሕዝብ 50 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ እየጠየቁ ወደ ማኅበራት ቤት ግንባታ እንዲገባ ማድረግ ካለው የመክፈል አቅም ጋር እንዴት ይታያል? ስትል አዲስ ማለዳ የጠየቀቻቸው የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሰናይት ዳምጠው የገንዘብ አቅም ችግሩን ለመቅረፍ ከባንክና ሌሎች የገንዘብ ተቋማት ጋር እየተነጋገሩ እንደሚወስኑ ገልፀዋል።

የኮንዶሚኒየም ቤት ለማግኘት ተመዝግበው ለሚገኙት ግን የ50 በመቶ ቅድሚያ ቁጠባ መጠኑ እንደሚቀነስ አስረድተዋል። ይኸውም በ20/80 ተመዝግበው የነበሩት 20 በመቶውን ብቻ፣ በ40/60 የተመዘገቡት ደግሞ 40 በመቶውን ብቻ አቅርበው ቤት መሥራት እንዲችሉ የሚፈቅድ መሆኑን ነግረውናል። ለቀሪው ክፍያ ደግሞ ከባንኮች ጋር የብድር አገልግሎት እንደሚመቻችላቸው ነው የተገለፀው።

በቀጣይ የሚደረገው የማኅበራት ቤት ሠሪዎች ምዝገባ ላይ ደግሞ በሚደረጉ ውይይቶች በሚደረስ ውሳኔ እየተፈታ እንደሚሔድ አክለዋል።

ባሳለፍነው ረቡዕ፣ የካቲት 6 የሪል ኢስቴት አልሚዎች ላይ የተደረገውን ጥናት ውጤት ያደመጡት ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ ለሪል ኢስቴት ግንባታ ተሰጥተው እስካሁን ቤት ያልተገነባባቸውን ቦታዎች ነጥቀው በቤቶች ልማትና አስተዳደር በኩል ለሌላ የቤት ልማት አገልግሎት እንደሚያስተላልፉ ውሳኔ አሳልፈዋል።

የተሰጣቸው ቦታ ላይ የሪል ኢስቴት ቤት መገንባት አልቻሉም በሚል ቦታውን እንዲነጠቁ የተወሰነባቸው 29 አልሚዎች በአምስት ክፍለ ከተሞች በድምሩ 960 ሺሕ 72 ካሬ ሜትር ስፋት ያለውን ቦታ ይዘው ይገኛሉ። ይህ ቦታ ተነጥቆ ለቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ይተላለፋል መባሉን ተከትሎ ለምን ዓይነት ቤት ልማት እንደሚጠቀሙበት አዲስ ማለዳ የጠየቀቻቸው የቢሮ ኃላፊዋ ሰናይት በማኅበራት ለሚገነቡ ቤቶች እንደሚውል ተናግረዋል። ቦታዎቹን ተረክበው የማኅበራት ቤቶቹን ለማስገንባት ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 14 የካቲት 9 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here